Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜና‹‹የቀድሞ የደኅንነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋን ለመያዝ ጥይት ተታኩሰን የሌላ ሰው ሕይወት...

‹‹የቀድሞ የደኅንነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋን ለመያዝ ጥይት ተታኩሰን የሌላ ሰው ሕይወት እንዲያልፍ አንፈልግም›› አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ

ቀን:

የትግራይ ክልል ተጠርጣሪዎችን ለማስረከብ ፈቃደኛ አይደለም ብለዋል

የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋ በትግራይ ክልል ተሸሽገው እንደሚገኙ መንግሥት መረጃ እንዳለው፣ ነገር ግን እሳቸውን በሕግ ቁጥጥር ሥር ለማዋል ሲባል ጥይት በመታኮስ የሌላ ሰው ሕይወት እንዲጠፋ ፍላጎት አለመኖሩን፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ለፓርላማ አሳወቁ።

 ዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ የመሥሪያ ቤታቸውን የአምስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት፣ በዜጎች ላይ አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲፈጸም በማድረግ የተጠረጠሩትን አቶ ጌታቸው አሰፋን በሕግ ቁጥጥር ሥር ለማዋል የክልሉ መንግሥት አሳልፎ እንዲሰጥ ጥያቄ ቢቀርብለትም፣ ትብብር ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆኑን ተናግረዋል።

- Advertisement -

 ከአቶ ጌታቸው ውጪ የክልሉ ተወላጅ ያልሆኑ ተጠርጣሪዎችንም ክልሉ ከለላ እንደሰጠና በሕግ ቁጥጥር ሥር ማዋል አለመቻሉን አስረድተዋል። ፓርላማው በዚህ ጉዳይ ላይ አቋም ይዞ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባም ጠይቀዋል።

ይሁን እንጂ አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት በጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ማብራራያ አልተደሰቱም።

መንግሥትም ሆነ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በዚህ ጉዳይ ላይ ፈራ ተባ ሊሉ እንደማይገባ የተናገሩ አንድ የምክር ቤት አባል፣ በደል የፈጸሙ ተጠርጣሪዎችን መንግሥት በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ ሳይችል ስለሕግ የበላይነት ማውራት እንደማይችል ገልጸዋል።

 ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ለመያዝ ያልተቻለው በክልላቸው በመሸሸጋቸውና ክልሉም ለተጠርጣሪዎች ከለላ ስለሰጠ ተቸግረናል ማለት፣ ለሌሎች ተጠርጣሪዎች የሚሰጠው ትርጉም ወንጀል ፈጽሞ ብሔር ውስጥ መሸሸግ የሚቻል መሆኑን ነው በማለት የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ብርሃኑን ማብራሪያ ተችተዋል።

 የተጠረጠሩት የቀድሞው የደኅንነት ኃላፊ በትክክል ያሉበት ቦታ ይታወቅ እንደሆነም ጠይቀዋል። አክለውም ተጠርጣሪውን ለመያዝ ያስቸገረው ምንድን እንደሆነ፣ ምናልባትም ግለሰቡ ያለመከሰስ መብት ይኖራቸው እንደሆነ የጠየቁት እኝሁ የምክር ቤቱ አባል፣ ተጠርጣሪውን ለመያዝ እየተጠበቀ ያለው በቀጣዩ ምርጫ ያለመከሰስ መብት እንዲያገኙ ካልሆነ በስተቀር አስቸጋሪው ምክንያት በዝርዝር ለምክር ቤቱ ሊቀርብ ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል።

  ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ አቶ ብርሃኑ በሰጡት ምላሽ፣ ተጠርጣሪው አቶ ጌታቸው የክልልም ሆነ የፌዴራል ምክር ቤት አባል እንዳልሆኑና ያለመከሰስ መብት እንደሌላቸው አስረድተዋል።

የትግራይ ክልል ግለሰቡን በቁጥጥር ሥር አውሎ እንዲያስረክብ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጥያቄ ቢቀርብም አለመፈጸሙን ተናግረዋል። ተጠርጣሪውን ለመያዝ የቀረበ ጥያቄ እንደሌለ በተለያዩ ሚዲያዎች የሚቀርበው መረጃ የተሳሳተ እንደሆነም ገልጸዋል።

 ተጠርጣሪው በክልሉ ውስጥ ተሸሽገው እንደሚገኙ መረጃ እንዳለ የተናገሩት አቶ ብርሃኑ፣ ክልሉ ሊተባበር ፈቃደኛ ባለመሆኑ ምክንያት ሊፈጸም አለመቻሉን አስረድተዋል።

 ‹‹ተጠርጣሪውን ለመያዝ ጥይት በመታኮስ የሌላ ሰው ሕይወት እንዲያልፍ አንፈልግም፤›› በማለት የኃይል ዕርምጃ ያልተወሰደበትን ምክንያት ጠቁመዋል።

ለግለሰቦች ከለላ በመስጠት የሕግ የበላይነትን ከመጣስ ይልቅ፣ በዜጎች ላይ የተፈጸሙ አሰቃቂ በደሎች ሊያስጨንቁ ይገባ እንደነበር በመጥቀስ ከለላ ሰጥቷል የተባለውን ክልል አመራሮች ወርፈዋል።

 አሁን ከተገኘው ለውጥ አስቀድሞ በነበሩት ዓመታት የነበረው የመንግሥት መዋቅር አመራሮች በዜጎች ላይ እንዲፈጸም ያስደረጉትና የፈጸሙት ኢሰብዓዊ በደል ከባድ፣ ውስብስብና ለመናገርም የሚከብድ መሆኑን አቶ ብርሃኑ ጠቁመዋል።

 ዜጎች ወንጀል እንዲሠሩ በደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ተመልምለው በወገኖቻቸው ላይ በደል እየፈጸሙ ክፍያ ያገኙ እንደነበር፣ ለፖለቲካዊ ጥቅም ሲባል ብቻ አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ ይደረግ እንደነበርም ገልጸዋል።

‹‹ከዚህ በላይ የሆነ ዘግናኝ ኢሰብዓዊ በደል በዜጎች ላይ ያደረሰ በሕግ እንዳይጠየቅ ከለላ የሚሰጥ አመራር፣ የእኔም ጉዳይ ነገ ይወጣብኛል ብሎ የሚያስብ ትንሽ የፖለቲካ አመራር ነው፤›› በማለት የሰላ ትችት ሰንዝረዋል።

 ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ እንደሚሉት የእሳቸው ተቋም ፖለቲካና ወንጀልን በመለየት ሕጋዊ ተጠያቂነት እንዲሰፍን የማድረግ ፍላጎት ብቻ ይዞ እንደሚንቀሳቀስ፣ የክልል አመራሮች ደግሞ ከለላ ከመስጠት ይልቅ በሕግ ሥርዓቱ ላይ እምነት እንዲጥሉ ጠይቀዋል።

ይህንንም ለማስረዳት የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) አመራር የነበሩት (ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው) በተያዙበት ወቅት አብረዋቸው የነበሩትን ሌላ አመራር አሳልፎ ለመስጠት ተጠይቆ እንደነበር፣ ነገር ግን በግለሰቡ ላይ የተጀመረ ምርመራ ባለመኖሩ ግለሰቡ እንዲለቀቁ መወሰኑን አብራርተዋል።

 በሌላ በኩል ወደ ፍርድ ሒደት የገቡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎችን በሚያስረዱ ምስክሮች፣ እንዲሁም ጠቋሚዎች ላይ በአሁኑ ወቅት ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰ መሆኑንም ገልጸዋል።

 በዚህ የተነሳም መንግሥት ለእነዚህ ምስክሮችና ጠቋሚዎች ከለላ መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል። ሕግን መሠረት በማድረግና ሁኔታዎችን በመመዘን አንዳንድ ምስክሮች ከመኖሪያ አካባቢያቸው ወደ ሌላ የተጠበቀ አካባቢ እንዲዘዋወሩ፣ አንዳንዶቹ ጥበቃ እንዲመደብላቸው፣ እንዲሁም መሣሪያ እንዲታጠቁ መደረጉን ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።

በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ የሕግ ተጠያቂነት ለማስፈን የተጀመረውን እንቅስቃሴ ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከበርካታ ሩቅ የክልል አካባቢዎች ጭምር ወደ ተቋሙ በመምጣት፣ በደላቸውን በመናገር ላይ መሆናቸውንና ይህም ምርመራውን ውስብስብ እንዳደረገው ተናግረዋል። በየትኛው ሕግ አስከባሪ እንደተያዙ የማያውቁ የተሰወሩ ቤተሰቦቻቸውን ፍለጋ ዜጎች ወደ ተቋሙ በከፍተኛ ቁጥር በመምጣት ላይ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

ምክር ቤቱ ሪፖርቱን ካዳመጠ በኃላ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግን የሚከታተለው የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲያዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ፎዚያ አሚን ሪፖርቱን የተመለከተ አስተያየት እንዲሰጡ አድርጓል፡፡ ወ/ሮ ፎዚያም ተቋሙ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን የፍትሕ ጥማትና የሕግ የበላይነት መከበር በተመለከተ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

 ዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ በትግራይ ክልል ላይ ያቀረቡትን ወቀሳ በተመለከተ ሪፖርተር የትግራይ ክልል ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊያ ታደሰ ምላሽ እንዲሰጡ ጥያቄ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም፣ ኃላፊዋ ለሥራ ከመቀሌ ውጭ ተጉዘው የነበረ በመሆኑ ዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ አሉ ስለተናገሩት ዝርዝር መረጃ ስለሌላቸው በዚህ ሁኔታ ምላሽ ለመስጠት ለጊዜው እንደሚቸገሩ ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...