Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሪል ስቴት ኩባንያዎች መረጃ እንዲልኩ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ጠየቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በአዲስ አበባ ከተማ በሪል ስቴት ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች፣ የገነቧቸውንና የሚገነቧቸውን ቤቶች መረጃ እንዲልኩለት ጠየቀ፡፡

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ ትልልቅ ሪል ስቴት ኩባንያዎች ታኅሳስ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ፣ ኩባንያዎቹ የገነቧቸውን ቤቶችና በግንባታ ላይ ያሉ ቤቶች መረጃ በየሦስት ወሩ እንዲልኩለት ጠይቋል፡፡

በሚኒስቴሩ የመኖርያ ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ፀጋዬ ሞሼ ፊርማ የወጣው ደብዳቤ፣ ሚኒስቴሩ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሪል ስቴት ኩባንያዎች በመገንባት ላይ የሚገኙ ቤቶች ብዛት ምን ያህል እንደሆነ መረጃ በማሰባሰብ የተደራጀ መረጃ መያዝ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል ይላል፡፡

‹‹መረጃው በየሩብ ዓመቱ የሚፈለግ መሆኑንና በግንባታ ላይ ያሉና ግንባታቸው የተጠናቀቁ ቤቶች በአጭር ጊዜ እንዲላክ እንጠይቃለን፤›› ሲል በአቶ ፀጋዬ ፊርማ የወጣው ደብዳቤ ጠይቋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በሪል ስቴት ኩባንያዎች የተገነቡ ቤቶች ቁጥርም ሆነ መረጃ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የለም ተብሏል፡፡ አቶ ፀጋዬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መንግሥት በሚያወጣው ፖሊሲና ስትራቴጂ የሪል ስቴት ኩባንያዎች በቤት ልማት ያላቸውን ተሳትፎና እንዴት ሊደገፉ እንደሚገባ ለማወቅ መረጃው አስፈላጊ ነው፡፡

አቶ ፀጋዬ እንዳሉት፣ መንግሥት በሒደት ከመኖርያ ቤት ልማት እየወጣ ለግሉ ዘርፍ የሚተው በመሆኑ ከወዲሁ አልሚዎች ያሉበት ደረጃና እንዴት ቢደገፉ የተሻለ አቅም ይፈጥራሉ የሚለውን ጉዳይ ማጤን ያስፈልጋል፡፡

በግል ዘርፍ የሚካሄድ የሪል ስቴት ልማት በተለይ የፋይናንስና የመሬት አቅርቦት ችግር ፈተና ሆነውበታል፡፡ ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው አብዛኛው የከተማ ነዋሪ የገንዘብ አቅሙ ዝቅተኛ በመሆኑ፣ የቤት ልማት ተሳትፎው የተዳከመ ነው፡፡ በቂ የቤት አቅርቦት ባለመኖሩ የቤት መሸጫ ዋጋ እየናረ ስለሚገኝ፣ ዝቅተኛ ገቢ ያለው በእጅጉ እየተፈተነ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለቤት ተጠቃሚዎች ብድር የሚያቀርብ ባንክ፣ ወይም ፈንድና አማራጭ የቤት ልማት ፋይናንስ ባለመኖሩ መደበኛ ባንኮች ብድር የሚሰጡት አዋጭነት ላላቸው ኢንቨስትመንቶች ስለሆነ ለቤት ግንባታ ፋይናንስ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር የሪል ስቴት ኩባንያዎች ካፒታላቸው አነስተኛ በመሆኑ ቤት ለመገንባት እየሞከሩ ያሉት ሕጋዊ ዋስትና በሌለው የቅድመ ሽያጭ ሥልት በመሆኑ፣ ዘርፉ ለችግር የተጋለጠ እንዲሆን ማድረጉ ይነገራል፡፡

በሌላ በኩል አብዛኞቹ የሪል ስቴት ኩባንያዎች ከ14 ዓመት በፊት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወሰዱትን ቦታ ገንብተውበት የጨረሱ ስለሆኑ፣ በድጋሚ መሬት ለማግኘት ደግሞ የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 ዘግቶታል፡፡

የሪል ስቴት አልሚዎች የቦታ አቅርቦት የሊዝ አዋጅ ያስቀመጣቸው ድንጋጌዎች አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድረዋል ይላሉ፡፡ ለሪል ስቴት አልሚ በጨረታ ከአንድ ሺሕ ቤት በላይ ለሚገነባ ብቻ መሬት እንደሚቀርብ ያስቀመጠው ድንጋጌ ጫና ማሳደሩ ይነገራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሪል ስቴት ልማትንና ግብይትን ሥርዓት ለማስያዝ የተዘጋጀው የሕግ ረቂቅ ፀድቆ ሳይወጣ ዓመታት ማስቆጠሩም ጫናውን የከፋ እንዳደረገው ይሰማል፡፡

አቶ ፀጋዬ እንደሚሉት በዘርፉ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት መረጃ ማሰባሰብና መተንተን ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ ስለሪል ስቴት ግብይት የሚደነግገው ረቂቅ አዋጅም በዚህ ዓመት እንደሚፀድቅ ያላቸውን እምነት አቶ ፀጋዬ ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች