Wednesday, December 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ለኢትዮጵያ አየር መንገድ አዳዲስ የቦርድ አባላት ተሾሙ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ሦስት አዳዲስ የቦርድ አባላት ሾሙ፡፡

  የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ግርማ ዋቄ፣ የናሽናል ኦይል ካምፓኒ (ኖክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ጥላሁንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አክሊሉ ኃይለ ሚካኤል (ዶ/ር) የአየር መንገዱን የዳይሬክተሮች ቦርድ እንደተቀላቀሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ቦርዱ ታኅሳስ 13 ቀን 2011 ዓ.ም. መደበኛ ስብሰባውን ባካሄደበት ዕለት አዲሱ የቦርድ አባላት ትውውቅ መደረጉ ታውቋል፡፡

  ዘጠኝ አባላት ያሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዳይሬክተሮች ቦርድ በቀድሞ አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ ሊቀመንበርነት የሚመራ ሲሆን፣ አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ ናቸው፡፡

  አንድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ አቶ ግርማ ዋቄ በቦርድ አባልነት ተመልሰው መምጣታቸው ለአየር መንገዱ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ ‹‹በአቶ ግርማ ሹመት ደስተኞች ነን፡፡ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ያካበቱትን ልምድ የሚያካፍሉን ስለሆኑ ተጠቃሚ እንሆናለን፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ማኅበረሰብ ውስጥ እንደ አባት የሚታዩ ናቸው፤›› ብለዋል ኃላፊው፡፡

  አቶ ግርማ ያደጉበትን የኢትዮጵያ አየር መንድ እንደገና ለማገልገል ዕድል በማግኘታቸው መደሰታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹ምንም ጊዜ ቢሆን ብሔራዊ አየር መንገዳችንን ለማገልገል ፈቃደኛ ነኝ፡፡ ከባልደረቦቼ ጋር ሆነን አየር መንገዱን በብቃት እንደምናገለግል እርግጠኛ ነኝ፤›› ብለዋል፡፡

  አቶ ግርማ በወጣትነታቸው ኢትዮጵያ አየር መንገድ በመግባት፣ እዚያው ተምረውና አድገው በተለያዩ ኃላፊነት ቦታዎች ለ34 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በመካከል ቅሬታ አድሮባቸው ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሄደው የገልፍ አየር መንድንና ዲኤችኤል ኩባንያን በኃላፊነት አገልግለዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2004 የኢትዮጵያ መንግሥት ያቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው አየር መንገዱን ለሰባት ዓመት በዋና ሥራ አስፈጻሚነት መርተዋል፡፡

  አቶ ግርማ ያቀረቡት የሥራ መልቀቂያ ተቀባይነት አግኝቶ እ.ኤ.አ. በ2011 በጡረታ ተሰናብተዋል፡፡ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ከለቀቁ በኋላ የሩዋንዳ አየር መንድ የቦርድ ሊቀመንበር፣ የሩዋንዳ የትራንስፖርት ሚኒስትር የአቪዬሽን ጉዳዮች አማካሪ በመሆን አገልግልዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የቶጎ ፕሬዚዳንት ልዩ አማካሪ በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኅብረት ኢንሹራንስ ቦርድ ሰብሳቢ ናቸው፡፡

  ከአዲሱ የቦርድ አባላት ሹመት ጥያቄ ያስነሳው የአቶ ታደሰ ጥላሁን ነው፡፡ አቶ ታደሰ የኖክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆናቸው ኩባንያቸው ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የአቪዬሽን ነዳጅ የሚያቀርብ ስለሆነ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦርድ አባል ሆነው መሾማቸው የጥቅም ግጭት ይፈጥራል የሚል አስተያየት ከባለድርሻ አካላት እየተሰነዘረ ይገኛል፡፡ በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አቶ ታደሰ፣ እሳቸው የተሾሙት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ በመሆኑ በመሠረተ ሐሳቡ እንደሚስማሙ ገልጸዋል፡፡

  የነዳጅ ግዥ በጨረታ የሚካሄድ በመሆኑ ቦርድ ዘንድ የሚቀርብ ጉዳይ እንዳልሆነ ገልጸው፣ በተለየ ምክንያት ለቦርድ የሚቀርብ ከሆነ ግን ራሳቸውን ከቦርድ ስብሰባው እንደሚያገሉ ተናግረዋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች