Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናሰማያዊ ፓርቲ ከአርበኞች ግንቦት ሰባትና ከኢዴፓ ጋር ሊዋሀድ ነው

ሰማያዊ ፓርቲ ከአርበኞች ግንቦት ሰባትና ከኢዴፓ ጋር ሊዋሀድ ነው

ቀን:

የተመሠረተበትን ሰባተኛ ዓመት ዛሬ በሚያካሂደው ጠቅላላ ጉባዔው የሚያከብረው ሰማያዊ ፓርቲ፣ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ንቅናቄ፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ጋር ውህደት ለመፈጸም የሚያስችሉ ሥራዎችን ማጠናቀቁን፣ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ አስታወቁ፡፡

ፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔውን እሑድ ታኅሳስ 21 ቀን 2011 ዓ.ም. እንደሚያደርግ ያስታወቁት ሊቀመንበሩ፣ በፓርቲው ሰባተኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ላይ ከውህደት ጋር በተያያዘ በየደረጃው ውሳኔ የተላለፈበት ሐሳብ በጉባዔው የመጨረሻ ውሳኔ ይፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡

ረቡዕ ታኅሳስ 17 ቀን 2011 ዓ.ም. በወቅታዊ ጉዳዮችና እየተከናወነ ስላለው የውህደት እንቅስቃሴ ‹‹የሰማያዊ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታና የሕዝባችንን የዘመናት ጥያቄ የሚመልስ እንደሚሆን እናምናለን›› በሚል ርዕስ በፓርቲው አመራሮች በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ ፓርቲዎች በጋራ በመሥራት ለፖለቲካዊ ችግሮችና ለሕዝቡ ጥያቄዎች የማያዳግም ምላሽ መስጠት እንደሚጠበቅባቸው በአፅንኦት አስታውቀዋል፡፡

በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ከመላው የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ የጉባዔው አባላት እንደሚሳተፉ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በውህደት አጀንዳ ላይ ከመወያየትና የመጨረሻ ውሳኔ ከመስጠት ባለፈ፣ ‹‹ፓርቲው በሰባት ዓመታት የትግል ወቅት ያበረከተው ጉልህ አስተዋጽኦ ይዘክራል፤›› ሲሉ የፓርቲው አመራሮች አክለው ገልጸዋል፡፡

ስለፓርቲዎች በጋራ የመሥራትና የመዋሀድ አጀንዳን በተመለከተ ደግሞ ሰማያዊ ፓርቲ ባለፉት ሁለት ዓመታት በዓላማ ከሚመሳሰሉት ጋር ለመዋሀድ በከፍተኛ ቁርጠኝነት ሲሠራ መቆየቱን በማስታወስ፣ ‹‹ባለፉት ዓመታት ፓርቲው ያከናውነው ጥረት ፍሬ አፍርቶ እነሆ በአሁኑ ወቅት ከአርበኞች ግንቦት ሰባት፣ ከኢዴፓና ከሌሎች ጋር ውህደት በመፈጸም ለኢትዮጵያ ሕዝብ የቆመ በጠንካራ መሠረት ላይ የተዋቀረ ፓርቲ በጋራ ለመመሥረት በዋዜማው ላይ እንገኛለን፤›› በማለት ፓርቲው ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመሥራት ሲያደርገው የነበረው ጥረት ወደ መሳካት ደረጃ መድረሱን አስታውቋል፡፡

አዲሱ ፓርቲም ለአገር ሰላም መሆንና ለሕዝብ መረጋጋት፣ እንዲሁም በቀጣይ በምርጫ ፖለቲካ ብቻ የሚደረግ የሥልጣን ሽግግር ውጤታማ እንዲሆን የድርሻውን ይወጣል የሚል እምነት እንዳለው የፓርቲው አመራሮች አስታውቀዋል፡፡

በመጨረሻም በየፊናቸው ለመቆም የሚውተረተሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም ሲሉ ወደ አንድነት መስመር ሊሰባሰቡ እንደሚገባ በመጠቆም፣ ‹‹የዜግነት ፖለቲካ እንዲያብብ የሚፈልጉ ፓርቲዎች፣ ስብስቦችና ግለሰቦች በዚህ የሰማያዊ፣ የአርበኞች ግንቦት ሰባት፣ የኢዴፓና ሌሎች ስብስብ ውስጥ ያላንዳች ማመንታት እንዲቀላቀሉ፤›› በማለት ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...