Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊበተማሩበት የመሥራት ፈተና

  በተማሩበት የመሥራት ፈተና

  ቀን:

  ከጠዋቱ አራት ሰዓት አካባቢ አራት ኪሎ ከሚገኘው ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ ሰሌዳ ዙርያ በርካታ ወጣቶች ዓይናቸውን ያማትራሉ፡፡ የተወሰኑት ደግሞ ክፍት የሥራ ቦታ የያዙ የጋዜጣ ክፍሎችን መሬት አንጥፈው የሚስማማቸውን ይፈልጋሉ፡፡ ከእነዚህ አንዱ የ23 ዓመቱ ናሆም ኃይለ ሥላሴ ነበር፡፡

  ‹‹በየቀኑ ጠዋት ጠዋት ከቃሊቲ አራት ኪሎ ከዚያም መገናኛ እየተመላለስኩ ክፍት የሥራ ቦታ ማማተር ከጀመርኩ አራት ወር አለፈኝ›› የሚለው ናሆም፣ በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ በ2010 ዓ.ም. መመረቁን፣ ከተመረቀ ጀምሮ ለትራንስፖርት ቤተሰቡን እያስቸገረ በየቀኑ ሥራ ፍለጋ እንደሚባትት ነግሮናል፡፡

  ‹‹ተመርቆ ሥራ አለመሥራት በጣም ያስጨንቃል፣ እውቀቴን እያጣሁት ነው፡፡ ለፍቼ የተማርኩትን ትምህርት ካልሠራሁበት ከውስጤ እየጠፋ ይሄዳል›› የሚለው ወጣቱ፣ ዘርፍ ለፈጠራ የተመቸ ቢሆንም የተመቻቸ ነገር ባለመኖሩ እውቀቱን ለመተግበር እንዳልቻለም ይናገራል፡፡

  እሱ በሠለጠነበት ዘርፍ በራስ ለመሥራት ወርክሾፕ እንደሚያስፈልግ፣ ለዚህ ደግሞ መነሻ ካፒታል ወሳኝ እንደሆነ በመግለጽም፣ መንግሥት ወርክሾፖችን ባላዘጋጀበት ተማሪዎች መፍጠር ስለቻሉ ብቻ ራሳቸውን ለመቅጠር እንደማይችሉም ይገልጻል፡፡

  ለአፓረንትሺፕ በወጣበት ጊዜ በሠራበት መሥሪያ ቤት ችግር ማየቱን፣ ችግሩን የሚፈታ ዲዛይን መቅረፅ እንደሚቻል ይህን ለማድረግ ግን እውቀቱ ያላቸው ተማሪዎች ተሰባስበው መፍትሔ የሚነድፉበት ወርክሾፕ በመንግሥት መዘጋጀት እንዳለበትም ይናገራል፡፡

  ከዲላ ዩኒቨርሲቲ በሰው ኃይል አስተዳደር ተመርቆ ለሁለት ዓመት ያህል የሠራው አቶ እሸቱ አሻግሬ ደግሞ፣ ዘርፍ ክፍት የሥራ ቦታ የሚወጣበት ቢሆንም እድሉን ለማግኘት ከባድ መሆኑን፣ ለአንድ የሥራ መደብ እስከ አንድ ሺሕ ሰው እንደሚያመለከት ይህንንም የፈጠረው ያልተመጣጠነ ፍላጎትና አቅርቦት መሆኑን ይናገራል፡፡

  ከጋዜጣ ላይ ክፍት የሥራ ቦታ እየፈለገ ስናገኘውም፣ ከዚህ ቀደም 2,700 ብር ተቀጥሮ ከሚሠራበት መሥርያ ቤት የለቀቀው ደመወዙን የቤት ኪራይ የሚወስደው በመሆኑ ኑሮን መቋቋም አቅቶት የራሱን ሥራ ለመፍጠር በዝግጅት ላይ ስለሆነ እንደሆነ ነግሮናል፡፡

