Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በመንታ መንገድ ላይ የሚገኘው የሪል ስቴት ልማት

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢሕአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረበት 1983 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 1996 ዓ.ም. ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ የሪል ስቴት ልማት ብዙም አይታወቅም ነበር፡፡

በእርግጥ በ1990ዎቹ መጀመርያ አያት መኖሪያ ቤቶች፣ ሰንሻይን ኮንስትራክሽን፣ ጃክሮስና ሀቢታት ኒው ፍላዎር በተወሰነ ደረጃ ፈር ቀዳጅ በመሆን ግንባታ ጀምረው ነበር፡፡

ነገር ግን አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) የከተማውን ቁልፍ ከተረከቡ በኋላ፣ በመንግሥትና በግል ዘርፍ የሚካሄዱ ሁለት የመኖሪያ ቤት ግንባታ ፕሮግራሞችን ሲያስተዋውቁ በርካታ ተዋንያን ተፈጥረዋል፡፡ 

በመንግሥት በተጀመረው ፕሮግራም ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ፣ ከ1999 ዓ.ም. በክልሎች 385 ሺሕ ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ በዚህ ሥራ ውስጥ ሁለት ሺሕ ኮንትራክተሮች፣ 12 ሺሕ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የተሳተፉ ሲሆን፣ ለአንድ ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡

በአርከበ (ዶ/ር) በ1996 ዓ.ም. የሚመራው የአዲስ አበባ ከተማ ጊዜያዊ አስተዳደር የንግዱ ማኅበረሰብ በሪል ስቴት ዘርፍ እንዲሰማራ ጥሪ አቅርቧል፡፡ በጥሪው መሠረት በወቅቱ 130 የሚጠጉ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት እያንዳንዳቸው ከአሥር ሺሕ እስከ 50 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ተረክበዋል፡፡

የመሬት አሰጣጡ ብቻ ሳይሆን የሪል ስቴት ልማት በከተማው እምብዛም የማይታወቅ ስለነበረ፣ በወቅቱ ብዙ ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡ ነገር ግን ቦታዎቹ በአብዛኛው የሚገኙት ከመሀል ከተማ ወጣ ያሉ ስለነበሩ ከፍተኛ ችግር ተፈጥሮ ነበር፡፡ በስምንተኛው ማስተር ፕላን እንደተገለጸው፣ የአዲስ አበባ ከተማ ጠቅላላ ይዞታ 54 ሺሕ ሔክታር ስፋት አለው፣ ከዚህ ውስጥ 30 ሺሕ ሔክታር መሬት በመሀል ከተማ የሚገኝ ሲሆን፣ ቀሪው በማስፋፊያ ክፍላተ ከተሞች ማለትም በቦሌ፣ በአቃቂ ቃሊቲ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ በየካና በኮልፌ ቀራኒዮ የሚገኝ ነው፡፡

አብዛኛዎቹ የማስፋፊያ ቦታዎች የአርሶ አደር ይዞታዎች ሲሆኑ የመሠረተ ልማት በተለይም መንገድ፣ ኤሌክትሪክና ውኃ አቅርቦት አልተሟላላቸውም፡፡ የመሠረተ ልማት አቅርቦት ያልተሟላ በመሆኑ፣ በወቅቱ የነበረው የንግዱ ማኅበረሰብም ልምድም፣ አቅምም የሌለው ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ በተሰጠው ጊዜ ገደብ ወደ ግንባታ መግባት አልቻሉም ነበር፡፡

በወቅቱ ከተካሄደው ምርጫ 97 በኋላ አገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ በመግባቷ፣ የከተማውን ቁልፍ የተረከበው የፖለቲካ ሥልጣን የሌለው ባለአደራ አስተዳደር ችግሩን ሊፈታው አልቻለም ነበር፡፡

ቦታዎቹን የተረከቡት የሪል ስቴት አልሚዎች ቦታውን ካላለሙ የሚነጠቁ መሆኑን በተደጋጋሚ በመስማታቸው፣ የሰውና የጋማ ከብቶችን ጉልበት በመጠቀም  ግንባታውን ለማካሄድ መሞከራቸው ይታይ ነበር፡፡

ነገር ግን አቶ ኩማ ደመቅሳ የከተማውን ቁልፍ በተረከቡ በሦስተኛ ዓመት በሪል ስቴት አልሚዎች ላይ ዘመቻ ተከፍቷል፡፡ የዘመቻው ማጠንጠኛ የሪል ስቴት አልሚዎች በገቡት ውል መሠረት ግንባታ አለማካሄዳቸው፣ በውል ከወሰዱት ቦታ ውጪ ቦታ አስፋፍተው መያዛቸውና ግንባታ ሳያካሂዱ ለሦስተኛ ወገን መሬት አሳልፈው መስጠታቸው ተጠቃሽ ምክንያቶች ነበሩ፡፡  

በዚያ ጊዜ በሪል ስቴት ግብይት የመጀመርያው ቀውስ ተፈጥሯል፡፡ የሪል ስቴት ቤቶችን ለመግዛት ገንዘብ ከፍለው የሚጠባበቁ፣ ክፍያ በመፈጸም ሒደት ላይ የነበሩና በአጠቃላይ በሪል ስቴት ቤቶች ፍላጎት የነበራቸው ተዋናዮች ውዥንብር ውስጥ ገብተው ነበር፡፡

ከዚያ በኋላ የሪል ስቴት ገበያው ለመስተካከል ብዙ ጊዜ የወሰደበት ሲሆን፣ በመስተካከል ላይ እያለ የአክሰስ ሪል ስቴት ጉዳይ ተከሰተ፡፡ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ አክሰስ ሪል ስቴት 2,500 ለሚሆኑ ደንበኞች ቤት ሠርቶ እንደሚያስረክብ በመግለጽ 1.4 ቢሊዮን ብር ከሰበሰበ በኋላ፣ በገባው ውል መሠረት ቤቶቹን ሠርቶ ማስረከብ አልቻለም፡፡

በዚህ ምክንያት የሪል ስቴት ገበያው ላለፉት ሦስት ዓመታት በከፍተኛ ያለመተማመን ስሜት ውስጥ ቆይቷል፡፡

በመንግሥትም ሆነ በገበያተኞቹ በጥርጣሬ የሚታየው የሪል ስቴት ዘርፍ ከሦስት ዓመታት በላይ ተቀዛቅዞ ከቆየ በኋላ አዳዲስ ሐሳብ ይዘው በመጡ አልሚዎች በድጋሚ ማንሰራራት ጀምሮ ነበር፡፡

በተለይ ኖኅ ሪል ስቴት፣ ፍሊንት ስቶን ሆምስ ከመንግሥት ሳይሆን ከግለሰቦች ቦታ በማፈላለግ መኖሪያ ቤት እየገነቡ ማስረከባቸው ለገበያው በድጋሚ መነሳሳት አስተዋጽኦ እንዳበረከተ የዘርፉ ተዋናዮች ያምናሉ፡፡

ይህ የሪል ስቴት ዘርፍ የገበያ መነቃቃት ብዙም ሳይጓዝ ከታኅሳስ ሁለተኛው ሳምንት ጀምሮ በድጋሚ ወደ ቀድሞው ቀውስ ውስጥ ገብቷል፡፡

ለቀውሱ መፈጠር ምክንያቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ፣ ታኅሳስ 8 ቀን 2011 ዓ.ም. አገልግሎት መስጠት ማቆሙና የፌዴራል ፖሊስ ታኅሳስ 9 ቀን 2011 ዓ.ም. ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ተቋማት በጻፈው ደብዳቤ፣ 28 ሪል ስቴት አልሚዎች እንዲታገዱና ከሪል ስቴት ኩባንያዎቹ ጋር የተገናኘ መረጃ እንዲላክለት በመጠየቁ ነው፡፡

ፌዴራል ፖሊስ ለተቋማቱ በጻፈው ደብዳቤ፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሙስና ወንጀል በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ የምርመራ ማጣራት እየሠራ እንደሚገኝ በመግለጽ፣ የሪል ስቴት አልሚዎቹ ባለቤት እነማን እንደሆኑ፣ የመሬት ሊዝ የከፈሉበት ሰነድ፣ ቤት ገንብተው ያስተላለፉላቸው ግለሰቦች ዝርዝር እንዲላክለት ጠይቋል፡፡  

‹‹የፀረ ሙስና ልዩ ሥነ ሥርዓትና ማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 434/97 አንቀጽ 8(4) (በአዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ አምስት እንደተሻሻለው) መሠረት ታግዶ ሕንፃዎቹ በማን ስም እንደሚገኙና የቦታዎችን አሰጣጥ ሕጋዊነት፣ እንዲሁም ቦታዎቹ ከተጠርጣሪው ግለሰብ ወደ ሦስተኛ ወገን ተላልፈው ከሆነ ለማንና እንዴት እንደተላለፈ አጣርታችሁ መረጃ ላኩ፤›› በማለት የጠየቀው የፌዴራል ፖሊስ ደብዳቤ፣ ‹‹በተሻሻለው የፀረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 433/97 አንቀጽ 36 ንዑስ አንቀጽ 3 እና 4 መሠረት፣ እንዲሁም ጉዳዩ በፍርድ ቤት ቀጠሮ ላይ የሚገኝ መሆኑን በመገንዘብ ማስረጃውን በተቻለ ፍጥነት እንድትልኩ፤›› በማለት ፌዴራል ፖሊስ በደብዳቤው ጠይቋል፡፡

ከዚህ በኋላ የሪል ስቴት ገበያው አገልግሎት ብቻም ሳይሆን በመታገዱ ጭምር በድጋሚ የተቀዛቀዘ ሲሆን፣ በደንበኞችና በአልሚዎች መካከልም ቀውስ ተፈጥሯል፡፡

ተስፋ የተጣለበት ነገር ግን በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የሚገኘው የሪል ስቴት ዘርፍ፣ እንደ አዲስ ለማበብ ወይም ለመክሰም ሁለት ጉዳዮች ከፊት ለፊቱ ይጠብቁታል፡፡

የፌዴራል መንግሥት በአዲስ አበባም ሆነ በክልል ከተሞች በመንግሥትና በግል አጋርነት የቤት ልማት ፕሮግራሞችን ለማካሄድ ማሰብ መጀመሩ ለዘርፉ አዲስ ተስፋ ነው፡፡ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ኅዳር 2011 ዓ.ም. ባቀረበው ምክረ ሐሳብ፣ የአገር ውስጥ አልሚዎችን በግልና በመንግሥት አጋርነት ለማሳተፍ ጥናት ማካሄድ መጀመሩን አስታውቋል፡፡

የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ከመንግሥት ጋር አንድ ላይ ሆነው ግንባታ ቢያካሂዱ ሊኖር የሚችለውን ጥቅም ሚኒስቴሩ አብራርቷል፡፡ በዚህም መሠረት የመኖሪያ ቤት ገበያ ከዓለም አቀፍ ውድድር ውጪ የሆነና በማደግ ላይ ባለ ኢኮኖሚ ደግሞ ፍላጎቱ ከፍተኛና አትራፊ ስለሆነ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ለማሳደግ ይረዳል፡፡

በተጨማሪም የግንባታ አቅም ከሥራ ውጪ ስለማይገነባ የአገር ውስጥ ባለሀብቶቹ በስፋት ዕድል ሲሰጣቸው፣ በተግባር እየተማሩ የመፈጸምና የማስፈጸም አቅማቸውን መገንባት ያስችላል የሚል ነው፡፡

ከዚህ ባሻገር የመኖሪያ ቤት ግንባታ በኢትዮጵያ ገንዘብ ማከናወን መቻሉ ነው፡፡ ከፌዴራል መንግሥት በተጨማሪ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት ግንባታ በመንግሥትና በግል አጋርነት ለማካሄድ ዕቅድ አውጥቷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ በአዲስ መንገድ የሚያዋቅረው የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ከተሰጡት ኃላፊነቶች መካከል መንግሥትና የግል ባለሀብቶች በአጋርነት የቤት ልማት ማካሄድ የሚችሉበት ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡ እነዚህ የመንግሥት አዳዲስ ዕቅዶች የሪል ስቴት አልሚው ተስፋዎች ሆነው ተመዝግበዋል፡፡  

መንግሥት ዘግይቶም ቢሆን ለመጀመር ያቀደው የመንግሥትና የግል አጋርነት ፕሮግራም ለሪል ስቴት አልሚዎች እንደ በረከት የሚታይ መሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡

ነገር ግን የሪል ስቴት አልሚዎች መርገምትም ከፊታቸው አለ፡፡ የሪል ስቴት አልሚዎች በጥሩ መንገድ እየታዩ ያለመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ያለባቸው በመሆኑ ከደንበኛ ሰብስበው ነው ወደ ግንባታ የሚገቡት፡፡

የሞርጌጅ ባንክ በዋነኛነት ለቤት ተጠቃሚ ብድር ሥርጭት የሚውል ቢሆንም፣ ቤት አልሚው ሊጠቀመበት የሚችል አማራጭም ነው፡፡ ይህ ሥርዓት አሁን በመደበኛነት በኢትዮጵያ የለም፡፡ ለኮንዶሚኒየም እየቀረበ ያለው ብድር የመደበኛ ቁጠባ በመንግሥት ዋስትና የሚገኝ ነው፡፡ ለብድር በገንዘብ ምንጭነት የሚታዩት የኢንሹራንስና ጡረታ ፈንዶች፣ ራሱን የቻለ የቤት ፈንድ፣ የቤት አቅርቦት ዋስትና ሥርጭት ፈንድ የተጠቃሚው ዋስትና እንዲረጋገጥ ገቢ በየወሩ የሚከፈልበት አሠራር በበርካታ አገሮች እየተሠራበት ይገኛል፡፡

ነገር ግን መንግሥት ቅድሚያ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ትኩረት በመስጠቱ፣ መኖሪያ ቤት እንደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የውጭ ምንዛሪ የማያስገኝ በመሆኑ ቅድሚያ አልተሰጠውም፡፡ ይህ አሠራር ካልተስተካከለ ፈተናው ይቀጥላል፡፡

የሪል ስቴት አልሚዎች በብዙ ውጣ ውረድ አልፈው 15ኛ ዓመታቸውን ቢያስቆጥሩም፣ በሒደት በተለይ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዚያ ወቅት ባገኙት መሬት ላይ ግንባታ አካሄደው እየጨረሱ ይገኛሉ፡፡

የዘርፉ ዋነኛ ተዋናዮች እንደሚሉት ከግለሰቦች ቦታ እየገዙ ግንባታ ማካሄድ ያን ያህል አዋጭ አይደለም፡፡ ስለዚህ ከውጣ ውረድ በኋላ ብዙ ልምድ ያካበቱበትን ሥራ ለቀው ለመውጣት ጫፍ እየደረሱ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግልና የመንግሥት አጋርነት ፕሮግራሙን መቼ እንደሚጀምር በውል አልገለጸም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ አገልግሎት መስጫ ለሆኑ ሪል ስቴት የመሳሰሉ ልማቶች ቦታ በድርድር አይፈቅድም፡፡ የሊዝ አዋጅን ለማሻሻል ለሚኒስትሮች ምከር ቤት የቀረበው ረቂቅ አዋጅም የውኃ ሽታ ሆኖ በመቅረቱ፣ የሪል ስቴት አልሚዎች በመንታ መንገድ ላይ ይገኛሉ፡፡     

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች