Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በዚህ ዓመት ብቻ እስከ 80 ሚሊዮን ብር የሚገመት የላቦራቶሪ ዕቃዎች እያሟላን ነው›› አቶ ኮራ ጦሹኔ የጂማ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት

ጂማ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቀደምት ከሚባሉት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ነው፡፡ መሠረታዊ የመማሪያ መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋት ላይ ትኩረቱን አድርጎ ይሠራ የነበረው ዩኒቨርሲቲው የመማሪያ ክፍሎች፣ የላቦራቶሪና ወርክሾፕ እንዲሁም የተማሪዎች ማደሪያ ሕንፃዎች ግንባታ ላይ በስፋት ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የትምህርት ጥራት ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየሠራ እንደሚገኝ የሚገልጹት አቶ ኮራ ጦሹኔ የጂማ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከቅድመ ምረቃው ይልቅ ለድኅረ ምረቃ የትምህርት ፕሮግራሞች  ትኩረት ሰጥቶ ማስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡ ድኅረ ምርቃ እንደ ቅድመ ምረቃው ፕሮግራም የተማሪዎች ማደሪያ ስለማያስፈልገው ለፕሮግራሙ የሚመጥን የትምህርት ግብዓት የላቦራቶሪ፣ የውይይት፣ የኮንፍረንስ ማዕከላትና የመሳሰሉትን የማስፋፋት ተግባር እያከናወነ ይገኛል፡፡ የሕክምና ማዕከልና አንድ ስታዲዮም አስገንብቶ ከቀናት በፊት አስመርቋል፡፡ ጂማ ዩኒቨርሲቲ በሚያከናውናቸው የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ዙሪያ ሻሂዳ ሁሴን አቶ ኮራ ጦሹኔን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ዩኒቨርሲቲው ካከናወናቸው ግዙፍ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች መካከል የጂማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል አንዱ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ከተጀመረ ዓመታት ፈጅቷል፡፡ ሥራ ይጀምራል ከተባለበት ጊዜም ዘግይቷል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ምንድነው?

አቶ ኮራ፡- የጂማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል በአሁኑ ጊዜ ስሙ ተቀይሮ ጂማ የሕክምና ማዕከል ነው የምንለው፡፡ ምክንያቱም አገልግሎቱን የሚጠቀሙ የጂማ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆኑ አጠቃላይ በደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍል የሚኖሩ ዜጎች ናቸው፡፡ ምዕራብ ኦሮሚያ፣ ጋምቤላ፣ በተወሰነ መጠን ደቡብና ቤንሻንጉል ክልል ሕክምና ማዕከሉ ተደራሽ የሚያደርጋቸው የአገሪቱ ክፍሎች ናቸው፡፡ የሕክምና ማዕከል የሚባለው አገልግሎት የመስጠት አቅሙ ከሆስፒታል ደረጃ ከፍ ያለ ስለሆነ ነው፡፡ የስፔሻሊቲ አገልግሎቶች የመስጠት አቅሙ እንዲኖረው፣ አገሪቱ በሕክምና ቱሪዝም ሰበብ በየዓመቱ የምታጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረትና በአገር ውስጥ የማይሰጡ የሕክምና ዓይነቶችን እንዲሰጥ ታቅዶ የተገነባ ነው፡፡ ይህ የሕክምና ማዕከል ግንባታው እ.ኤ.አ. በ2007 የተጀመረ ነው፡፡ ግንባታው በሁለት ምዕራፍ የተከናወነ ሲሆን፣ አንደኛው ምዕራፍ አልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የማስፋፊያ ምዕራፍ የሚባለው ነው፡፡ ሌላው የመጀመሪያ ግንባታ ውስጥ ያልተካተቱ የውኃ ማጠራቀሚያ የመሳሰሉ ወሳኝ ግንባታዎች የተከናወኑበት ነው፡፡ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ነው፡፡ ምዕራፍ ሁለት የተባለው የግንባታው ክፍል ነው፡፡ የሁለቱ ፕሮጀክቶች አጠቃላይ ወጪ ከ720 ሚሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ የመጀመሪያው ግንባታ ምዕራፍ ይጠናቀቃል ከተባለበት ጊዜ ብዙ ዓመት ወደ ኋላ ቀርቷል፡፡ አንዱ ምክንያት ሆስፒታሉ ግንባታው ሲጀመር በአገሪቱ መሠረታዊ የግንባታ ግብዓቶች ከፍተኛ እጥረት ስለነበር፣ ግንባታው ከተጠናቀቀም በኋላ የኃይል አቅርቦት ችግር ስለነበር ነው፡፡ ወሳኝ የሆኑ የሕክምና መሣሪያዎችና ዓብዓቶችን ከውጭ ለማስገባት የነበረው የውጭ ምንዛሪ እጥረትም አገልግሎቱ ወቅቱን ጠብቆ እንዳይጀመር ሌላው ማነቆ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያን የሕክምና መዳረሻ ለማድረግ ዓላማ ሰንቃችሁ እየተንቀሳቀሳችሁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ወደ ተግባር ለመግባት ግን ምን ያህል ዝግጁ ናችሁ? ምን ዓይነትስ ፈተናዎች ይኖራሉ?

አቶ ኮራ፡- በኢትዮጵያ ሜዲካል ቱሪዝም ለመጀመር በጣም ብዙ ነገር ያስፈልገናል፡፡ ባለሙያ፣ ዘመናዊ መሣሪያዎች እንዲሁም የማይቆራረጥ የአላቂ ዓብዓቶች አቅርቦት ያስፈልገናል፡፡ አላቂ የሚባሉት ግብዓቶች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ናቸው፡፡ የአቅርቦት መስመራቸው ሳይቆራረጥ ቀጣይነት ባለው መልኩ መቅረብ አለባቸው፡፡ ይህ ዓይነቱ ኬሚካል ሪኤጀንት አልቋል ሲባል ወዲያው መቅረብ ቢኖርበትም እየቀረበ አይደለም፡፡ ይህ ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም የተለመደ ነው፡፡ አቅራቢዎች የውጭ ምንዛሪ ወረፋ ስለሚኖርባቸው የተጠየቁትን በወቅቱ አያቀርቡም፡፡ ሌላው በኢትዮጵያ ልምድ ያካበቱ የሕክምና ባለሙያዎች ቁጥር በጣም ውስን ቢሆንም የተሟላ የግብዓት አቅርቦት ይፈልጋሉ፡፡ መሥራት የሚፈልጉትም እንደ አዲስ አበባ ባሉ ሰፊፋ ከተሞች ነው፡፡ በሌሎች አካባቢዎች እንዲሠሩ የሚስባቸው ነገር ያስፈልጋቸዋል፡፡ በአጠቃላይ የሰው ኃይል ማሟላትና ግብዓት ሳይቆራረጥ ማቅረብ ላይ ትልቅ ችግር አለ፡፡ ነገር ግን ይህ እንደ ተቋም የሚፈታ አይደለም፡፡ አገራዊ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ነው የተሻለ ሕክምና ፍለጋ ሰዎች ከአገር የሚወጡት፡፡ ለውጭ ሕክምና በየዓመቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እናወጣለን፡፡ ይኼንን ያህል ገንዘብ ቢያወጡም ድነው ይመጣሉ ማለት ግን አይደለም፡፡ በቋንቋ ችግር ምክንያት ሞቶ የሚመለስ ብዙ ነው፡፡ በየዓመቱ የሚወጣውን ቢሊዮኖችና የሚሞቱ ሰዎችን ለመታደግ በአገሪቱ ውስጥ የበቃ የጤና አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አቅም መገንባት የግድ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ እነዚህን የሕክምና ግብዓቶችና ኬሚካሎች ማምረት የሚችሉ ተቋማትም ሊመሠረቱ ይገባል፡፡ ያላስቀመጡት ራዕይ አይደረስበትምና አገሪቱን የሕክምና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ያሉትን ፈተናዎች አውቀን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንሠራለን፡፡ ጂማ፣ ጥቁር አንበሳና ጎንደር ሆስፒታሎች ተለይተው ጥናት እየተደረገላቸውም ነው፡፡ እኛም የተሻለ አገልግሎት መስጠትን ታሳቢ አድርገን ነው ሕንፃውን የገነባነው፡፡ ማዕከሉ የአየር አምቡላንስ ማሳረፊያ፣ ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶች ማቃጠያ፣ የኦክሲጂን ማምረቻ እንዲኖረው ተደርጎ ተገንብቷል፡፡ 75 በመቶ የሚሆኑ ሕመምተኞች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታከሙት በዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ የተወሰኑትን መርጦ ማጠናከርና ብቁ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ድጋፍ ማድረግ በየዓመቱ አገሪቱ የምታጣውን የውጭ ምንዛሪ ማዳን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሆስፒታሉ ምን ያህል የሕክምና ባለሙያዎች አሉት? ምን ያህል ዘመናዊ የሕክምና አገልግሎት መስጠት የሚችሉ መሣሪያዎችስ አሉት?

አቶ ኮራ፡- ከመሣሪያ አንፃር ስናይ ከሞላ ጎደል መሥራት የሚያስችሉ መሣሪያዎች አሉ፡፡ ብዙ የሚያሳስበን የግብዓት ጉዳይ ነው፡፡ የሰው ኃይል የማቆየት ፈተናም ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ ጂማ ዩኒቨርሲቲ ብዙ የሕክምና ባለሙያዎች አሉት ነገር ግን በየጊዜው ይለቃሉ፡፡ ፈተና የሆነብንም ይህ ጉዳይ ነው፡፡ ይኼንን ከጤና ጥበቃ ጋር በመሆን መፍትሄ ለመስጠት እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ባለሙያዎችን ለመሳብ፣ ያሉትንም ማስቀረት የሚቻልባቸውን መንገዶች እያሰብን ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ሆስፒታሉ የኤምአርአይ፣ የሲቲስካን፣ ዲጂታል ኤክስሬይ የመሳሰሉት መሣሪያዎች አሉት፡፡ ትልቁ እመርታ የምንለው የጨረር ሕክምና ለመጀመር ዝግጁ መሆናችንን ነው፡፡ የኩላሊት ሕክምና አጠባ አገልግሎት የሚሰጡ መሣሪያዎቻች በቁጥርም ቢሆን አለን፡፡ በቅርቡ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተጨማሪ አሥር ማሽን እናገኛለን፡፡

የሕክምና ሥራ የአንድ ሰው ሥራ ሳይሆን የቡድን ነው፡፡ የቀዶ ሕክምና ሐኪም ካለ በዚያ ሙያ የሠለጠነ ነርስ፣ ሰመመን ሰጪ የመሰሳሉት ያስፈልጉናል፡፡ ሰፊ የሰው ኃይልና ቡድኖችን የማሟላት ሥራ አለብን፡፡ ይኼንን አቅም በመገንባት ሒደት ላይም እንገኛለን፡፡ እስከዚያ ድረስ ግን የውጭ አገር ዜጎችን እያመጣን አገልግሎት መስጠት እንጀምራለን፡፡ የተሟላ አገልግሎት መስጠት ባይቻልም ባለው በከፊልም ቢሆን እንዲጀምር ይደረጋል፡፡ የተወሰኑት የሕክምና ዓይነቶች ደግሞ ባለሙያዎች ሥልጠና እስኪጨርሱ ድረስ ይቆያሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ተጨማሪ የሕክምና ማዕከል ማስፋፊያ ግንባታ ታስባላችሁ?

አቶ ኮራ፡- የድንገተኛ የአደጋ ሕክምና መስጫ ሕንፃ ለብቻው መሠራት አለበት፡፡ በእኛ አገር ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ ያጋጥማል፡፡ ሆስፒታሉን አጨናንቀው የሚገኙትም የአደጋ በተለይም የትራፊክ አደጋ ታካሚዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ የግድ ለብቻው ወጥቶ እንዲሠራ ይፈለጋል፡፡ በዚህ ላይ ከጤና ጥበቃ ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ዩኒቨርሲቲው አዲስ ስታዲዮም አስመርቋል? ለግንባታው የወጣው አጠቃላይ ወጪ ምን ያህል ነው? ግንባታውን ያከናወነው የኮንስትራክሽን ድርጅትስ ማን ነው?

አቶ ኮራ፡- እኛ ስታዲዮም ሳይሆን የስፖርት አካዴሚ ነው ያስመረቅነው፡፡ ጂማ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ይሰጣል፡፡ ብቁ የማስተማሪያ ቦታ ግን አልነበረውም፡፡ ስለዚህም ነው አካዴሚውን መገንባት ያስፈለገው፡፡ አካዴሚው የእግር ኳስ ሜዳ፣ የአትሌቲክስ መሮጫ፣ በአንድ ቦታ ሦስት በሚባለው አሠራር የቮሊቮል፣ የቅርጫት ኳስና የእጅ ኳስ ስፖርት የሚካሄድባቸው ሁለት ሜዳና የሜዳ ቴኒስ መጫወቻ ሜዳም ያካተተ ነው፡፡ በተጨማሪም የመዋኛ ገንዳና ጂምናዚየም በሌላ ኮንትራክተር እያሠራን ነው፡፡ በቅርቡ የተመረቀው አካዴሚው 40,000 ተመልካቾችን መያዝ የሚችል ስታዲዮም አለው፡፡ በ450 ሚሊዮን የወጣበትን አካዴሚ የገነባው አፍሮፂዮን ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ነው፡፡

ሪፖርተር፡-  ጂማ ዩኒቨርሲቲ በከተማው ውስጥ ሌሎች ምን ዓይነት የማስፋፊያ ሥራዎችን እየሠራ ነው?

አቶ ኮራ፡- የሆቴልና ቱሪዝም ማሠልጠኛ ተቋም እያስገነባን ነው፡፡ ሌላ አንድ የምርምር ተቋም ለማስገንባትም ቦታ ጠይቀናል፡፡ በከማዋ በሚገኙ በተለያዩ ቦታዎች ላይ እንድንገነባ ቦታ ከተሰጠን በኋላ መልሰው ለሌላ ፕሮጀክት ስለተሰጡ ምትክ ቦታ እስኪሰጠን እየጠበቅን ነው፡፡

ሪፖርተር፡-  አጋሮ ላይ ስለሚገነባው ኮሌጅ ፕሮጀክት ቢያብራሩልን?

አቶ ኮራ፡- የአጋሮ ኮሌጅ ግንባታ በሕዝቡ ጥያቄ የተጀመረ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ከሞላ ጎደል እስከ 400 ሚሊዮን ብር ድረስ የሚያስፈልገው ነው፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በእጃችን ላይ የሚገኘው 50 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው፡፡ ይህ ሲያልቅ እንግዲህ ሌላ እንጠይቃለን፡፡

130 ሄክታር ቦታ ተሰጠቶንም ግንባታ ጀምረናል፡፡ ለግንባታው ወደ 200 ሰዎች የተነሱ ሲሆን፣ ወደ 120 ሚሊዮን ብር ካሳም ከፍለናል፡፡ ግንባታውም ተጀምሯል፡፡ ጨረታውን አሸንፎ የወሰደው የመጀመሪያው ኮንትራክተር በነበረበት የአቅም ውስንነት አሰናብተነው ራማ ኮንስትራክሽን እንዲሠራው ሆኗል፡፡ ፕሮጀክቱ ከተጀመረ ዘንድሮ ሦስተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ በ2012 ዓ.ም. ግንባታው ተጠናቆ ተማሪዎችን መቀበል እንጀምራለን ብለን እናስባለን፡፡ አሁን እየተሠሩ ያሉት የተማሪ ማደሪያ ክፍሎች ናቸው፡፡ አጋሮ የቡና ቦታ ስለሆነ የግብርና ትምህርትና ምርምር ኮሌጅ እንዲሆን ነው የታሰበው፡፡ በመጀመሪያ ዓመት እስከ 400 ተማሪዎች እንቀበላለን፡፡

ሪፖርተር፡- ዩኒቨርሲቲው የዓመታት ታሪኩ እንደሚያሳየው በየጊዜው ሰፋፊ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን እንደሚሠራ ነው፡፡ ወደፊትም ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች እንዳሉት ተናግረዋል፡፡ ለመሆኑ እነዚህን ፕሮጀክቶት ለመሥራት ዓመታዊ በጀቱ ይፈቅድለታል? ወይስ የውጭ ድጋፎች አሉት?

አቶ ኮራ፡- የዩኒቨርሲቲው በጀት እንዲያውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ነው የመጣው፡፡ ዘንድሮ የተመረቁት አምናና ሀቻምና ማለቅ የነበረባቸው ነገር ግን በጥሬ ገንዘብ እጥረት ሲንከባለሉ እዚህ የደረሱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በ2011 ዓ.ም. ለጂማ ዩኒቨርሲቲ የተመደበው ከሁሉም ዩኒቨርሲቲ ያነሰ ነበር፡፡ በበጀት ዓመቱ የተመደበልን 300 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው፡፡ በከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ጫና ውስጥ ነን፡፡ ከዚህ ባሻገርም ዩኒቨርሲቲው ገንዘብ እያለው ነገር ግን የጥሬ ገንዘብ ችግር ስለነበር አምና 140 ሚሊዮን ሀቻምና ደግሞ 180 ሚሊዮን ብር መንግሥት ጋር ቀርቶበታል፡፡ በጀትም ተገኝቶ ጥሬ ገንዘብ ከሌለ ዋጋ የለውም፡፡ የዘንድሮ በጀት ደግሞ በጣም ቀነሰ፡፡ ስለዚህ በተገኘችው ገንዘብ የላቦራቶሪ የውስጥ ዕቃ ማሟላት ላይ አትኩረን እየሠራን ነው፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ እስከ 80 ሚሊዮን ብር የሚገመት የላቦራቶሪ ዕቃዎች እያሟላን ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከቢሻን ጋሪ እስከ ዶባ ቢሻን

ቢሻን ጋሪ ፒውሪፊኬሽን ኢንዱስትሪ ወደ ውኃ የማከም ቴክኖሎጂ ሥራ የገባው በየጊዜው በኢትዮጵያ የተከሰቱ ውኃ ወለድ በሽታዎች መደጋገምን ዓይቶና ጥናት አድርጎ ነው፡፡ በ2000 ዓ.ም. ቢሻን...

ለሴቶች ድምፅ ለመሆን የተዘጋጀው ንቅናቄ

ፓሽኔት ፎር ኤቨር ኢትዮጵያ ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ በፆታ እኩልነት፣ በእናቶችና ሕፃናት ጤና እንዲሁም የሴቶችን ማኅበራዊ ችግር በማቃለል ዙሪያ በተለያዩ ክልሎች ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ...

ሕይወትን ለመቀየር ያለሙ የቁጠባና ብድር ማኅበራት

ወ/ሮ ቅድስት ሽመልስ በግሎባል ስተዲስ ኤንድ ኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በፕሮጀክት ማኔጅመንት እንዲሁም በኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ ሠርተዋል፡፡ በኮርፖሬት ፋይናንስ ካናዳ ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ...