Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየብሔራዊ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን መቋቋም ፓርላማውንም ሆነ ገዥውን ፓርቲ እውነተኛ ይቅርታ እንዲጠይቁ...

የብሔራዊ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን መቋቋም ፓርላማውንም ሆነ ገዥውን ፓርቲ እውነተኛ ይቅርታ እንዲጠይቁ ዕድል እንደሚሰጥ ተገለጸ

ቀን:

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ አስፈጻሚው ተረቆ የቀረበለትን የብሔራዊ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅን ማክሰኞ ታኅሳስ 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ሲያፀድቅ፣ አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ምክር ቤቱ ራሱ ኃላፊነቱን ባለመወጣት በሕዝብ ላይ ለደረሰ በደል እውነተኛ ይቅርታን ማግኘት እንደሚያስችለው በመግለጽ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።

ጥቂት የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው በዚህ አገር ሕዝብ ከሕዝብ አለመጣላቱንና የኮሚሽኑ መቋቋምም አስፈላጊ አለመሆኑን በመግለጽ ተከራክረዋል።

በረቂቅ ማቋቋሚያ አዋጁ ላይ ዝርዝር ምርመራ በማድረግ የውሳኔ ሐሳብ ያቀረቡት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ፣ በተለያዩ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ በደሎች ሕዝብ መከፋቱን አብራርተው የኮሚሽኑ መቋቋም እውነተኛ ይቅርታ በመጠያየቅና የተበደሉ ወገኖችን ሕመም መጋራትና ማከም፣ በዚህም የቁርሾ ታሪክ ተዘግቶ ወደፊት ለመራመድ ከፍተኛ ፋይዳ የሚኖረው በመሆኑ ኮሚሽኑ እንዲቋቋም ጠይቀዋል። በተወሰኑ የረቂቅ አዋጁ ቃላት ላይ ማስተካከያ መደረጉንም አብራርተዋል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሪፖርተር አቶ ተስፋዬ ዳባን በጉዳዩ ላይ ያነጋገረ ሲሆን፣ እሳቸውም የኮሚሽኑ መቋቋም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደ ተቋም ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ በሕዝብ ላይ ለደረሱ በደሎች ተጠያቂ ሊሆን እንደሚችልና የኮሚሽኑ መቋቋምም ምክር ቤቱ ለፈጸመው ያልተገባ ተግባር በይፋ ይቅርታ የመጠየቅ ዕድል እንደሚሰጠው ገልጸዋል።

ይህ የሚወሰነው ኮሚሽኑ ሥራውን ጀምሮ በደል የደረሰባቸው በሚያቀርቧቸው ቅሬታዎች ላይ በመነሳት እንደሚሆንም አስረድተዋል።

 ለምሳሌ በደል የደረሰባቸው ወገኖች ለተፈጸሙባቸው በደሎች ፓርላማው ያወጣቸውን ሕጎች የሚጠቅሱና ኮሚሽኑም ተገቢነቱ ላይ ካመነ ፓርላማው ሕዝቡን በይፋ ይቅርታ ሊጠይቅ እንደሚገባ፣ ይህም ለፓርላማውም የተሰጠ ዕድል እንደሆነ ተናግረዋል።

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ባለፈው ዓመት ባደረገው የ17 ቀናት ስብሰባ በአገሪቱ ለተፈጠሩ በደሎች ራሱን ተጠያቂ በማድረግ ማኅበረሰቡን ይቅርታ እንደሚጠይቅ መግለጹን ያስታወሱት አቶ ተስፋዬ፣ ይቅርታ በመግለጫ ለይስሙላ የሚጠይቅ ሳይሆን ሥነ ሥርዓቱን ጠብቆና የእውነት ሆኖ በይፋ መጠየቅ እንዳለበት አስረድተዋል። በመሆኑም የኮሚሽኑ መቋቋም ለገዥው ፓርቲም ዕድል የሚሰጥ ነው ብለዋል።

የሚቋቋመው ኮሚሽን በአገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ጭምር ኃላፊነቱን እንደሚወጣም ገልጸዋል።

ማንኛውም ተበድያለሁ የሚል የኅብረተሰብ ክፍል ያለ ጊዜ ወሰን ቅሬታውን ለኮሚሽኑ እንደሚያቀርብም አቶ ተስፋዬ አስረድተዋል። የኮሚሽኑ ሥልጣንን በተመለከተ የደረሱ በደሎችን በተመለከተ ምርመራ ያደርጋል የሚለው አገላለጽ ማጣራት ያደርጋል በሚል መሻሻሉን፣ ይህ የሆነውም ከፖሊስ የወንጀል ምርመራ ተግባር ጋር እንዳይጣረስ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ኮሚሽኑ ማናቸውንም ሰነዶችና መረጃዎች የመጠየቅና የመመልከት መብት እንዳለው በረቂቅ አዋጁ ላይ የተገለጸው ድንጋጌ ተሻሽሎ፣ ከአገር ደኅንነትና ጥቅም ጋር ተያይዞ በሕግ በሚስጥር እንዲያዙ የሚደረጉ ሚስጥሮችን የማየት መብት እንዳይኖረው ገደብ መጣሉን ተናግረዋል።

የቀረበው ረቂቅ አዋጅ እንደሚያስረዳው ኮሚሽኑ የሚቋቋምበት መሠረታዊ ዓላማ በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ግጭቶች ምክንያት በሕዝቦች መካከል የተደራረቡ የቁርሾ ስሜቶችን እውነትና ፍትሕ ላይ በመመሥረት ለማከም፣ በእነዚህ የታሪክ አጋጣሚዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የሌላ በደል ተጠቂዎች ወይም ተጠቂ ነን ብለው የሚያምኑ ዜጎች ስለበደላቸው የሚናገሩበት፣ እንዲሁም በደል ያደረሱ ያደረሱትን በደል በግልጽ በማውጣት የሚፀፀቱበትና ይቅርታ የሚጠይቁበትን መንገድ ለማበጀት መሆኑን የአዋጁ አባሪ ማብራሪያ ያስረዳል።

በውጤቱም በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ሰላም፣ ፍትሕ፣ ብሔራዊ አንድነት፣ መግባባትና ዕርቅ እንዲሰፍን በማድረግ እየፈረሰ የሚሠራ ሳይሆን፣ እየተገነባ የሚሄድ ሥርዓት እንዲፈጠር ማስቻል መሆኑን የአዋጁ አንቀጾች ያመለክታሉ።

የኮሚሽኑ አባላት በመንግሥት እንደሚሰየሙና ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢና ሌሎች አባላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚሰየሙ፣ እንዲሁም ኮሚሽኑ ኃላፊነቱን ለመወጣት እንዲያስችለው ራሱን የቻለ ጽሕፈት ቤት እንደሚኖረው የሕግ ሰነዱ ይገልጻል።

 የኮሚሽኑ ጽሕፈት ቤት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሾም ኃላፊና ሌሎች አስፈላጊ ሠራተኞች እንደሚኖሩትም አዋጁ ይገልጻል። በተጨማሪም ኮሚሽኑ ሥራውን በነፃነትና በገለልተኝነት እንደሚያከናውን የተመለከተ ሲሆን፣ የኮሚሽኑ ተጠሪነትም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሆን በአዋጁ ተደንግጓል። የኮሚሽኑ የሥራ ዘመን ሦስት ዓመት እንደሚሆን፣ ነገር ግን እንደ ሁኔታው ሊራዘም እንደሚችል ተገልጿል።

የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ በአንድ ተቃውሞና በአንድ ድሞፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...