Monday, December 4, 2023

የመከላከያ ሠራዊትን ሀብትና ንብረት ወደ ጥብቅ የቁጥጥር ሥርዓት የሚያስገባው አዋጅና አዳዲስ ድንጋጌዎቹ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

መንግሥት በ2004 ዓ.ም. ከመደበው በጀት ውስጥ ከ6.5 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነውን ወጪና ገቢ ትክክለኛነት ማረጋገጥ አለመቻሉን፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር በ2005 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት ይፋ ማድረጉ ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሶ ነበር።

በወቅቱ በቀረበው ሪፖርት መሠረት ዘጠኝ መሥሪያ ቤቶች 3.5 ቢሊዮን ብር ባልተሟላ ሰነድ ወጪ ማድረጋቸው ተጠቅሷል። ከዚህ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የያዙት የደኅንነት ተቋማት ነበሩ፡፡ በተለይም የመከላከያ ሚኒስቴርና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በሪፖርቱ መሠረት ከተጠቀሰው ባልተሟላ ሰነድ ከተፈጸመ 3.5 ቢሊዮን ብር ውስጥ የመከላከያ ሚኒስቴር 3.2 ቢሊዮን ብር ድርሻ ነበረው።

 የኦዲት ሪፖርቱ ባጋለጣቸውና ሌሎች የኦዲት ሪፖርቱ ይዘቶች ላይ በወቅቱ የነበሩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሥራ አስፈጻሚው መንግሥት ላይ ከፍተኛ ትችት ሰንዝረው ነበር።

 ‹‹ይህ ኪራይ ሰብሳቢነት አይደለም፣ በስሙ ልንጠራው ይገባል ሌብነት ነው፤›› በማለት ድርጊቱን ያወገዙት በወቅቱ በፓርላማ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል (በአሁኑ ወቅት የሰላም ሚኒስትር ናቸው) ይታወሳሉ፡፡ መከላከያና ሌሎች የደኅንነት ተቋማት ላይ የተገኘው ኦዲት መደረግ ያልቻለ ሀብት ከአገር ደኅንነት አንፃር ኦዲት ለሚያደርገው ተቋም መገለጽ የሚችል ባለመሆኑ፣ የተፈጠረ የኦዲት ግኝት ሊሆን ስለሚችል ወቀሳ ከመሰንዘር ይልቅ መከላከያን ጨምሮ ሌሎች የደኅንነት ተቋማት እንዴት ኦዲት ይደረጉ? ዓለም አቀፍ ተሞክሮውስ ምን ያሳያል? የሚለው ተጠንቶ ሥርዓት ቢበጅለት እንደሚሻል አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ባነሱት ሐሳብ ላይ በወቅቱ መግባባት ተደርሶ ነበር። ይኼንንም መሠረት በማድረግ ራሱ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የሌሎች አገሮችን ልምድና ተሞክሮ በመቀመር፣ እነዚህ ተቋማት እንዴት ኦዲት መደረግ እንደሚችሉ በማጥናት ለፓርላማው የጥናት ውጤቱን ሪፖርት እንዲያደርግ በወቅቱ ኃላፊነት እንደተሰጠው ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የተባለውን ጥናት እያከናወኑ ባለበት ወቅት፣ ሥራ አስፈጻሚው መንግሥት በ2006 ዓ.ም. መጀመርያ ላይ የመከላከያ ሚኒስቴርን፣ እንዲሁም በዚሁ ዓመት የተለያዩ ወራት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነትና ኢሚግሬሽን፣ የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ተቋማትን ማቋቋሚያ የሚያሻሽሉ አዋጆች ለፓርላማ እንዲቀርቡ ተደርጓል።

በእነዚህ ማሻሻያ አዋጆች የፌዴራል ዋና ኦዲተር ከአገር ደኅንነት ጋር የተያያዙ ሚስጥሮችን ለመጠበቅ ሲባል፣ ተቋማቱ ሚስጥር ናቸው ብለው የሚለዩዋቸውን ጉዳዮች በተመለከተ የኦዲት ምርመራ እንዳያደርግ በሕግ ገደብ እንዲጣልበት ተደርጓል።

ቀዳሚ ሆኖ በ2006 ዓ.ም. ጥቅምት ወር ላይ የቀረበው ሕግ የመከላከያ ሠራዊትን ማቋቋሚያ የሚያሻሽል አዋጅ ነበር። ዋና ኦዲተር በመከላከያ ሠራዊቱ የሀብት አጠቃቀም ላይ የሚያደርገው የኦዲት ምርመራ ከሞላ ጎደል ተገድቦ፣ ማሻሻያው አዋጅ ቁጥር 806/2006 ሆኖ በምክር ቤቱ ፀድቆ እስከ ታኅሳስ 2011 ዓ.ም. በሥራ ላይ ይገኛል።

በዚህ አዋጅ አንቀጽ 69 መሠረት የመከላከያ ሠራዊቱ ከመንግሥት የሚያገኘው በጀት እንደሚኖረው፣ በተጨማሪም ሠራዊቱ በሰላም ጊዜ የሚኖረውን የማምረትና አገልግሎት የመስጠት አቅም ለገቢ ማስገኛ ተግባር እንዲውል በማድረግ፣ ለመከላከያ ጠቀሜታ የማያስፈልጉ ንብረቶችን በማስወገድ፣ በተቆጣጣሪ ባለሥልጣንነት ከሚመራቸው ድርጅቶች የሚገኘውን የትርፍ ድርሻና ከሰላም ማስከበር ሥምሪቶች የሚያገኘውን ገቢ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በማስፈቀድ እንደሚጠቀም ይደነግጋል። ከላይ የተገለጹት ገቢ ዓይነቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋላቸውን በተመለከተ ዋናው ኦዲተር ወይም እሱ በሚሰይማቸው ኦዲተሮች በየዓመቱ ኦዲት ማድረግ እንደሚችሉ ይደነግጋል።

ይሁን እንጂ በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 72 ንዑስ አንቀጽ ሦስት ሥር ዋና ኦዲተር ምርመራ እንዲያደርግባቸው ከላይ የተፈቀዱ የገቢ ዓይነቶች ቢኖሩም፣ የመከላከያ ሠራዊቱ አገራዊ ጥቅምንና ደኅንነትን ለመከላከል ሲባል እጅግ ጥብቅ ሚስጥር ብሎ የሚሰይማቸውን ማናቸውም የሰው ኃይል ፕሮፋይል፣ የሒሳብ መዝገቦች፣ ሰነዶችና የክፍያ ማስረጃዎች ለማንም አካል እንዳይገለጹ የማድረግ ሥልጣን ይሰጠዋል።

በዚህ ድንጋጌ መሠረትም ለዋና ኦዲተር ተለይቶ ኦዲት እንዲደረግበት የተፈቀደው ምን እንደሆነ በግልጽ ተለይቶ አለመታወቁ፣ እንዲሁም አገራዊ ጥቅምንና ደኅንነት ለመከላከል ሲባል ለማንም የማይገለጹ ጥብቅ ሚስጥር እንደሚሆኑ የሚፈለጉት የወጪ ዓይነቶች ባለመለየታቸው፣ የሀብት አጠቃቀሙን ጤነኛነት ለማረጋገጥ አዳጋች ሆኖ ቆይቷል።

የመከላከያ ሠራዊቱ ከላይ በተጠቀሰው አዋጅ መሠረት ለአገሪቱ ብሔራዊ ጥቅምና ለደኅንነት ሲባል ሚስጥር ብሎ የለያቸውን የሀብት አጠቃቀሞች ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ በሚስጥርነት መያዝ ጀምሯል። ይሁን እንጂ የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሚስጥር አለመሆናቸው ተገልጾ ለኦዲት ቁጥጥር ክፍት የተደረጉ መዝገቦች ላይ ብቻ የኦዲት ሥራውን ባደረገባቸው ባለፋት አምስት ዓመታት፣ በየዓመቱ ተመሳሳይ የኦዲት ችግሮች በመከላከያ ሚኒስቴር የሀብት አጠቃቀም ላይ መታየት ቀጥለዋል።

ለአብነት ያህል ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ በግንቦት ወር 2009 ዓ.ም. ባቀረቡት የኦዲት ግኝት ሪፖርት ላይ፣ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር በተለያዩ የኦዲት ዓይነቶች ከ400 ሚሊዮን ብሮች በላይ የተመለከቱ የሀብት አጠቃቀም ጤናማነት ችግሮች መኖራቸውን አስታውቀዋል።

 በአዋጁ መሠረት ሚስጥር አለመሆኑን ራሱ ተቋሙ ለይቶ ለኦዲት ክፍት ባደረገው የሒሳብ መዝገብ ላይ በተደረገ ኦዲት የተገኘ ችግር መሆኑንም ዋና ኦዲተሩ በወቅቱ ገልጸዋል።

በመጋቢት 2010 ዓ.ም. ወደ ሥልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ግን ይህ ሁኔታ ያለ መፍትሔ መቀጠል የለበትም ብለው የቆረጡ ይመስላል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን በመጡ ማግሥት ከፍተኛ ትኩረት ከሰጧቸው ጉዳዮች ሁሉ የግንባር ቀደምትነት ደረጃን የሚይዘው፣ በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ የጀመሩት ተቋማዊ ሪፎርም መሆኑን መናገር ይቻላል። ላለፋት 17 ዓመታት የሠራዊቱ ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩትን ጄኔራል ሳሞራ የኑስ በጡረታ በክብር በማሰናበት አዲስ ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ከመሰየም አንስቶ የሠራዊትን ከፍተኛ አመራር የብሔር ስብጥር ሚዛን የማስጠበቅ ዕርምጃና ሌሎች የማስተካከያ ተግባራትን አከናውነዋል።

የመከላከያ ሠራዊቱ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ የሕግ ማሻሻያዎች በማድረግም፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ታኅሳስ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ፀድቋል።

ይህ የማሻሻያ አዋጅ የሠራዊቱ አደረጃጀት ላለፋት ዓመታት ከሚታወቁት የእግረኛና የአየር ኃይል ተቋማት በተጨማሪ፣ የባህር ኃይልና የልዩ ዘመቻ ኃይል የሠራዊቱ መደበኛ አደረጃጀት እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ ከፍተኛ ትኩረት የሰጠው ከመከላከያ ሠራዊቱ የሀብት አጠቃቀም ጋር የተገናኙ አንቀጾችን በማሻሻል ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበትን ሥርዓት ማበጀት ነው።

‹‹በዋናነት ተቋማዊ አሠራሩ ግልጽና ተጠያቂ እንዲሆን ለማድረግና በተለይም በሚስጥራዊነትና በግልጽነት አሠራር መካከል ያለውን ሚዛን መጠበቅ በማስፈለጉ ነው፤›› በማለት፣ በአዋጁ ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ያስፈለገበትን ምክንያት የአዋጁ አባሪ ሰነድ ያስረዳል።

በዚህ መሠረት የመከላከያ ሠራዊቱ በየዓመቱ ከመንግሥት የሚያገኘውን በጀት፣ እንዲሁም ሠራዊቱ በሰላም ጊዜ የሚኖረውን የማምረት አቅም በመጠቀም የሚያመነጨውን ገቢ፣ ጥቅም ላይ የማይውሉ ንብረቶችን በማስወገድ የሚገኝ ገቢ፣ በተቆጣጣሪነት ከሚመራቸው ድርጅቶች (እንደ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን፣ መከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝና ሌሎች) የሚያገኘውን የትርፍ ድርሻና ከሰላም ማስከበር ሥምሪቶች የሚያገኘውን ገቢ (ለምሳሌ በተመድ ሥር ላሉ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር ለአንድ ሰላም አስከባሪ ወታደር በየወሩ አንድ ሺሕ ዶላር ለደመወዝ እንደሚከፍል ከተመድ ድረ ገጽ የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ) ይኼንን በተመለከተ፣ የፌዴራል የፋይናንስ አስተዳደር ሕጎችን ተከትሎ መጠቀም እንደሚገባውና በዚህ የገቢ አጠቃቀም ላይ የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር በየዓመቱ የኦዲት ቁጥጥር እንደሚያደርግ ተሻሽሎ ተደንግጓል።

በተጨማሪም መከላከያ ሠራዊቱ የተሟላና ትክክለኛ የሆነ የሒሳብ መዝገብ መያዝ እንዳለበት በማሻሻያው ተመልክቷል።

ሥራ ላይ የነበረው አዋጅ የአገር ጥቅምና ደኅንነትን ለመጠበቅ ሲባል ሚስጥር ናቸው የሚላቸውን ሰነዶች ለማንም አለማሳየት እንደሚችል የሚደነግገው አንቀጽ ከፍተኛ ማሻሻያ የተደረገበት ነው።

“በመከላከያ ሚኒስትሩና በጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹሙ አቅራቢነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገራዊ ጥቅምንና ደኅንነትን ለመከላከል ሲባል እጅግ ጥብቅ ሚስጥር ብሎ የሚሰይማቸውን የጦር መሣሪያና የውጊያ ቁሳቁስ የግዥ የሒሳብ መዛግብትና ሰነዶች፣ ለመረጃ የወጡ የክፍያ ማስረጃዎች እንዳይገለጽ ሊያደረግ ይችላል፤›› በማለት ደንግጓል።

በዚህም መሠረት ሚስጥር ተብለው ሊለዩ የሚችሉት የግዥ ዓይነቶች ተወስነው የተቀመጡ ከመሆኑ ባሻገር፣ ውሳኔውን ማን እንደሚሰጥ ጭምር በሕጉ አመልክቷል።

ከዚህ በተጨማሪ ለመከላከያ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም ያልነበሩ ኃላፊነቶችን በመስጠት፣ የተቋሙን የሀብት አጠቃቀም የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነት ይሰጣል።

ከእነዚህም መካከል መከላከያ በተቆጣጣሪነት የሚመራቸውን የልማት ድርጅቶችና የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽንን የመቆጣጠር፣ እንዲሁም እነዚህን ተቋማት ጨምሮ አጠቃላይ የመከላከያ ሠራዊቱ ሀብት ለታለመለት ዓላማ መዋሉን የመቆጣጠር ኃላፊነት ሰቪል ሆኖ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በፓርላማው በሚሾመው የመከላከያ ሚኒስትር ላይ ይጥላል።

ሌሎች ጉዳዮች

የተቋሙን የሀብት አጠቃቀም በጥብቅ ለመቆጣጠር ከተደረጉት ማሻሻያዎች በተጨማሪ፣ ሠራዊቱን ለማትጋትና ለማበረታታት የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች እንዲፈቀዱና ሕጋዊ ዕውቅና እንዲኖራቸው አድርጓል።

የመከላከያ ሠራዊት አባላት ወታደራዊ አገልግሎታቸውን በላቀ ሞራል እንዲያበረክቱ ለማበረታት እንደየ ብቃትና የአገልግሎት ዘመናቸው፣ የግል አውቶሞቢል ያለ ቀረጥ እንዲያስገቡና የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታ አመቻችቷል።

በሌላ በኩል የመከላከያ ሠራዊቱ በሚገኝባቸው አካባቢዎች ሊፈጸሙ የሚችሉ ወንጀሎች ስለመኖራቸው በቂ ጥርጣሬ በሚኖርበት ጊዜ፣ በየደረጃው ያለ አዛዥ ፈጣን ዕርምጃ የመውሰድ ግዴታ እንዲጣልበት አድርጓል። የበፊቱ አዋጅ ጥርጣሬ ያለው ማንኛውም በየደረጃው ያለ የሠራዊቱ አዛዥ ሕጋዊ ዕርምጃ ለመውሰድ ለአለቃው በማሳወቅ፣ አለቃውም ለወታደራዊ የፍትሕ አካል በስልክ ወይም በተቻለው የመገናኛ ዘዴ እንዲያሳውቅ ይገደድ ነበር።

ይሁን እንጂ በተደረገው ማሻሻያ ‹‹በወታደራዊ ካምፖች፣ ቢሮዎች፣ ወይም የግል የሠራዊት መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ጊዜ የማይሰጥና አደገኛ ወንጀል ወይም የፀጥታ መደፍረስ ሊከሰት ወይም ይከሰታል የሚል በቂ ጥርጣሬ ሲኖረው ያለ አዛዥ እስር ወይም ብርበራ ማካሄድ ይችላል፤›› የሚል ማሻሻያ ተደርጓል።

 በዚህ መንገድ የተደረገ እስር ወይም በብርበራ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት መደረግ ያለበት ሆኖ፣ ለማጓጓዝ ያለውን ጊዜ ሳይጨምር በ48 ሰዓት ወስጥ ለፍርድ ቤት ወይም እንደ ነገሩ ሁኔታ ለመደበኛ ፖሊስ መቅረብ እንዳለበት ይደነግጋል።

ማሻሻያዎቹን የያዘው አዋጅም ባለፈው ሳምንት በፓርላማው ፀድቋል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -