ከናይሮቢ በተሰማው ዜና መሠረት አራት የአፍሪካ አየር መንገዶች ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ለመፎካከር የሚያስችላቸውን የጋራ ስምምነት በማድረግ ጥምረት ለመፍጠር መነሳታቸው አነጋጋሪ ሆኗል፡፡
የኬንያ መገናኛ ብዙኃን ታኅሳስ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ባሠራጩት ዘገባ መሠረት፣ ተጣምረው የኢትዮጵያ አየር መንገድን ለመፎካከርና የበላይነቱን ለመቋቋም የተነሱት የደቡብ አፍሪካው ‹‹ሳውዝ አፍሪካን ኤርዌይስ››፣ የሞሪሸሱ ‹‹ኤር ሞሪሸስ››፣ የሩዋንዳው ‹‹ሩዋንዳኤር›› እንዲሁም የኬንያው አየር መንገድ ናቸው፡፡ እነዚህ አየር መንገዶች በጋራ በመሆን የገበያ ድርሻውን ለማስፋትና አቅማቸውን ለማሳደግ መነሳታቸውን ዘገባዎቹ አመላክቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በመጪው መጋቢት ወር የአፍሪካ አቪዬሽን ትብብር የተሰኘ ጥምረት ይፋ ለማድረግ ማቀዳቸውም ተሰምቷል፡፡
የአየር መንገዶቹ መጣመር የወጪ ቅነሳ እንዲያገኙ ከማስቻል ባሻገር የተሳለጠ የበረራ ማዕከል (ሀብ) ለመፍጠር፣ እንዲሁም የኮድ ሼር ስምምነት በማድረግ በርካታ መዳረሻዎችን ለማስፋፋትና የኢትዮጵያ አየር መንገድንና ከአፍሪካ ውጭ ያሉትን ኩባንያዎች በመፎካከር በአፍሪካ ያላቸውን ተደራሽነት ማስፋት በጥምረታቸው ለማሳካት ከሚፈልጓቸው መካከል የሚጠቀሱት ናቸው፡፡
የአፍሪካ አቪዬሽን ዘርፍ ከፍተኛ ታክስ፣ ከፍተኛ የአየር ትራንስፖርት ዋጋ የሚጠየቅበት፣ የአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ ውድ የሆነበትና፣ ደካማ የኤርፖርት መሠረተ ልማት የተንሰራፋበት ከመሆኑም ባሻገር፣ በአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ውስጥ የገልፍ አገሮች ኩባንያዎች ገበያውን የተቆጣጠሩት መሆኑ ፈታኝ ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ ጎልተው ይወጣሉ፡፡ በእነዚህ ጫናዎች ሳቢያም ከኤር ሞሪሸስ በስተቀር ሦስቱ አየር መንገዶች ያለፉትን አራት ዓመታት በኪሳራ ማሳለፋቸው በጥምረት ለመሥራት የሚያስችላቸውን ኅብረት ለመመሥረት ሲመክሩ መቆየታቸው ተሰምቷል፡፡ ከአንድ ዓመት በላይ በጉዳዩ ላይ ሲነጋገሩበት ስለመቆየታቸውም ተዘግቧል፡፡
እንዲህ ያሉት ዘገባዎች ቢወጡም በኦፊሴል መግለጫ የሰጠባቸው አካል አልተጠቀሰም፡፡ የኬንያ መገናኛ ብዙኃን ምንጮቻቸውን ዋቢ በማድረግ ከመዘገባቸው በቀር ይህ ነው የሚባል መግለጫ አላካተቱም፡፡ ይህም ሲባል ግን የኬንያ አየር መንገድ የቦርድ ሊቀመንበር ማይክል ጆሴፍ ከሌሎች የአፍሪካ አየር መንገዶች ጋር ውይይቶች እየተካሄዱ ስለመሆናቸው ከወራት በፊት ፍንጭ መስጠታቸው ሳይጠቀስ አልቀረም፡፡
ስለዚህ ጉዳይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የስትራቴጂክ ፕላንና ትብብር ዘርፍን በምክትል ፕሬዚዳንትነት የሚመሩት አቶ ሔኖክ ተፈራ፣ የአራቱ አየር መንገዶች ዜና እንግዳ እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡ ከመገናኛ ብዙኃን ከመስማታቸው ውጭ ስለጉዳዩ በኦፊሴል የሚያውቁትና የሰሙት ነገር እንደሌለ የጠቀሱት አቶ ሔኖክ፣ የነገሩ እውነትነት እንደሚያጠራጥራቸውም አልሸሸጉም፡፡
እንደ አቶ ሔኖክ ማብራሪያ ከሆነ፣ ዋናውን የአፍሪካን ገበያ የተቆጣጠሩት የውጭ አየር መንገዶች በተለይም የገልፍ አየር መንገዶች በመሆናቸው፣ 80 በመቶውን የአየር ትራስፖርት ገበያ ይዘው ባለበት ወቅት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን እንቀናቀናለን የሚለው የአራቱ ኩባንያዎች አካሄድ ከአየር ትራንስፖርት ንግድ አኳያ የማያስኬድ ነው፡፡
‹‹እኛም እንደ እናንተው ነው የሰማነው፡፡ እውነታውን ገና ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡ ነገር ግን የአፍሪካን ገበያ የተቆጣጠሩት ዋነኞቹ አየር መንገዶች የውጭዎቹ እንጂ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አይደለም፡፡ 80 በመቶውን ገበያ የተቆጣጠሩት እነሱ ናቸው፤›› ያሉት አቶ ሔኖክ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አቋም፣ ከዚህ ቀደም በነበረውም ሆነ በአሁን ወቅትና ወደፊትም ቢሆን ከሌሎች የአፍሪካ አየር መንገዶች ጋር አብሮ በመተባበርና በመሥራት የውጭ ተፎካካሪዎችን ጫና መቀነስ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ከፍተኛ የሚባሉት ወጪዎች ላይ በትብብር በመሥራት የገቢ ህዳግን ማስፋት የሚያስችሉ ትብብሮች ላይ ትከረት ማድረግ እንደሚያስሚፈልግ ሲያብራሩ፣ ትልልቅ ወጪዎች ከሚያስከትሉ ጉዳዮች መካከል የአውሮፕላን ኪራይ፣ የአውሮፕላን ጥገና፣ የአውሮፕላን ክፍሎችና መለዋወጫዎችና የመሳሰሉት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ በመሆናቸው እንዲህ ያሉትን ወጪዎች ለመቀነስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሌሎች የአፍሪካ አየር መንገዶች ጋር በመተባበርና በመተጋገዝ መሥራት ላይ ቅድሚያ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡
በመሆኑም የውጭ አየር መንገዶችን 80 በመቶውን የገበያ የበላይነት የያዙበትን አቅም በመፎካከር ቢያንስ ወደ 50 በመቶ መቀነስ የሚቻልበት ትብብር በአፍሪካ አየር መንገዶች መካከል እንደሚጠበቅ ያብራሩት አቶ ሔኖክ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድም በዚህ መሠረት በአፍሪካ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በአፍሪካ 80 በመቶውን የአየር ትራንስፖርት ተቆጣጥረዋል ከሚባሉት ውስጥ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶቹ ኢትሀድና ኤምሬትስ አየር መንገዶች ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር የኳታር አየር መንገድና የቱርክ አየር መንገድ ሰፋፊ የገበያ ድርሻ ይዘው ይገኛሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ እስከ 500 መዳረሻ ያላቸውና በነዳጅ ረገድም ድጎማ የሚረግላቸው ከፍተኛ ሀብት ያፈሩ አየር መንገዶች ናቸው፡፡
ከ120 በላይ የበረራ መዳረሻዎችን የፈጠረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የሩዋንዳ አየር መንገድን ጨምሮ ለበርካታ የአፍሪካ አየር መንገዶች የቴክኒክ ድጋፍና የጥገና አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ እንደ አቶ ሔኖክ ከሆነም የኢትዮጵያ አየር መንገዶች ቴክኒሻኖች የጥገና አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ አስታውሰዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የሥልጠና ድጋፎችም በአየር መንገዱ ያገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በከፊል የአክሲዮን ድርሻውን እንዲሸጥ በመንግሥት በተወሰነው መሠረት፣ ጥያቄዎች ከቀረቡለት አቅሙ ላላቸው የአፍሪካ አየር መንገዶች የተወሰኑ ድርሻዎችን ሊሸጥላቸው እንደሚችል የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ከቅርቡ ለሪፖርተር መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ሰማይ ከፍተኛውን የገበያ ድርሻ ከያዙት የውጭ ኩባንያዎች ጋር እየተፎካከረ የአፍሪካ አየር መንገዶች ከውድድር ውጪ እንዳይሆኑ እየታገለ የሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደሆነ የገለጹት አቶ ተወልደ፣ መዳረሻዎችን ከማስፋፋት ባሻገር ተወዳዳሪዎቹ ለሆኑ አየር መንገዶች የአቅም ግንባታና የቴክኒክ ድጋፍ ከመስጠት ባሻገር፣ ለኪሳራ የተዳረጉትም እንዲያንሰራሩ በማድረግ፣ ድርሻቸውን በመግዛትና በማስተዳደር ሥራዎች ውስጥ እየተሳተፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