Tuesday, July 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናፍርድ ቤቶች ነፃና ገለልተኛ ሆነው መሥራት አለመቻላቸውን ፕሬዚዳንቷ ተናገሩ

ፍርድ ቤቶች ነፃና ገለልተኛ ሆነው መሥራት አለመቻላቸውን ፕሬዚዳንቷ ተናገሩ

ቀን:

በሶማሌ ክልል የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ሰብሳቢ የክልሉ ፕሬዚዳንት ነበሩ

የፌዴራልም ሆኑ የክልል ዳኞች የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በሕገ መንግሥቱ ከፍተኛ ኃላፊነት የተጣለባቸው ቢሆንም፣ የዳኝነት ነፃነታቸው በአስፈጻሚውና በሌሎች አካላት ጣልቃ ገብነት ምክንያት በመገደቡ ገለልተኛ እንዳልነበሩ፣ ዜጎችም በዳኝነት አካሉ ላይ አመኔታ እንዳይኖራቸው ማድረጉን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ተናገሩ፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዳኝነት ሥራ አስተዳደር የሚያጋጥሙ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮችን እየፈተሸ መፍትሔ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ጉባዔ በአዋጅ ቁጥር 25/88 ከአንቀጽ 31 እስከ 34 ድንጋጌ መሠረት ያቋቋመና በዓመት አንድ ጊዜ ጉባዔ ማድረግ እንዳለበት የተደነገገ ቢሆንም፣ በ25 ዓመታት ውስጥ ሦስተኛውን ጉባዔ እሑድ ታኅሳስ 21 ቀን 2011 ዓ.ም. አድርጓል፡፡ ፕሬዚዳንቷ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ የጉባዔው ሦስተኛ ዓመታዊ ስብሰባ ሲካሄድ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፣ ጉባዔው ዕቅድ አዘጋጅቶና የሚመራበትን ደንብ አውጥቶ ወደ ሥራ በመግባት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት አሠራርን ለማሻሻል የሚረዱ አቅጣጫዎችን የማመላከት፣ የዳኝነት ሥርዓቱን ነፃ፣ ግልጽና የተቀላጠፈ ለማድረግ የሚያግዙ ተግባራትን የማከናወን ኃላፊነት ተሰጥቶት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ጉባዔው በ27 ዓመታት ውስጥ ሁለት ጊዜ ብቻ መሰብሰቡንና ላለፉት 25 ዓመታት ሳይሰበሰብ መቅረቱን ጠቁመው፣ ይኼም የዳኝነት ነፃነት የሚጋፋ አሠራር እንዲበራከትና ዜጎችም በዳኝነት አካሉ ላይ አመኔታ እንዳይኖራቸው ማድረጉን አስረድተዋል፡፡ የፍርድ ቤቶች ታሪክ እንደሚያስረዳው የዳኝነት አገልግሎቱ ፍትሕ ተደራሽ እንዲሆን ሲሠራ የነበረ ተቋም ቢሆንም፣ ባለፉት ዓመታት የዳኝነት አካሉ ነፃነትና ገለልተኛነቱ በመጣሱ፣ ፍርድ ቤቶች ከመዳከማቸውም በላይ ኅብረተሰቡ በፍርድ ቤቶች ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸር ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

የመንግሥት ኃላፊዎች ስለዳኝነትና ገለልተኛነት ግንዛቤ አለመኖር፣ በዳኞች ምልመላና ሹመት ላይ ክፍተት መኖሩ፣ ዳኞች የሚጠየቁበት ግልጽ መመዘኛ አለመኖር፣ የሥነ ምግባር ችግርና የተጠናከረ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አለመሠራቱ ችግሩ ተባብሶ እንዲቀጥል ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡ ፕሬዚዳንቷ ጉባዔውን ከከፈቱ በኋላ የጉባዔው አባላት የሆኑት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የበላይ አመራሮች፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞችና ሁሉም የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የዳኝነት ችግር ሥር የሰደደ መሆኑን የገለጹት የጉባዔው ተሳታፊዎች፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች የሚጋጥሟቸው ችግሮችን ገልጸዋል፡፡ ከችግሮቹ መካከል ጭብጥ የመለየት ችግር፣ አቤቱታውን ተቀብለው ረዥም ጊዜ ካቆዩ በኋላ አያስቀርብም ብሎ መዝጋት፣ በማይነበብ ጽሑፍ ውሳኔ መጻፍ፣ የሥራ ቋንቋቸው አማርኛ ያልሆኑ ክልሎች የሚሰጡትን የፍርድ ቤት ውሳኔ በባለሙያ ባለመተርጎማቸው የትርጉም መጣረስና ሌሎች በርካታ ችግሮች እንደሚገጥማቸው አስረድተዋል፡፡ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚደርሱ አቤቱታዎች በአብዛኛው ከመሬት ባለቤትነት ጋር የተገናኙና በአርሶ አደሮች የሚቀርቡ በመሆናቸው፣ ክልሎች የሚሰጡትን ፍርድ ለማስተርጎም በገጽ 50 ብር እየከፈሉ ማስተርጎም ስለማይችሉ ይኼም አንዱ ችግር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ የመጨረሻና ውሳኔውም እንደ ሕግ የሚቆጠር ቢሆንም፣ ክልሎች በተለይ የኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች ውሳኔውን ባለመቀበልና የውሳኔ መዝገቡን ባለመጥቀሳቸው አቤቱታዎች በብዛት ወደ ሰበር ችሎት እየመጡ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ተመሳሳይ ክሶችን ባጭሩ ምላሽ ለመስጠት ትርጉም የተሰጠባቸውን የሰበር መዝገቦች በመጥቀስ ችግሩን ማቃለል ሲቻል፣ ‹‹አልታዘዝም›› ባይነት በመብዛቱ ችግሩን እያባባሰው መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ በመሆኑም የፌዴራልና የክልል ፍርድ ቤቶች ግንኙነትና አሠራር ሊፈተሽ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የዳኝነት ሥርዓቱን ሊመራ የሚችል ተቋም አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የክልልም ሆነ የፌዴራል ፍርድ ቤቶችና ዳኞች ወጥ አሠራር እንዲኖራቸው፣ ተቋማዊ የአቅም ግንባታና የጋራ ሥልጠና አስፈላጊ መሆኑንም አባላቱ ተናግረዋል፡፡ የክልል ፍርድ ቤቶች፣ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤትን የሚታይን ክስ፣ የክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶችና የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትን ክስ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች በውክልና እንደሚያዩና ጉዳዮቹም የብሔር ግጭት፣ የታክስና ሌሎች  መሆናቸውን አስታውሰው፣ በዚህ አሠራር ዙሪያም ችግሮች ስላሉ ሊፈተሽ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ ተዘዋዋሪ ችሎት ከፌዴራል ወደ ክልል የሚሄደው በየሦስት ወራት በመሆኑ ዜጎች የተፋጠነ፣ ነፃና ቀልጣፋ ፍትሕ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እየተጨፈለቀ መሆኑን፣ በተለይ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶች ተናግረዋል፡፡

በክልል የሚገኙ አብዛኞቹ ዳኞች የተማሩት መንግሥት በሚያውቃቸውና ዕውቅና ባላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ሳይሆን፣ በግልና ብዙም ዕውቅና በሌላቸው  ዩኒቨርሲቲዎች በመሆኑ፣ የአጻጻፍና የተለያዩ ሕግ ነክ ጉዳዮች ላይ የሚሰጡ ውሳኔዎችና ትዕዛዞች ላይ ችግር እንደሚከሰትም ጠቁመዋል፡፡ በጀትን በሚመለከት የፌዴራልም ሆነ የክልል ፍርድ ቤቶች ችግር እንዳለባቸው ጠቁመው፣ በክልል ምክር ቤቶችና በፓርላማ የሚፀድቅላቸው በጀት በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ቢሆንም፣ የሚሰጣቸው ግን 300,000 ብር ብቻ መሆኑን ገልጸው፣ በቂ እንዳልሆነና ቀሪውን ማን እንደሚወስደው ግራ እንደገባቸው ተናግረው እንዲታሰብበት አሳስበዋል፡፡

ጣልቃ ገብነትን በሚመለከት የጋምቤላ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት፣ ከመዝገብ ጋር በተገናኘ በቀጥታ ጣልቃ ገብነት ነበር ብለዋል፡፡ የክልሉ ፕሬዚዳንት፣ ‹‹እኔ ያሰርኩትን ለምን ትፈታለህ? ማን ሥልጣን ሰጠህ?›› የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ አሁን ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ቀድሞ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ስለነበሩ፣ በሕግ ጉዳይ ላይ ጣልቃ እንደማይገቡ እምነታቸው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ሁሉም ክልሎች በተለይ ከ2010 ዓ.ም. እስከ 2011 ዓ.ም. አራተኛ ወር ድረስ ያከናወኗቸውን ሥራዎች ገልጸዋል፡፡ የሶማሌ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ለየት ያለና ሁሉንም ያስገረመ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ የክልሉ ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ሰብሳቢ ፕሬዚዳንቱ አቶ አብዲ መሐመድ (አብዲ ኢሌ) እንደነበሩ ገልጸው፣ ምን ያህል ጣልቃ ገብነት እንደነበር አሳይተዋል፡፡ በሰርተፍኬት ደረጃ የሚሠሩ ዳኞች በክልሉ እንደነበሩና አሁን በሪፎርሙ እያስተካከሉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከሁሉም ክልሎች የተሻለና ለፌዴራል ፍርድ ቤቶችም ጭምር ተምሳሌት መሆን አለበት የተባለ አደረጃጀትና አጠቃላይ አሠራር መዘርጋቱን ያስታወቀው የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው፡፡ በፕሬዚዳንቱ የቀረበው ሪፖርት ሁሉንም ያስደመመና በፕሬዚዳንቷ ጭምር ምሥጋና የተቸረው ነበር፡፡ አስተያየት የሰጡ አንዳንድ የጉባዔው ተሳታፊዎች ያነሱት ጥያቄ በሁሉም የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶች ላይ ጣልቃ መገባት እንደሌለበት አስረግጠው ሲናገሩ፣ የዳኝነት ነፃነት መከበር እንዳለበትና እስከ መጨረሻው ይኼ ቁርጠኝነት መቀጠል ስለመቻሉ ነበር፡፡

በአጠቃላይ ጉባዔው ሙሉ ቀን ውይይት ካደረገ በኋላ ባለ 11 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡ ዳኞች ነፃነታቸውን ማስጠበቅ እንዳለባቸው፣ ጉባዔው መደበኛ ሆኖ በየዓመቱ መካሄድ እንዳለበት፣ የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎች በክልሎች መተግበር እንዳለባቸው የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶች ኃላፊነት መውሰዳቸውን፣ የክልል ፍርድ ቤቶች የፌዴራል ጉዳዮችን በውክልና ስለሚያዩ የበጀት ድጋፍ እንዲደረግላቸውና በሌሎችም አቋሞች ላይ በመስማማት አጠናቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...