Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበሜቴክ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ላይ ክስ ሳይቀርብ የዋስትና መቃወሚያ በመቅረቡ ጠበቆቻቸው ተቃወሙ

በሜቴክ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ላይ ክስ ሳይቀርብ የዋስትና መቃወሚያ በመቅረቡ ጠበቆቻቸው ተቃወሙ

ቀን:

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ከተጠረጠሩባቸው 19 የወንጀል ድርጊቶች ውስጥ ምርመራቸው ተጠናቆ በደረሱት ሦስት የምርመራ መዝገቦች ላይ ክስ ሳይመሠረት ለፍርድ ቤት ያቀረበው የዋስትና መቃወሚያ አቤቱታ፣ ከሕግ አግባብ ውጪ ነው ሲሉ ጠበቆቻቸው ተቃወሙ፡፡

የዋስትና መቃወሚያ አቤቱታው በአገሪቱ በማንኛውም የሕግ ድንጋጌ መሠረት የሌለውና ከሕግ አግባብ ውጪ መሆኑን፣ ጊዜ ቀጠሮውን እያየው ለሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አሥረኛ ወንጀል ችሎት ያቀረቡት የሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ጠበቆች አቶ ዘረሰናይ ምሥግናና አቶ ሀፍቶም ከሰተ ናቸው፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን በሜቴክ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር በተጠረጠሩባቸውና እያካሄዳቸው ከነበሩት 19 የወንጀል ድርጊቶች ውስጥ የሪቬራ ኢንተርናሽናል ሆቴልና ፒቪሲ ፕሮፋይል ማምረቻ ፋብሪካ ግዥ ጋር በተያያዘ 202,882,885 ብር፣ እንዲሁም ከኢምፔሪያል ሆቴል ግዥ ጋር በተያያዘ 103,809,755 ብር እንዲባክን አድርገዋል የሚለውን የምርመራ ሒደት ማጠናቀቁን ገልጿል፡፡ በመሆኑም የምርመራ መዝገቡን ለዓቃቤ ሕግ ማስረከቡንም መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ የመርማሪ ቡድኑን ተከትሎ ዓቃቤ ሕግ ያረጋገጠው የተገለጹት መዝገቦች እንደደረሱት ሲሆን፣ ጉዳዩ ከሌሎች ተጠርጣሪዎች (እነ ብርጋዴር ጄኔራል ጠና ቁርንዲ 11 ተጠርጣሪዎች) ጋር የሚያያዝ በመሆኑ፣ ከእነሱ ጋር አጠቃሎ ክስ ለማቅረብ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 109(1) መሠረት አሥር ቀናት የክስ መመሥረቻ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ በመቀጠልም ጄኔራሉ ሌሎች ከተጠረጠሩባቸው ወንጀሎች ጋር በተያያዘ ከ545,483,103 ብር እንዲባክን በማድረግ በመንግሥት ላይ ከባድ ጉዳት ማድረሳቸውን በመጠቆም፣ በተጠርጣሪው ላይ ወደፊት የሚቀርቡት ክሶች ተደራራቢ መሆናቸውን ገልጿል፡፡

- Advertisement -

በመሆኑም በፀረ ሙስና አዋጅ ቁጥር 434/97 እና በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 2(3) መሠረት ከአሥር ዓመታት በላይ እስራት ሊያስቀጣቸው እንደሚችል በመጥቀስ፣ የዋስትና መብታቸው እንዳይፈቀድ አመልክቷል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን በተጨማሪ ለፍርድ ቤቱ እንዳመለከተው፣ ዋና ዳይሬክተሩ የተጠረጠሩባቸውን 16 የወንጀል ድርጊቶች በሚመለከት ዓቃቤ ሕግ የክስ መመሥረቻ በጠየቀባቸው አሥር ቀናት ውስጥ አጠናቆ ያስረክባል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ያቀረበው ማመልከቻ ግልጽ ያልሆነለት ፍርድ ቤቱ፣ ‹‹ምርመራህን አጠናቀህ መዝገቡን ዘግተሃል? ወይስ ተጨማሪ ጊዜ እየጠየቅህ ነው?›› የሚል ጥያቄ ሲያቀርብ ዓቃቤ ሕግ ሲያስረዳ በጠበቆች በቀረበ ተቃውሞ ተቋርጧል፡፡

ዓቃቤ ሕግና መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት አቤቱታ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ጠበቆች እንዳስረዱት፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 109(1) ዓላማ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ሳይሆን ተጠርጣሪው የተፋጠነ ፍትሕ እንዲያገኝ ማድረግ ነው፡፡ መርማሪ ቡድኑ የምርመራ ሥራውን አጠናቆ መዝገቡን ለዓቃቤ ሕግ ካስረከበ፣ ተጠርጣሪው በዋስትና ጉዳይ በሚያቀርቡት ጥያቄ ላይ ክርክር ማድረግ እንጂ ሥነ ሥርዓቱን ጠቅሶ ጊዜ እንዲሰጠው መጠየቁ የሕግ መሠረት እንደሌለው አስረድተዋል፡፡ በሕጉ ደግሞ የዋስትና ክርክር የሚደረገው፣ ፖሊስ ካልተገኘ ከዓቃቤ ሕግ ጋር ወይም ዓቃቤ ሕግ ከሌለ ከፖሊስ ጋር መሆኑን በመጠቆም፣ መርማሪ ፖሊስ ስላለ ዓቃቤ ሕግ መከራከር እንደማይችል ጠበቆቹ አስረድተዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው ተቃውሞ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግን እንደገና ባቋቋመው አዋጅ ቁጥር 943 መሠረት፣ ዓቃቤ ሕግ የወንጀል ድርጊቶችን እንደሚመረምር፣ እንደሚከታተልና እንደሚከራከር ሥልጣን ስለተሰጠው መከራከር እንደሚችል ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡  

ዓቃቤ ሕግ፣ ‹‹ተጠርጣሪ በእስር ላይ ሆኖ ክስ እስከምመሠርት ድረስ ይጠብቀኝ፤›› ማለቱ የሕግ መሠረት የሌለው ከመሆኑም በተጨማሪ፣ በአዋጅ ቁጥር 943 የተሰጠው ሥልጣን የፖሊስን የምርመራ ሥራ መቆጣጠር፣ የምርመራ ሪፖርቱን መቀበል፣ መምራትና ክስ መመሥረት እንጂ በጊዜ ቀጠሮ ላይ ፍርድ ቤት ቀርቦ መከራከር እንዲችል አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ የተጠናቀቀ የምርመራ መዝገብ ይዞ መርማሪ ቡድኑ አጠናቆ ባልሰጠው ክርክሮች ላይ ሊከራከር እንደማይችልም አክለዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ እንደገለጸው የፀረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 434/97፣ በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 882/97 እና በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 882/2007  መሠረት አንድ የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪ በሚቀርብበት ክስና ፍርድ ቤቱ በሚሰጠው ትዛዝ መሠረት ዋስትና የሚከለክል ቢሆንም፣ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው ዓይነት መከራከሪያ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ ደንበኛው በተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ክስ ሳይመሠረትባቸውና ክስ ሊያስመሠርት የሚችል ቅድመ ማስረጃ (Prima Facie Evidence) ሳይቀርብባቸውና ፍርድ ቤቱ ሳያረጋግጥ ዓቃቤ ሕግ ተጠርጣሪው በከባድ ሙስና ስለተጠረጠሩ፣ ምርመራው ውስብስብና ባክኗል የተባለው ገንዘብ አገራዊ ፋይዳ ያለው እንደሆነ በመግለጽ ዋስትና ሊያስከለክላቸው እንደማይችል ጠበቆቹ ገልጸዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ እንዳቀረበው ከሆነ በተጠርጣሪና ተከሳሽ መካከል ልዩነት ላይኖር እንደሚችልም አክለዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ከአሥር ዓመት በላይ የሚያስቀጣ እንደሆነ እየገለጸ ዋስትና የሚያስከለክል ከሆነ ተጠርጣሪው መቼም ቢሆን ሊፈቱ እንደማይችሉ የሚያሳይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም መርማሪ ቡድኑ በዋስትና ጉዳይ ላይ ያለው ነገር ስለሌለ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤቱ የተጠርጣሪ ጠበቆች ያቀረቡትን ክርክር ከሰማ በኋላ በሰጠው ትዕዛዝ፣ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው የአሥር ቀናት የክስ መመሥረቻ ጊዜ ጥያቄ ተከሳሹን የሚጎዳ ባለመሆኑ መቀበሉን ገልጾ፣ የተጠርጣሪ ጠበቆች ያቀረቡትን መከራከሪያ ሐሳብ አልፎታል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ክሱን ለጥር 2 ቀን 2011 ዓ.ም. እንዲያቀርብም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...