Sunday, April 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሚጠበቅበትን ያህል እየጠቀመ ያልሆነው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዳዊት ታዬ

የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለአገር ውስጥ ቴክኖሎጂ ሽግግር ያበረከተውን አስተዋጽኦ በተመለከተ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሰሞኑን አንድ የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የአገሪቱን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴንና እየሰጠ ያለውን ጥቅም አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት፣ በኢንቨስትመንት ኮሚሽን የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ ስንታየሁ መንግሥቴ ናቸው፡፡ አቶ ስንታየሁ ኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንት በመሳብ የተለያዩ ጠቀሜታዎች መገኘቱን ያመለክታሉ፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኢንዱስትሪ ሀብ ትሆናለች ተብሎ የተወጠነ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ስንታየሁ፣ ይህንን ውጥን ለማሳካት አገሪቷ የውጭ ኩባንያዎችን እየቀሰቀሰች በማምጣት ላይ ስለመሆኗም ተናግረዋል፡፡ ይህንንም ለማገዝ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ መካሄዱና እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቀጥታ ኢንቨስትመንት ፋና ወጊ ናቸው ብለው በቀዳሚነት ያስቀመጡዋቸው አገሮች የቻይናና ህንድን ነው፡፡ ሆላንድ ሌላዋ በኢትዮጵያ የቀጥታ ኢንቨስትመንት ውስጥ ተጠቃሽ ስም ያላት ነች፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚያፈሱ የአሜሪካ ትላልቅ ኩባንያዎች እየመጡና ሥራ እስከ መጀመር ስለመድረሳቸው አቶ ስንታየሁ አብራርተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ተመራጭ የሆነችበት ምክንያት ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የተቀመጠውን መስፈርት በማሟላት ነው የሚልም እምነታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከመሳብ አንፃር ተገኘ ያሉትን ውጤት በምሳሌ ከጠቀሱዋቸው ውስጥ አንዱ በቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት የተገኘውን የውጭ ምንዛሪ ነው፡፡ ከጥር እስከ ነሐሴ 2010 ዓ.ም. ድረስ ብቻ 3.7 ቢሊዮን ዶላር ከቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት እንደተገኘም ገልጸዋል፡፡  

የቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት መግባት ለአገራዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ለማስረዳት ሰፋ ያለ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ስንታየሁ፣ የቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት መግባት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የግድ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ ዛሬ አደጉ የምንላቸው አገሮች ይህንን መንገድ ተከትለው በመምጣታቸው ያገኙት ውጤት መሆኑን ጠቁዋል፡፡ በተለይ የውጭ ኩባንያ መምጣት ለውጭ ምንዛሪ ግኝትና ለዕውቀት ሽግግር ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ጭምር መሆኑ ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው ብለዋል፡፡ እስካሁንም ወደ ኢትዮጵያ በቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት የገቡ የውጭ ኩባንያዎች እስከ 138 ሺሕ የሥራ ዕድል ፈጥረዋል ተብሏል፡፡  

ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት በራሱ ለዘቄታዊ ዕድገት ይበጃል ተብሎ ባይታሰብም አስፈላጊ ነው ያሉት አቶ ስንታየሁ፣ ትርጉም የሚኖረው የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ቴክኖሎጂውን ተቀብለው ሲሠሩ ብቻ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ይህ የዕውቀት ሽግግር በበቂ ሁኔታ እየተተገበረ አይደለም፡፡ የቴክኖሎጂ ሽግግር መሠረታዊ ጉዳይ በመሆኑ ይህንን ቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ ደግሞ የቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ግድ ማለቱንም ይገልጻሉ፡፡

የቻይናና ሲንጋፖርን ውጤታማ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን እንደ ምሳሌ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ በተለይ ሲንጋፖር የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ ካልቻለች ለውጥ ልታመጣ እንደማትችል ታምኖ ማሠልጠኛ ተቋማትን በማቋቋም የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች በጆይንት ቬንቸር እንዲሠሩ የሚያስችል አሠራር በመፍጠር የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግም ውጤታማ መሆን ችላለች፡፡  

በዕለቱ የአቶ ስንታየሁ ማብራሪያን ተከትሎ አስተያየት የሰጡት አብዛኛዎቹ የንግድ ኅብረተሰቡ አባላት በቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ዙሪያ በርካታ ችግሮች ስለመኖራቸውና ያስገኛል የተባለው የቴክኖሎጂ ሽግግር ያለማድረጉን ተናግረዋል፡፡

በተለይ ኢትዮጵያ ከቴክኖሎጂ ሽግግር እየተጠቀመች ነው የሚለው ላይ ማረጋገጫዎቹ ምንድናቸው? የሚለው ግልጽ አለመሆኑን ያስረዱት አንድ ተሳታፊ፣ እርግጥ በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የሚቀጠረው ሠራተኛ እየጨመረ ስለመሆኑ ይስማማሉ፡፡ ቢሆንም የሠራተኛ ቁጥር መጨመር ብቻ ቴክኖሎጂ ሽግግር ተደርጓል ለማለት አያስችልም ያሉት ተሳታፊው፣ አቶ ስንታየሁ በምሳሌነት ያነሱዋቸውን ቻይናና ሲንጋፖር ሽግግሩን ማሳካት የቻሉት ውጤታማ ፖሊሲ ቀርፀው ነው ይላሉ፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪው ገለጻ፣ ቻይና ቴክኖሎጂ ሽግግሩን ማሳካት የቻለችው ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትን በጆይንት ቬንቸር የአገር ውስጥ ኩባንያን ከውጭ ኩባንያዎች ጋር የሚቀናጅ ፖሊሲ ስለተከተለች ነው፡፡ ሲንጋፖር ያደረገችው ደግሞ ለሁሉም ክፍት የሆነ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ስለተከተለች ነው፡፡ ይህ ማለት ከፍተኛ ፋይናንሻል ሊብራላይዜሽን  ያለበት ኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተልና ስትራቴጂ በመንደፍ መሆኑን በማስታወስ፣ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለመተግበሩ ከቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ቴክኖሎጂ ማሸጋገር ተችሏል ማለት እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡ አያይዘውም ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ የውጭ ኢንቨስትመንት ስኬት አስገኝቷል ብሎ ለመግለጽ አስቸጋሪ መሆኑን የሚያንፀባርቅ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ከቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት አገሪቷ አገኘች ተብሎ የተጠቀሰው 3.7 ቢሊዮን ዶላርም ገብቷል መባሉ ላይ ጥያቄ እንዳላቸውም የገለጹ አሉ፡፡ መጣ ከተባለው የውጭ ኢንቨስትመንት ውስጥስ ስንቱ ኩባንያ ነው ከኢትዮጵያዊ ጋር ጀይንት ቬንቸር ያደረገው? ስለዚህ ይህ አመላካች ነው በማለት አገሪቱ ቴክኖሎጂውን ለመቀበል ብዙ ሥራ መሠራት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

‹‹በቻይና፣ ህንድና ቱርክ ኩባንያዎች ውስጥ የሚቀጠሩ ኢትዮጵያውያኖች የቤት ኪራያቸውን ለመክፈል እየተቸገሩ ነው፤›› ያሉት አስተያየት ሰጪ ደግሞ፣ ሠራተኞች በአግባቡ የማይዙ ናቸው ብለዋል፡፡ እነዚህ በቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት የሚገቡ የውጭ ኩባንያዎች የሠራተኞች ፍልሰት ያለባቸው መሆን ደግሞ ቴክኖሎጂ ተሸጋግሯል ማለት አያስችልም በማለት የአቶ ስንታየሁን ማብራሪያ ሞግተዋል፡፡ አቶ ስንታየሁ በዚህ ዙሪያ ሠራተኞች ክህሎትን እንደ ዋነኛ ችግር አንስተዋል፡፡ ብዙ ሠራተኞች የማምረት አቅም አነስተኛ ከመሆን ጋር የተያያዘም ነው ይላሉ፡፡   

ሌላው ተናጋሪ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ያለመሳተፋቸው ምክንያት መንግሥት ለአገር ውስጥ ኩባንያዎች ያን ያህል ትኩረት ካለማድረጉ ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደዚህ እንዲገቡ አይበረታታም የሚል እምነት አላቸው፡፡

ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት የሥራ ዕድል ያሳድጋል በሚለው ላይ ከአቶ ስንታየሁ የተለየ ሐሳብ እንዳላቸው የገለጹት እኝሁ ተናጋሪ፣ የሥራ ዕድሉን ከጉልበት ብዝበዛ ጋር አመሳስለውታል፡፡ የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ የቻይና ኩባንያዎቹ ሾፌር ሳይቀር ከአገራቸው የሚያመጡ መሆኑና ሌሎች ትንንሽ ሥራዎች ሁሉ በእነሱ የሚሠራ በመሆኑ፣ ‹‹የቀን ሥራ ነው የእኛዎቹ የሚሠሩት፤ የቀን ሥራ ነው፤›› ብለው ጉዳዩ ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባ ያመለክታሉ፡፡                     

ከዚህ ባሻገር ግን የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለመግባት ከኢንቨስትመንቱ ጠቅላላ ወጪ 15 በመቶ ይዘው ቀሪው በብድር እንዲሸፈን ድጋፍ ይደረጋል ስለተባለው ጉዳይ ተግባራዊነት ጥርጣሬ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ሌላው ከተሳታፊዎች በተለየ መልኩ አስተያየት የተሰጣቸው እነዚህ በውጭ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት መልክ የሚገቡ ኩባንያዎች እንደ ግብዓት የሚጠቀሙዋቸው ጥሬ ዕቃዎች ያለመኖሩ ትልቅ ችግር ነው ብለዋል፡፡ እንደ ግብዓት የሚጠቀሙት ምርት አለ ወይ? ግብዓታቸው ከውጭ የሚመጣ ከሆነ ጉዳቱ ሊያመዝን ስለሚችል ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ከዚህ ጋር የተሳሰረ ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ እንደ ትልቅ ችግር ተደርጎ የተነሳው፣ የውጭ ኩባንያዎች ከአገር ውስጥ ኩባንያዎች ጋር በሽርክና እንዲሠሩ ለማድረግ የሚያስችል አሠራር አለመኖሩ ነው፡፡ ከተወያዮቹ ዘንድ እንደተነሳውም ለውጭ ኢንቨስተሮች መንግሥት ብድር በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል እሰጣችኋለሁ ይላል፡፡ ይህ አካሄድ የሚያዋጣ እንዳልሆነ በመግለጽ፣ መፍትሔው ስቶክ ማርኬቱን መክፈት ነው ብለዋል፡፡ ነገር ግን ስቶክ ማርኬቱን ለመክፈት አልተቻለም፡፡ ለኢንቨስትመንት የሚፈለገውን ካፒታል ከሕዝብ በስቶክ ማርኬት በኩል ማዋጣት ሲቻል መንግሥት ሰጪና ደጓሚ መሆኑ አግባብ አይደለም ብለው፣ አሁንም የፋይናንስ ዘርፉ አካሄድ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማነቆ ነው ተብሏል፡፡

ከ1995 ዓ.ም. ጀምሮ ካፒታል ማርኬት ለመፍጠር ያልተቻለበት ምክንያት ግራ የሚያጋባ መሆኑን የጠቆሙት እኚህ አስተያየት ሰጪ፣ ከዚህ ቀደም በዚህ ጉዳይ አቶ መለስ ዜናዊ ያሉትንም አስታውሰዋል፡፡ የውጭ ባንኮችና ስቶክ ማርኬት ለምን ዘገየ? ለሚለው አቶ መለስ ‹‹የአገር ውስጥ ባንኮች አቅማቸው ስላላደገና የውጭ ገበያ ዕውቀት ስለሌለን እነዚህን ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት አስፈላጊ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ ስለዚህ ይህንን ለመፈጸም ስንት ዓመት እንጠብቅ? ከ1995 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2011 ዓ.ም. ድረስ ብሔራዊ ባንክ አቅሙን ማሳደግ ካልቻለ ምንድነው የሚደረገው? ምን እንሁንለት? ብሔራዊ ባንክ ይፍረስ እንበል? እስከ ማለት ደርሰዋል፡፡ እሱ አቅም መገንባት ካልቻለ ሌላ አካል ይቋቋም በማለት የስቶክ ማርኬት አለመቋቋም ጉዳይ ብዙ ጥፋት የፈጠረ ነው ተብሏል፡፡ አቶ ስንታየሁ የካፒታል ማርኬት ነገር የተጀመረ ነገር ያለመሆኑን ጠቁመው፣ ጉዳዩ በንግድ ምክር ቤት በኩል ተይዞ ቢታይ ጥሩ ነው ብለዋል፡፡ ከንግዱ ኅብረተሰብ የተሰጠውን አስተያየትና ጥያቄ ተመርኩዘው አቶ ስንታየሁ በሰጡት ምላሽ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግሩ በሚፈለገው ደረጃ ባይሆንም ጅምሮች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ አሁንም ብዙ የሚቀር መሆኑን በመግለጽ ለዚህ ደግሞ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሚገቡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የተለያዩ ማበረታቻዎች ስለመስጠታቸው ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ይህንን የተፈቀደውን ማበረታቻ እንኳን መጠቀም እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡ ኢንዱስትሪ ፓርክ ላይ መንግሥት ለውጭ ኩባንያዎች ማበረታቻ ሰጥቶ ሲያስገባቸው ለአገር ውስጥ ኩባንያዎችም የተለየ ማበረታቻ ሰጥቷል ይላሉ፡፡ ለአገር ውስጥ ኩባንያዎች የተሰጠው የተለየ ማበረታቻ ቴክኖሎጂን እንዲሸጋገር ለማድረግ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡

ለአገር ውስጥ የተሰጠው ማበረታቻ በዋናነት አምስት ዓይነት ስለመሆናቸው ይጠቅሳሉ፡፡ እነሱም ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ለሚገባ የአገር ውስጥ ባለሀብት ከጠቅላላ ኢንቨስትመንቱ 15 በመቶ ይዞ ከመጣ 85 በመቶውን ከልማት ባንክ ብድር ተመቻችቷል፡፡ ሁለተኛ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ፓርኩ ሲመጡ አዲስ እንደመሆናቸው መጠን ቴክኖሎጂውን ለማሻገር መንግሥት የባለሙያዎቹን ሥልጠና በሰፊው ያግዛል፡፡ ሌላው እንደ ማበረታቻ የተቀመጠ ነው ያሉት የአገር ውስጥ ባለሀብቱ በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚሠራው የውጭ ቴክኖሎጂ በማስመጣት በመሆኑ የውጭ ኤክስፐርት መቅጠር ግድ ስለሚሆንበት ለኤክስፖርቱ የሚወጣውን ወጪ መንግሥት የሚጋራ መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያሉትን ማበረታቻዎች መጠቀም ያልቻሉ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ ውጪ በኢንዲስትሪ ፓርኮች የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ከወጪዎቹ ጋር የሚጋሩት ሌላው ማበረታቻ የአሥር ዓመት ከታክስ ነፃ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች አልተጠቀሙበትም ይላሉ፡፡፡ አቶ ስንታየሁ ይህንን ይበሉ እንጂ በእነዚህ ፓርኮች ውስጥ ገብቶ እየሠራ ያለ የአገር ውስጥ ባለሀብት የለም፡፡ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ጋር የተደረገ የማናጄራል ዕውቀት አንፃራዊ ስለመሆኑ አምነዋል፡፡ መንግሥት ሥልጠና ቢሰጥም በቂ ያለመሆኑን በማከልም ገለጻ አድርገዋል፡፡ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ሲመጣ የአካባቢና የማኅበራዊ ኃላፊነትን በተመለከተ በኢንቨስት ኮሚሽን ሥር ራሱን የቻለ ተቆጣጣሪ ማዕከል በመኖሩ ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ ፋብሪካዎችን እስከ መዝጋት የሚደርስ ዕርምጃ ተወስዷል ያሉት አቶ ስንታየሁ፣ ለአንድ ለሁለት ወር ሁሉ የተዘጉ አሉ ብለዋል፡፡ ነገር ግን በበቂ ሁኔታ ተሠርቷል ተብሎ እንደማያምኑም አስረድተዋል፡፡

የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ከማበረታታትና የአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃዎችን ከመጠቀም አንፃር ታሳቢ የተደረጉበት በቅርቡ ግንባታቸው አልቆ ሥራ ይጀምራሉ የሚባሉት የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ናቸው፡፡ በአራቱ ክልሎች የሚገነቡት እነዚህ አግሮ ፓርኮች፣ የአገር ውስጥ ምርቶች ተቀነባብረው ሁሉ ነገር አልቆላቸው ወደ ውጭ እንዲላኩ ለማድረግ ነው፡፡ እነዚህ አግሮ ፓርኮች ትልቁ ዓላማቸው የአርሶ አደሩን ምርት ተቀብለው እሴት ተጨምሮባቸው በትክክል ለገበያ ለማቅረብ ነው፡፡ በእነዚህ ፓርኮች የሚገቡት የአገር ውስጥ ኩባንያዎች መሆናቸው በዘርፉ የሚገቡትን ያበረታታል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ረጋሳ በበኩላቸው ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በጆይንት ቬንቸር ለመሥራት ኩባንያዎች የሒሳብ አያያዝ ጉዳይ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የውጭ ኩባንያዎች ለጥምረት ከሚጠይቋቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ ይህ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ አቶ ስንታየሁ ደግሞ የቀረቡ አስተያየቶችን ተቀብለው አሁንም ግን በቂ ማበረታቻ ስላለ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርክ ኑ ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች