Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ድክ ድክ የሚለው የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ያገኙት የሕዝብ ድጋፍ አገሪቱን ወደፊት ለማራመድ እንደ መልካም ዕድል የሚወሰድ ስለመሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ይህ ድጋፍ በተለያዩ መንገዶች የተገለጸ ሲሆን፣ በተለይ ዳያስፖራው ለእርሳቸው የሰጠው ግምት ከፍተኛ ነው፡፡ ለዚህም ዳያስፖራው ከአንድ ማኪያቶው በቀን አንድ ዶላር አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ያደረጉትን ጥሪ በደስታ ነበር የተቀበለው፡፡ ሆኖም በተጠበቀው መሠረት ዳያስፖራውን ይህንን ድጋፍ እያደረገ ያለመሆኑ የታወቀው ከሁለት ወራት በኋላ ነው፡፡ ይህ ለምን ሆነ የሚለው ነገር አነጋጋሪም ነበር፡፡

ዳያስፖራው የታሰበውን ያህል ድጋፍ ያለማድረጉን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው፡፡ እስካሁን ሁለት ሺሕ ዳያስፖራ ብቻ ተሳታፊ ሆኗል፡፡ ይህ ቁጥር ግን ካለው ዳያስፖራ ቁጥር አንፃር ሲታይ አነስተኛ መሆኑን በመጠቆም፣ ቆንጠጥ ያለ መልዕክት እስከማስተላለፍ ደርሰዋል፡፡ ይህ መልዕክት ከተደመጠ በኋላ ወደ ዳያስፖራ ትረስት ፈንዱ ቋት እጃቸውን የዘረጉ ዳያስፖራዎች ቁጥር ከአምስት ሺሕ በላይ ስለመድረሱ ተገልጿል፡፡ በየዕለቱም ቁጥሩ እየጨመረ ሄዷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉትም ሆነ በግልጽ እንደሚታየው ከሦስት ሚሊዮን በላይ ከሚሆን ዳያስፖራ በሁለትና ሦስት ወር ውስጥ አምስት ሺሕዎች ብቻ የተገባን ቃል ፈጽመዋል መባሉ በእርግጥም ብዥታ ይፈጥራል፡፡

ማናችንም ብንሆን ግን ዳያስፖራዎቻችን በቀን አንድ ዶላር ለፈንዱ ገቢ ማድረግ ይከብዳቸዋል ብለን አናስብም፡፡ ይህ የአንድ ዶላር ድጋፍ ምናልባት ዳያስፖራዎቻችን ለአገራቸው መፈጸም ይችላሉ ተብሎ ከሚታመነው ዘርፈ ብዙ እገዛዎች እጅግ ኢምንቷ ነች ተብሎም ይታመናል፡፡

ቃል መከበር አለበት የሚለው እምነት እንደተጠበቀ ሆኖ እጅግ የበዛው ዳያስፖራ በቀን አንድ ዶላር ለመለገስ ጉልበት ያጣበት ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ካለመደገፍ ጋር የተያያዘ ይሆናል ተብሎም ፈጽሞ አይታሰብም፡፡

ነገር ግን ሰዎች ነንና የቱንም ያህል የማድረግ ፍላጎታችን የበረታ ቢሆን ጎትጓችና የተፈለገውን ለማድረግ ምቹ ሁኔታ መሻታችን እንዳለ መዘንጋት የለበትም፡፡ ሌላው ይህንን ገንዘብ ለማስገባት የተዘረጋው የገንዘብ ማሰባሰብያ ዘዴ ደካማ ሆኖ ሊሆን እንደሚችል መገመትም ስህተት ላይ አይጥልም፡፡

ለምሳሌ እንኳን የዳያስፖራ ትረስት ፈንዱ በይፋ መጀመሩ ከተገለጸና ለዚህ ገንዘብ ማሰባሰቢያ የሚሆነው የባንክ አካውንት ከተገለጸ በኋላ ይህንን መረጃ የሚገልጸው ማስታወቂያ የሄደው እጅግ ለአጭር ጊዜ ነው፡፡ ይህ መሆኑ አንድ ክፍተት ነው፡፡ ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዳያፖራው የተሰበሰበውን የገንዘብ መጠንና እስካሁን ተሳታፊ የሆኑትን ዳያስፖራዎች ቁጥር ከገለጹ በኋላ ፈንዱን ለማሰባሰብ የሚያስችል ማስታወቂያ መለቀቅ ጀምሯል፡፡ ግን እንዲህ ያሉ እንደ ማስታወሻ ሊቆጠሩ የሚችሉ መልዕክቶች በተለያዩ መንገዶች መለቀቅ አለባቸው፡፡ በየጊዜው እንዲያስታውሱት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ በየጊዜው እየተገኘ ያለውን የገንዘብ መጠን ሳይቆራረጥ መግለጹም አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለት ሺሕ ዳያስፖራዎች ብቻ ናቸው እስካሁን ገንዘቡን ያስገቡት ባሉ በቀናት ልዩነት በሁለትና በሦስት ወራት ያልተገኘው ገቢ ሊገባ የቻለው፡፡ ስለዚህ ማስታወቂያና እየተደረገ ያለውን ድጋፍ መረጃ በመስጠት የፈንድ ማሰባሰብን ሥራ በተፈለገው መጠን ከፍ ማድረግ እንደሚቻል ግንዛቤ መወሰድ አለበት፡፡

ፈንዱን ለማሰባሰብ ኃላፊነት የተሰጠው ኮሚቴም ዳያስፖራው መረጃው በቀላሉ የሚደርስበትን መንገድ በአግባቡ እየሠራ መሆኑን መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ ቤት እያንኳኳ ‹‹እንዴ ቃል የገባችሁትን ረሳችሁት እንዴ?›› ማለት የሚጠበቅበት ባይሆንም፣ ጊዜው የቴክኖሎጂ ነውና ማስታወሱ የግድ ነው፡፡

ከዚህም ሌላ ፈንዱ የሚሰባሰብበት መንገድ ጠባብ መሆንም ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ ፈንዱ ይሰባሰብበታል የተባለው በአንድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንት ብቻ መሆን ዳያስፖራውን አማራጭ ሊያሳጣው ይችላል፡፡

በእርግጥ በአንድ አካውንት ብቻ እንዲገባ መደረጉ ምክንያት ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን በአንድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንት ብቻ እንዲገባ መደረጉ የታሰበውን ያህል ለመሰብሰብ ያልተቻለ ይሆናል፡፡

ምናልባት ፈንዱ የሚሰበሰብበት አካውንት በአንድ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ መሆኑ ቀርቶ በሌሎች የግል ባንኮች ጭምር ሆኖ የአካውንቶቹ ቁጥር ቢጨምር የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ እንዲህ ማድረጉ አማራጭ የሚሰጥ ስለመሆኑ ጉዳዩን አንስቼ ያዋየኋቸው የባንክ ሰዎች አማራጭ ማስፋቱ መሆኑን አስረድተውኛል፡፡

እንደውም በሁሉም ባንኮች ቢሆን ዳያስፖራው በየባንኮች ለዚሁ በተዘጋጀ ዝግ አካውንት ፈንዱን አሰባስበው እዚህ አዲስ አበባ በተዘጋጀው ወደ ዋናው የፈንዱ ማሰባሰቢያ የመንግሥት አካውንት ማስገባት ይቻላል በሚል ሐሳቤን አጠናክረውልኛል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ አማራጮችን መጠቀም ይቻላል፡፡

ምክንያቱም በውጭ የሚገኘው ዳያስፖራ ወደ አገር ቤት ገንዘብ ሲልክ እንደ አማራጭ የሚጠቀመው የተለያዩ ባንኮችን ከመሆኑ አንፃር፣ ለፈንዱ የሚገባውንም ገንዘብ በዚያው ባንክ በኩል ለመላክ ያስችለዋል፡፡

ስለዚህ ፈንዱ የሚሰባሰብበት የባንክ አካውንት በሌሎች ባንኮችም ጭምር እንዲሆን በማድረግ ዳያስፖራው ቃል የገባውን እንዲፈጽም ማድረግ ይቻላል፡፡ የሚፈለገው ገንዘብ እየጨመረ ሲሄድም ከሥር ከሥር የዳያስፖራው ማስታወሻዎች ይሆናሉ የተባሉት እንደ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ይጀመራሉና ሁሉም የበኩሉን ያድርግ፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት