Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊቱሪዝም ኢትዮጵያ አስጎብኚዎችን ይቅርታ የጠየቀበት መድረክ

ቱሪዝም ኢትዮጵያ አስጎብኚዎችን ይቅርታ የጠየቀበት መድረክ

ቀን:

አባጣ ጎርባጣ ለበዛበት ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ መፍትሔ እንዲሆን በአዋጅ የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት በአሁኑ ስያሜው ‹‹ቱሪዝም ኢትዮጵያ›› በመስኩ ሊያመጣ ይችላል ተብሎ የተጠበቀውን ለውጥ ማምጣት ቀርቶ ባለጉዳዮችን እንኳ በአግባቡ ማስተናገድ ያልቻለ ድርጅት ነው የሚሉት ግን ጥቂት አይደሉም፡፡ ሥራ በጀመረባቸው ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ አምስቴ የአመራር ለውጥ ቢያደርግም ‹‹ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም›› እንዲሉ ይህ ነው የሚባል ነገር አልሠራም ይላሉ በቅርበት የሚያውቁት ቱር ኦፕሬተሮች፡፡

ድርጅቱ ታኅሣሥ 23 ቀን 2011 ዓ.ም. በሀርመኒ ሆቴል ባዘጋጀው የውይይት መድረክ የተለያዩ የአስጎብኝ ድርጅቶች አመራሮችና ተወካዮች በድርጅቱ አሠራር ላይ ያላቸውን ቅሬታ ገልጸዋል፡፡ ከተነሱ ቅሬታዎች መካከልም ከአስጎብኚ ድርጅቶች ጋር ቀጥታ ግንኙነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ እንኳ ድርጅቱ እንደ ባለድርሻ አካል ሳያወያያቸው ድንገት የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች መኖራቸው አንዱ ነው፡፡

የመስኩ ተዋናዮችን አስተባብሮ ከመሥራት አኳያ ያለበት ችግር ለሚቀርቡለት ጥያቄዎች ምላሽ እስካለመስጠት እንደሚደርስ ከመድረኩ ታዝበናል፡፡ አንድ አስተያየት ሰጪ ‹‹ቢሯችሁ ብንመጣም እኮ የሚያነጋግረን ሰው አናገኘም፡፡ ቢሮ ውስጥ እንኳ አትኖሩም፤›› በማለት የተቋሙ አሠራር መሠታዊ ችግር እንዳለበት አንስተዋል፡፡ ድርጅቱ የተቋቋመበትን ኢትዮጵያን ለቀሪው ዓለም የማስተዋወቅ ተልዕኮ እየተወጣ አለመሆኑንም አክለዋል፡፡ እንዲያውም ተግባሩ በተቃራኒው ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ያላትን ቦታ የሚያሳጣት ነውም ብለዋል፡፡

በዚህ ረገድ አስተያየት ሰጪዎች የሚያነሱት ነጥብ ቱሪዝም ላይ ያተኮረውና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ላይ በሚካሄደው የንግድ ዓውደ ርዕይ ኢትዮጵያ እንድትሳተፍ በቅርቡ የተላለፈውን ውሳኔ ነው፡፡ በአውሮፓ ስፔን ማድሪድ፣ በጣሊያን ሚላኖ፣ በጀርመን በርሊን፣ በእንግሊዝ ሎንዶን፣ በሩሲያ ሞስኮ ላይ በተለያዩ ጊዜያት የሚካሄዱ የቱሪዝም የንግድ ዓውደ ርዕዮች ላይ ኢትዮጵያ ላለፉት ሃያ ዓመታት ስትሳተፍ ቆይታለች፡፡

በዚህ መድረክ ላይ የሚሳተፉ ቱር ኦፕሬተሮች የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብትና ልዩ ልዩ መዳረሻ ሥፍራዎች የማስተዋወቅ ሥራ ይሠራሉ፡፡ ቀዳሚው ተግባር በቀሪው ዓለም ስሟ በድርቅና ረሃብ የሚታወቀውን የኢትዮጵያን ሌላኛውን ገጽታ ማስተዋወቅ ነው፡፡ በዚህ ዓውደ ርዕይ ላይ የሚሳተፉ ቱር ኦፕሬተሮች እያንዳንዳቸው ከሩብ ሚሊዮን ብር የማያንስ ወጪ እንደሚያወጡ የሚናገሩት በኢትዮጵያ ቱር ኦፕሬተሮች ማኅበር የቦርድ አባሉ አቶ አበበ ተስፋዬ ናቸው፡፡ እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎች የቱሪዝምን ሀብት በማስተዋወቅ ረገድ የተሻለ ዕድል እንዳላቸው የታወቀ ቢሆንም በቅርቡ ቱሪዝም ኢትዮጵያ አገሪቱ በቱሪዝም ዓውደ ርዕይ ላይ እንደማትሳተፍ ውሳኔ ማስተላለፉ ግን ቅሬታ ፈጥሯል፡፡

ብዙ ለፍተን አገሪቱን የማስተዋወቅ ሥራ የሠራንበትን ይህንን ፕሮግራም እንዲቀር መወሰን ተገቢ አይደለም ያሉት የመድረኩ ተሳታፊዎች በአንድ ድምፅ ነው፡፡

አቶ ያዕቆብ መላኩ የተባሉ የአንድ አስጎብኝ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ኢትዮጵያ የቱሪዝም የንግድ ዓውደ ርዕይ እንዳትሳተፍ ማገድ አገሪቱን ከዓለም የቱሪዝም ካርታ ላይ ማጥፋት ነውም ብለዋል፡፡ በቱሪዝም ዓውደ ርዕይ ኢትዮጵያ ምን አተረፈች? ምን ያህል ገንዘብ አገኘች? የሚለውን በዋጋ መተመን አስቸጋሪ ነው የሚሉት አቶ ያዕቆብ መሰል መድረኮች ዓላማቸው ኢትዮጵያን ማስተዋወቅ እንደሆነ፣ እስካሁንም የማይናቅ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል፡፡

‹‹በቱሪዝም ዓውደ ርዕይ ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ ተሳትፎ አታደርግም ሲሉ እኛን ሳያማክሩን ድንገት ነው የሰማነው፤›› የሚሉት አቶ አበበ ደግሞ ለዓመታት ተሳትፎ አድርገው አገሪቱን በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አስጎብኝ ድርጅቶች እንኳ መነገር ነበረበት ብለዋል፡፡

አቶ አበበ ድርጅቱ የተቋቋመለትን ተልዕኮ እንኳንስ ሊያሳካ በሕገወጥ ተግባር የተሰማሩ የገዛ ሠራተኞቹን እንኳ መቆጣጠር እንዳልቻለም ይገልጻሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ‹‹ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ውስጥ በተዘጋጀላቸው የእንግዳ መቀበያ መስኮት ውስጥ የሚቀመጡ አንዳንድ የቱሪዝም ኢትዮጵያ ሠራተኞች መረጃ በመስጠት ፋንታ እንግዶችን ተቀብለው የማስጎብኝት ሥራ ይሠራሉ፡፡ የፓኬጅ የዋጋ ተመኖችን እያዘጋጁ በዋጋ የሚደራደሩ ሲሆን፣ ደረጃቸውን ባልጠበቁ የቤት መኪኖች ጎብኚዎችን ይዘው ሲሽከረከሩም ታይተዋል፡፡››

ሕጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው የመንግሥት ሠራተኛ መሆናቸው የፈጠረላቸውን መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው የተሰማሩበት ተግባር በድብቅ የውጭ አገር ገንዘቦችን በጥቁር ገበያ እስከ መመንዘር ይደርሳልም ሲሉ አክለዋል፡፡

‹‹እኛ ይህንን መረጃ የምናገኘው ከደንበኞቻችን ነው፡፡ ደግሞም በቂ መረጃ ይዘን ነው የምንናገረው፤›› የሚሉት አቶ አበበ፣ አስጎብኚዎች ኤርፖርት ተርሚናሉ ውስጥ ገብተው እንግዳ መቀበል ስለማይፈቀድላቸው ደንበኞቻቸውን ቀጥታ ማግኘት እንደማይችሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ኢንተርኔት ረዘም ላለ ጊዜ ተቋርጦ በነበረበት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት ከባድ ችግር አጋጥሞም እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ እንግዶቹ ወደ መረጃ ዴስኮች ሲሄዱ ‹‹የአስጎብኚነት ሥራ እንሠራለን›› የሚሉ የቱሪዝም ኢትዮጵያ ሠራተኞች በሥራቸው ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ፈጥረው እንደነበር አብራርተዋል፡፡ ለሙያቸው የማይገዙ የሆቴል ሠራተኞችም ይህንን ሕገወጥ መንገድ ተከትለው የማስጎብኘቱን ሥራ እንደሚሻሟቸው ገልጸዋል፡፡

እየተወዳደርን ያለነው ለመንግሥት ግብር ከማይከፍሉ ሕገወጦች ጋር ነው የሚሉት አቶ አበበ በዚህ ተግባር የውጭ አገር ሰዎችም እንደሚሳተፉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የውጭ አገር ዜጎች እንዲህ ባለ ተግባር የሚሰማሩት በጉብኝት ፕሮግራም ሁለትና ሦስት ጊዜ ያህል ኢትዮጵያ ተመልሰው መግቢያና መውጫዎችን ካጠኑ በኋላ ነው፡፡ ‹‹ብዙም ቁጥጥር ስለማይደረግ መኪና ከመንገድ ላይ ተከራይተው በራሳቸው ጋይድ እያደረጉ፣ በራሳቸው ሆቴል እየያዙ ፈቃድ ሳይኖራቸው ኢትዮጵያን ያስጎበኛሉ፡፡ ይህ ብዙ ጊዜ የሚያጋጥመን ነገር ነው፡፡ ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ለገቢዎችና ጉምሩክ ሪፖርት አድርገናል፡፡ ነገር ግን እስካሁን ምንም ዓይነት ምላሽ አልተሰጠንም፤›› ሲሉ ከቁጥጥር ውጭ የሆነውን አሠራር ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

በመሰል ተግባር ለተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ቢያንስ ማስጠንቀቂያ መስጠት፣ ለውጭ አገር ዜጎች ደግሞ ጉዳዩ ከአገር ደኅንነትም ጋር የተያያዘ ስለሆነ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ግድ ነው ይላሉ፡፡ ከአምስትና ስድስት ዓመታት በፊት በነበረው ጠበቅ ያለ አሠራር እንዲህ ፈር የለቀቀ ነገር እንደሚታይ የሚያስታውሱት አቶ አበበ፣ ከዚህ ቀደም የነበረው ተናቦ የመሥራት ልምድ በአሁኑ ወቅት የአገርን ደኅንነት አደጋ ላይ በሚጥልበት ሁኔታ መላላቱን ያስረዳሉ፡፡

በየጊዜው በሚታተሙ ብሮሸሮች፣ መጽሔቶችና በመሳሰሉት የሚታወቁት የመዳረሻ ሥፍራዎች ውስን መሆንም ሌላው በዘርፉ የሚታይ ችግር ነው፡፡ የተለመዱት እነ አክሱም፣ ላሊበላ፣ ጣና፣ ጢስ ዓባይና የመሳሰሉትን ብቻ ነው የቱሪዝም መዳረሻ አድርገው የሚጠቀሙት፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን በአገሪቱ ስለሚገኙ ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ በኢትዮጵያ ከ250 በላይ ፍል ውኃዎች እንዳሉ የሚናገሩት አቶ አበበ፣ በጉብኝት መዳረሻነት የሚካተቱት ግን አዲስ አበባ የሚገኘው ፍል ውኃ፣ ሶደሬ፣ ወንዶ ገነትና የመሳሰሉትን ብቻ እንደሆኑ የተቀሩትን ማንም እንደማያውቃቸውና ጥቅም ላይ መዋል አለመቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

በመሠረተ ልማት ችግር የማይደርስባቸው ጎብኚዎች ያላዩዋቸው ሌሎች በርካታ ቦታዎችም አሉ፡፡ በብዛት ከሚታወቁት ላንጋኖ፣ አቢጃታና ሻላ ባሻገር ልዩ መስህብነት ያለው ጪቱ ሐይቅን ብዙ ኢትዮጵያውያን፣ አስጎብኚዎችም አያውቁትም፡፡ ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ ወንጪ ሐይቅ የታወቀ ነው፣ ደንዲ ሐይቅን ግን የሚያውቀው የለም፡፡ የፊታ ውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ ጥንታዊ ቤት ያለበት ቦታ ቢሆንም አካባቢው ግን ብዙዎች እንደማያውቁት አቶ አበበ ሲገልጹ በምሬት ነው፡፡ መዳረሻ ሥፍራዎችን ማስተዋወቅ ላይ ካለው ችግር ባሻገር መዳረሻ መሆን የሚችሉ ሀብቶችን ጠብቆ ከማቆየት ጋር በተያያዘ ትልቅ ክፍተት ይታያል፡፡

እነዚህና መሰል ጉዳዮች ሴክተሩ እንዲሻሻል ያሉበትንም ማነቆዎች እንዲፈታ፣  የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች እንዲያለማና እንዲያስተዋውቅ የተቋቋመው ቱሪዝም ኢትዮጵያ ተግባሩን እየተወጣ አይደለም የሚል ትችት ይሰነዘርበት ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ከሚደርሱበት ወቀሳዎች መካከል ከባለድርሻ አካላት ጋር አብሮ አይሠራም የሚለው ብዙዎች የሚጋሩት ነው፡፡ ያሉበትን ችግሮች በአዲስ አመራሮችና አሠራር ለመፍታት የጀመረውን ጥረትም አቶ ያዕቆብ ‹‹በር ተዘግቶ ቤት አይፀዳም፤ ያለውን ችግር አብረን ሁላችንም ተመካክረን እንፍታ አብረን እናፅዳ፣ ጉዳዩ የሁላችንም ኃላፊነት ነው፤›› ሲሉ ሁሉን አሳታፊና ግልጽ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡

‹‹በጋራ እንድንሠራ መጠየቅ የነበረብን አሁን ሳይሆን ድሮ ነበር፡፡ አሁንም አብረን እንሥራ ካላችሁን እኛን አድምጡ ችግራችንን ስሙ›› ያሉት አንድ ተሳታፊም በመጀመርያ እስካሁን ለተፈጠሩት የአሠራር ክፍተቶች ቱሪዝም ኢትዮጵያ ይቅርታ መጠየቅ አለበት ብለዋል፡፡

የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሌንሳ መኰንን፣ ድርጅቱ የተለያዩ ክፍተቶች እንዳሉበት አምነዋል፡፡ የቱሪዝም ፈንድ ከማቋቋም ጀምሮ ችግሮች አሉም ብለዋል፡፡ በቂ የሰው ኃይል አለመኖሩም ሌላ ፈተና እንደሆነ፣ አሉ ለተባሉ ችግሮች በሙሉ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡

ያለው የሰው ኃይል ችግር ከትምህርት ዝግጅት፣ ከብቃት ማነስ በላይ የፍላጎትና ተነሳሽነት ጉዳይ መሆኑ አሳሳቢ እንደሆነ በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡ የቱሪዝም ኢትዮጵያ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰርጸ ፍሬስብሐት ‹‹ተቋሙን እኮ ስናገኘው ተቋም ሆኖ አይደለም፡፡ ወዶገቦች ተሰብስበው ይሠሩበት የነበረ ድርጅት ነው፡፡ ትልቁ ችግር ግን የሰው ኃይል አይደለም፡፡ ብዙ አቅም ያላቸው ሰዎች አሉበት፡፡ ክፍተቱ የነበረው ከመንግሥት በመጣለት የሥራ መዋቅር ላይ ነው፡፡ ማን ምንድነው የሚሠራው? የሚለው የኃላፊነት ወሰን ሲቀረፅ ችግር ነበረበት፤›› በማለት ከጀርባ የነበረውን የአሠራር ቀውስ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...