  ከወሎ ዩኒቨርሲቲ በአፕላይድ ፊዚክስ ለተመረቀችው መስተዋት ክፈተው ግን ሁኔታዎች ግራ የሚያጋቡ ሆነውባታል፡፡ አፕላይድ ፊዚክስ ተብሎ የሚወጣ ክፍት የሥራ መደብ ማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነባቸው አባቷ አቶ ክፈተው ዳኜ ይናገራሉ፡፡ አቶ ክፈተው እንደሚሉት፣ ልጃቸው መስተዋት በ2010 ዓ.ም. በዲግሪ ከተመረቀች ወዲህ በዘርፉ እንድትሠራ ቢመኙም ይህ አልሆነም፡፡ ያለ ትምህርት ዘርፏ አስተማሪነት ብታገኝ እንኳን ብለው ቢለፉም አልተሳካም፡፡ ከትምህርቱ ጋር ተያያዥነት ያለው መሥሪያ ቤት ፈልገው ቢያነጋግሩም ለጊዜው ክፍት የሥራ ቦታ የለም ተብለዋል፡፡ ‹‹ልጄ ቤት ቁጭ ብላለች፡፡ በጭንቀት እንዳትጎዳብን እሠጋለሁ›› የሚሉት አቶ ክፈተው፣ በተማረችበት ትምህርት የራሷን ሥራ ለመሥራት እንኳን እንዴት መሥራትና ምን መደረግ እንዳለበት ለማወቅም አስቸጋሪ መሆኑን፣ ትምህርቱን ወደ ተግባር ለመቀየር እንኳን ብዙ የምርምር ቁሳቁሶችንና ገንዘብን ብሎም ልምድንና በጋራ አብሮ መሥራትን የሚጠይቅ በመሆኑ የሚታሰብ እንዳልሆነም ይገልጻሉ፡፡

  በተማሩት ትምህርት ሥራ አለማግኘት፣ ራስንም ለመቅጠር የተመቻቸ ሁኔታ አለመኖር፣ ተማሪዎች ፍላጎታቸው ባልሆኑ የትምህርት ዘርፎች መመደብ፣ በየዩኒቨርሲቲዎች አዲስ ከተከፈቱ ፕሮግራሞች ተመርቆ ሥራ አለማግኘትና በአጠቃላይም ለሥራ አጥነት አንዱ መንስኤ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት አለማግኘትና አለመማር ነው፡፡

  ለዚህም ትምህርት መስፋፋት አለበት፣ ዜጎች መማር አለባቸው፣ ለአገር ዕድገት  የሰው ኃይል ያስፈልጋል በሚል ታቅዶ በትምህርቱ ዘርፍ እየተሠራበት ነው፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሠለፍ የሚደረገው ጥረት ቀላል አይደለም፡፡ ይህንን ከግብ ለማድረስ 46 ዩኒቨርሲቲዎች ሥራ ላይ መሆናቸውን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ይገልጻል፡፡ በዚሁ ልክም በየዩኒቨርሲቲዎቹ የተከፈቱ የትምህርት ክፍሎች በዝተዋል፡፡

  በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሰው ኃይል ልማት ይሆናሉ የሚባሉ ፕሮግራሞች እንዴት ይከፈታሉ?

  በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የምርምርና አካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል  ኤባ ሚጀና (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ ፕሮግራም የሚከፈተው በዲፓርትመንት ጥናት ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው የትኛው ዘርፍ የትኛውን አገልግሎት ይፈልጋል፣ መረጃው እንዴት ተሰብስቧል፣ ምን መሠራት አለበት በሚለው ላይ የፍላጎት ዳሰሳ አካሂዶ፣ በዲፓርትመንት ካውንስል ተገምግሞ፣ ሥርዓተ ትምህርቱ ተዘጋጅቶና የዩኒቨርሲቲው የውስጥ አካላት በተገኙበት ተፈትሾ ይሁንታ ካገኘ በኋላ በዩኒቨርሲቲው ሴኔትና ቦርድ ይታያል፡፡ ይህንን አልፎ  በቀድሞው ትምህርት ሚኒስቴር በአሁኑ ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ታይቶ ፕሮግራሙ መከፈት ካለበት ይሁንታ አግኝቶ ለዩኒቨርሲቲው ይላካል፡፡

  ይህንን ሁሉ ሒደት አልፈው የተከፈቱ ፕሮግራሞች ግን ችግር ሊገጠማቸው እንደሚችል ዶ/ር ኤባ ይገልጻሉ፡፡ አንዳንዴም ዲፓርትመንቶች ይህንን አካሄድ ሳይከተሉ ሊከፈቱ ይችላሉ፡፡ አሁን ግን ይህንን ለማስቀረት ዝርዝር የአሠራር መመርያ እየተዘጋጀ ነው፡፡

  በትምህርት ዘርፍ ፍላጎት ምንድነው?  

  በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ለብዙ ዓመታት መነጋገሪያ የሆነውና ተማሪውም በተደጋጋሚ የሚጠይቀው ፍላጎቱ ባልሆነው የትምህርት ዘርፍ እንዲማር መገደዱን ነው፡፡ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሕክምና ትምህርትና ሌሎችም ማኅበረሰቡ በሚያደንቃቸው ዘርፎች የሚማሩበት ዕድል አለ፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ሕክምና መማር የአገሪቱ ፍላጎት ይሁንም አይሁን፣ ተማሪው ይፈልገውም አይፈልገውም የቤተሰብና በአጠቃላይም ከውጭ ያሉ ግፊቶች ተማሪዎችን ስለሚያስገድዱ ያለ ፍላጎት ወደ ዘርፉ የሚገቡም አሉ፡፡ ከዚሁ በተቃራኒ ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው ምናልባት የሕክምና ትምህርት በመሠረታዊነት ለማይጠይቀው ሒሳብና ፊዚክስ መለስተኛ እውቀት ኖሯቸው፣ በባዮሎጂና ሌሎች በሚነበቡ ትምህርቶች ክህሎትና ለሕክምና ትምህርትም ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት ባለማስመዝገባቸው ብቻ ወደማይፈልጓቸውና አንችላቸውም ብለው ወደሚገምቷቸው የቁጥርና የፊዚክስ ቀመርን አፍታትቶ ማወቅን ወደሚጠይቁ ትምህርት ክፍሎች ሲገቡ ይስተዋላሉ፡፡

  በዚህ ላይ አስተያየት የሰጠን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፎሪን ፖሊሲና ዲፕሎማሲ የድኅረ ምረቃ ሁለተኛ ዓመት ተማሪ ሙሉቀን አየለ እንደሚለው፣ በከፍተኛ ትምህርት የሚሰጡ የትምህርት ዘርፎችን ለመማር ተማሪው የሚያመጣው ውጤት ይወስነዋል፡፡ ‹‹የምናመጣው ውጤት እንጂ ፍላጎታችን የምንማረውን አይወስነውም›› የሚለው ሙሉቀን፣ በተማሩበት ዘርፍ ሥራ ለማግኘትም ሆነ ራስን ለመቅጠር አዳጋች የሆነው ተማሪው ከአፀደ ሕፃናት ጀምሮ ለሚፈለገው ግብ ተቀርፆ ካለመማሩም በተጨማሪ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቆ ከወጣ በኋላ የተመቻቸ ሁኔታ ባለመኖሩ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡

  ለመሥራት ዕድሎች ቢኖሩም አቅጣጫ የሚያሳይ ባለመኖሩም ብዙ ተመራቂ ተማሪዎች ባልተማሩበት ዘርፍ ሲሠሩ፣ አሊያም የትምህርት ዘርፍ ቀይረው የማታ ሲማሩና ገበያ ወዳላቸው የሥራ ዘርፎች ሲቀላቀሉ ይስተዋላሉ የሚለው ሙሉቀን፣ ባልተማሩበት ዘርፍ ለመሥራት ከመገደድ ጎን ለጎንም ታች ከመጀመርያ ደረጃ ጀምሮ መሠረት ያልተጣለባቸው ትምህርቶች ዩኒቨርሲቲ ላይ በዲፓርትመንት ተከፍተው ተማሪዎች ያለምንም መሠረት የሚጀምሯቸው መሆኑም በመማር ማስተማሩ ሒደት ያሉትን በሙሉ ያደናግራሉ ይላል፡፡ ፊሎሶፊና የውጭ ግንኙነት ትምህርትንም ለአብነት ያነሳል፡፡ ፍላጎት ከሥር ታንጾ እንዲያድግም በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የሚከፈቱ ፕሮግራሞችን ያማከለ ትምህርት ከታች ጀምሮ ቢሰጥ ተማሪዎችንም አገርንም መጥቀም ይቻላል ብሏል፡፡

  ዶ/ር ኤባ አንድ አገር ለማደግ የሚያስቀምጠውን ስትራቴጂ ለመተግበር የሚያስፈልጉ ትምህርቶችንና የሰው ኃይልን እንደሚያስቀምጥና የትምህርት ሥልጠና የሚሰጠውም የአገሪቷና የዘርፍ ፍላጎት ታየቶ ተማሪው ተመርቆ ሥራ ለመፍጠር ይችላል አይችልም ተብሎ ጥናት ተካሂዶ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

  ሆኖም በቅርቡ ተረቅቆ በውይይት ላይ የሚገኘው የትምህርት ፍኖተ ካርታ በትምህርት ፕሮግራሞች ላይ ክፍተት እንደነበር አሳይቷል፡፡ 

  በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ተማሪው የሚመርጠው የትኛውን ፕሮግራም ነው?

  ሰው የፍላጎቱን መርጦ መማር እንዳለበት ቢታመንም ኢትዮጵያ ለዕድገቷ ከሚያስፈልጋት የተማረ የሰው ኃይል አንፃር ይህንን ማስተናገድ አልተቻለም፡፡ አስገዳጁ ሁኔታ የአገሪቷ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ልጆች በወላጆቻቸው ተፅዕኖ የሚማሩበት ሁኔታ መኖሩም ነው፡፡ ወላጆች ማኅበረሰቡ ያገዘፈውንና ገበያ አለው ብለው በሚያምኗቸው የሕክምና፣ የበረራና ሌሎችም ትምህርቶች ልጆቻቸው እንዲገቡ ግፊት ማድረጋቸውም የተለመደ ነው፡፡ ተማሪዎች በራሳቸው ፍላጎት ለመማርም ቢሆን ስለ ምርጫቸው ወላጆችንና የአካባቢያቸውን ሰዎች አማክረው በሚያገኙት የተለያየ ግብረ መልስ ፍላጎታቸው ያልሆነው ላይ የሚወድቁበት አጋጣሚ አለ፡፡ በራስም ሆነ በአገሪቷ ፍላጎት ላይ ለመማር መሠረት የሚጣልበት የትምህርት ሥርዓትም እምብዛም የለም፡፡

  በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የፋርማሲ ትምህርት ቤት መምህር አቶ መልዓክ ገዳሙ፣ ሕክምና ትምህርት ውስጥ የገቡት በቤተሰብ ጫና እንጂ የሳቸው ፍላጎት ሆኖ እንዳልነበር ያስታውሳሉ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው በሒሳብ፣ ፊዚክስና ኬሚስትሪ ከፍተኛ ውጤት እንደነበራቸውና እነዚህን ትምህርቶች ከሌላው አብልጠው እንደሚወዱ እንደ አጠቃላይ ግን ጎበዝ በመሆናቸውና ጥሩ ውጤትም በማምጣቸው ዛሬ ባልገመቱት ቦታ ላይ የፋርማሲ ትምህርት ቤት መምህር መሆናቸውን ያወሳሉ፡፡ የሳቸው ፍላጎት የነበረው ግን የቁጥር ቀመር ካላቸው የትምህርት ዘርፎች ላይ መገኘት ነበር፡፡

       አቶ መልዓክ እንደሚሉት፣ ተማሪዎች በአገር ፍላጎትም ሆነ በወላጅ ተፅዕኖ ምክንያት በፍላጎታቸውም ሆነ ያለ ፍላጎታቸው ከፍተኛ ትምህርት ገብተው ለሚማሯቸውና ለሚመረቁባቸው ትምህርቶች ወደ ሥራ መተግበር በአገሪቱ የተመቻቹ ሁኔታዎች መኖር አለባቸው፡፡ ዲፓርትመንት ሲከፈትም ተማሪዎቹ ሲመረቁ ምን ይሠራሉ? የት ይሠራሉ? በተማሩት ራሳቸውን መቅጠር ይችላሉ ወይ? የሚለው አጀንዳ ትኩረት ተሰጥቶትም ሊሠራ ይገባል፡፡

  በተለይ አዳዲስ ዲፓርትመንቶች ሲከፈቱ ለተማሪውም ሆነ ለመምህሩ ግራ የሚያጋቡ፣ በትምህርት ክፍሎቹ የሚሠሩ መምህራን ስለሚያስተምሩት ትምህርት ራሳቸውን ለማብቃት የሚያስችል የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ትምህርት ስለመኖሩ መረጋገጥ አለበት ይላሉ፡፡

  የማስተርስ ተማሪ ማስተርስ የሚያስተምርበት፣ የትምህርቱ ዘርፍ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የፔኤችዲ ትምህርት የማይገኝለት እንዳይሆንም መጠንቀቅ እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡

  ተማሪዎች ወይም ማኅበረሰቡ የሚመርጧቸው ፕሮግራሞችም ቢሆኑ ለምን ይመረጣሉ? የማይመርጡትስ ለምንድነው? የሚለውን መፈተሽ አስፈላጊ ነው፡፡

  ዶ/ር ኤባ እንደሚሉት፣ ለምሳሌ ፊዚክስ አስፈላጊ ትምህርት ነው፡፡ ነገር ግን በተማሪዎች ብዙ ላይመረጥ ይችላል፡፡ በመሆኑም ፕሮግራሞች እንዴት ይመረጣሉ? ተማሪዎች በእያንዳንዱ ፕሮግራም ላይ እውቀት አላቸው ወይ? የሚለው መሠራት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ተማሪው ከታች ጀምሮ ለሳይንስ፣ ለኢንጂነሪንግ፣ ለጤና ትምህርትና ለሌሎቹ ያለው ፍላጎት ምን ይመስላል የሚለው መታየት አለበት፡፡

  ‹የተማሪው ፍላጎት ከሦስትና አራት የትምህርት ዘርፎች አይዘልም፤›› የሚሉት ዶ/ር ኤባ፣  አመለካከት ለውጥ ለማምጣት ከመዋዕለ ሕፃናት ጀምሮ ሠርቶ የአገሪቷን ሁኔታ መቀየር ያስፈልጋል ሲሉም አክለዋል፡፡

  እያንዳንዱ ፕሮግራም ለአገሪቷ እንደሚያስፈልግና መሠራት ያለበት ተማሪዎች እንዴት ይማራሉ፣ ራስን ለመቅጠርም ሆነ ተቀጥሮ ለመሥራት ምን ያስፈልጋል፣ የሚለውን ለይቶ ማወቅና አሁን ያለው የተማሪው ፍላጎት ከልምድ፣ ወይም ከሌሎች ልምድ በመነሳት በመሆኑ ከታች ጀምሮ ለመሥራት የሚያስችል ብሔራዊ ስትራቴጂ እንዲኖር በሐሳብ ደረጃ መያዙንም ነግረውናል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የትምህርትና ሥልጠና ችግሮችን የሚለይና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የሚያስቀምጥ የአጠቃላይ ትምህርት ፍኖታ ካርታ እየተዘጋጀ ነው፡፡

  በረቂቅ ላይ ያለው ፍኖተ ካርታ ፋይዳ

  በኢትዮጵያ ያለውን የትምህርት ጥራት ለማሻሻልና እየተንከባለሉ የመጡና ለአገሪቷም ሆነ ለዜጎቿ ፈተና የሆኑ የትምህርቱ ዘርፍ ችግሮችን ለመቅረፍ ያስችላል የተባለ የትምህርት ፍኖተ ካርታ በምሑራን ተረቆ ከከፍተኛ ባለሥልጣናት እስከ ወረዳና ብሎም ማኅበረሰቡ እንዲወያይበት ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡

  የትምህርት ፍኖተ ካርታው በትምህርት ዘርፍ ያሉ ችግሮችን በመቅረፍም የአገሪቷን ለውጥ ያረጋግጣል፣ ብቁ ዜጎችን ለማውጣት ያስችላል የሚል እምነትም ተጥሎበታል፡፡ ዶ/ር ኤባም ፍኖተ ካርታው አጠቃላይ በትምህርቱ ዘርፍ ያሉ ችግሮችን በመቅረፍ የአገሪቷን ልማት ያፋጥናል ብለዋል፡፡

  ከአፀደ ሕፃናት አንስቶ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርት እንዴት ይመራል፣ ሥርዓተ ትምህርቱ ምን መሆን አለበት፣ ፕሮግራሞች እንዴት ይከፈታሉ? የመምህራን ሥልጠና በምን መልኩ መሆን አለበት? የሚሉትንና ሌሎችም የትምህርቱ ዘርፍ አንኳር አጀንዳዎችን የሚያነሳና ችግሮችን የሚፈታ ነው፡፡

  ተማሪዎች ትምህርት ሲገቡ ጀምሮ ፍላጎታቸውና ችሎታቸው እየታየ የሚማሩበትና እንዴት አቅጣጫ መያዝ እንደሚችሉ፣ መምህራንም ለተማሪዎቻቸው ለራሳቸውም ለአገራቸውም የሚሆን እውቀት እንዲያስጨብጡ በሚያስችል መልኩ ይሰለጥናሉ፡፡

  ‹‹እንደ ባለሙያ የማያስፈልግ ፕሮግራም የለም›› የሚሉት ዶ/ር ኤባ የአጠቃቀምና የእውቀት ማነስ ችግሩን ፈጥሮታል ብለዋል፡፡

  ‹‹የተማረ ሁሉ መቀጠር አለበት ብለን ካሰብን ብዙ ፕሮግራም አያስፈልግም ልንል እንችላለን፣ ችግሩ የፕሮግራሙ ሳይሆን የትምህርት ጥራቱ ላይ ትኩረት ሰጥቶ አለመሥራት ነበር፤›› በማለትም ፍኖተ ካርታው ተማሪው የሚማረውን ትምህርት ዓላማና ምንነት፣ በትምህርቱ ምን መሥራት እንደሚችል አውቆና አቅጣጫ ተሰንቆለት እንዲወጣ የሚያደርግ ይሆናል ብለዋል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img