በደቡብ ክልል በካፋ ዞን ዴቻ ወረዳ በተፈጸመ ድንገተኛ ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸው ታወቀ፡፡
በዞኑ ከሚገኙ አሥር ወረዳዎች አንዱ የሆነው የዴቻ ወረዳ ከቤንች ማጂና ከደቡብ ኦሞ ዞኖች ጋር የሚዋሰኑ ሲሆን፣ በአካባቢው ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሄዱ ነዋሪዎች ያሉበት የሠፈራ ጣቢያ ይገኛል፡፡ ጥቃቱ የተፈጸመው በዚሁ የሠፈራ ጣቢያ ውስጥ መሆኑን፣ የሪፖርተር ምንጮች ከሥፍራው አስታውቀዋል፡፡
ቅዳሜ ታኅሳስ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. በተፈጸመው ጥቃት ከሞቱት በተጨማሪ አራት ሰዎች መጎዳታቸውንና ንብረት መውደሙን የገለጹት ምንጮች፣ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ የቀንድ ከብቶች መዘረፋቸውን አክለዋል፡፡
የሠፈራ ጣቢያው በ1996 ዓ.ም. የተቋቋመ ሲሆን፣ በዋናነት አርብቶ አደር የሆኑ የመኤኒት ብሔረሰብ አባላት ተመሳሳይ ዓይነት ጥቃቶችን ይፈጽሙ እንደነበር ታውቋል፡፡ ይሁንና የዚህኛው ዙር ጥቃት በማየሉ፣ እንዲሁም የሞቱ ሰዎች ቁጥርና የተዘረፉ ከብቶች ብዛት ካሁን በፊት ከነበሩት ጋር ሲነፃፀር የገዘፈ እንደሆነ ምንጮች ተናግረዋል፡፡
በአርብቶ አደርነት ከቦታ ቦታ እየዞሩ የሚኖሩ መኤኒቶች በካፋ ዞን ጠረፋማ አካባቢዎች፣ በቤንች ማጂና በደቡብ ኦሞ አካባቢ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ በየዓመቱ በተደጋጋሚ እንዲህ ዓይነት ጥቃቶችን ሲፈጽሙ የሚታወቁ መሆናቸውን፣ ከብቶች በመዝረፍና ቤቶች በማቃጠል ጥቃቶችን ያደርሱ እንደነበር ምንጮች አክለዋል፡፡
ካሁን ቀደም በዚሁ ወረዳ በተሰነዘረ ጥቃት ከአሥር በላይ ሰዎች መሞታቸውንና ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ የቀንድ ከብቶች መዘረፋቸውን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ የአካባቢው የፀጥታ አካላት ወደ ሥፍራው በመሄድ ማረጋጋታቸው አይዘነጋም፡፡
የአሁኑን ጥቃት ተከትሎ የዞኑ የፀጥታ አካላትን ያቀፈ ቡድን ወደ ሥፍራው ማክሰኞ ታኅሳስ 23 ቀን 2011 ዓ.ም. መሄዱ ታውቋል፡፡