Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአዲስ አበባ መሥሪያ ቤቶችን ቅርፅ የሚለውጥ መዋቅር ለምክር ቤት ቀረበ

የአዲስ አበባ መሥሪያ ቤቶችን ቅርፅ የሚለውጥ መዋቅር ለምክር ቤት ቀረበ

ቀን:

የቤቶች ግንባታ የሚያካሂድ ኮርፖሬሽን ይቋቋማል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 114 መሥሪያ ቤቶችን ቅርፅና ይዘት በከፍተኛ ደረጃ የሚለውጥ አዲስ መዋቅር ለከተማው ምክር ቤት ቀረበ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ቀኑ ካልተለወጠ በስተቀር በመዋቅሩ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ለማሳለፍ ለታኅሳስ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. ተጠርቷል፡፡

አዲሱ የመዋቅር ለውጥ በምክትል ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) በሚመራው ካቢኔ ታይቶ ይሁንታ አግኝቷል፡፡ መዋቅሩ በምክር ቤት ከፀደቀ ተግባራዊ የሚደረገው በከተማው አስተዳደር ሥር የሚገኙ በ114 ተቋማትን ወደ 63 ዝቅ የሚያደርግ ሲሆን፣ የሚዋሀዱ፣ የሚፈርሱና አዲስ የሚቋቋሙ ተቋማት ይኖራሉ ተብሏል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እንደ አዲስ ከሚቋቋሙ ተቋማት መካከል የአዲስ አበባ ከተማ የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ዓቃቤ ሕግ ቢሮ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን፣ የግንባታ ኢንተርፕራይዝና የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ይገኙበታል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያዘጋጀው ይህ መዋቅር፣ በፌዴራል መንግሥት ሪፎርሙ ያመጣውን የመዋቅር ለውጥና የአዲስ አበባ ከተማ የመዋቅር ጥናት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ያካሄደውን የመዋቅር ጥናት መነሻ አድርጓል ተብሏል፡፡

ምክትል ከንቲባ ታከለ እንዳሉት፣ የመዋቅሩ አደረጃጀት ካልተፈተሸ በስተቀር የሌቦችን ዋሻ መናድ ያስቸግራል፡፡ በሌላ በኩልም የመንግሥት ወጪ መቆጠብና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት አስፈላጊ ብቻም ሳይሆን ግዴታ ነው ተብሏል፡፡

ለምክር ቤቱ በቀረበው ረቂቅ ሰነድ የ20/80 እና የ40/60 ቤቶችን ለመገንባት የተቋቋሙት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤትና ኢንተርፕራይዝ ተዋህደው፣ በኮርፖሬሽን መልክ እንዲደራጁ ሐሳብ ቀርቧል፡፡

በቀረበው ሐሳብ መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝና የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ተዋህደው፣ አንድ የቤቶች ኮርፖሬሽን ይቋቋማል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ተጠሪነቱ ለቤቶች ልማት ቢሮ ሲሆን፣ የተጀመሩትን የቤት ልማት ፕሮግራሞችን አቀናጅቶ እንዲያካሂድ ኃላፊነት ይሰጠዋል ተብሏል፡፡

በቀረበው ረቂቅ ሰነድ ላይ ለኮርፖሬሽኑ ከተሰጡት ኃላፊነቶች መካከል፣ የቤቶች ግንባታ የሚያከናውኑ አማካሪዎችንና ሥራ ተቋራጮችን በሕግ መሠረት ይመዘግባል፣ ይመለምላል፣ ወደ ሥራ ያሰማራል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በተገቢው ውል መሠረት የጥራት ደረጃ፣ የጊዜና የዋጋ ገደብ ተጠብቆ መሠራቱን ለማረጋገጥ የሚያስችል የቁጥጥር ሥርዓት ይዘረጋል፣ በበላይነትም ይቆጣጠራል፡፡

ፋይናንስን በተመለከተም ኮርፖሬሽኑ ለቤቶች ልማት የሚያስፈልገውን ገንዘብ በከተማ በአስተዳደሩ ዋስትና ከአበዳሪ ባንኮች ይበደራል፡፡ በቤት ልማት ፕሮግራሙ ተጠቃሚ ለሚሆን የተመዘገቡና በባንክ የሚቆጥቡ ነዋሪዎችን ቁጠባ ኮርፖሬሽኑ ለመጠቀም፣ የብድር ወለድ ምጣኔውን በተመለከተ ከባንክ ጋር ድርድር ያደርጋል፡፡

በቀድሞ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ የሥልጣን ቆይታ መጨረሻ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አካላትን በድጋሚ ለማቋቋም ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡

በረቂቅ አዋጁ ተካተው ከነበሩ አንቀጾች መካከል አንቀጽ 84 የሚገኝበት ሲሆን፣ ይህ አንቀጽ የከተማ አስተዳደሩ አስፈጻሚና የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አካላትን እንደገና ስለማደራጀት ይደነግጋል፡፡

የከተማው ካቢኔ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ደንብ በማውጣት ማንኛውም አስፈጻሚ ወይም ማዘጋጃ ቤት አካል እንዲታጠፍ፣ ከሌላ አስፈጻሚ ወይም ማዘጋጃ ቤት አገልግሎት አካል ጋር እንዲዋሀድ፣ እንዲከፋፈል፣ ሥልጣንና ተግባሩ እንዲለወጥ በማድረግ ወይም አዲስ አስፈጻሚ አካል እንዲቋቋም በማድረግ፣ የከተማ አስተዳደሩ አስፈጻሚ አካላትን እንደገና የማደራጀት ሥልጣን በረቂቅ አዋጅ ተሰጥቶት ነበር፡፡

ነገር ግን በወቅቱ በዚህ አዋጅ ላይ የምክር ቤት አባላት በርካታ ጥያቄዎችን በማንሳታቸው ሳይፀድቅ ቀርቷል፡፡ ይህ አዋጅ በወቅቱ ቢፀድቅ አዲሱ የመዋቅር ለውጥ ምክር ቤት መሄድ ሳያስፈልገው ካቢኔው በሚያወጣው ደንብ ብቻ ተግባር ላይ ሊውል ይችል እንደነበር የሕግ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

ነገር ግን በወቅቱ የቀረበው አዋጅ በምክር ቤቱ ባለመፅደቁ አዲሱ መዋቅር ለምክር ቤት ቀርቧል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...