Wednesday, February 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ይህ ቀልድ የፈረንጆች ነው፡፡ በአንድ ወቅት ባልና ሚስት የ30 ዓመታት የጋብቻ በዓላቸውን ባከበሩ ማግሥት፣ ባል በረንዳ ተቀምጦ ወረቀቶችን እያገላበጠ ነበር፡፡ በዚህ መሀል የጋብቻ የምስክር ወረቃታቸውን ያገኘዋል፡፡ ከዚያም የጋብቻ ምስክር ወረቀቱ ላይ እንዳፈጠጠ ሚስት ቡና ይዛለት ትመጣለች፡፡ የባሏ አኳኋን ግራ አጋብቷት፣ ‹‹ምን እያደረግክ ነው?›› ስትለው፣ ‹‹ምንም!›› በማለት በአጭሩ ይመልስላታል፡፡ ሚስት እንደገና፣ ‹‹ምንም ትላለህ እንዴ? እያየሁ እኮ ነው፡፡ የጋብቻ የምስክር ወረቃታችንን እያነበብክ አይደል?›› በማለት ጥያቄ ስታቀርብለት፣ ‹‹በእርግጥ እያነበብኩ ነው. . .›› ብሎ ያልተሟላ መልስ ይሰጣታል፡፡ ሚስት በመገረም፣ ‹‹የምስክር ወረቀቱ ላይ ምን አስፈጠጠህ ታዲያ?›› ስትለው በታከተ ድምፅ፣ ‹‹ይኼ የምስክር ወረቀት ‹ኤክስፓይሬሽን ዴት› የለውም እንዴ?›› ብሎ ሚስቱን ክው አደረጋት አሉ፡፡ ‹‹ፍቅር ሲያረጅ. . .›› መሆኑ ነው፡፡

ይኼንን ቀልድ መሳይ ቁም ነገር መነሻ በማድረግ ለመጻፍ የፈለግኩት ከትዳር አጋሮቻችን፣ ከልብ ወዳጆቻችንና በቅርበት ከሚያውቁን ሰዎች ጋር የሚኖረን ግንኙነት ለምን እንከን ይገጥመዋል በሚለው ጉዳይ ላይ ነው፡፡ አንድ የቀድሞ ጓደኛችን ከዛሬ 15 ዓመታት በፊት ድል አድርጎ ደግሶ የበላነው ሥጋ የጠጣነው ጠጅ አይረሳኝም፡፡ ያንን ሠርግ ሳስታውስ ከምግቡና ከመጠጡ በላይ እሱ ልጅቱን እጁ ለማግባት ያደረገው ወደር የለሽ ጥረትም ከቶ አይዘነጋኝም፡፡ እሱ በወቅቱ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ተቀጣሪ የነበረ ሲሆን፣ ደመወዙ ከ800 ብር አይበልጥም ነበር፡፡ እሷ ደግሞ አነስተኛ ስቴሽነሪ ነበራት፡፡ እሱ ሚኒ ባስ ሲጋፋ እሷ ፊያት 127 አውቶሞቢል ትነዳ ነበር፡፡ ይኼ መልከ መልካም ጓደኛችን እግር በእግር እየተከተላት መውጪያ መግቢያ አሳጥቶ፣ በአማላጅ ጋጋታ ለጋብቻ እሺ ያሰኛታል፡፡ ከጥቂት ወጣ ገባ ማለት በኋላ ሽማግሌ ልኮ ከተፈቀደለት በኋላ ሠርግ ይደግሳል፡፡ ይህ ጥረቱ የተሳካለት ጓደኛችን ይነበብበት የነበረው ደስታ እጅግ ከመግዘፉ የተነሳ፣ በዚህ ምድር ላይ እንደ እሱ ደስተኛ ሰው ያለ አይመስልም ነበር፡፡

እኛም የደስታው ተጋሪ በመሆን ‹‹ሃይሎጋ›› ብለን ጨፍረን ዳርነው፡፡ በዓመቱ ሴት ልጅ ስትወለድ ለክርስትና የነበረው ድግስ ከሠርጉ አይተናነስም ነበር፡፡ አጅሬም ከሚስቱ ጋር አብሮ ለመሥራት ከመንግሥት ሥራ ለቀቀ፡፡ መልከ መልካምና አፈ ጮሌ ስለነበረ የንግድ ሥራው ተስማማው፡፡ በአጭር ጊዜ ተጨማሪ ስቴሽነሪ ከፈቱ፡፡ አዲሱ ስቴሽነሪ ሰፋ ያለና በርካታ አቅርቦቶች ስለነበሩት ገንዘብ እንደ ቅጠል ይረግፍ ጀመር፡፡ እሷ የድሮዋን ይዛ እየሠራች ቢሆንም፣ እሱ ግን በአጭር ጊዜ ተተኮሰ፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ሦስት ዓይነት መኪኖች ቀያየረ፡፡ መንግሥት ቤት ሆኖ ሞዴል ስድስት ላይ ስሙ የማይጠፋው ታታሪ ተበዳሪ፣ አሁን የናጠጠ ሀብታም ሆነ፡፡ የድሮ ጓደኞቹንም መራቅ አመጣ፡፡ ለይቶለትም ውሎውን ከፍ ያለ ቦታ በማድረጉ መገናኘት ጠፋ፡፡ በወሬ ግን ዱባይና ቻይና ሁለተኛ አገሮቹ መሆናቸውን እንሰማለን፡፡ ለገጣፎ የሠራው ጂ ፕላስ ስሪ፣ ለቡ ያስገነባው እኔ ነኝ ያለ ቪላ፣ ቦሌ አካባቢ ያስጀመረው ሕንፃ. . . ወሬው ይደርሰናል፡፡ ብቻ ምን አለፋችሁ ከበርቴ ሆኗል፡፡

በአንድ ወቅት አንድ እሑድ ማለዳ ለቅሶ ለመድረስ ወደ ለገጣፎ እሄዳለሁ፡፡ እዚያ አካባቢ ሄጄ ስለማላውቅ ዓይኔ ባየው ነገር ሁሉ ስደመም ነበር፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተወልጄ አድጌ፣ እንዲሁም ኖሬ እንዲህ ዓይነት ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶችን ማየት ብርቅ ነው የሆነብኝ፡፡ ለማንኛውም ለቅሶ የምደርሰው ሰው ለዚህ አካባቢ የሚመጥን ደንደን ያለ ሀብታም ስለነበር በራሴና በቢጤዎቼ አኗኗር እየተከዝኩ ከታክሲ ስወርድ፣ ሽንጠ ረጂም ሊሞዚን በሚያብረቀርቁ በርከት ያሉ ጥቁር መርሰዲሶች ታጅቦ ቆሟል፡፡ የአንዱ ሀብታም ሠርግ መሆኑ ነው፡፡ ፊት ለፊት ካለ የሚያንፀባርቅ ትልቅ ባለ ቪላ ግቢ ውስጥ ሙሽራው በሚዜዎቹና በአጃቢዎቹ ታጅቦ ‹‹ሃይሎጋ››  እየተባለ ሲወጣ ዓይኔን ማመን አቃተኝ፡፡ ሙሽራው ምንም ቢደላውና ወዙ ቢለወጥም፣ ያ ሳቂታና ፎልፏላ የድሮ ጓደኛችን መሆኑን በፍፁም አልተጠራጠርኩም፡፡ ለማንኛውም ብዬ  ትንሽ ጠጋ ብዬ ሳየው ዓይን ለዓይን ተጋጨን፡፡ እንደማያውቀኝ ሆኖ ፊቱን ዞር አደረገው፡፡ በሚዜዎቹና በአጃቢዎቹ ደምቆ ሊሞዚኑ ውስጥ ገባ፡፡ ከዚያም ወደ ሙሽሪት ቤት ጉዞውን ቀጠለ፡፡

እኔም የሄድኩበትን ለቅሶ ደርሼ ወደ ቤቴ ስለመለስ ለአንድ የቅርብ ጓደኛዬ ደወልኩለት፡፡ በዓይኔ በብረቱ ያየሁትን ጉድ ነገርኩት፡፡ እሱ ግን ምንም አልተገረመም፡፡  እንዲሁ እንደ ዋዛ፣ ‹‹አንተ ሰውዬ በአገሩ አልነበርክም እንዴ?›› ብሎ ሲጠይቀኝ፣ ‹‹ከአገሬ ወጥቼ እንደማላውቅማ ታውቃለህ፤›› ብዬ መለስኩለት፡፡ እሱም፣ ‹‹ያ የድሮ ጓደኛችን ያቺን ታታሪና ቆንጆ ሚስቱን ከፈታ እኮ ቆየ፤›› አለኝ፡፡ ምክንያቱን እንደነገረኝ ያቺ ታታሪ ሚስት ለዚህ ደረጃ ያበቃችው ቢሆንም፣ ሀብት በሀብት ላይ ሲቆለል ግን አቶ ጥጋብ ይዞታል፡፡ በዚያ ላይ ፈጣንና ደፋር በመሆኑም እያምታታ ጭምር ሀብት ሲያጋብስ በሚስቱ ላይ መሄድ፣ ከዘመነኛ ሀብታሞች ጋር ገጥሞ ማምሸትና እሷን መናቅ ልማዱ ሆነ፡፡ በዚያ ላይ ከእሷ እየደበቀ የተለያዩ ቢዝነሶች ያካሂዳል፡፡ በዚህም ሳቢያ አብረው መቀጠል የማይቻልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ ለመለያየት በቁ፡፡ እንደዚያ ጠብ እርግፍ ያለላት ወመኔ ዓይንሽ ላፈር ብሎ እብደት ውስጥ ገባ፡፡

ይህ ነገር በጣም እየከነከነ ስላስቸገረኝ እንደምንም አፈላልጌ የድሮ ጓደኛችንን ሚስት አገኘኋት፡፡ ባሏን ከመፍታቷ ውጪ አሪፍ የሚባል ስቴሽነሪና የግንባታ ማቴሪያሎች መደብር አሉዋት፡፡ እሷም በጥሩ የኑሮ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ወደ እሷ ለመሄድ የተገደድኩት ሁኔታዋን በዓይኔ ለማየት ነበር፡፡ ነገር ግን እሷ ከጠበቅኳት በላይ የራስ መተማመንና ጥንካሬ ይታይታባል፡፡ የቀድሞ ባሏን በአጋጣሚ ተሞሽሮ እንዳየሁትና ፊቱን እንዳዞረብኝ ስነግራት ከት ብላ ሳቀች፡፡ ‹‹ምነው?›› አልኳት፡፡ እሷም፣ ‹‹እሱ እኮ ከእኔ በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ ነው ሲዳር ያየኸው. . .›› እያለች ከሳቋ ጋር ስትታገል ደነገጥኩ፡፡ ሳቋን ስትጨርስ፣ ‹‹አይዞህ አትደንግጥ፡፡ እንደሱ ዓይነት የሕይወት ጣዕም የጠፋባቸው ከንቱዎች እኮ ሞልተዋል፡፡ ልክ እንደ ቀላዋጭ በየደረሱበት ያገኙትን ሲያግበሰብሱ እንደተናቁ ይቀራሉ፡፡ የሚያሳዝነኝ ግን የእነሱ ሰለባ የሚሆኑት እህቶቼ ናቸው. . .›› ብላ ስትተክዝ እኔም በሐሳብ ጭልጥ አልኩ፡፡ ለነገሩ እኔም የድሮውን ብቻ ይዤ የምንገታገት ሆኜ እንጂ፣ በዚህ ዘመን ስንትና ስንት አስደናቂ ነገሮች እያየን ይኼ ምን ይገርማል፡፡ ‹‹አገር ሲያረጅ ጃርት ያፈራል›› የተባለው ለዚህ ዘመን ሰው እየመሰለኝ ነው፡፡

(ዋለልኝ አሰፋ፣ ከአዋሬ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በወቅታዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የቀረበላቸውን ምክረ ሐሳብ እያደመጡ ነው]

ችግሩ ምን እንደሆነ በትክልል ለይተነዋል ግን ግን ምን? በይፋ መናገር አልነበረብንም። ለምን? ችግሩን...

የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤትና እንደምታው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የትምህርትን...

ንግድ ባንክ ከቪዛና ማስተር ካርድ ጋር ተደራድሮ ያስጀመረው የገንዘብ ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂና ፋይዳው

ከውጭ ወደ አገር በሕጋዊ መንገድ የሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) መጠን...

ይኼ አመላችን የት ያደርሰን ይሆን?

እነሆ ከፒያሳ ወደ ካዛንቺስ። ‹‹አዳም ሆይ በግንባር ወዝ ትበላለህ››...