Wednesday, May 22, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ሰላም ከቃል በላይ ተግባር ይሻል!

ቃልና ተግባር አልገናኝ እያለ እንጂ ስለሰላም ያልተባለ ነገር የለም፡፡ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣ ፖለቲከኞችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተገኘው አጋጣሚ ስለሰላም ብዙ ብለዋል፡፡ አሁን ግልጽ እየሆነ የመጣው ግን ችግሩ ሕዝብ ውስጥ ሳይሆን፣ ሥልጣን በአቋራጭ ለማግኘት የሚፈልጉ ኃይሎች ዘንድ መሆኑ ነው፡፡ ለሕዝብ ሕይወትና አካላዊ ደኅንነት ደንታ የማይሰጣቸው ወገኖች ሰላም እያደፈረሱ አገርን ቀውስ ውስጥ በመክተት፣ የሚመኙትን ሥልጣን ለመቆጣጠር ምንም ነገር ከማድረግ እንደማይመለሱ በግልጽ እያሳዩ ነው፡፡ ሥልጣን በሕዝብ ፈቃድ የሚገኝ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አንዱ መደላድል መሆን ሲገባው፣ ከዚህ በተቃራኒ በሕገወጥ መንገድ የሚደረግ እንቅስቃሴ ሰላም እያደፈረሰ ነው፡፡ በአደባባይ ስለሰላም የሚሰብኩ ወገኖችም ደፈር ብለው አጥፊውን በማውገዝ መስመር ማስያዝ ሲገባቸው፣ ከታይታ የዘለለ ተግባር ማከናወን እያቃታቸው ቃል ብቻ አየሩን ናኝቶታል፡፡ በዚህ ሁኔታ መቀጠል እንደማይቻል ግን የሁሉም ልቦና ያውቀዋል፡፡ ሰላምን መስበክ አስፈላጊ ቢሆንም ተግባር ግን መተኪያ የለውም፡፡

ሰላም ሰዎች ከፍርኃት፣ ከጥላቻ፣ ከግጭትና ከውድመት ተጠብቀው በነፃነት የሚኖሩበት ድባብ መገለጫ ጽንሰ ሐሳብ ከመሆኑም በላይ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ መስኮች ደግሞ አገርን ለማሳደግ የሚረዳ መሣሪያ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው አስተዳደር በይፋ ሥራ ከጀመረበት ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ወዲህ በርካታ አዎንታዊና ተስፋ ሰጪ ጅምሮች ቢታዩም፣ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ባጋጠሙ ግጭቶች ምክንያት በርካቶች ተገድለዋል፣ ለአካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ተዳርገዋል፣ ተፈናቅለዋል፡፡ ምንም እንኳ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ብዛት ያላቸው ታዋቂ ግለሰቦች ስለሰላም በተደጋጋሚ ቢሰብኩም፣ በየቦታው ግጭቶች እያገረሹ የአገር ሰላም ደፍርሷል፡፡ በሕዝብ መሀል ምንም ዓይነት ችግር ሳይፈጠር፣ የግጭት ነጋዴዎች በሚቀሰቅሱት ሁከት ሳቢያ የሰላም ያለህ ማለት የተለመደ ሆኗል፡፡ ስለሰላም ቃል በተደጋጋሚ ቢሰማም ተግባር ግን ጠፍቷል፡፡

የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የተለያዩ የሕዝብ መገናኛ ቦታዎች በግጭት ቀስቃሾች የተሞሉ በመሆናቸው ሰላም ማስፈን ከብዷል፡፡ መንግሥት ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱ መሆኑ የተረሳ ይመስል፣ በብዙ ሥፍራዎች የአስተዳደርና የፀጥታ መዋቅሮች ሥራቸውን በአግባቡ እያከናወኑ አይደሉም፡፡ የሕግ የበላይነት ሲጠፋ ደግሞ ሥርዓተ አልበኝነት መስፈኑ አይቀሬ ነው፡፡ መንግሥት የሕዝብን ደኅንነት ማስከበር ሲያቅተውና ሕገወጦች የበላይነቱን ሲይዙ ቀውስ ይፈጠራል፡፡ ቀውሱን የሚፈልጉ አካላት አጋጣሚውን በመጠቀም ያባብሱታል፡፡ እየሆነ ያለውም ይኸው ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥትና የክልል ብሔራዊ መንግሥታት እየተናበቡ ካልሆነ ደግሞ፣ እንኳንስ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ለማምራት ይቅርና ከቀውስ ውስጥ መውጣት አይሞከርም፡፡ ስለዚህ መንግሥት የዜጎችን መብት እያከበረና ሕጋዊ አካሄዶችን አሟጦ እየተጠቀመ ሕግ ማስከበር አለበት፡፡ ከሕጋዊነት በማፈንገጥ ሕገወጥነትን የሚያቀነቅን ኃይልን በሕግ ልክ የማስገባት ኃላፊነት እንዳለበት መዘንጋት የለበትም፡፡ ኢትዮጵያዊያን በገዛ አገራቸው በነፃነት መንቀሳቀስ እያቃታቸው መንግሥት እጁን አጣጥፎ መቀመጥ የለበትም፡፡ ወጣቶችን በአደናጋሪ ቅስቀሳ ሰላም እንዲያደፈርሱ የሚያበረታቱ ኃይሎች ፍላጎታቸው በአቋራጭ ሥልጣን ለመያዝ መሆኑ እየታወቀ፣ ሕዝብን የሚያተራምስና አገርን ቀውስ ውስጥ የሚከት ፉከራ በአደባባይ እየተሰማ ዝም ማለት ከመንግሥት አይጠበቅም፡፡ ለሁሉም ነገር ልክ አለውና ሕጋዊ ዕርምጃ ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ስለሰላም መለፈፍ ፋይዳ ቢስ ይሆናል፡፡

የጋሞ የአገር ሽማግሌዎች ገድል በታላቅ ምሥጋና ከጫፍ እስከ ጫፍ መነጋገሪያ የሆነው፣ እነሱ ከቃል በላይ በተግባር የሚገለጽ ወሳኝ ዕርምጃ በመውሰዳቸው ነው፡፡ የአባቶቻቸውን ምልጃ በመስማት ከጥፋት ድርጊታቸው የተመለሱት ወጣቶችም የተመሠገኑት ተግባር ከቃል በላይ ስለገዘፈ ነው፡፡ ይህ ታላቅ ገድል በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ግጭትን በማስቆም ሰላም ለማስፈን የውኃ ልክ መሆን ሲገባው፣ የግጭት ነጋዴዎች እንደፈለጉ እየፈነጩ አገር ይታመሳል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ግልጽ ነው፡፡ ከሚከሰቱ ግጭቶች በስተጀርባ በዋነኝነት ፖለቲከኞችና ሸሪኮቻቸው የሆኑ ኃይሎች አሉ፡፡ ይገኛል ተብሎ ከሚታሰበው የአቋራጭ ሥልጣን ተጠቃሚ ለመሆን የሚያደቡ በአደባባይ ሰላም ቢሰብኩም፣ ከኋላ ሆነው ‹ግፋ በለው› ባዮች እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ የጋሞ የአገር ሽማግሌዎችንና ወጣቶችን አርዓያነት ያደነቁ በርካታ ሰዎች በታዩባት አገር ውስጥ፣ ሰላምን ማስፈን አዳጋች ሆኖ እናቶች ኳስ ሜዳ ድረስ እየሄዱ በእንባ ይለምኑ ነበር? ዋናው ችግር ቃልና ተግባርን ማጣጣም ስላልተፈለገ መሆኑን መተማመን የግድ ይላል፡፡ ሌላው ቀርቶ በተንቀሳቃሽ ስልክ በጽሑፍ ስለሰላም መልዕክት ሲተላለፍ፣ ስንቶች እንደሚያላግጡ ለማወቅ የማኅበራዊ ሚዲያውን እንቶ ፈንቶ መመልከት በቂ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለማንም አይጠቅምም፡፡

ሰላም መስፈን ያለበት በሕግ የበላይነት ነው፡፡ ‹‹ሕግ የማይገዛውን ኃይል ይገዛዋል›› የሚባል አባባል ቢኖርም፣ ኃይል ሲቀላቀል ሕገወጥነት ሊያጋጥም ስለሚችል በተቻለ መጠን ለሕግ የበላይነት ቅድሚያ መስጠት ይገባል፡፡ ፍትሕ የማያስገኝ ኃይል ለሰላም ጠንቅ ስለሚሆን፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም ሆኑ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለሕግ የበላይነት ክብደት መስጠት አለባቸው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት በለውጥ ሒደት ውስጥ በምትገኝ አገር ችግሮች ማጋጠማቸው የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ንፁኃን ደማቸው እየፈሰሰና እየተፈናቀሉ ጥፋተኞችን እሹሩሩ ማለት አይገባም፡፡ መንግሥት እንደ ኃላፊነቱ መጠን በሕግ አግባብ ተግባራዊ ዕርምጃ መውሰድ ግዴታው ነው፡፡ የሃይማኖት መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች ደፈር ብለው ሕዝቡ ውስጥ በመግባት፣ አጥፊዎችን ከንፁኃን መለየትና ማውገዝ አለባቸው፡፡ ወጣቶችንና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በአፅንኦት ስለሰላም ማስተማር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ራሳቸውንም ከጎራ ፖለቲካ በማላቀቅ ለአገር ሰላምና ደኅንነት መትጋት ይኖርባቸዋል፡፡ ከእነሱ የማይጠበቅ ድርጊት እየፈጸሙ መጠቋቆሚያ አይሁኑ፡፡ ምሁራንና የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ደግሞ በተቻለ መጠን ስለሰላም ቢያስተምሩና ራሳቸውም ከአላስፈላጊ ድርጊቶች ቢታቀቡ መልካም ነው፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያ ውስጥ የሚሳተፉ ወገኖች ሐሰተኛ መረጃዎችን ከማራገብ ቢቆጠቡ ይመከራሉ፡፡ ሥልጣንን ከሕዝብ ድምፅ ሳይሆን በአቋራጭ ለማግኘት ያስፈሰፉ ኃይሎችም ከማያዋጣው ድርጊታቸው ተቆጥበው፣ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን ፖለቲካ ቢያራምዱ ይሻላቸዋል፡፡ በተለይ ሕዝብ መስዋዕትነት ከፍሎ ለዚህ እንዳበቃቸው እያወቁ የሚታበዩ ከታሪክ ቢማሩ ጥሩ ነው፡፡ ትዕቢት ለውርደት እንጂ ለክብር ቅርብ አይደለምና፡፡ ሰላም ሳይኖር ዓላማውን ማሳካት የሚችል የለምና ሰላም ከቃል በላይ ተግባር እንደሚሻ መተማመን ያስፈልጋል!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...

ያልነቃ ህሊና!

ከሽሮሜዳ ወደ አራት ኪሎ ልንጓዝ ነው። ነቀፋ አንሶላው፣ ትችት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፖለቲካውም ሆነ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት አይጉደለው!

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሁለቱን አገሮች የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት አስመልክቶ ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ በመንግሥት በኩል ቁጣ አዘል ምላሽ ነበር ያገኘው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያና...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...