Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከ500 በላይ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ወታደሮች ካምፕ ሊገቡ ነው

ከ500 በላይ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ወታደሮች ካምፕ ሊገቡ ነው

ቀን:

ለረዥም ጊዜ በበረሃ በመቆየታቸው ቤት ንብረታቸው በመፍረሱና መሄጃ በማጣታቸው የትም መሄድ የማይችሉ 550 ያህል የአርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ የታጠቁ ኃይሎች ወደ ካምፕ እንዲገቡ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን፣ የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አስታወቁ፡፡

ድርጅቱ ባለፈው መስከረም ወር ወደ አገር ቤት ከገባ ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ‹‹አርበኞች ግንቦት ሰባት በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ለመታገል ቆርጦ የተነሳ ድርጅት ነው›› በሚል ርዕስ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ነው ይህን ያስታወቀው፡፡

የታጠቁ ኃይሎችን በተመለከተ፣ ‹‹አገር ውስጥ የነበሩና ከእኛ ጋር ተሳስረው ይሠሩ የነበሩ የታጠቁ ኃይሎችን መንግሥት ካምፕ አዘጋጅቶና በጀት መድቦ መግባት የሚገባቸውን ማስገባት ባለመቻሉ እንጂ እስካሁን የቆየነው፣ በእኛ ፍላጎት አይደለም፤›› ሲሉ የታጠቁት የድርጅቱ ኃይሎች ወደ ካምፕ ያልገቡት በመንግሥት ምክንያት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

‹‹አሁን የደረስንበት ስምምነት አለ፣ በመንግሥት በኩል ካምፕ ተገኝቷል፡፡ ለዚህ የሚሆነው በጀትም እንዲለቀቅ መመርያ ተሰጥቷል፡፡ ስለዚህ በሚቀጥሉ ጥቂት ቀናት ውስጥ በረሃ ውስጥ ያሉት በሙሉ በዚህ መንገድ ወደ ካምፕ ይገባሉ፡፡ መልሶ የማቋቋም ሥራም ይጀመራል ብለን እናስባለን፤›› ሲሉ አቶ አንዳርጋቸው አብራርተዋል፡፡

‹‹ንቅናቄያችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሲንቀሳቀሱ ለነበሩ ታጣቂዎች በምንም ዓይነት የአመፅ እንቅስቃሴ እንዳይሳተፉ መመርያ ከሰጠበት ዕለት አንስቶ እስካለንበት ወቅት ምንም ችግር አልተፈጠረም፡፡ አባላቶቻችን ለሰላም መስፈንና ለሕግ የበላይነት መከበር ካላቸው ቀናዒነት የተነሳ ወደፊት ምንም ዓይነት ችግር እንደማይፈጠር እርግጠኞች ነን፤›› በማለት ንቅናቄው አስታውቋል፡፡

የመጪው ምርጫ ተሳትፎና ዝግጅትን አስመልክቶ ከሪፖርተር ለቀረበ ጥያቄ አቶ አንዳርጋቸው፣ ‹‹የምርጫ መራዘምና አለመራዘም ጉዳይ እኛ ተዘጋጅተናል አልተዘጋጀንም ከሚለው ጉዳይ ጋር ፈጽሞ አይገናኝም፡፡ አገሪቱ ሰላም የሰፈነባት፣ የሕግ የበላይነት የተከበረባትና ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ነፃ የሆኑ ተቋማት በተቃዋሚ ድርጅቶች ዕይታ ነፃና ገለልተኛ መሆናቸው እስከታመነበት ሕዝብም ይህ ምርጫ እውነትም ነፃ፣ ገለልተኛ፣ እንዲሁም ሰላማዊ ሊሆን ይችላል ብሎ እስካመነ ድረስና ተዘጋጀን አልተዘጋጀን ምርጫው በተያዘለት ቀጠሮ ሊካሄድ ይችላል፡፡ ቅድሚያ መሰጠት ያለበት የአገር ጉዳይ እንጂ የአንድ ድርጅት ጉዳይ ነው ብለን አናምንም፤›› በማለት  ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹ሆኖም ማሳሰብ የምንፈልገው ነገር ምርጫው ቀነ ቀጠሮ ተይዞለታል ተብሎ አገር ባልተረጋጋበት፣ ሰላምና መረጋጋት በሌለበት፣ የሕግ የበላይነት ባልሰፈነበት፣ እንዲሁም በርካታ ተቋማት ነፃ ባልሆኑበት ሁኔታ ምርጫ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ እንዴት ሊደረግ እንደሚችል ከወዲሁ በደንብ ሊታሰብበት ይገባል ብለን እናምናለን፤›› በማለት፣ ከምርጫው በፊት ምኅዳር ማስፋቱና ማጠናከሩ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ አቶ አንዳርጋቸው በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...