በአገር ውስጥ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ባለበት ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪና የኢትዮጵያ የመገበያያ ብርን ከአገር የማሸሽ የወንጀል ድርጊት በየዕለቱ ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑን፣ ትኩረት ተሰጥቶት ችግሩን ከምንጩ ለይቶ መግታት ካልተቻለ ውጤቱ አሳሳቢ እንደሚሆን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ። ለዚህም የባንኮችን አሠራር መፈተሽ አስፈላጊ ነው ተብሏል፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴርና ለሚኒስቴሩ ተጠሪ የሆነው የጉምሩክ ኮሚሽን ሰኞ ታኅሳስ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ዕቅድና የሥራ አፈጻጸማቸውን በተመለከተ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢዎች በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡበት ወቅት ነው ይኼንን የተናገሩት።
በቅርቡ እንደ አዲስ የተቋቋመው የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቀበታ ለቋሚ ኮሚቴው በሰጡት ማብራሪያ፣ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል ሥራዎች በትብብር እየተከናወኑ ቢሆንም ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አስረድተዋል።
የውጭ አገር ገንዘቦች በዋናነትም ዶላርን ከአገር ለማሸሽ የሚደረገውን የወንጀል ድርጊት ለመግታት ከፍተኛ ክትትል ኮሚሽኑ እያደረገ እንደሆነ፣ በዚህም በበርካታ ሺዎች የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ በየቀኑ እየተያዘ ቢሆንም፣ ዘዴዎችን በመቀያየር የውጭ ምንዛሪ የማሸሽ ድርጊቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን አቶ ደበሌ ገልጸዋል። ኮሚሽኑ በቁጥጥር ሥር እያዋለ የሚገኘው ሕገወጥ የውጭ ምንዛሪ በመረጃ ላይ በተመሠረተ ጠንካራ ክትትል መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ የኮሚሽኑን ቁጥጥር አልፈው ወይም በማይደረስባቸው ድንበሮች የሚያመልጡ ሊኖሩ እንደሚችሉ አስረድተዋል።
ይኼንን የወንጀል ድርጊት አሳሳቢ የሚያደርገው መንግሥት የአገር ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትን በሚፈለገው መጠን ማቅረብ ባልቻለበት ጊዜ መሆኑን ገልጸው፣ የዚህ የውጭ ምንዛሪ ምንጩ የት እንደሆነ አለመታወቁን ተናግረዋል።
በመሆኑም የውጭ ምንዛሪ ምንጩ ከየት እንደሆነ ለማወቅ የአገሪቱን ባንኮች መፈተሽ እንደሚያስፈልግ ለምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አስታውቀዋል።
አብዛኛው የውጭ ምንዛሪ ዝውውር መነሻ የአዲስ አበባ ከተማ መሆኑን ያስረዱት ኮሚሽነሩ፣ ከአዲስ አበባ ውጪ የሶማሌ ክልል ከሶማሌላንድ የሚዋሰንበት ቶጎ ጫሌ ድንበር ሌላኛው ከፍተኛ የዶላር ዝውውር የሚደረግበት አካባቢ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለያዩ ጊዜያት በቀረቡ ዘገባዎች የድንበር ከተማ በሆነችው ቶጎ ጫሌ ከፍተኛ የዶላር ዝውውርና ግብይት መኖሩ መገለጹ ይታወሳል።
ይህ የውጭ ምንዛሪ ገበያ የአገሪቱን ባንኮች ቀልብ የሚስብ በመሆኑ ከሞላ ጎደል ሁሉም ባንኮች በቶጎ ጫሌ ቅርንጫፍ ባንኮችን በመክፈት፣ የባንክ አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ በርካታ ዓመታት መቆጠራቸውንም መዘገባችን ይታወሳል።
የጉምሩክ ኮሚሽነሩ አቶ ደበሌ ለቋሚ ኮሚቴው እንዳስረዱት፣ ከሕገወጥ የውጭ ምንዛሪ ዝውውሩ በተጨማሪ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ በተለይም በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በኩል በመግባት ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተሰራጨ ነው፡፡ ሕገወጥ የነዳጅ ዝውውርም በተመሳሳይ መጨመሩን ተናግረዋል።
ይህ ድርጊት ከሕገወጥነት ያለፈ ፖለቲካዊ ቀውስ ከመፍጠር ጋር የሚገናኝ በመሆኑ፣ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን በማመን ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስረድተዋል።
በሌላ በኩል ከአዳዲስ አልባሳት፣ ከኤሌክትሮኒክስና ከአደንዛዥ ዕፆች ከ406 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዛቸውን ገልጸዋል።
የገቢዎች ሚኒስትሯ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፣ ዓመታዊ የአገሪቱ የግብር ገቢ ዝቅተኛ መሆኑንና ይኼንን ችግር ለመቅረፍ መወሰድ የተጀመሩ የመፍትሔ ተግባሮችን በተመለከተ ዝርዝር ሪፖርት አቅርበዋል።
በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት የአገሪቱ ዓመታዊ የግብር ገቢ እያሽቆለቆለ በመምጣቱ፣ አገር ለመምራት አስቸጋሪ ሁኔታ የተፈጠረበት ደረጃ ተደርሶ እንደነበር ጠቁመዋል።
ችግሩን ለመፍታት ቀደም ሲል ተለይተው የነበሩ ጉዳዮችን እንደ አዲስ የተደራጀው የገቢዎች ሚኒስቴርና በአመራርነት የተመደቡ አመራሮች ልዩ ትኩረት በመስጠት፣ ባለፉት ሦስት ወራት መንቀሳቀሳቸውን ተናግረዋል።
በተለይ ከቀረጥ ነፃ አሠራር ላስከተላቸው ግዙፍ ችግሮች ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሠራበት እንደሚገኝ ጠቁመዋል። የቀረጥ ነፃ መብት ኢንቨስትመንትን ከማበረታታት በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ለመፍጠር ታስቦ የተፈቀደ አሠራር ቢሆንም፣ ማበረታቻውን በመበዝበዝ መንግሥትና ሕዝብ ማግኘት ያለባቸው ሀብት የግለሰቦች ኪስ ሲሳይ ሆኖ ለዓመታት መቆየቱን አስረድተዋል።
ከቀረጥ ነፃ ዕድል በመሰጠቱ ምክንያት ከ2002 እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ ከ400 ቢሊዮን በላይ ብር ገቢ አለመሰብሰቡን ገልጸዋል።
ግብር በመክፈል የሚኮራ ኅብረተሰብ ለመፍጠር ግንዛቤ የማስፋት፣ ኮንትሮባንድን ለመከላከል የጉምሩክ ፖሊስ የተሰኘ ቡድን የማቋቋምና ለሙስና አጋላጭ የሆኑ አሠራሮችን የማሻሻል ሥራዎች መጀመራቸውንም አስረድተዋል።
ሚኒስቴሩ ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ ከ102 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ እንደነበር ገልጸው፣ መፈጸም የተቻለው 83 ቢሊዮን ብር እንደሆነና ውጤቱ ከዕቅዱ በታች ቢሆንም አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።
የተሰበሰበው ገቢ በ2009 ዓ.ም. ተመሳሳይ አምስት ወራት ከተሰበሰበው 76.93 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር በስድስት ቢሊዮን ብር ጭማሪ ከፍ ያለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ከተሰበሰበው 83 ቢሊዮን ብር ውስጥ ከአገር ውስጥ የገቢ ዓይነቶች የተገኘው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በዘጠኝ ቢሊዮን ብር እንደሚበልጥም ገልጸዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ ለምለም ሐድጉ በገቢ አሰባሰብ ረገድ ከችግር ለመውጣት እየተወሰዱ ያሉ ዕርምጃዎችን በማበረታታት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
ሕገወጥነትን በመከላከል ረገድ አሁንም የመንግሥትን ልዩ ትኩረት እንደሚሻ፣ የፍተሻ ኬላዎችን ጨምሮ አጠቃላይ አሠራርን በቴክኖሎጂ መደገፍ እንደሚገባም ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።