Monday, March 4, 2024

የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ጉዳይ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በኢሕአዴግ ውስጥ ከተፈጠረው የአመራር ለውጥ ወዲህ፣ አገሪቱ የተለያዩ አወዛጋቢ ጉዳዮችን እያስተናገደች ትገኛለች፡፡ ከእነዚህ አወዛጋቢ ጉዳዮች ውስጥ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግዘፍ ነስቶ ግለሰቦችን፣ ፖለቲከኞችን፣ እንዲሁም የሕገ መንግሥትና የመንግሥት አስተዳደር ምሁራንን በከፍተኛ ሁኔታ እያወዛገበና እያወያየ የሚገኘው ደግሞ ሕገ መንግሥቱ ነው፡፡

ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም. የፀደቀው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ባለመሆኑ፣ ባለፉት ዓመታት ከሕገ መንግሥታዊ መርሆዎች ይልቅ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች በመበርከታቸው፣ አሁን ለሕገ መንግሥት ውይይቶችና ሙግቶች በር ከፋች ሆኗል፡፡

ከቅርብ ወራት ወዲህ ሕገ መንግሥቱ ተጥሷል የሚሉ ወገኖች መበራከትና ሕገ መንግሥቱ መቼ ተከብሮ ያውቃል? የሚሉ ሁለት ሙግቶች ዋነኛዎቹ የዚህ ውዝግብ ማሳያ ናቸው፡፡

ሕገ መንግሥቱን ከመተርጎም፣ ከማስፈጸም እንዲሁም በሕገ መንግሥቱ ላይ የሠፈሩትን መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች ከማክበርና ከማስከበር አንፃር በነበሩ ክፍተቶች ሳቢያ፣ ሕገ መንግሥቱ መቼ ተከብሮ ያውቅና ነው የሚሉት ወገኖች መከራከርያ ሲያቀርቡ፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የተመሠረተው የፌዴራል ሥርዓትና አወቃቀር፣ የፌዴራል መንግሥቱ እዚህም እዚያም የሚፈጠሩ ብሔር ተኮር ግጭቶችን ለማረቅ አለመቻል ደግሞ ሕገ መንግሥቱ ተጥሷል በሚሉ ወገኖች የሚነሳ መከራከሪያ ነው፡፡

ቅዳሜ ታኅሳስ 20 ቀን 2011 ዓ.ም. የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት የተለያዩ የክልል ባለሥልጣናት፣ የፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶችና የሕግ ባለሙያዎች፣ እንዲሁም ምሁራን የታደሙበት በሕገ መንግሥት አተረጓጎምና መጠናከር ስለሚቻልባቸው ጉዳዮች ለመምከር የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡

የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ጉዳይ

 

በምክክር መድረኩ ላይ የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የፌዴራሊዝምና ሥነ መንግሥት ምሁር አሰፋ ፍሰሐ (ዶ/ር) ሲሆኑ፣ የጉባዔው አባል የሆኑት አቶ ሚሊዮን አሰፋ ደግሞ በጉባዔው ውሳኔ በተሰጣቸው ጉዳዮች ላይ በመነሳት ዘለግ ያለ ማብራሪያ ሰጥተው ነበር፡፡

በዚህም መሠረት አሰፋ ፍሰሐ (ዶ/ር) የሕገ መንግሥት አጣሪ ሆኖ የሚሰየም አካል ስለሚኖረውና ስለሚገባው ኃላፊነቶችና መብቶች፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን መሠረት በማድረግ የአገሪቱን ተርጓሚዎች ሚናና ክፍተት ለተወያዮች አቅርበዋል፡፡

የሕገ መንግሥት አጣሪ አካል ከምንም በላይ ገለልተኛ የመሆን ኃላፊነት እንዳለበት በአፅንኦት አስረድተው፣ ይህንንም ለማስረገጥ የእግር ኳስ ዳኝነትን ምሳሌ በማንሳት ሜዳው ላይ ያሉትን የሁለቱንም ወገን ተጫዋቾች በገለልተኝነቱ ማገልገል እንዳለበት ሁሉ፣ የሕገ መንግሥት ተርጓሚ አካልም እንዲሁ በገለልተኝነት ዳኝነት በመስጠት ጨዋታውን ፈርጅ የማስያዝ ኃላፊነት አለበት ብለዋል፡፡ በዚህም መሠረት ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍትሔ መስጠት፣ የሕገ መንግሥት ተርጓሚው አካል ኃላፊነት ነው በማለት አስረድተዋል፡፡

ሌላው ምሁሩ ያነሱት ነጥብ ደግሞ በተለይ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ የተረቀቁት የአብዛኞቹ ሕገ መንግሥቶች ይነስም ይብዛ የዜጎችን ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መብቶችን ያካተቱ ከመሆናቸው አንፃር መንግሥት የዜጎችን መብትና ነፃነት በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ማክበር ሲያቅተው፣ ይህንን የሚከታተለው ሕገ መንግሥቱን የሚተረጉመው አካል እንደሆነ አውስተዋል፡፡

በዚህም ኃላፊነት መሠረት የሥልጣን ገደብህን አልፈሃል፣ የዜጎችን ነፃነትና መብት ተላልፈሃል በማለት ልጓም የሚያበጀው የሕገ መንግሥት ተርጓሚው አካል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳን የሕገ መንግሥት ተርጓሚው አካል የዜጎችን መሠረታዊ ሰብዓዊ መብትና ነፃነት እንዲተገበር የመሥራት ኃላፊነት እንዳለበት ቢጠቅሱም፣ በእርሳቸው ትዝብት መሠረት ግን መሠረታዊ የዜጎችን መብቶች የያዘው የሕገ መንግሥቱ ምዕራፍ ሦስት በአሁን ጊዜ ባለቤት ያጣ ምዕራፍ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

በተመሳሳይ የፍትሕ ምልክት ተደርጋ የምትቆጠረውን እንስት በምሳሌነት አንስተዋል፡፡ ሕገ መንግሥት የሚተረጉመው አካል በተለያዩ ፍርድ ቤቶችና የሕግ ትምህርት ቤቶች አፀድ ውስጥ የምትገኘውን ዓይኗ በጨርቅ የተሸፈነውንና በግራና በቀኝ እጇ ሰይፍና ሚዛን የያዘችውን እንስት ትዕምርታዊ ምሳሌነት በማውሳት፣ ሕገ መንግሥት የመተርጎም የተሰጠው አካልም ከየትኛውም ወገን ሳይወግን በገለልተኝነት ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ኃላፊነት እንዳለበት አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

‹‹ሕገ መንግሥት ተርጓሚው አካል ከዚህ መሠረታዊ የፍትሕና ርትዕ መርህ በመነሳት፣ ለየትኛውም ወገን ባለማድላት ተጥሰዋል ተብሎ የቀረበለትን የሕገ መንግሥት መርሆዎች ለማፅናትና ለማስከበር ገለልተኛ መሆን ይገባዋል፤›› በማለት ያብራሩ ሲሆን፣ በዚህ መርህ መሠረትም ተርጓሚው አካል እጅግ ወሳኝ ሚና የሚጫወት መሆኑን መገንዘብ አስፈላጊው እንደሆነ አስምረውበታል፡፡

ሌላው ሕገ መንግሥትን ከመተርጎም አንፃር አዲስ ክስተት ወይም ጽንሰ ሐሳብ የሆነው የሕገ መንግሥት ኢንሹራንስ የሚለውንም አስፈላጊነትን አብራርተዋል፡፡ ሕገ መንግሥት ተርጓሚው አካል በተለይ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት በሚከተሉ አገሮች ውስጥ፣ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ዋስትና የሚሰጥ አካል እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

‹‹የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት የሚከተል የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ፓርቲዎች ይቀያየራሉ፡፡ ስለሆነም አንድ ፓርቲ ከሥልጣን ከወረደ በኋላ ምንም አድልኦ በሌለበት ሁኔታ በሚቀጥለው ምርጫ የምረጡኝ ቅስቀሳና ዘመቻ አድርጎ ወደ ሥልጣን እንዲመለስ ዋስትና ያስፈልገዋል፡፡ ስለዚህ ሰላማዊ የሆነ የሥልጣን ሽግግር እንዲኖር እንደ ኢንሹራንስ ዋስትና የሚሰጥ ተቋም ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም ተርጓሚው አካል ይህ ጽንሰ ሐሳብ ሕይወት ኖሮት እንዲቀጥል የማድረግ ኃላፊነት እንደሚኖረውና ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት መረዳቱ ተገቢ ነው፤›› በማለት፣ ተርጓሚው አካል ለሰላማዊ የሥልጣን ሽግግርና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከፍተኛ ሚና ሊጫወት እንደሚችል አስገንዝበዋል፡፡

ሌላው በምሁሩ የቀረበው የተርጓሚ አካላት ኃላፊነት ደግሞ የሕጎችን ወጥነት ማረጋገጥ ነው፡፡ ‹‹በሕጎች ዙሪያ ወጥነት መፍጠር በሚኖርበትና በሚያስፈልግበት ጊዜ፣ የሕጎችን ወጥነት የሚያረጋግጥልን አካል ይኸው ከፍተኛ ኃላፊነት የተጣለበት የሕገ መንግሥት ተርጓሚ አካል ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የፌዴራልና የክልል ሕጎችን በምንተረጉምበት ጊዜ በየደረጃው ያሉ ተርጓሚ አካላት የተለያየ አረዳድና አተረጓጎም ስለሚኖር፣ ሁሉም በፈለገው መንገድ ቢተረጉም ሥርዓት አልበኝነት ስለሚፈጠር፣ ከዚህ ሥርዓት አልበኝነት ለመውጣት ሲባል ልዩነቶች ሲኖሩ የሚያርቅና የሚያስተካክል አካል ያስፈልጋል፡፡ በዚህ መሠረትም ተርጓሚው አካል ይህንን አቅጣጫ የማስያዝ ኃላፊነት እንዳለበት እንመለከታለን፤›› በማለት፣ ተርጓሚው አካል ሕገ መንግሥቱን ከሌሎች ሕጎች ጋር የማጣጣምና ወጥነት የመፍጠር ኃላፊነትም ዋነኛ ሚናው እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡

የአሰፋ ፍሰሐ (ዶ/ር) ማብራሪያና ገለጻን ተከትሎ ባለፉት ዓመታት ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ የቀረቡትን ጉዳዮች በማውሳት ማብራሪያ የሰጡት አቶ ሚሊዮን አሰፋ ናቸው፡፡ እንደ እርሳቸው ገለጻ ባለፉት ዓመታት ለጉባዔው ከሦስት ሺሕ በላይ ጉዳዮች መቅረባቸውን፣ ከእነዚህ ውስጥ ግን ወደ 60 ገደማ የሚሆኑት ብቻ የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል ተብለው በጉባዔው መታየታቸውን ገልጸዋል፡፡

አጣሪ ጉባዔው ስለተመለከታቸው ጉዳዮች አንድ በአንድ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ሚሊዮን ገለጻቸውንና ጉዳዮቹን ለመፍታት የተሄደበትን መንገድ ማብራሪያ ተከትሎ ደግሞ፣ ተሳታፊዎች በቀረቡት ሐሳቦችና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ጥያቄዎችና አስተያየቶች ሰንዝረዋል፡፡

በዚህም መሠረት ከሐረሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመጡት ተወካይ፣ ‹‹የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሁለት ግለሰቦች መካከል በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የመጨረሻ ውሳኔ ያገኘን ጉዳይ የሕገ መንግሥት ጥያቄን ምክንያት በማድረግ የመጨረሻ ውሳኔ ያገኘ ውሳኔ ላይ ፍርድ ሲሰጥ፣ ሲያሻሽል፣ ሲሽረውና ሲያፀናው በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የፌዴሬሽን ምክር ቤት የዳኝነት አካል አይሆንም ወይ?›› በማለት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡

ይህንን ጥያቄ ያቀረቡትም የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 80 ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የበላይና የመጨረሻው የዳንነት ሥልጣን ያለው አካል ነው ከሚለው መርህ አንፃር ነው ብለዋል፡፡

‹‹በሕገ መንግሥቱ እንዲህ በግልጽ የተቀመጠ አንቀጽ እያለ እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎችን ወስዶ መሻር፣ መለወጥና ማፅናት ዳኝነት አይሆንም ወይ? ከሕገ መነግሥቱ አንቀጽ ጋርስ አይጣረስም ወይ?›› በማለት ተጨማሪ ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል፡፡

የሶማሌ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አብዱላሂ ሰዒድ በበኩላቸው፣ ወቅታዊ የአገሪቱን ሁኔታ የተመለከቱ ጥያቄዎች በመሰንዘር ከመድረኩ መፍትሔ ጠይቀዋል፡፡ በርካታ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ያወሱት አቶ አብዱላሂ፣ ከዚህ ጋር ተያይዞም የዜጎች መብት ጥያቄ ውስጥ በመግባቱ፣ በመድረኩ ላይ ከመወያየት ባለፈ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ቢቀመጡ መልካም እንደሆነ አሳስበዋል፡፡

የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ ጉዳዮች አማካሪ፣ ተርጓሚው አካል ነፃና ገለልተኛ የመሆኑን ጉዳይ ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር መመልከቱ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹በእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ ሕገ መንግሥትን የመተርጎም ሥልጣን የተሰጠው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ ይህ ምክር ቤት ደግሞ ከፍተኛ የፖለቲካ ሥልጣን ያለው አካል ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በተለይ ከመንግሥት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ምን ያህል ነፃና ገለልተኛ ሆኖ ነው የሚሠራው?›› በማለት ጥያቄ ሰንዝረዋል፡፡

እነዚህና መሰል ጥያቄዎች ከተሳታፊዎች ከተሰነዘሩ በኋላ፣ ለተወሰኑት ምላሽ ሲሰጥ የተወሰኑትን ደግሞ እንደ አስተያየት መውሰዳቸውን የመነሻ ጽሑፍ አቅራቢዎቹ ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን በግለሰብ ጉዳዮች ላይ እየገባ የሚለው የሐረሪውን ተወካይ ጥያቄ አስመልክቶ፣ ‹‹የግለሰቦችም ሆነ የሴቶች አልያም የሕፃናት ጉዳይ የሕገ መንግሥት ትርጉም ካስነሳ ሊታለፍ የሚችል ነገር አይደለም፣ በዚህ ምክንያት ሊሆን ይችላል፤›› በማለት አሰፋ ፍሰሐ (ዶ/ር) ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱን ማን ይተርጉመው?

ሕገ መንግሥት የመተርጎም ሥልጣን የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደሆነና የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ደግሞ የማማከር ድርሻ እንዳለው የሚያሳየው ግንዛቤ ተቀባይነት ያለው አሠራር ነው፡፡ ይህ አሠራር ያለ ቢሆንም እንደ አሰፋ ፍሰሐ (ዶ/ር) ገለጻ ግን፣ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ፍርድ ቤቶች ይህን ኃላፊነትን መጋራት አለባቸው፡፡

‹‹ይህ አረዳድና ግንዛቤ ያለና በአብዛኛው የሚሠራበት ቢሆንም፣ በተለይ የሕገ መንግሥቱን ምዕራፍ ሦስት ክፍሎች ከመተርጎም አኳያ ግን ፍርድ ቤቶችም ሥልጣን ሊኖራቸው ይገባል የሚለው ሐሳብ ደጋፊ ነኝ፤›› በማለት አቋማቸውን አንፀባርቀዋል፡፡

በመጨረሻም ባለፉት ዓመታት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የባለሙያ ሥራውን ሲሠራ አጣሪ ጉባዔው የፖለቲካ ሥራ ሲያከናውን እንደነበር በመግለጽ ይህንንም ሁኔታ፣ ‹‹የሚያሳዝን ግን መሬት ላይ ያለ እውነታ፤›› በማለት አሰፋ (ዶ/ር) በአገሪቱ ያለውን የሕግ አተረጓጎም መዛነፍ አስረድተዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየታዩ ያሉት የተለያዩ ሕጎችን የማሻሻል ሥራዎች እንዲህ ያሉ መሠረታዊ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎችን ጨምሮ መፍትሔ ይሰጣሉ ተብሎ የሚጠበቅ በመሆኑ፣ ሕገ መንግሥትን ማን ይተርጉመው የሚለው ሐሳብ ምንም እንኳን የሕገ መንግሥት ማሻሻያ የሚሻ ቢሆንም ወጥነት ባለው መንገድ አቅጣጫ ይቀመጥለታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የብዙዎች ተስፋ ሆኗል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -