Sunday, February 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርሕገወጥነት ሊቀጥል አይችልም!

ሕገወጥነት ሊቀጥል አይችልም!

ቀን:

ሪፖርተር በእሑድ ኅዳር 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ዕትሙ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎችን የሚያስመጡ ነጋዴዎች ‹‹ፍትሕ አጓደለብን›› በማለት ገቢዎችን ወቀሱ የሚል ርዕስ ዘገባ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ በዘገባው ላይ እንደተገለፈው የአስመጪዎቹ ቅሬታ መነሻ የቶዮታ ሥሪት የሆኑ ኮሮላ ሞዴል መኪኖች ሞተር ተቀይሮ መምጣት ነው፡፡ የቅሬታው መነሻ መለያ ቁጥራቸው በNZE141 እና NZE121 የሚጀምሩ የቶዮታ ኮሮላ ተሽከርካሪዎች አምራቹ ሲያመርታቸው የገጠመላቸው ሞተር ጉልበት 1,500 ሲሲ በመቀየሩ ምክንያት ታሪፍ ላይ ያስከተለው ለውጥ ሲሆን፣ የአስመጪዎች ጥያቄ ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ታሪፍ መሰላት ያለበት ኢትዮጵያ ተስማምታ በተቀበለችውና የሕግ አካል አድርጋ በማፅደቅ በምትሠራባቸው የዓለም ጉምሩክ ኅብረት ግልጽ የሕግ ድንጋጌና አሠራር መሠረት  ሳይሆን በተቃራኒ 1500 ሲሲ ጉልበት ያለው ኦሪጂናል ሞተራቸው ተነቅሎ ጉልበቱ 1298 ሲሲ በሆነ ሌላ ሞተር በመቀየሩ ታሪፉም (ኤክሳይዝ ታክስ) ተቀይሮ መሰላት አለበት በሚል የቀረበ ቅሬታ ነው፡፡

በመሆኑም ለቅሬታም መነሻ የሆነው አስመጪዎቹ እንደሚሉት ኦሪጂናሉ ሞተር ለምን ተቀየረ? መቀየር ይቻላል ወይስ አይችልም የሚል ጉዳይ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የተሽከርካሪ ቴክኒካል የመቆጣጠር ኃላፊነት የገቢዎች ሚኒስቴር ወይም የጉምሩክ ኮሚሽን ኃላፊነት አይደለም፡፡ ጉዳዩ የሞተር ጉልበቱ ይቀየርም አይቀየር የቀረጥ ታሪፍ የሚሰላው እንዴት ነው የሚል ነው፡፡ ከአስመጪዎች ጋር ያለን ልዩነትም ይህና ይኸው ብቻ ነው፡፡

እንደሚታወቀው 1,500 ሲሲ ጉልበት ያላቸው ተሽከርካሪዎች 60 በመቶ ኤክስይዝ ታክስ የሚከፈልባቸው ሲሆኑ፣ 1298 ሲሲ ጉልበት ያላቸው ተሽከርካሪዎች ደግሞ 30 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ይከፈልባቸዋል፡፡ ሞተር ቀይሮ ተሽከርካሪዎችን ወደ አገር ውስጥ የማስገባት ዋና ዓላማም የኤክሳይዝ ታክሱን ከ60 በመቶ ወደ 30 በመቶ ለመቀነስ፣ ለመንግሥት ሊከፈል የሚገባውን ታክስ ለማስቀረት ከሆነ ጉዳዩ ስህተት (ማጭበርበር) ይሆናል፡፡ በመሆኑም ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች አምራቹ ሲያመርታቸው በገጠመላቸው ኦሪጂናል የሞተር ጉልበት መሠረት ብቻ ቀረጥና ታክስ የሚከፈልባቸው ስለመሆኑ ኮሚቴ ተቋቁሞ በተሠራበትም ሒደት ሆነ በተደረጉት የጋራ ውይይት ወቅትም ለአስመጪዎቹ ግልጽ ተደርጎላቸዋል፡፡ ሕጉም ተነቦ ኮፒውንም እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

በዚሁ መሠረት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የተሽከርካሪዎቹን ታሪፍ አመዳደብ በተመለከተ በጉምሩክ አዋጅ 859/2006 አንቀጽ 5(1) መሠረት አስመጪዎቹ ራሳቸው ወይም በወኪሎቻቸው በኩል ለጉምሩክ ባሳወቁት መሠረት ብቻ ተሽከርካሪዎቹ ተገጥሞላቸው በመጣው ሞተር ጉልበት (1,298 ሲሲ) ነው ብለው ባሳወቁት ላይ በመመሥረት የታሪፍ አመዳደቡን ሲወስን ቆይቷል፡፡ በዚህ ቅሬታ በተፈጠረበት ጉዳይ ማጣራት ሒደት ግን አስመጪዎቹ ራሳቸው አምነው ያሳወቁን ከዚህ በፊት ያስገቧቸውን ተሽከርካሪዎች ሞተር ጉልበት እየቀየሩ እንደነበርና ይኼንንም ከጉምሩክ ፈታሾች ጋር በመናበብ ይሠሩት እንደነበር ነው፡፡ ሆኖም ይህ ድርጊት ሕገወጥ መሆኑን ሊቀበሉ ግን አልቻሉም፡፡

አስቀድመው ማስጠንቀቂያ ሳይሰጠን በድንገት አዲስ መመርያ ወጣ የሚለው ቅሬታ ከእውነት የራቀ ነው፡፡ ምክንያቱም በተሽከርካሪዎች ታሪፍ አመዳዳብና ቀረጥና ታክስ አወሳሰን ሒደቱም የትኛውም ስህተት መኖሩን ሲያረጋግጥ፣ ስህተቱ እንዲታረም ለማድረግ አስፈላጊውን ጉምሩክ ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰድ እንዳለበት በጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 አንቀጽ 113 ላይ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ በተመሳሳይ በዚሁ የጉምሩክ አዋጅ አንቀጽ 121 እና 122(1) መሠረት ደግሞ አስመጪው ወይም ወኪሉ ለጉምሩክ ያሳወቀው መረጃ ትክክለኛ መሆኑን ለማረጋገጥ ዕቃው ከተለቀቀ በኋላ እስከ አምስት ዓመት ድረስ ወደ ኋላ በመሄድ የድኅረ ዕቃ ኦዲት በማድረግ በማናቸውም አስመጪ ያልተከፈለ ቀረጥና ታክስ ወይም ሊከፈል ከሚገባው በማሳነስ ከፍሎ በዚህ ምክንያት ያልተከፈለ ቀሪ ቀረጥና ታክስ የተገኘ እንደሆነ፣ ያልተከፈለውን ወይም በቀሪነት የሚፈለገውን ወይም በልዩነት ሊከፈል የሚገባውን ቀረጥና ታክስ ሳይከፈል በቀረበት ጊዜ ጀምሮ በአምስት ዓመት ውስጥ ጉምሩክ ሊያስከፍል እንደሚችል ተደንግጓል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ሞተር ቀይረው ወደ አገር ውስጥ እየገቡ ያሉ ተሽከርካሪዎችን በተሽከርካሪ መለያ ቁጥራቸው መሠረት ማጣራት ሲያደርጉ፣ በተሽከርካሪዎቹ ላይ የተገጠመው ሞተር የተቀየረ መሆኑና የተሽከርካሪዎቹ ኦሪጂናል ሞተር 1,298 ሲሲ ሳይሆን፣ 1,500 ሲሲ እንደነበሩ ለማረጋገጥ ችለዋል፡፡ አስመጪዎቹ ይኼንን አልካዱም፡፡ በዚሁ መሠረት የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ለዋና መሥሪያ ቤት የጉምሩክ ዘርፍ ጥያቄ ባቀረቡት መሠረት ዘርፉ አምራች ድርጅቱ ሲያመርተው በተገጠመላቸው ኦሪጂናል ሞተር ጉልበት መሠረት የተሽከርካሪው ታሪፍ አመዳደብ መወሰን እንዳለበት መልስ ሰጥቷል፡፡

አስመጪዎቹም ይኼንኑ ውሳኔ በመቃወም ቅሬታቸውን ውሳኔው በተሰጠበት ወቅት ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቅርበው የነበሩ ሲሆን፣ ለተሽከርካሪዎቹ ታሪፍ መድቦ የሚከፈለውን ቀረጥና ታክስ የመወሰን ሙሉ ሥልጣን የባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት ቢሆንም የአቤቱታ አቅራቢዎቹ ድምፅ እንዲሰማና በግልጽነት አንፃር ዋና ዳይሬክተሩ ጉዳዩን አጣርቶ የውሳኔ ሐሳብ የሚያቀርብ የአስመጪዎቹን ተወካይ ያካተተ ኮሚቴ ማቋቋማቸው ትክክል ነው፡፡ ኮሚቴውም ጉዳዩን ከጉምሩክ አዋጅና ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች አንፃር በመመልከት በተቻለ መጠን መንግሥትንም አስመጪዎችንም የማይጎዳ ሕጉንም የማይሰጥ የውሳኔ ሐሳብ ለማቅረብ ጥረት አድርጓል፡፡

በዚሁ መሠረት ኮሚቴው በመጀመርያ ያየው ጉዳይ ሞተር ቀይረው የሚመጡ ተሽከርካሪዎች ታሪፍ እንዴት ይመደባል የሚለውን ጥያቄ መመለስ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም ጉምሩክ ድርጅት ተዘጋጅቶ የፀደቀውን ዓለም አቀፍ ዕቃዎች አሰያየምና አመዳደብ ሥርዓት በአዋጅ ቁጥር 67/1985 ተቀብላ ካፀደቀችበት ጊዜ ጀምሮ ወደ አገር የሚገቡ ዕቃዎች የታሪፍ አመዳደብ የሚወሰነው በዚሁ ስምምነት መሠረት እየተዘጋጀ ሥራ ላይ በሚውለው የጉምሩክ ታሪፍ ደንብ ነው፡፡ በሥራ ላይ ባለው የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 አንቀጽ 102 ንዑስ አንቀጽ 3 ላይ ይኼንኑ በማጠናከር ስለዕቃዎች የታሪፍ አመዳደብ ‹‹የዓለም ጉምሩክ ድርጅት ስለሸቀጦች የታሪፍ አመዳደብ የሚያወጣው ሰነድ ስለዕቃዎች የታሪፍ አመዳደብ ወሳኝ ማስረጃ ተደርጎ ይወሰዳል፤›› ብሎ ደንግጓል፡፡ የአዋጁ ድንጋጌዎች በገቢዎች ሚኒስቴርም ሆነ በአስመጪዎች ላይ እኩል ተፈጻሚነት ይኖራቸዋል፡፡

በመሆኑም የተጠቀሱት ተሽከርካሪዎች ዓለም አቀፍ በሆነው የሀርሞናይዝድ ሲስተም የዕቃዎች አሰያየምና አመዳደብ ሥርዓት መሠረት በታሪፍ ደንቡ በምዕራፍ 87 ውስጥ በአንቀጽ 87.03 የሚመደቡ ናቸው፡፡ ኮሚቴው ለውሳኔ ይረዳው ዘንድ የአንቀጽ 87.03 ንዑስ አንቀጾችን አወቃቀር በማገናዘብ የተሽከርካሪዎቹ ታሪፍ አመዳደብ የሚወሰነው ተሽከርካሪዎቹ ዲዛይን ሲደረጉና ሲመረቱ የተገጠመላቸውን የሞተር ጉልበት መሠረት በማድረግ እንጂ ተቀይሮ የተገጠመውን የሞተር ጉልበት መሠረት በማድረግ አለመሆኑን ለመገንዘብ ችሏል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የዓለም ጉምሩክ ድርጅት የሀርሞናይዝድ ሲስተም የዕቃዎች አሰያየምና አመዳደብ ሥርዓት አተረጋጎምን ለማገዝ ባዘጋጀው የማብራሪያ ሰነድ (WCO Explanatory Note 2012 Edition) ገጽ XVLL-87-1 እና XVll-87-1  ላይ በምዕራፍ 87 የሚመደቡ ተሽከርካሪዎችን የታሪፍ አመዳደብ በተመለከተ በቂ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

በዚሁ መሠረት አንድ ተሽከርካሪ በአምራቹ ተገጣጥሞ ከተጠናቀቀ በኋላ በተሽከርካሪው ላይ የሚከናወኑ የተለያዩ አካላዊ ለውጦች በመሠረቱ የተሽከርካሪውን ታሪፍ አመዳደብ የማይለውጡ መሆኑንና የተሽከርካሪው ታሪፍ አመዳደብ የሚወሰነው አምራቹ ተሽከርካሪውን ሲያመርት በገጠመው ኦሪጂናል ሞተር መሠረት የሚወሰን መሆኑ ነው፡፡ በተጨማሪም በማብራሪያው ላይ አንድ ተሽከርካሪ ሞተር ሳይገጠምለት እንኳን ወደ አገር ቢገባ የታሪፍ አመዳደቡ የሚወሰነው አንድ ዓይነት በሆነና ሥራው በተጠናቀቀ ሌላ ተሽከርካሪ የሞተር ጉልበት መሠረት እንደሚሆን ያብራራል፡፡

ሆኖም አቤቱታ አቅራቢዎቹ ከዚህ በፊት ሲስተናገዱ የቆዩት ራሳቸው ባሳወቁት መሠረት እንደነበር እንጂ የተሽከርካሪዎቹን የሞተር ጉልበት በተቀየረው የሞተር ጉልበት አለመሆኑ ሕገወጥ ድርጊት መሆኑን መግለጽ አልፈለጉም፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ሕጉ ቢጣስም እኛ ስናቀርብ በነበርነው ልክ የተሽከርካሪዎች መግለጫ ስንስተናገድ ቆይተናልና በችግሩ ውስጥ የጉምሩክ ሠራተኞችም ስላሉበት ሕገወጥ ድርጊት ባለበት መቀጠል አለበት እንደማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደምም ቢሆን በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በኩል ስህተት ከነበረም ስህተቱ የተወሰኑ ሠራተኞች ከአስመጪዎቹ ጋር በመግባባት ያደረጉት እንጂ ሆን ተብሎ ሕግና አሠራር ተጥሶ እንዲስተናገዱ ስለመደረጉ የሚያረጋግጥ ምንም ማስረጃ የለም፡፡ ይህ ተደርጎ እንኳን ቢሆን ሕጉን መጣስ ማለት የተሽከርካሪዎቹን ታሪፍ፣ ቀረጥና ታክስ ማጭበርበር ውጤት ያለው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም የተለመደ አሠራር ነውና የሕግ ጥሰቱ በነበረበት ይቀጥል የተባለው ጥያቄ በጉምሩክ ኮሚሽኑም ሆነ በገቢዎች ሚኒስቴር በኩል ተቀባይነት አላገኘም፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አስመጪዎቹ ተረጋግጦ እንዲከፍሉ በተጠየቁት የተሽከርካሪዎቹ ታሪፍ ሕጋዊ አሠራር መሠት ቀረጥና ታክሳቸውን እንዲከፍሉ ማድረግ ሕጉ የሚያስገድድ ሲሆን፣ ነገር ግን ከዚህ በፊት ተፈጥረው ለነበሩት ችግሮች የአስመጪዎች ብቻ ባለመሆኑ ያለፈውን ተመልሶ ኦዲት በማድረግ ማስከፈል ቀሪ እንዲሆን እንዲሁም የአሁኑ ክፍያውን በአንዴ እንዲከፍሉ ሲደረግ አስመጪዎቹ ከሚከፍሉት የገንዘብ መጠን ከፍተኛነት የተነሳ ከሚኖርባቸው የገንዘብ ጫና አንፃር በአከፋፈል ሕጋዊ ሥርዓቱ መሠረት ማለትም በጉምሩክ አዋጅ 859/2006 አንቀጽ 25 መሠረት የክፍያ ጊዜ ስምምነት ገብተው በተራዘመ ጊዜ እንዲከፍሉ ይፈቀድላቸው ዘንድ ከውሳኔ ላይ መድረሳችን ተገልጾላቸዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ይህም ችግራችንን አይፈታውም ከተባለ የገቢዎች ሚኒስቴር ባወጣው ሕግ መሠረት ቀረጥና ታክስ መሰብሰብ እንጂ ቀረጥና ታክስ መቀነስም ሆነ የማንሳት ሥልጣን ስለሌለው፣ ሥልጣን ለተሰጠው የመንግሥት አካል ችግሩን አቅርቦ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲታይላቸው ከማቅረብ ባለፈ በየሚዲያው እንዲሰማ በማድረግ ጫና ፈጥረን ቀረጥና ታክስ እናስቀራለን ብሎ ማስብ ትክክል አይደለም፡፡ በተጨማሪም በተለመደ አኳኋን ሕግ ተጥሶ መስተናገድ አለብን የሚለው ጥያቄ በምንም መልኩ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፡፡

ስለተሽከርካሪዎቹ ከአስመጪዎቹ የቀረበው ቅሬታ እንዲጣራ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክር የነበሩት ባቋቋሙት ኮሚቴ የተደረገው የማጣራት ሥራን በሚመለከት የአስመጪዎቹን ቅሬታ መስማትና ሕጋዊ መፍትሔ የመስጠት ተገቢነት ታምኖበት የተሠራ ሥራ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ የአስመጪዎቹን ቅሬታ በቀጥታ ለመስማት አስመጪዎቹ ራሳቸው ክብርት የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዘንድ እንዲሁም በኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስቴርና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ዘንድ ቀርበው ጉዳያቸውን እንዲያቀርቡ በማድረግ ከእነዚህ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡ በዚሁ አግባብም ጉዳያቸው ከታሪፍ ሕጋዊ አሠራሩ አኳያ የታየ መሆኑ ከከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎቹ ጋር መግባባት የተደረሰበት ነው፡፡ የኮሚቴን ሐሳብ በተመለከተ ኮሚቴው የሚያቀርበው ሐሳብ ሕጋዊ /ሕጉን የተከተለ/ ከሆነ ተቀባይነት ሲኖረው ከሕግ ውጪ ከሆነ ግን ውድቅ ሊሆን እንደሚችል መታወቅ አለበት፡፡ ይህ ኮሚቴ አጣርቶ ያቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ግን በአብዛኛው በግብዓትነት ተወስዷል፡፡ በሌላ በኩል ኃላፊዎች በመቀያየራቸው ምክንያት የተጓተተም ሆነ የተሻረ ውሳኔ የሌለ ሲሆን የሥራ ኃላፊዎች የተቀያየሩ ቢሆንም፣ ሕጉና መሥሪያ ቤቱ ያልተቀየረና አንዱ የሥራ ኃላፊ ጉዳዩን ለማጣራት የሄደበት ሒደት ለሕጋዊ ውሳኔው አጋዥ እስከሆነ ድረስ በግብዓትነት የሚወሰድ እንጂ አዲስ የሥራ ኃላፊ ስለተቀየረ ስለጉዳዩ አዲስ ማጣራት ማድረግ ነበረበት የሚለው ቅሬታና አዲሶቹ የሥራ ኃላፊዎች ራሳቸውን ችለው ለምን ውሳኔ ይወስናሉ በማለት የተነሳውም አግባብነት የለውም፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን ሕጋዊ ንግድን ማበረታታትና ሕገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን የመከላከል ሕጋዊ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ የተሽከርካሪዎችን ሞተር ቀይረው ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቡ አስመጪዎች ምንም ዓይነት የሞተር ለውጥ ሳያደርጉ በሚያስገቡ ያገለገሉ ተሽከርካሪ አስመጪዎች የገበያ ተወዳዳሪነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ብቻ ሳይሆኑ በሒደትም ከገበያ ሊያስወጧቸውም ስለሚችሉ፣ በሕገወጥ እንቅስቃሴዎች ላይ ተገቢውን ዕርምጃ በመውሰድ አስመጪዎቹ ያስመጧቸውን ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች በትክክለኛ ታሪፍ መደባቸው ላይ በመመደብ የመንግሥት ቀረጥና ታክስ ማስከፈልና ሕጋዊ የንግድ እንቅስቃሴውን ከጉዳት የመጠበቅ ሕጋዊ ሥልጣንና ኃላፊነት ያለው መሆኑ ሊታወቅ ይገባለ፡፡ ከዚህ አንፃር የሪፖርተር ጋዜጣም ጉዳዩን አስመልክቶ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤታችንም ሆነ የጉምሩክ ኮሚሽን ሐሳብ ጠይቆ ምላሻችንን ሳያካትት የአንድን አካል አቤቱታ ብቻ በመስማት ወደ አንድ ወገን ያደላ መረጃ ማውጣቱ አግባብነት የሌለውና መደገም የሌለበት መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡  

(የገቢዎች ሚኒስቴር)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በጦርነቱ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ የመገንባቱ ውጥን

በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል በሦስት ዙር ተካሄዶ በነበረው ጦርነት ምክንያት...

በርካታ ሰዎችን እያጠቁ የሚገኙት የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች

ትኩረት የሚሹ የትሮፒካል /ሐሩራማ በሽታዎች በአብዛኛው ተላላፊ ሲሆኑ፣ በዓይን...

ስለአገር ኢኮኖሚ ማሰብ የነበረባቸው ጭንቅላቶች በማያባሩ ግጭቶች ተነጥቀዋል!

አገራችን ኢትዮጵያ ውጪያዊና ውስጣዊ ፈተናዎቿ መብዛት ብዙ ዋጋ እያስከፈላት...