Monday, July 15, 2024

የኦነግና የኦዴፓ ውዝግብ አገራዊ አንድምታ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡበት መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ወዲህ በተለያዩ ምክንያቶች ከኢትዮጵያ ርቀው በውጭ ሲንቀሳቀሱ የቆዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ወደ አገር ቤት እንዲመለሱና ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንዲያደርጉ በተደጋጋሚ ጥሪዎች ሲያደርጉ ተደምጠዋል፡፡ ይኼንን ጥሪ በመከተልም ካሁን ቀደም በጉልህ ስማቸው የሚታወቁም ሆነ የማይታወቁ የፖለቲካ ቡድኖች ወደ አገር ቤት ተመልሰው ለመታገል የሚያስችላቸው ሁኔታ በመፈጠሩ እንደተመለሱ እየተናገሩ፣ ገሚሱ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተቀሩት ደግሞ በተለያዩ መጓጓዣዎች ድንበር አቋርጠው ገብተዋል፡፡

እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገር ቤት ከገቡ አንስቶ በስፋት የፖለቲካ ሥራዎችን ሲያከናውኑ ባይታዩም፣ አንዳንዶቹ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ሕዝብን ማወያየት፣ በተለያዩ የፖለቲካ ውይይቶች ላይ እሳቤዎቻቸውንና አቋሞቻቸውን ማንፀባረቅና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር ደጋፊዎቻቸውን ሲያነቃቁ ተስተውለዋል፡፡ በዛ የሚሉት በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል ያግዛሉ ባሏቸው ዘርፎች ከመንግሥት ጋር በመተባበር ለመሥራት ፍላጎት ሲያሳዩ፣ የተወሰኑት ራቅ ብለው በመጓዝ የገዥው አዲስ አባል ድርጅት ከሆኑ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት እስከ መፍጠር ደርሰዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ከኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) ጋር ተዋህኦ ለመቀጠል የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረመው በአቶ ሌንጮ ለታ የሚመራው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) እና ውህደት የፈጸሙት የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) እና የአማራ ዴሞክራሲ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን) ይጠቀሳሉ፡፡

የኦነግና የኦዴፓ ውዝግብ አገራዊ አንድምታ

ይሁንና በመንግሥት ጥሪና በተለየ ድርድር ወደ አገር ቤት የተመለሰው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በተመለከተ የሚታየው ግን የመተባበርና አብሮ የመሥራት ሳይሆን ተገዳዳሪነት የሚታይበት ነው ሲሉ፣ በርካታ ፖለቲከኞችና ተንታኞች ምልከታቸውን ያሰማሉ፡፡ ይህም የኦነግና የኦዴፓ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በሚሰጧቸው መግለጫዎችና በሚያወጧቸው ጽሑፎች በተደጋጋሚ የታየ ሲሆን፣ የሚሾሙ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን በተመለከተ ለምን ሾማችሁ የሚል ጥያቄ ከኦነግ ወገን እየመጣ መሆኑን ኦዴፓ በመጥቀስ ሲወቅስ፣ ኦነግ ደግሞ ከመምጣታችን በፊት የተስማማንባቸው ጉዳዮችን በመፈጸም ረገድ መንግሥት መለሳለስ እያሳየ ነው ሲል ይኮንናል፡፡

ይህ የሁለቱ ወገኖች ክርክር በመካከላቸው የተደረገው ስምምነት ምን ነበር? ስምምነቱስ የተፈጸመው በፌዴራል መንግሥት ነው? ወይስ በክልሉ መንግሥት? የሚሉ ጥያቄዎች በብዛት እንዲነሱ ያደረገ ነው፡፡ ይህም ‹‹ለፍርድ የማይመች›› ሁኔታ እንደሆነ በርካቶች ይስማማሉ፡፡ ምክንያቱም ኦነግ ተስማማበት የተባለውና ለሕዝብ ይፋ የተደረገው ባለ ሦስት ነጥብ ስምምነት ድፍን መሆኑና ምን ምን ተግባራትን እንደሚያካትት የተነገረ ነገር ባለመኖሩ ነው፡፡ እነዚህ ነጥቦች ጦርነት ማቆምና ታጣቂዎች አገር ውስጥ ገብተው ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ፣ በጋራ ለመሥራትና ጠላትነትን ለማቆም፣ ብሎም የተደረሰውን ስምምነት የሚያስፈጽም የጋራ ኮሚቴ ማቋቋም የሚሉ ሲሆን እንዴት ይፈጸማሉ? በምን አግባብ ይፈጸማሉ? ምን ዓይነት ኮሚቴ ነው የሚቋቋመው? እነ ማንን ያካተተ ኮሚቴ ነው የሚሆነው? ወታደሮቹን፣ መንግሥትንና ሌሎች የሚመለከታቸውን ኃይሎች እንዴት አካትቶ ይሠራል? የሚሉ ጥያቄዎች መልስ ያላገኙና ለአሁኑ ውዝግቦች በር የከፈቱ ጉዳዮች ናቸው የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡

‹‹መጀመሪያውኑ እነዚህ የታጠቁ ኃይሎች የመጡት በጥሪ ነው፡፡ ነገር ግን በአሸባሪነት በፈረጃቸውና በኋላም ነፃ ባደረጋቸው ፓርላማ ነበር ጥሪውም፡፡ ስምምነት ካስፈለገ እርሱም መሆን የነበረበት፤›› የሚሉት የኢዴፓ የቀድሞ የሥራ አመራር አባልና ፖለቲከኛ አቶ ሙሼ ሰሙ፣ ‹‹ከጥሪው በላይ ተጨማሪ ርቀት ተኪዶ አስመራ ስምምነት ተደርጎ ነው እንዲመጡ የተደረገው፡፡ እዚህ ላይ የመጀመሪያው ጥያቄ ተደራዳሪ ሆነው የሄዱትን ሰዎች ስናይ ጉዳዩን አገራዊ? ወይስ የፓርቲ አድርገው ነው የያዙት? የሚል ይሆናል፤›› ይላሉ፡፡

በተጨማሪም ምን ዓይነት ስምምነት እንደተደረገ እንደማይታወቅና ይህ ለሕዝቡ ይፋ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ ኦነግ ምን ያህል ሠራዊት እንዳለውና ምን ያህሉን ከውጭ ይዞ እንደሚገባ፣ አገር ውስጥም ምን ያህል እንዳለው ታውቆ መፍትሔው ቀላል ይሆን ነበር ይላሉ፡፡ ይህ ባለበት ሁኔታ ኦነግ ትጥቅ ይፍታ ሲባል ‹ማነው ፈቺው? ማነው አስፈቺው?› የሚል ጥያቄ እንዲመጣ፣ ኦነግም ይኼንን ማድረግ ያስፈለገ/ አንዱ ምክንያት ከደርግ ጋር ከነበረው የትጥቅ ትግል በኋላ፣ በትጥቅ መፍታት ምክንያት በተፈጠረ ውዝግብ ትውስታዊ ሥጋት ሊሆን እንደሚችል  አቶ ሙሼ ይገምታሉ፡፡

ይኼንን ሐሳብ በመጋራት ከኦነግ ጋር የተደረገው ስምምነት ግልጽነት ማጣት ለዚህ ሁሉ እሰጥ አገባ እንዳበቃ በማመላከት የሚከራከሩት ደግሞ፣ የኦዴግ ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታ ናቸው፡፡ እሳቸው ይህ ስምምነት ድብቅ መሆኑ ሕዝቡ እንዳይጠይቅና አጥፊውን በመለየት የራሱን ፍርድ እንዳይሰጥ አዳጋች እንዳደረገው ያስረዳሉ፡፡ ስምምነቱ ለዚህ ሁሉ ውዝግብ መንስዔ ከመሆን ባሻገር ‹‹ለፍርድ ያስቸገረ›› ነው ሲሉም ያብራራሉ፡፡

‹‹ኦነግ ሰላማዊ ትግልን ለመከተል በማሰብ እስከመጣ ድረስ የታጠቀ ኃይል ምን ያደርግለታል? በሰላም ለመታገል እስከተስማማ ድረስ መፍትሔው ቀላል ነው፡፡ በፓርቲው ሊቀመንበር ትዕዛዝ ተላልፎ ሠራዊቱ አንድ ቦታ እንዲሰበስብና ወደ ካምፕ እንዲገባ ማድረግ፣ አሻፈረኝ የሚል ካለም ይህ የኦነግ ሠራዊት አባል አይደለምና መንግሥት የሚወስደውን ዕርምጃ መውሰድ ነው፡፡ ይኼንን ያህል ቀላል በመሆኑ ድርድርም ሁሉ ላያስፈልግ ይችላል፤›› ሲሉ ይከራከራሉ፡፡

ነገር ግን ሪፖርተር ያናገራቸው ስማቸው ባላቸው የሥራ ኃላፊነት ገደብ ምክንያት እንዳይጠቀስ የጠየቁ ከፍተኛ የኦነግ አመራር ስምምነቱን እነሱ በቻሉት መጠን ይፋ ለማድረግ እንደጣሩ፣ ነገር ግን መንግሥት ይፋ ለማድረግ እምብዛም ትኩረት አላደረገም ይላሉ፡፡ በስምምነቱም ኦነግ ያለውን ሠራዊት በክፍለ ጦር አሳውቆ አባላቱ ወደ ኦሮሚያ ፀጥታ ቢሮዎችና ወደ መከላከያ ማስገባትን ያካተተ ሲሆን፣ እስካሁን 1,300 ወታደሮች ወደ ማሠልጠኛ ካምፕ እንደገቡ ያስረዳሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 700 አባላት በፖሊስ ኮሌጅ በሥልጠና ላይ የሚገኙ መሆናቸውን፣ 600 ደግሞ አርዳኢታ በሥልጠና ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ይሁንና እንደ ኃላፊው ገለጻ በምዕራብ ወለጋ አካባቢ ያሉ ወታደሮችን ጨምሮ በአገሪቱ ደቡባዊና ምሥራቃዊ አካባቢዎች በርካታ የኦነግ ሠራዊት እንዳለ፣ ነገር ግን መንግሥትም ሆነ ሌላው አካል እሳቸው በግልጽ በማያውቁት ምክንያት ትኩረቱን ምዕራብ ወለጋ ያለው ጦር ላይ እንዳደረገ ይናገራሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ እንደ እሳቸው ምልከታ መንግሥት ከኦነግ ጋር ያደረገው ስምምነት ግልጽ አለመሆን የፈጠረው ክፍተት ቢኖርም፣ ዋናው ግን የኦዴፓ አባላት በማኅበራዊ ድረ ገጾችና በተለያዩ መድረኮች የሚያስሟቸው ክሶች ለመፍትሔ እንቅፋት ናቸው ይላሉ፡፡

‹‹እንደ አቶ አዲሱ አረጋ ያሉ የፓርቲው አባላት በፌስቡክ የሚያቀርቡት ክስ እንቅፋት ሆኗል፡፡ በወቅቱ ሲነገሩ የነበሩ ትጥቅ ይፈታልና ካምፕ ይገባል የሚሉት ንግግሮች ስሜታዊነትን ያስከተሉ ነበሩ፤›› የሚሉት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊው፣ ‹‹አንዳችን በሌላው ላይ ፕሮፓጋንዳ እንደማናደርግ ከስምምነት ደርሰን የነበረውን በተደጋጋሚ ጥሰዋል፤›› ሲሉ ይወቅሳሉ፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ ከሆነ ሠራዊቱ ወደ መንግሥት ፀጥታ አካላት የሚካተትበት እንጂ፣ አንዱ ፈቺ ሌላው አስፈቺ የሚል ስምምነት አልተደረገም፡፡ በዚህም ባለድርሻ አካላት በሙሉ እንዲሳተፉ ስምምነት መደረጉን ተናግረው፣ ያስታጠቀው ሕዝብ፣ የሚታገለው ሠራዊትና የፓርቲው አመራሮች ተሳታፊ እንዲሆኑ ስምምነት መደረጉን አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም የኦነግ ሠራዊት ሥልጠናውን ጨርሶ እስኪሰማራ ድረስ ከሁለቱም ወገኖች የፓርቲ አመራሮች እንዲጎበኟቿውና የሚሠለጥኑበትም ካሪኩለምና ሞጁል በጋራ መሰናዳቱን ተናግረው፣ የኦነግ አመራሮች ግን ለጉብኝት ሲሄዱ እንዲመለሱ መደረጉን ያስረዳሉ፡፡ የወታደሮቹ ማሠልጠኛ ካሪኩለምና ሞጁል በጋራ በተቋቋመ ኮሚቴ እንደተዘጋጀ ያስረዱት ኃላፊው፣ እንደ ካሁን ቀደሙ የፓርቲ ተገዥ የሚያደርግ ሥልጠና እንዳይኖር የማረጋገጥ ጉብኝት ማድረግ በስምምነት የተደረሰበት ሲሆን፣ ከሥልጠናው በኋላ ደግሞ ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ግንኙነት እንዳይኖር ስምምነት መደረሱን ገልጸዋል፡፡

ይህ የተደረገው ስምምነት ከኦሮሚያና ከኦዴፓ አመራሮች ጋር ቢሆንም፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እንደ ክልል ስምምነት አላደረግንም ያሉት ኃላፊው፣ የልዑካን ቡድኑ አባላት ከኦሮሚያ የሆኑት ለጉዳዩ ቅርበት አላቸው በሚል ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡

በአስመራ ከኦነግ ጋር የተደረገው ስምምነት በኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ፣ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳና በኦዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) መካከል መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡

ምንም እንኳን ስምምነት ቢደረስበትም ኦነግ ሙሉ በሙሉ ያለውን ሠራዊት ወደ መንግሥት ሠራዊት እንዳላስገባ የተናገሩት እኚህ ኃላፊ፣ ካምፕ የገቡት የሚያሰሙት ቅሬታና የመንግሥት መግለጫዎች ከፍተኛ ጫና በሠራዊቱ ላይ በማሳደሩ ማሳካት እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡ በካምፕ ያሉት ‹እንደ እስረኛ ነው የምንታየው› በማለት የሚያሰሙት ቅሬታ መኖሩን፣ ይኼንንም ለማረጋገጥ የፓርቲው አመራሮች መሄድና መጎብኘት አለመቻላቸውን ያስረዳሉ፡፡

የሠራዊቱን የሥልጠና ካሪኩለምና ሞጁል ያዘጋጀው ኮሚቴ ከኦነግ፣ ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንና ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ የቴክኒክ አማሪዎችን ያካተተ ነው፡፡

‹‹በእኛ በኩል ስምምነቱን ለማክበር ቁርጠኝነት አለን፡፡ የሚወጡት መግለጫዎች ግን እንቅፋት የሚፈጥሩ ናቸው፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ኦነግ ገደላቸው ስለሚባሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችም ስም፣ የት እንደሚሠሩና በምን ሁኔታ እንደተገደሉ መረጃ ሳይሰጥ በደፈናው ወቀሳ እንደሚሰነዘርባቸው ተናግረዋል፡፡ በአስገድዶ መድፈርም የኦነግ ሠራዊት እንደሚታማ ገልጸዋል፡፡

‹‹ስለሠራዊቱ ትንሽ ዕውቀት ያለው ሰው ይህ ምን ያህል ሥነ ልቦናዊ ጫና እንደሚያስከትል ይረዳል፡፡ የእኛ ሠራዊት ግን በዲሲፕሊን የሚመራ ነው፤›› ሲሉም ያስተባብላሉ፡፡

በድርድር የተጀመረ ጉዳይ እንዲህ ለዜናና ለሚዲያ ፍጆታ መዋል አልነበረበትም የሚሉት አቶ ሙሼ፣ ‹‹በውስጥ እንደተጀመረ በውስጥ መፈታት ነበረበት፡፡ ምክንያቱም የሚያስከትለው የፖለቲካ ቀውስ የበዛ ነው፡፡ ሁሉም በኦነግ ስም እየተደራጀ ክፍተትን መጠቀም በመጀመሩ፣ መንግሥት ኃላፊነቱን መወጣት አልቻለም የሚል አስተሳሰብ በመምጣቱ ሕዝቡ በመሀል እየተጎዳ ነው፤›› ብለው፣ ‹‹ይህ አቅም የማሳያ ትርዒት መሆን የለበትም፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

ነገር ግን ኦነግ እያሳየ ያለው የተገዳዳሪነት መንፈስ ከዚህ በላይ ምን ሊደረግለት ቃል ተገብቶለት ነበር የሚል ጥያቄም እንደሚያጭር አቶ ሙሼ ይናገራሉ፡፡ የኦሮሚያ ክልል መንግሥትና ኦነግ የሚያወጧቸው መግለጫዎች የተጣረሱ ከመሆናቸው የተነሳ፣ በድርድር ላይ ያሉ ቡድኖች የሚሰጡት እንደማይመስልና ኦነግም እንደ መንግሥት እየተንቀሳቀስ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ነገር ግን በዚህም ሄደ በዚያ ኦነግ ትጥቅ ፈትቶ መንግሥት ብቸኛው ታጣቂ ያለው ኃይል እንደሚሆን ጥርጥር የላቸውም፡፡

‹‹መንግሥት መንግሥት መሆን ካልቻለ የማንም መጫወቻ ነው የሚሆነው፤›› ብለው፣ ‹‹ለኦነግ ዕገዛ መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡ ኦነግንም መግፋት አያስፈልግም፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

ይህ ክስተት ግን በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ሥጋት የደቀነ አደገኛ አስተሳሰብ የሚያስከትል እንዳልሆነ አቶ ሌንጮ ይናገራሉ፡፡ ስለዚህም መንግሥት ታጣቂዎቹ ትጥቃቸውን እንዲፈቱ ለማድረግ አስፈላጊውን ጥረት ሁሉ ማድረግ አለበት ይላሉ፡፡ ይህ ጥረት ካልተሳካም መንግሥት ምን ማድረግ እንደሚችል ግልጽ ነው ሲሉም ያስገነዝባሉ፡፡

 አቶ ሙሼ አሁን በኦነግና በኦዴፓ መካከል ከሚታየው ውዝግብ ሌሎች ፓርቲዎች ምንም ትምህርት መውሰድ እንደሌለባቸው፣ ከልባቸው በሰላማዊ መንገድ ለመታገል እስከመጡ ድረስ ሌላ አማራጭ ማማተር እንደማይኖርባቸው ይናገራሉ፡፡ ያሉት አመቺ መደላድሎች እስካልተዘጉ ድረስ ሌላ አማራጭ ማየት የለባቸውም ባይ ናቸው፡፡

‹‹ሌሎች ፓርቲዎች እንዲያውም መግባባታቸውንና ግንኙነት ተጠቅመው ዕገዛ ማድረግ ነው ያለባቸው፤›› ያሉት አቶ ሙሼ፣ ‹‹ከመንግሥት ጋር በትጥቅ መታገል አዋጭ አይደለም፡፡ እንኳን አሁን ይቅርና መንግሥት ተዳክሟል ሲባል በነበረበት ጊዜ እንኳን ይህ አካሄድ አልተሳካም፡፡ ከመንግሥት ጋር የጉልበት ትርዒት ማሳየት አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ይህ መንገድ አዋጭ እንዳልሆነ የተናገሩት አቶ ሌንጮ፣ ‹‹ሕዝቡ በባዶ እጁ ከታጠቀ የመንግሥት ኃይል ጋር ሲታገል በነበረበት ወቅት ወታደሩ የት ነበር? ያኔ ነው እንጂ አሁን ወታደር አያስፈልግም፤›› ይላሉ፡፡

አቶ ሙሼና አቶ ሌንጮ ኦነግ በምርጫ ተወዳድሮ ለሕዝቡ አማራጭ ሆኖ የተሻለ ሥራ የሚሠራበትን ዕድል መፈለግ እንዳለበት ይስማማሉ፡፡

ከሪፖርተር ጋር ቆይታ ያደረጉት የኦነግ ከፍተኛ አመራርም እንዲሁ፣ ኦነግ የተፈጸመው ስምምነት ተግባራዊ እስከተደረገ ድረስ ‹‹ለአንድ ወርም ታጥቆ የመቆየት ፍላጎት የለውም፤›› ብለው፣ እስካሁንም ይቆያል ብለው እንዳላሰቡ ያስረዳሉ፡፡

‹‹ለውጡን እንደግፋለን ብቻ ሳይሆን ለውጡ የእኛም ነው፡፡ እኛም ዋጋ ከፍለንበታል፤›› ያሉት ኃላፊው፣ ‹‹እኛ የመጣነው ገንቢ ተሳትፎ ለማድረግ ነው፡፡ ይኼንን ሒደት ማደናቀፍ አንፈልግም፡፡ በምርጫ ተፎካካሪ ሆነን ካሸነፍን መንግሥት ለመሆን፣ ካልሆነና በፍትሐዊ ምርጫ ከተሸነፍን በፀጋ ለመቀበል ነው ዝግጁነታችን፤›› ብለዋል፡፡

መንግሥት እንደ መንግሥት የትኛውንም ግለሰብ የመሾም መብት ቢኖረውም፣ ሠራዊቱን አስቀይሞ የወጣን ሰው መሾም ተመልሶ በዚያ ግለሰብ ሥር ለሚገባው ሠራዊት ተነሳሽነት ገዳይ ስለሆነ፣ ለሰላም ሲባል ይኼንን መተው ያስፈልግ እንደነበር ኃላፊው ያስረዳሉ፡፡

አሁንም ቢሆን የኦነግ ፍላጎቶች እንዲሟሉ የሚጠይቁት እኚህ ኃላፊ፣ በተለይ ከኦሮሞ ተራድኦ ማኅበር ንብረቶችንና መልሶ መቋቋምን በሚመለከቱ ጉዳዮች፣ በአዲስ አበባና በክልሎች የሚገኙ የኦነግ ቢሮዎች እንዲመለሱ ፍላጎታቸው መሆኑን፣ ለስምምነቱ ተግባራዊነት አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ያስገነዝባሉ፡፡ የማኅበሩ ተመልሶ መቋቋም አንደኛው የስምምነታቸው አካል መሆኑን በማስረዳት፡፡

ነገር ግን በሠራዊቱ ውስጥ የትግራይ ተወላጆች እንዳሉ የተነገረው ስህተት  ሲሉ ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡ በመርህ ደረጃ ኦነግ ለኦሮሞ ነፃነት የሚታገለው ኦሮሞ ብቻ ነው  ብሎ እንደሚያምን፣ የሌሎች ብሔሮች አባላት ቢኖሩም ሰፊ ተቀባይነት እንደሚያገኝ የሚናገሩት ኃላፊው፣ የተነገረው ግን ከእውነት የራቀ ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ‹ኦነግ ሠራዊቴ ነው የሚለው የኩምሳ ድሪባ ሠራዊትን ነው መባሉንም ያስተባበሉ ሲሆን፣ ካሁን ቀደም ሊቀመንበሩ በሥፍራው ሄደው ሠራዊቱን እንደጎበኙ ተናግረው፣ ለሁለተኛ ጉብኝት ሲሄዱ በኦነግና በመከላከያ ሠራዊት መካከል በተፈጠረ ግጭት ከቤጊ መመለሳቸውን አስረድተዋል፡፡

በመደበኛው ሚዲያም ሆነ በማኅበራዊ ሚዲያዎች በአመዛኙ የሚሰሙት ድምፆች ግን፣ ኦነግ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለመሳተፍ ወስኖ ወደ አገር ቤት ከተመለሰ በኋላ የሚደረድራቸውን ምክንያቶች አይቀበሉም፡፡ አገሪቱ ለውጥ ውስጥ ሆና የተለያዩ የለውጥ ዕርምጃዎች እየተወሰዱ ባሉበት ጊዜ፣ ለሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የማይመጥኑ ቅድመ ሁኔታዎችን መደርደሩን በማቆም እንደ ሌሎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመጪው ምርጫ ራሱን በሚገባ ቢያዘጋጅ ይሻለዋል ይላሉ፡፡ በተጨማሪም ምርጫውም ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ከወዲሁ የተመቻቸ ምኅዳር መፍጠር ስለሚያስፈልግ፣ ኦነግም የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ ቢያበረክት ጠቃሚ መሆኑን ያስገነዝባሉ፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -