Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹አካሄዱን አልተከተላችሁም ተብለን ፋብሪካ ለመገንባት የገዛነውን ማሽን ለማስቀመጥ ተገደናል›› አቶ ሲራክ ከተማ፣ የኔግራ ዘይት ፋብሪካ ባለቤት

አቶ ሲራክ ከተማ ይባላሉ፡፡ ተወልደው ያደጉት በአዲስ አበባ ከተማ ካዛንቺስ አካባቢ ነው፡፡ የመጀመርያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በናዝሬት መጽሐፍ ቅዱስ አካዴሚ እስከ 11ኛ ክፍል ተምረዋል፡፡ የ11ኛ ክፍል ተማሪ እያሉ ደርግ የንጉሡን አገዛዝ በኃይል በመገልበጥ ሥልጣን ላይ የወጣበት ዘመን ነበር፡፡ በመሆኑም በወቅቱ ወጣቶች እየተለቀሙ የሚታሰሩበትና የሚረሸኑበት ጊዜ ስለነበር፣ አቶ ሲራክም ይኼንን በመፍራት ወደ ሌላ አገር መሰደዳቸውን ተናግረዋል፡፡ አቶ ሲራክ በአሁኑ ጊዜ የ62 ዓመት ጎልማሳ ሲሆኑ፣ ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ናቸው፡፡ ከ40 ዓመታት በላይ በስደት ይኖሩበት ከነበረው አሜሪካ ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ በአገራቸው ኢንቨስት ማድረግ እንደሚችሉ ተነግሯቸው ስለመጡ በዘይት ምርት ላይ ለመሰማራት በመወሰን የማምረቻ ማሽን ገዝተው ያስገቡ ቢሆንም፣ የተለያዩ ችግሮች እንደገጠሟቸው እየተናገሩ ነው፡፡ አቶ ሲራክ አሁን ስላሉበት ሁኔታና በሥራቸውም ላይ ስለገጠማቸው አጠቃላይ ሁኔታ ታምሩ ጽጌ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከኢትዮጵያ የወጡት መቼና በምን ምክንያት ነው?

አቶ ሲራክ፡- ከኢትዮጵያ የወጣሁት የ11ኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ነው፡፡ የሄድኩትም ወደ አሜሪካ ነው፡፡ ከአገር ልወጣ የቻልኩት የንጉሡ ሥልጣን በደርግ በመተካቱና ደርግ ደግሞ ማሰርና መግደል በመጀመሩ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ተጠቂዎች ደግሞ በወቅቱ በእኔ ዕድሜ ያሉ ወጣቶች ነበሩ፡፡ በዚህ ምክንያት አብዛኛው ወጣት በኬንያ፣ በጂቡቲና በሱዳን ወደ ተለያዩ አገሮች ሲሰደድ፣ እኔም ኬንያ የምሄድበት አጋጣሚ በመፈጠሩ ሄድኩኝ፡፡ ከኬንያ ወደ እስራኤል፣ ከዚያም ወደ ግሪክ ከሄድን በኋላ አሜሪካ ገብተን ላለፉት 40 ዓመታት እዚያው ኖርን፡፡ ከእኛ ቀደም ብለው አሜሪካ የሚኖሩ በመኖራቸው እኛ ለመልመድ አልተቸገርንም፡፡ በስደት ቀደም ብለው በብዛት የወጡ ጓደኞቻችን ስለነበሩ አገሩን ቶሎ ለመቀላቀልና ሥራ ለማግኘት አልተቸገርንም፡፡ 

ሪፖርተር፡- ከአገር ሲወጡ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ስለነበሩ አሜሪካ እንደገቡ ሥራ ነው የጀመሩት? 

አቶ ሲራክ፡- ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ስላልጨረስኩ ትምህርት ቤት ገባሁ፡፡ 12ኛ ክፍል ካጠናቀቅሁ በኋላ ሳንፍራንሲስኮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በአድቨርታይዚንግ ኤንድ ፕሮሞሽን የመጀመርያ ዲግሪዬን አግኝቻለሁ፡፡ ከዚያም በንግድ ሥራ፣ በኮርፖሬትና በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ስሠራ ቆይቻለሁ፡፡

ሪፖርተር፡-  ወደ ኢትዮጵያ እንዴት ልትመለሱ ቻላችሁ?

አቶ ሲራክ፡- በአገራችን ውስጥ መልካም ሁኔታዎች መፍጠራቸውንና በተለያዩ ምክንያት ከአገራቸው ርቀው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ዘርፎች መሰማራት እንደሚችሉ የመንግሥት አካላት ይናገሩ ነበር፡፡ በወቅቱ ልጆቻችን ገና ሕፃናት ስለነበሩ ወዲያውኑ መምጣት ባንችልም ልባችን ግን አላረፈም፡፡ ልጆቼም ወደ ቤተሰቦቻቸው አገር ለመምጣት ከፍተኛ ጉጉት ስለደረሰባቸው ዘወትር ይወተውቱኝ ነበር፡፡ በመሆኑም ከአሥር ዓመታት በፊት ልንመጣ ችለናል፡፡ እኔም ለአገሬና ለወገኔ ከፍተኛ የሆነ ፍቅር ስላለኝ፣ እንዲሁም ልጆቼ የሰው አገር ዜጋ ሆነው እንዳይቀሩ እመኝ ስለነበር፣ ኢትዮጵያዊነትን በውስጣቸው ለማስቀረትም ፍላጎቱ ስለነበረን ይዘናቸው መጣን፡፡

ሪፖርተር፡- የመንግሥት ተወካዮች ኢንቨስትመንት ላይ ለመሰማራት ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉ ሲናገሩ በምን ዓይነት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ ለመሰማራት ወሰኑ?

አቶ ሲራክ፡- ወደ አሜሪካ መጥተው የነበሩ የመንግሥት ተወካዮች ዳያስፖራው በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፍ መሰማራት እንደሚችል ይናገሩ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ የዘይት እጥረት ከፍተኛ እንደሆነና ዘይት በማምረት ዘርፍ ብንሰማራ መንግሥትም አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግልን ነገሩን፡፡ 90 በመቶ የሚሆነው የዘይት አቅርቦት ከውጭ በመሆኑ፣ ይኼንን ምርት በአገር ውስጥ ምርት ብትሸፍኑት ለአገራችሁም ሆነ ለእናንተ ትልቅ ጥቅም ያስገኛል ብለውን ነበር፡፡ ከአሜሪካ እንደመጣን እጥረት አለ በተባለበት የዘይት አቅርቦት ላይ ለመሰማራት ብንነሳም፣ በተለያዩ ምክንያቶች እንደፈለግነውና እንደተነገረን ሊሆን ባለመቻሉ፣ በእርሻ ኢንቨስትመንት ላይ ተሰማራን፡፡ በኦሮሚያ ክልል በኬ በሚባል አካባቢ ከአርሶ አደር ላይ መሬት ተከራይተን ነጭ ሽንኩርት ማምረት ጀመረን፡፡  

ሪፖርተር፡- መንግሥት መሬት አልሰጣችሁም?

አቶ ሲራክ፡- አልሰጠንም፡፡ የአርሶ አደር መሬት ተከራይተን ነጭ ሽንኩርት ማምረት ብንጀምርም በሥራው መዝለቅ አልቻልንም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የአካባቢው የመንግሥት ተወካዮች ያስፈራሩን ጀመር፡፡ ቦታው ለሽንኩርት ማምረቻ እንዳልተፈቀደ በመግለጽ ሠራተኛ እንዳይቀጠርና መሬት ያከራየንን አርሶ አደር ማስፈራራት በመጀመራቸው የአካባቢው ነዋሪ በመፍራቱ ሠራተኛ ማግኘት አልቻልንም፡፡   

ሪፖርተር፡- ለምንድነው መንግሥት የሚያስፈራራው? ራሱ ጠርቶ?

አቶ ሲራክ፡- መንግሥት በክልሎች በምን በምን ዓይነት ኢንቨስትመንት መሰማራት እንዳለበት ወስኖ ነበር፡፡ ለወተት፣ ለአትክልንና ፍራፍሬ፣ ለአዝርዕትና ለመሳሰሉት ቦታዎችንና ክልሎችን ከፋፍሎ ስለነበር፣ እኔ ደግሞ እንደፍላጎቴና አቅሜ ሊሄድልኝ ስላልቻለ፣ ከዋና ከተማው ብዙም ርቀት በሌለው ቦታ ላይ የሽንኩርት ማምረት ላይ ብሰማራም ተፅዕኖው በመብዛቱ ሳይሳካልኝ ቀረ፡፡ ከስሬ ተውኩት፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ዘይት እንዴት ገቡ?

አቶ ሲራክ፡- የመንግሥት ተወካዮች ወደ አሜሪካ በመጡ ጊዜ ከተናገሩት ውስጥ አንዱ የዘይት ፋብሪካ መገንባት ነበር፡፡ እኔም በውስጤ ያሰብኩት በዘይት ምርት ላይ ለመሰማራት ነበር፡፡፡ እዚህም ከመጣን በኋላ ከፍተኛ ችግር የገጠመን ንጹሕ ዘይት ማግኘት ነበር፡፡ በመሆኑም ዘመናዊ የሆኑ የዘይት ማምረቻ መሣሪያዎችን ከቻይና ገዝቼ አመጣሁ፡፡ መሣሪያውን ካመጣሁ በኋላ ፋብሪካውን መገንቢያ መሬት ስጠይቅ ሊሰጠኝ አልቻለም፡፡ ነገር ግን መንግሥት ፋብሪካውን መገንቢያ ቦታ እስከሚሰጠኝ ድረስ ማሽኑን ከማስቀመጥ ብዬ የግለሰብ ቦታ በመከራየት ላለፉት አራት ዓመታት እንደፈለኩት ባይሆንም ንፁሕ ዘይት እያመረትኩ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- እርስዎ ወደ ዘይት ማምረት የገቡት አስጠንተውና ከመንግሥት ማግኘት የሚገባዎትን መሬትና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ሳያገኙ ነው እንዴ? 

አቶ ሲራክ፡- ስለ ዘይት እኔ የተሻለ ዕውቀት አለኝ፡፡ ሌላው ደግሞ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት መሥሪያ ቤት ያወጣውን የተለያዩ መግለጫዎችንና ሰነዶችን ተመልክቼ ነው ወደ ሥራው የገባሁት፡፡ ደግሞም መንግሥት ራሱ ያለበት ችግር የዘይት መሆኑን ገልጾና ገፋፍቶን ስለነበር ነገሮች ይኼንን ያህል ችግር ይፈጥራሉ የሚል ነገር አልገመትኩም፡፡ በመሆኑም ማሽን ገዝቼ መጣሁ፡፡ ማሽን መትከያ ቦታ ስጠይቅ እንዳሰብኩት ባለመሆኑ ቦታ ተከራይቼ መሥራት ጀመርኩ፡፡ ምንም ያልተቀላቀለበትና በተለያዩ የጤና ተቋማትና የመንግሥት ተቆጣጣሪ ተቋማት የተረጋገጠ ዘይት ማምረት በመጀመራችን በርካታ ደንበኞችን ማፍራት ቻልን፡፡   

ሪፖርተር፡- መንግሥት ኑ ብሎ ጠርቶ መሬት ስትጠይቁት ለምን ከለከላችሁ? ችግሩ ምንድነው?

አቶ ሲራክ፡- እንደመጣን ወደ ኢንቨስትመንት ቢሮ ስንሄድ ወደ ልማት ባንክ ላከን፡፡ ልማት ባንክ እንዴት መሥራት እንደፈለግን ጠይቆን ስናስረዳው አመጣጣችሁ ትክክል አይደለም አለን፡፡ የእኛን መሥፈርት (አካሄድ) ተከትላችሁ አልመጣችሁም አለን፡፡   

ሪፖርተር፡- የልማት ባንክ መሥፈርት ምንድነው?

አቶ ሲራክ፡-  እነሱ መሥፈርት ነው ብለው የነገሩን ሰባት ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ዶላር በቀጥታ በልማት ባንክ ማስቀመጥ እንዳለብን ነገሩን፡፡ ባንኩ ያንን ብር ይዞና በምናቀርበው ፕሮጀክት መሠረት መሥራት እንደነበረብን የሚገልጽ ነው፡፡ እኛ ግን ይኼንን መሥፈርት ስላላወቅን ወይም አሜሪካ በመጡ ጊዜ ይኼንን ስላልነገሩን ቶሎ ወደ ምርቱ ለመግባት ማሽኑን ገዝተን መጣን፡፡ ማሽኑን ቀድመን በመግዛታችን መስመሩን ተከትላችሁ አልጣችሁም አለን፡፡ ‹‹ስህተቱ የእናንተ ነው›› ተብለን መሬት ሊሰጡ አልቻሉም፡፡ ምንም ዓይነት ዕርዳታ አላገኘንም፡፡ እስካሁን በማንኛውም በኩል ዕርዳታ ማግኘት አልቻልንም፡፡  

ሪፖርተር፡- ልማት ባንክ ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ እንድታስቀምጡ እንደ ግዳጅ ያስቀመጠበት ምክንያት ምንድነው?

አቶ ሲራክ፡- ምክንያቱ ለእኔም አልገባኝም፡፡ ድፍን ያለ መልስ የሰጡን፣ ‹‹ከእኛ መሥፈርት ጋር አብሮ አልሄደም›› የሚል ብቻ ነው፡፡ ‹‹ፕሮሲጀሩን ጠብቃችሁ የተጠቀሰውን ያህል ገንዘብ በዶላር አስቀምጣችሁ ቢሆን ኖሮ፣ የፕሮጀክት ጥናታችሁን አይተን 80 በመቶ ብድር እንሰጣችሁ ነበር፤›› ብለውናል፡፡ በእኛ በኩል ማሽኑ ተገዝቶ በመግባቱ፣ ‹‹ማስያዣ ሕንፃም ሆነ ሌላ ነገር ስለሌላችሁ ምንም ማድረግ አንችልም›› ሲሉን የገባን ማስቀመጥ የነበረብንን ገንዘብ እንደ መያዣ ያገለግላል ማለት ነው የሚል ነው፡፡ እንደ አማራጭ የነገሩን ደግሞ 7.5 ሚሊዮን ብር በባንክ እንድናስቀምጥና ከዚያ በኋላ እንደሚያዩልን ነው፡፡ እኔ ደግሞ በጣም ትልቅና ዘመናዊ ማሽን ስለገዛሁበት የጠየቁትን ገንዘብ ላስቀምጥ አልቻልኩም፡፡

ሪፖርተር፡-  አሁን እየሠራችሁ ያላችሁት በሙሉ አቅማችሁ አይደለም፡፡ በኪራይ ቦታ ላይ ለተወሰነ የኅብረተሰብ አካል የሚደርስ የዘይት ምርት ብቻ በመሥራት ላይ ናችሁ፡፡ በቀጣይ ምን ለማድረግ አስባችኋል?

አቶ ሲራክ፡- ያለንን ነገር ሁሉ በማስረዳትና በማሳየት መንግሥት ፋብሪካ መገንቢያ ቦታ እንዲሰጥን በተደጋጋሚ ጠይቀናል፡፡ በተከራየናት አናሳ ቦታ ላይ እያመረትን የምናገኘውን ዘይት ለመንግሥት ኃላፊዎች ጭምር በማሳየት አድናቆታቸውን ሰጥተውናል፡፡ የሚመለከታቸውም ተቆጣጣሪ ተቋማት የዘይታችንን ጥራትና ንፅሕና በመመልከት ወደ ውጭ ኤክስፖርት እንድናደርግ ሰርተፍኬት በመስጠት ጭምር እየገፋፉን ነው፡፡ ነገር ግን በአገር ቤት ያለውን ሕዝብ ሳናዳርስና እኛም በብቃትና በብዛት ማምረት ሳንጀምር ‹‹ጀምረው አቋረጡ›› መባል ስለማንፈልግ መላክ አልጀመርንም፡፡ ሕዝባችን በከፍተኛ የጤና ጉዳት ከሚንገላታባቸውና ከሚሰቃይባቸው የምግብ ዓይነቶች አንዱ ዘይት ነው፡፡ ለጤና ተስማሚ የሆነን ንፁሕና ያልተደበላለቀ ዘይት ማግኘት ስለማይቻል፡፡ ይኼንን ደግሞ በአገራችን ምርቶች ብቻ አምርተን ንፅህናውንና ጥራቱን ጠብቀን የዜጎቻችንን ጤንነት በመጠበቅ በቀጣይ ወደ ሌላው ዓለም ለማዳረስ ነው የእኛ ዓላማ የነበረው፡፡ አሁንም ተስፋ ባለመቁረጥ ተጨማሪ ጥናት በማስጠናት ለኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስገብተናል፡፡  

ሪፖርተር፡- በመንግሥት በኩል ብድርም ሆነ መሬት ማግኘት አልቻላችሁም፡፡ በሌላ በኩል ግዙፍ ማሽን ገዝታችሁ አስገብታችኋል፡፡ በቀጣይ ምን ልታደርጉ ነው? 

አቶ ሲራክ፡- አሁን የኢሕአዴግ መንግሥት አመራሩን ቀይሯል፡፡ በዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው መንግሥት ቀደም ብለው ከነበሩት አመራሮች የተሻለ አስተሳሰብ ያላቸውን ባለሙያዎች በአስፈጻሚነት ሾሟል፡፡ የተሻለ የሥራ እንቅስቃሴም እየታየ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ ‹‹አገራችንን በምንችለው ሁሉ እንደግፍ፣ እናሳድግ›› እያሉ ነው፡፡ ምናልባትም የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ለውጥ ያደርጋል የሚል እምነት አድሮብኛል፡፡ በመሆኑም እኛ ያለንን ማሽንና ፍላጎት በማየት ፋብሪካ መገንቢያ ቦታ ሆነ ብድር ሰጥቶን ዓላማችንን እናሳካለን፣ ትልቅ ተስፋ አለን፡፡ ይኼ ደግሞ ለእኛ፣ ለሕዝቡና ለመንግሥት ጠቃሚ ነው፡፡ ለሌሎች የውጭ ኢንቨስተሮች እንደሚደረገው ድጋፍ ለእኛ ለአገር በቀሎቹ ኢንቨስተሮች ትንሽ ማበረታቻ ቢደረግልን ማለትም በተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ቦታ ቢሰጠን ትልቁን ችግር መቅረፍ እንችላለን፡፡ ጥቅማችንም ቀላል አይደለም፡፡ የተወሰነ የሥራ አጥን ችግር እንቀርፋለን፡፡ ወደ ውጭ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ እናስቀራለን፡፡ በአግባቡና በወቅቱ ታክስ በመክፈል ሌላው ልማት እንዲቀንስና እንዲስፋፋ እናደርጋለን፡፡ የሚገርመው ነገር አሁን ተከራይተን በምናመርተው ዘይት ብዙ ደንበኞችን አፍርተናል፡፡ አንዱና ትልቁ ደንበኛችን የመንግሥት ተቋም አትክልትና ፍራፍሬ ነው፡፡ ከብዙ ድርጅቶችም ጋር ኮንትራት ወስደን እየሠራን ነው፡፡ ችግሩ የደንበኛ ሳይሆን የአቅርቦት ችግር ነው፡፡ ሰፊ ቦታ ኖሮን ማሽናችን ተክለንና በርካታ ሠራተኞችን በመቅጠር በብዛት ማምረት ባለመቻላችን የትም መድረስ አልቻልንም፡፡ እነዚህ ደንበኞችን እንደ መያዣ (ኮላተራል) ሊታዩ ይገባል የሚል እምነት አለን፡፡ መንግሥት ቢረዳንና ፋብሪካ ገንብተን መሥራት ብንችል ለሕዝቡ ጤናማ የሆነ ምርት ማቅረብ እንችላለን፡፡ ወደ ውጪ በመላክም ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት እንችላለን፡፡ በኖርንባት አሜሪካም ሆነ ሌሎች የአውሮፓ አገሮች የቢዝነስ ኮንትራት የሚታየው እንደ ዋስትና ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት የሚያበድረው የሕዝብን ገንዘብ ነው፡፡ ለዚያ ደግሞ ዋስትና አስፈላጊ ነው፡፡ በእኛ አገር አሠራር የደንበኞች መብዛት እንደ ዋስትና ሊወሰድ አይስተዋልም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አንዱ ለተበደረው ሌላኛው አካል ያለውን ንብረት በዋስትና መልክ ካላስያዘለት በስተቀር ሁለቱ ወገኖች ብቻ ባላቸው የቢዝነስ ግንኙነት አንዱ ለሌላኛው ዋስትና ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ ሲሠራበት አይስተዋልምና ይኼንን እንዴት ማስተካከል ይቻላል?

አቶ ሲራክ፡- ልክ ነው፡፡ የተወሰነ አደጋ ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን ሁልጊዜ አደጋ ይደርሳል ብለን የምንፈራ ከሆነ መሥራት አንችልም፡፡ መንግሥት ውስን የሆነ ነገር (Limited Risk) ሊወስድ ይገባል፡፡ ውስን የሆነ አደጋን መውሰድ በጣም ከፍተኛ የሆነም ጥቅም ያስገኛል፡፡ መንግሥት ይኼንን ሁሉ መሠረተ ልማት ሲሠራ፣ ለውጭ ኢንቨስተሮች ሲያበድር አደጋ (Risk) ሊያጋጥመው ይችላል፡፡ ነገር ግን አደጋ ያጋጥመኛል ብሎ ቁጭ ሊል አይችልም፡፡ መንግሥት በቢሊዮን የሚገመት ገንዘብ በመደጎም ዘይት እንዲገባ የሚያደርገው ለሕዝብ ጥቅም ሲል ነው፡፡ የሚያመጣውን ጥቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት ብዙ ነገር ይደረጋል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ላለፉት አራት ዓመታት በተከራዩት ትንሽ ቦታ ላይ ንፁሕና ጥራቱን የጠበቀ ዘይት እያመረታችሁ መሆኑን ነግረውኛል፡፡ ከምን ዓይነት የቅባት እህል ነው የምታመርቱት? መጠሪያ ስያሜውስ ምንድነው?

አቶ ሲራክ፡- ዘይቱ ‹‹ኔግራ ዘይት›› ይባላል፡፡ መቶ በመቶ ከኑግ ነው የምንሠራው፡፡ ማሽናችን ራሱ አበጥሮና ንፁህ መሆኑን አረጋግጦ ጨምቆ ያወጣል፡፡ ማምረት ከጀመርን አራት ዓመታት ሆኖናል፡፡ ለምርታችን ንፁሕነት ምስክሮቻችን ደንበኞቻችን ናቸው፡፡ አራት ዓመታት በብዛት የሚወስዱ ደንበኞች አሉን፡፡ አንድም ቀን ተቃውሞ አቅርበው አያውቁም፡፡ ሁልጊዜ ምሥጋናቸውን እንደገለጹልን ነው፡፡ ኢትፍሩትን ጨምሮ በከተማው ውስጥ አሉ የተባሉ ሬስቶራንቶች የምሥጋና ሰርተፍኬት እየሰጡን ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- በርካታ ዘይት አምራቾች አሉ፡፡ የኑግ፣ የሱፍ፣ የሰሊጥና የሌሎች የቅባት እህሎችን በመጠቀም ያመርታሉ፡፡ የእናንተ ለየት የሚያደርገውና የተሻለ ነው የምትሉት በምን ምክንያት ነው?  

አቶ ሲራክ፡- የኑግ ዘይት በባህሪው ከሌሎች ይለያል፡፡ ልክ እንደ ወይራ ዘይት የተስተካከለ ንጥረ ነገሮችን የያዘ ነው፡፡ በተለይ በውስጡ የሚገኘው ሊኖሊክ አሲድ ለደም ሥርና ለልብ ጠቃሚ ነው፡፡ ኑግ ዘይት የሆነውን ኮሌስትሮል የሚያስወግደውን ኤችዲኤል (HDL) በሰውነት ውስጥ እንዲፋፋና እንዲበዛ የሚያደርግ ነው፡፡ ትኩረታችን ጤናና ንፁሕ መሆኑ ላይ በመሆኑ እንጂ ለገበያና ትርፍ ብቻ ለማግኘት ቢሆን ሌሎቹ ይሻላሉ፡፡ ኔግራ ዘይትን በንፅሕና በማምረት ጤናን መጠበቅ ዋናው ዓላማችን በመሆኑ ከሌሎቹ ዘይቶች ከፍ ባለ ዋጋ ቢሸጥም፣ የሚያስገኘው ጥቅም ግን እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ይኼንን የምንለው ደግሞ ራሳችንን ለማስወደድ ወይም ዝም ብለን በባዶ ሜዳ ልዩ ነን ለማለት ሳይሆን፣ በግለሰቦችም ሆነ በመንግሥት የጤና ተቆጣጣሪ ተቋማት የተመሰከረልን መሆኑን ስንናገር በኩራት ነው፡፡ እያንዳንዱ የኅብረተሰብ ክፍል በአንድም በሌላ ዘይት ተጠቃሚ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ለጤና ጠቃሚ በመሆኑ ተፈላጊነቱም በዚያው ልክ ነው፡፡     

ሪፖርተር፡- ምግብ ነክ ምርቶችን የሚቆጣጠሩ የመንግሥት ተቋማት በዘይት ምርታችሁ ላይ የሰጡት የዋስትና ማረጋገጫ ፈቃድ አላችሁ? ቁጥጥር የሚያደርጉትስ እንዴት ነው?

አቶ ሲራክ፡- ከደረጃ መዳቢዎች የተስማሚነትና ምዘና ኤጀንሲ ባለሙያዎች በማምረቻ ቦታ መጥተው፣ ጥራቱንና ንፀሕናውን በመመርመርና በመለካት የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬትና ዕውቅና ሰጥተውናል፡፡ ‹‹ለምን ወደ ውጭ ኤክስፖርት አታደርጉም?›› ብለው እስከመጠየቅም ደርሰዋል፡፡ የምንሠራው ሥራ በኤክስፖርት ደረጃ ያለ መሆኑንም አረጋግጠው ሰርተፍኬት ሰጥተውናል፡፡ እንዲያውም ‹‹አይሶ ሰርተፊኬት የምታገኙበትን መንገድ ሁሉ እናመቻችላችኋለን›› ብለውናል፡፡ ትልቁ ሐሳባቸው ኮሜሳ ውስጥ እንድንገባ ነበር፡፡ ነገር ግን እነሱ ያሉንን ሁሉ ተቀብለን እንዳንጓዝ፣ ምርቱን በብዛትና በጥራት አምርተን ለማዳረስ ፋብሪካውን አስፋፍተን ማምረቻ ማሽኖችን መጠቀም አለብን፡፡ ይኼንን ለማድረግ ደግሞ መሬት ወይም ሰፊ ቦታ ያስፈልጋናል፣ እኛ ማምረቻ ማሽኑን የገዛን ቢሆንም ከላይ እንደጠቀስኩት፣ ‹‹ፕሮሲጀሩን አልተከተላችሁም›› ተብለን መሬት ሊሰጠን አልቻለም፡፡ በኪራይ ቦታ ውስጥ ግን የተባለውን ሁሉ ማሳካት አይቻልም፡፡ ከባድም ነው፡፡ ያለንን ማሽን ለሥራው ምን ያህል ትኩረት ሰጥተን እየሠራን መሆኑንና በቀጣይም ለሕዝባችንና ለአገራችን ያለውን ጠቀሜታ ጭምር የሚመለከተው የመንግሥት አካል ተመልክቶ፣ ፋብሪካ መገንቢያ ቦታ ይሰጠናል በሚል ተስፋ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን በተከራያችሁት ቦታ ላይ በቀን ምን ያህል ሊትር ዘይት እያመረታችሁ ነው?

አቶ ሲራክ፡- ማሽናችንን በሙሉ ተክለን መሥራት ብንችል በቀን ከ3,000 ሊትር በላይ ማምረት እንችል ነበር፡፡ አሁን ግን ከ1,500 ሊትር በላይ ማምረት አልቻልንም፡፡ በቦታ ጥበት የተነሳ ተገድበናል፡፡   

ሪፖርተር፡-  በፋብሪካችሁ ውስጥ ያሉ ሠራተኞች በሙያው የሠለጠኑ ናቸው?

አቶ ሲራክ፡- በኬሚስትሪ፣ ስፔሻላይዝ ያደረገና በዘይት ምርት ዙሪያ ልዩ ጥናት ያደረገ ኬሚስት በፋብሪካው ውስጥ በኃላፊነት የሚመራ ሠራተኛ አለን፡፡ በሙያው ከፍተኛ ልምድና ዕውቀት ያሏቸው ሠራተኞች አሉን፡፡ ከበታች ሠራተኞች ጀምሮ እስከ ኃላፊ ደረስ ያሉ ከ20 በላይ የሚሆኑ ሠራተኞቻችን በዘርፉ ዕውቀት ያላቸው ናቸው፡፡ 

ሪፖርተር፡-  ዘይታችሁ ተመርቶ የሚቆየው ለምን ያህል ጊዜ ነው?

አቶ ሲራክ፡-  የኑግ ዘይት ተመርቶ እስከ ሁለት ዓመት ሊቆይ ይችላል፡፡ በቆየ ቁጥር ግን ጣዕሙ እየቀነሰ ስለሚመጣ እንደተመረተ ቢበላ ጥሩ ነው፡፡ እኛ ግን ካለን የምርት ውስንነት አንፃር የምናመርተው ከደንበኞቻችን ጋር በገባነው ውል መሠረት በመሆኑ በብዛት አምርተን አናስቀምጥም፡፡ እናምርት ብንልም ሰፊ ቦታ ስለሌለን አንችልም፡፡ የምርት ጊዜውንና ከፋብሪካው ውጪ የተደረገበትን ጊዜ የሚገልጹ መለያዎች በመያዣዎቹ ላይ ስለምናስቀምጥ እኩይ ባህርይ ባላቸው ነጋዴዎች እንዳይጭበረበርም ልዩ ጥንቃቄ እናደርጋለን፡፡  

ሪፖርተር፡- ትልቁ ችግር የቅባት እህሎችን ማግኘት እንዲሆን ይነገራል፡፡ የኑግ ምርት የምታገኙት ከየት ነው?   

አቶ ሲራክ፡- እስካሁን የምንሠራው በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የቅባት እህሎች ከሚያመርቱና ከአርሶ አደሩ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- መንግሥት ለአገር ውስጥ አምራቾች ምን ማድረግ አለበት ይላሉ? 

አቶ ሲራክ፡- ሊደግፈን፣ ሊያበረታታንና ከውጭ ተገዝተው የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በማምረትና በመላክ የውጭ ምንዛሪ ወጪያችንን ማዳን ላይ እንድንሠራ ማድረግ አለበት፡፡ እኛ ማሽን ይዘን ፋብሪካ መገንቢያ ቦታ በማጣታችን ተቸግረናል፡፡ መሬት ሊሰጠን ይገባል፡፡ ወይም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ሰፊ ሼድ በረዥም የኮንትራት ጊዜ እንድናገኝ ሊፈቀድልን ይገባል፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ምንም ዓይነት መዛባት ሳንፈጥር ንፁሕና ለጤና ተስማሚ የሆነ፣ ‹‹ኔግራ ዘይት›› እያመረትን በመሸጥ ላይ ነን፡፡ በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው የመንግሥት አካል ጭምር እየተመገቡት ነው፡፡ ኔግራ የሚል ስያሜ የሰጠነው የጥቁር አፍሪካውያን መገለጫችን ስያሜና በአጋጣሚም ‹‹ኑግ›› የሚል ስያሜም ስላለው ነው፡፡ ሌላው ልዩ የሚያደርገው በተለያዩ ኬሚስቶች ተመርምሮ ከኮሌስትሮል ነፃ የሆነ ዘይት መሆኑ ነው፡፡ እኛን የያዘን የተነሳንበት ዓላማ ሕዝባችንንም ሆነ መንግሥትን በቅንትና በታማኝነት ለማገልገል፣ ሕዝባችን በተለያዩ ምግቦች ያጣውን ጤና በተለየ ከዘይት ጋር በተገናኘ እየተፈጠረበት ያለውን የተለያየ የጤና እክል ለመታደግ ንፁሕ ዘይት ለማምረትና ለማዳረስ እንጂ፣ ገንዘብ ለማግኘት ቢሆን ኖሮ የተለያዩ የማጭበርበሪያ ዘዴዎችን ተጠቅሞ ማግኘት ቀላል ነው፡፡ ነገር ግን አቅማችን እስከፈቀደ መንግሥት ለማስቸገርና ቦታ ተሰጥቶን ምርቱን በስፋትና በጥራት ለማቅረብ እንጥራለን እንጂ በማይሆን ሥራ ላይ መቼም ቢሆን አንሰማራም፡፡      

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ጉራጌን በክላስተር ለመጨፍለቅ የሚደረገውን ጥረት እንደሚቃወም ጎጎት ፓርቲ አስታወቀ

ለጉራጌ ሕዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር እንደሚታገል የሚናገረው አዲሱ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

‹‹ኢኮኖሚው ላይ የሚታዩ ውጫዊ ጫናዎችን ለመቀልበስ የፖሊሲ ሪፎርሞች ያስፈልጋሉ›› ዓለም ባንክ

በዓለም ደረጃ ከተፈጠረው የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ጋር በተገናኘ፣ በኢትዮጵያ ውጫዊ...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...