Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመንግሥታዊ  ያልሆኑ ድርጅቶችን ተሳትፎ ገድቦ የቆየውን ሕግ የሚያሻሻል ረቂቅ ለፓርላማ ተላከ

መንግሥታዊ  ያልሆኑ ድርጅቶችን ተሳትፎ ገድቦ የቆየውን ሕግ የሚያሻሻል ረቂቅ ለፓርላማ ተላከ

ቀን:

መንግሥታዊ ያልሆኑ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በፖለቲካዊና በሰብዓዊ መብቶች መከበር ያደርጉ የነበረውን ንቅናቄ ላለፉት አሥር ዓመታት ገድቦ የቆየውን ሕግ የሚተካ፣ በከፍተኛ ደረጃ የሚያሻሽልና ማንኛውም መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በፈለገው ዘርፍ መሰማራት እንዲችል የሚፈቅድ ረቂቅ ሕግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተላከ።

የሚኒስሮች ምክር ቤት ከቀናት በፊት ያፀደቀው ይህ የሕግ ሰነድ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ረቂቅ አዋጅ የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት  ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩን ለማረጋገጥ ተችሏል።

ረቂቅ አዋጁ በፍጥነት እንዲፀድቅ መንግሥት የሚፈልግ ስለሆነ፣ ምክር ቤቱ ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲመለከተው አፅንኦት ተሰጥቶበት መላኩንም ሪፖርተር ለማወቅ ችሏል። ረቂቁ የሚፀድቅ ከሆነ በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ የሚገኘውንና በአገር ውስጥ የሚገኙ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶችንም ሆነ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ አፋኝ ተብሎ ሲተች የነበረውን የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ ቁጥር 621/2001 እና ሌሎች ተመሳሳይ ሕጎችን የሚሰርዝ ነው።

ይህ በሥራ ላይ የሚገኘው አዋጅ አገር በቀል የሆኑና 90 በመቶ የሚሆነውን መንቀሳቀሻ በጀታቸውን ከአገር ውስጥ የሚያመነጩ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ብቻ በፖለቲካና ሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ዙሪያ መንቀሳቀስ የሚችሉ መሆናቸውን በመደንገጉ፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች የፖለቲካና የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ በማድረግ ረገድ ቀደም ብሎ የነበራቸው ሚና በእጅጉ እንዲገደብ፣ በርካቶቹም እንዲፈርሱና አዳዲስ ድርጅቶችም እንዳይመሠረቱ ምክንያት መሆኑ ይጠቀሳል።

የውጭ አገር የሲቪክ ማኅበራት በኢትዮጵያ ውስጥ መንቀሳቀስ የሚችሉት ከፖለቲካዊና ከሰብዓዊ መብት ጉዳዮች በመለስ ባሉ የልማትና የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ ብቻ እንዲሆን፣ በፖለቲካዊና የሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ ለመሳተፍ ከተመሠረቱ አገር በቀል ድርጅቶች ሊያደርጉ የሚችሉት የፋይናንስ ድጋፍ ከአሥር በመቶ መብለጥ እንደማይችል ይኸው ሕግ የሚደነግግ መሆኑ፣ የሲቪክ ማኅበራት እንቅስቃሴን እንዳዳከመው ሲነገር ቆይቷል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰሞኑን ያፀደቀው ማሻሻያ ረቂቅ ሕግ ከላይ የተዘረዘሩትን አፋኝ ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ በመሰረዝ፣ ማንኛውም የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅት በመረጠው ዘርፍ መሰማራት የሚችልበትን ሁኔታ ይፈጥራል።

ሪፖርተር ያገኘው ይህ ረቂቅ ሰነድ ‹‹የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅት ማለት ሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ሰዎች ፈቃደኝነት የሚመሠረት የመንግሥት አካል የሆነ፣ ለትርፍ ያልተቋቋመ፣ ሕጋዊ ዓላማን ለማሳካት ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ ስብስብ ሲሆን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ የሙያ ማኅበራትንና  ኅብረቶችን ያጠቃልላል፤›› የሚል ትርጓሜ ይሰጠዋል።

የሲቪክ ማኅበራቱ የተቋቋሙበትን ዓላማ ለመወጣት የሚያስፈልጋቸውን ፋይናንስ ከሚያመነጩበት በመነሳት በፖለቲካና በሰብዓዊ መብት መንቀሳቀስ እንዳይችሉ የሚከለክለው ድንጋጌም ከረቂቁ የወጣ ሲሆን፣ የፋይናንስ ምንጫቸውን ከየትም ማግኘት እንደሚችሉ ነገር ግን በመተዳደሪያ ደንባቸው መሠረት መንቀሳቀስ እንደሚኖርባቸው በረቂቁ ተካቷል።

 በሥራ ላይ የነበረው ሕግ ተቋማቱ የሚያገኙትን ፋይናንስ 70 በመቶ ለተቋቋሙበት ዓላማ እንዲያውሉ፣ የተቀረው 30 በመቶ ደግሞ ለአስተዳደራዊ ወጪ በሚል የተቀመጠው ድንጋጌ ሌላው የተቋማቱን እንቅስቃሴ አሰናክሏል በሚል የሚተች ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ማሻሻያ ያደረገው ረቂቅ ሰነዱ ለተቋቋሙበት ዓላማና ለአስተዳደር የሚያውሉትን ምጣኔ 80/20 ሆኖ እንዲሻሻል ደንጋጌ አስቀምጧል፡፡ ይሁን እንጂ አስተዳደራዊ ወጪ ለሚለው ሰፊ የሆነ ትርጓሜ ይሰጣል።

‹‹የአስተዳደር ወጪ ማለት ድርጅቱ ከሚያከናውነው የፕሮጀክት ሥራ ጋር ተያያዥነት የሌለው፣ ነገር ግን ለድርጅቱ ህልውና ቀጣይነት አስፈላጊ የሆነና ከአስተዳደር ሥራዎች ጋር የተያያዘ ወጪ ሲሆን፣ የአስተዳደር ሠራተኞች የደመወዝና ጥቅማ ጥቅሞችን፣ ከአስተዳደር ሥራ ጋር የተያያዙ የአላቂና ቋሚ ዕቃዎች ግዥን፣ የጥገናና የእድሳት ወጪዎችን፣ የቢሮ ኪራይ፣ የፓርኪንግ ክፍያዎች፣ የኦዲት አገልግልት፣ የማስታወቂያ ክፍያ፣ የባንክ አገልግሎት፣ የመብራት፣ የስልክ፣ የፋክስ፣ የውኃ፣ የኢንተርኔት፣ የፖስታና የኅትመት አገልግሎት ወጪዎችን፣ ለታክስ፣ ለአስተዳደር ሥራ የሚውሉ ተሽከርካሪዎች ግዢ፣ ጥገና፣ የነዳጅና ዘይት፣ የመድን ግዥ ወጪዎችን፣ የቅጣት ክፍያዎችን፣ እንዲሁም የጥብቅና አገልግሎት ክፍያን ያካትታል፤›› በማለት ትርጓሜ ይሰጣል።

 ረቂቁ በጥቂት ቀናት ውስጥ ለምክር ቤቱ ስብሰባ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...