Thursday, December 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናበሜቴክ ተጠርጣሪ ላይ ፖሊስ ተዓማኒነት የጎደለውና ከአቅም በታች እየሠራ ነው መባሉ ቁጣ...

  በሜቴክ ተጠርጣሪ ላይ ፖሊስ ተዓማኒነት የጎደለውና ከአቅም በታች እየሠራ ነው መባሉ ቁጣ አስነሳ

  ቀን:

  ፍርድ ቤት ለጠበቆች የመጨረሻ ተግሳፅ ሰጠ

  ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ጋር በተያያዘ በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩት የሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ወንድም አቶ ኢሳያስ ዳኘው ጠበቆች፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን የደንበኛቸውን የምርመራ ሒደት እየሠራ ያለው እምነት በጎደለውና ከአቅም በታች መሆኑን ለፍርድ ቤት መናገራቸው ቁጣ አስነሳ፡፡

  የተቋማቸውንም ሆነ የእነሱን ስም ያላግባብ ማጉደፍ መሆኑን የገለጸው የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን፣ ቁጣውን ለፍርድ ቤቱ አሰምቷል፡፡ ፍርድ ቤቱም የተጠቀሱትን ቃላት መርምሮ ለአቶ ኢሳያስ ጠበቆች የመጨረሻ ተግሳፅ ሰጥቷል፡፡

  በፍርድ ቤቱ ውስጥ ቁጣ ያስነሳው ክርክር የተፈጠረው፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን እስከ ታኅሳስ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ተሰጥቶት በነበረው ተጨማሪ አሥር የምርመራ ቀናት ውስጥ የሠራውንና ይቀረኛል ያለውን የምርመራ ሒደት አቅርቦ፣ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት በመጠየቁ ምክንያት ነው፡፡

  አቶ ኢሳያስ በኢትዮ ቴሌኮም የኤንጂፒኦ ዳይሬክተር ሆነው በሚሠሩበት ወቅት፣ በሶማሌ ክልልና በኦሮሚያ ክልል በባሌ ዞን ለሞባይል ኔትወርክ ማስፋፊያ የቴሌ ታወር ተከላ ሥራዎችን፣ ያለ ምንም ጨረታ ወንድማቸው በዋና ዳይሬክተርነት ለሚመሩት ሜቴክ በመስጠትና ይኼም የተደረገው በሌላቸው ኃላፊነትና በጥቅም በመመሳጠር መሆኑን ተጠርጥረው ከታሰሩበት ጊዜ ጀምሮ መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዳ ቆይቷል፡፡

  ከላይ እንደተጠቀሰው ከሰኞ ታኅሳስ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀደም ባሉት አሥር ቀናት ውስጥ ባከናወናቸው የምርመራ ሒደቶች የአንድ ባለሙያ ምስክርነት ቃል መቀበሉን፣ ከኢትዮ ቴሌኮም ማስረጃ መሰብሰቡን፣ ከሜቴክ የኦዲት ሪፖርት ተጠናቆ እንዲላክለት መጠየቁንና ቀሪ ምስክሮችን በስልክ የማፈላለግ ሥራ ማከናወኑን አስረድቷል፡፡

  የቀሪ ምስክሮች ቃል መቀበል፣ ከሁለቱም ተቋማት የጠየቃቸውን የሰነድ ማስረጃዎች መሰብሰብ፣ ለኔትወርክ ማስፋፊያ የተተከሉ ታወሮችን በሚመለከት ርክክብ የተካሄደበትን ሰነድ መሰብሰብ እንደሚቀረው መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡ ርክክብ ከተደረገባቸው 58 ጣቢያዎች ውስጥ 17 ጉድለት ያለባቸው መሆናቸው በባለሙያዎች መረጋገጡንና ሦስት ጣቢያዎች ደግሞ ባለመሠራታቸው፣ ለርክክብ የተቋቋመው ኮሚቴ ሒሳባቸውን ቀንሶ በቃለ ጉባዔ በማስፈሩ ሰነድ ማሰባሰብ እንደሚቀረው ጠቁሞ፣ በቀጣይ መርምሮ ለማቅረብ ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

  የአቶ ኢሳያስ ዳኘው ጠበቆች አቶ ዘረሰናይ ምሥግናና አቶ ሀፍቶም ከሰተ ባቀረቡት መከራከሪያ መርማሪ ቡድኑ ቀድሞ በነበረው ችሎት ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዳ፣ ደንበኛቸው እንዲሻሻል ያደረጉት የሶማሌ ክልልና የባሌ ዞን የሞባይል ኔትወርክ ማስፋፊያ ታወር ተከላ ሥራ ክፍያ መቶ በመቶ መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡

  ሥራው 91.8 በመቶ መጠናቀቁንና 8.2 በመቶ ጉድለት እንዳለበት ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቱን ጠበቆቹ አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን እነሱ (ጠበቆቹ) ከደንበኛቸው (አቶ ኢሳያስ) እንዳረጋገጡት፣ ክፍያው መቶ በመቶ አለመከፈሉን ነው፡፡ መርማሪ ቡድኑ ቀሪ  ምስክሮች እንደሌሉት ጥርጣሬ እንዳላቸው የጠቆሙት ጠበቆቹ፣ የባለሙያ (ኦዲተር) ምስክርነት ቃል ለመቀበል ደንበኛቸውን በእስር ማቆየት ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ቀደም ባለው ችሎት ርክክቡ ተፈጽሞ መቶ በመቶ ክፍያ መፈጸሙንና ጉድለት እንዳለበት የገለጸውን 8.2 በመቶ ሥራ ገልጾ እያለ፣ በቀጣይ ችሎት (ታኅሳስ 15 ቀን 2011 ዓ.ም.) የርክክቡን ሰነድ እንዲላክለት መጠየቁ እርስ በርሱ የሚምታታና ሆን ተብሎ ጊዜ ቀጠሮ ለመጠየቂያ እንጂ ለምርመራ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን በሜቴክና በኢትዮ ቴሌኮም ርክክብ መፈጸሙን መንግሥትም እንደሚያውቅ አክለዋል፡፡

  በኢትዮ ቴሌኮም የሥራውን ሁኔታ እንዲያጣራ ተቋቁሞ የነበረው ኮሚቴ አጣርቶ ጉድለት ለተገኘባቸው ሥራዎች ሒሳብ መቀነሱን በሰነድ ላይ አስፍሮ እያለና በተቋሙ ውስጥ ተቀምጦ ባለበት ሁኔታ፣ ‹‹ኮሚቴው ሒሳብ የቀነሰበትን ሰነድ ለመቀበል›› በማለት ጊዜ ቀጠሮ መጠየቅ፣ ጥያቄ የሚያስነሳና እምነት የሚያጎድል የምርመራ ሒደት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ክፍያው ሙሉ ለሙሉ አለመከፈሉ እየታወቀ መርማሪ በመቀያየር አንድ ጊዜ መቶ በመቶ እንደተከፈለ፣ ሌላ ጊዜ እንዳልተከፈለና ጉድለት እንዳለበት ለፍርድ ቤት እየተገለጸ ተጨማሪ ጊዜ መጠየቅ ተገቢ ካለመሆኑም በተጨማሪ ፍርድ ቤቱን የማይመጥን መሆኑን ገልጸዋል፡፡

  መንግሥት አስፈላጊውን ሀብት መድቦለት እየሠራ መሆኑ ቢገመትም መርማሪ ቡድኑ ከአቅም በታች እየሠራ ነው የሚል ግምት እንዳደረባቸው የገለጹት ጠበቆቹ፣ ደንበኛቸው ከኅዳር 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ለ42 ቀናት በእስር ላይ ቢቆዩም ገና ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ እየተጠየቀባቸው መሆኑ፣ ሥራው በአግባቡ እየተሠራ አለመሆኑን አመላካች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ደንበኛቸው በቂ መጠርጠሪያ ነገር ሳይገኝባቸው በእስር ቆይተው የምርመራ መዝገቡ ለዓቃቤ ሕግ ሲዛወርለት፣ ክስ ሊያስመሠርትባቸው የሚችል ፍሬ ነገር እንዳልቀረበባቸው ገልጾ ውድቅ ቢያደርገው፣ በግፍ ታስረው ቅጣት እያስተናገዱ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ግምት እንዲወስድላቸው አሳስበዋል፡፡ ሙግት እየተጭበረበረ ነው የሚል ግምት እንዳላቸው የተናገሩት ጠበቆቹ፣ አቶ ኢሳያስ ያለ ምንም ጥፋታቸው ታስረው የሚገኙት የወንድማቸውን ሜጀር ጄኔራል ክንፈን ሞራል ለመንካት ነው የሚል እምነት እንዳደረባቸውም አስረድተዋል፡፡

  አቶ ኢሳያስ የተጠረጠሩበት ጉዳይ ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በፊት ሪፖርት የተደረገበትና ሁሉም የመንግሥትና የተቋሙ ኃላፊዎች የሚያውቁት መሆኑንም አክለዋል፡፡ ተቋሙ ቅጣት ሳይቀር ተቆራጭ ያደረገበት ሰነድ እያለ መርማሪ ቡድኑ መቶ በመቶ ክፍያ እንደተፈጸመ ሲገልጽ ቆይቶ፣ እንደገና ስንት እንደተቀነሰ ሰነድ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ለፍርድ ቤቱ ማስረዳታቸው፣ ተጠርጣሪ ትክክለኛ ማስረጃ ተገኝቶባቸው የታሰሩ ሳይሆን ሌላ ዓላማን ለማሳካት የታሰሩ ናቸው የሚል ግምት ውስጥ እንዳስገባቸው ጠበቆቹ አስረድተዋል፡፡

  መርማሪ ቡድኑ በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን ቦርድ በወሰነውና ባስተላለፈው የግዥ መመርያ መሠረት፣ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ግዥ ከተፈለገ በቦርድ ፈቃድ ብቻ እንደሚፈጸም በመግለጽ ለፍርድ ቤቱ የሚያስረዳበትን መከራከሪያ ሐሳብ ጠበቆቹ ተቃውመውታል፡፡ የተቃውሞ ምክንያታቸውን እንዳስረዱት፣ ቦርዱ ውሳኔ ያሳለፈበት የግዥ መመርያም ሆነ ራሱ ቦርዱ የነበረው ከ2003 ዓ.ም. በፊት ነው፡፡ ከ2003 ዓ.ም. ወዲህ የኮርፖሬሽኑ ቦርድና ማኔጅመንት (ምንም እንኳን ሁለቱ በወቅቱ ተመሳሳይ የነበሩ ቢሆንም) ፈርሶ፣ በፈረንሣይ ‹‹ፍራንስ ቴሌኮም› ተተክቷል፡፡ አዲስ በተሠራው የሥራ መዋቅር ውስጥ ደንበኛቸው (አቶ ኢሳያስ) ኃላፊ የነበሩበት ኤንጂፒኦ ዳይሬክቶሬት ከአሥር ሚሊዮን ብር በላይ ግዥ ውል መዋዋልና ውል ማሻሻል እንደሚችል ተደርጎ መሻሻሉን አስረድተዋል፡፡ ግልጽ በሆነ ነገር ላይ መርማሪ ቡድኑ በምርመራው እውነታን ከማፈላለግ ይልቅ፣ ነገሮችን እያወሳሰበ መሆኑንም አክለዋል፡፡ ውኃ የቋጠረ ክርክር እያደረጉ እንዳልሆነና ምርመራውን በእውነተኛነትና በገለልተኛነት እየተጣራላቸው እንዳልሆነ እንደሚሰማቸው ጥርጣሬያቸውንም ጠበቆቹ ተናግረዋል፡፡

  አቶ ኢሳያስ ከ1974 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ከ30 ዓመታት በላይ ማገልገላቸውን የጠቆሙት ጠበቆቹ፣ በአግባቡና በሕጉ መሠረት በመሥራት ሕዝባቸውንና መንግሥትን ሲያገለግሉ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ቀደም ባለው ችሎት ፍርድ ቤቱ ብይን ሲሰጥ፣ ምንም ዓይነት በሙስና የሚያስጠረጥር ማስረጃ እንዳልቀረበባቸው በመግለጽ፣ በሐሳብ በተለዩትና በአነስተኛ ድምፅ የተወሰነውን በመቀበል የዋስ መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡

  የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤቱ፣ ጠበቆቹ በክርክር ላይ የተጠቀሟቸውን ‹‹ለሌላ ዓላማ ነው፣ ከአቅም በታች ነው፣ ገለልተኛነቱን እንጠራጠራለን›› የሚሉትን ቃላት በማስታወስና ክርክሩ በግልጽ ችሎት እየተደረገ መሆኑን በመግለጽ፣ የሕግ መሠረት የሌላቸውንና ማስረጃ ማቅረብ የማይቻልባቸውን ቃላት መጠቀም ተገቢ አለመሆኑን አስታውቋል፡፡ በመሆኑም ተጨባጭ በሆነው ነገር ላይ ክርክራቸውን እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ በመስጠት፣ በድጋሚ ተመሳሳይና አላስፈላጊ ቃላት እንዳይጠቀሙ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡

  መርማሪ ቡድኑ በበኩሉ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ በርካታ ወታደራዊ ሳይንስ ተከትለው የሚሠሩና ብቃት ያላቸው የምርመራ ባለሙያዎች መኖራቸውን ጠቁሞ፣ ተቋሙ ስለተሰደበ የዲሲፕሊን ክስ ለማቅረብ እንዲችል ፍርድ ቤቱ ለጠበቆች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት እንዲያስተላልፍለት ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ፍርድ ቤቱ ከተመካከረ በኋላ በሰጠው ብይን ጠበቆች በችሎት ሲከራከሩ የተናገሩት አላስፈላጊ ቃላት ቢኖሩም፣ በችሎቱ ከመገሰፅ ወይም ቅጣት ከማስተላለፍ ባለፈ ለሌላ አካል የሚያስተላልፍበት የሕግ መሠረት እንደሌለ በመንገር፣ የመርማሪ ቡድኑ ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል፡፡ ነገር ግን የክርክር ግልባጭ መውሰድ እንደሚችሉ አክሏል፡፡

  በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ መዝገቡን ማየት እንዳለበት አስታውቆ፣ በአዳር ማክሰኞ ታኅሳስ 16 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጠው ትዕዛዝ የጠበቆቹን ክርክርና የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ፣ መርማሪ ቡድኑ ከጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ አሥር ቀናት በመፍቀድ ለታኅሳስ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...