Sunday, April 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በስም የቀረው የእንስሳት ሀብት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ያሏትን ኢኮኖሚያዊ ሀብቶች በአግባቡ መጠቀም ካለመቻሏም ባሻገር፣ ሀብቶቿን ለሕዝብ ጥቅም እንዲውሉ ለማድረግ የሚያስችሉ ፖሊሲዎች እየተቀረፁ በአግባቡ አለመተግበራቸውም ከአገሪቱ ችግሮች ውስጥ ይመደባል፡፡

ይህን ችግር በጉልህ ማየት ከሚቻልባቸው መካከል ለውጭ ገበያ የሚቀርቡት ምርቶች ይጠቀሳሉ፡፡ የውጭ ምንዛሪ ምንጮች የሆኑ የግብርና ምርቶችን ሳያቀነባብሩ በጥሬያቸው ወደ ውጭ መላካቸው፣ በተለይም ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ምርት በዓይነትና በጥራት አለመጨመሩ፣ ሄድ መለስ የሚለው ግጭትና ብጥብጥ ታክሎበት፣ እየቀረቡ ያሉት ጥቂት ምርቶችም ከመንገድ እየቀሩ መምጣታቸው የውጭ ምንዛሪ ገቢውን ቁልቁል ሲነዱት ሰንብተዋል፡፡

አብዝቶ ለኢትዮጵያ ከተሰጧት ፀጋዎች መካከል የኢትዮጵያ የእንስሳት ሀብት አንዱና ለወጪ ንግድ ገቢም ምንጭ ከሆኑት የሚፈረጅ ቢሆንም፣ በእጅጉ ጥቅም ላይ ካልዋሉት መካከል የሚፈረጅ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብቷ ከአፍሪካ ቀዳሚ ስለመሆኗና ከዓለም በሰባተኛ ደረጃ እንድትመደብ ለዘመናት ሲነገርለት ኖሯል፡፡ በዓለም የደረጃ ሰንጠረዥ ያፈናጠጣት ይህ ሀብት የሚያስገኘው የወጪ ንግድ ገቢ ይቅርና ክምችቱ በራሱ እያሽቆለቆለ ሊሄድ የሚችልበት አጋጣሚ እየተፈጠረ መምጣቱ እየታየ ነው፡፡

ቅዳሜ፣ ታኅሳስ 20 ቀን 2011 ዓ.ም. በባህር ዳር ከተማ ለውይይት የቀረበ አንድ ጽሑፍም የአገሪቱ የእንስሳት ሀብት ተገቢውን ጥቅም ሊያስገኝ የሚችልበት ደረጃ ላይ እንደማይገኝ አመላክቷል፡፡ በዘርፉ የሚታዩ ፈታኝ ችግሮችን፣ የመፍትሔ ሐሳቦችንና ወቅታዊ የእንስሳት ሀብትን የተመለከቱ መረጃዎችንም ያካተተው ጽሑፍ፣ የእንስሳት ሀብት ከሌሎች የግብርና ምርቶችም ይልቅ ጥቅም ሊሰጥ የሚችልበት አቅም እንዳለውም ይሞግታል፡፡

‹‹የአማራ ክልል የእንስሳት ሀብት ልማት ዕድሎች፣ ተግዳሮቶችና የመፍትሔ አማራጮች፤›› በሚል ርዕስ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ መላኩ እዘዘው (ኢንጂነር) ናቸው፡፡ እንደ አቶ መላኩ ገለጻ፣ የእንስሳት ሀብት ለኢትዮጵያ እንደ ነዳጅ የሚቆጠር ቢሆንም፣ ይህንን የሀብት ምንጭ ጥቅም ላይ ለማዋል በሚያስችል ደረጃ አልተሠራበትም፡፡ የአቶ መላኩ ጽሑፍ የአማራ ክልልን የእንስሳት ሀብት መነሻው በማድረግ የአገሪቱን አጠቃላይ የእንስሳት ሀብት አጠቃቀም ቃኝቷል፡፡

ክልሉ እንደ አብዛኞቹ አካባቢዎች የበርካታ ሥነ ምኅዳራዊ ሀብቶች ባለቤት በመሆኑ፣ በርካታ የእንስሳት ዝርያዎች ባለቤት መሆኑን የጠቆሙት አቶ መላኩ፣ በ2008 ምርት ዘመን ብቻ በአገር ደረጃ ከታረሰው መሬት 35.43 በመቶ፣ በምርት ረገድም 32.78 በመቶ ድርሻውን የያዘው የአማራ ክልል እንደሆነም በጽሑፋቸው አመላክተዋል፡፡ በጽሑፋቸው መግቢያ የክልሉን የእንስሳት ሀብት በአኅዛዊ መረጃዎች አዛምደው ያሳዩ ሲሆን፣ ‹‹ይህ ሀብት ትኩረት አግኝቶ ቢሠራበት እንደ ነዳጅ ሀብት የሚቆጠር ነው፤›› ብለውታል፡፡ የክልሉን የእንስሳት ሀብት ነጥለው ያቀረቡበት ዋናው ምክንያትም ከክልሉ ነዋሪዎች 50 በመቶው በእንስሳት ሀብት ላይ በተመሠረተ ኑሮ የሚተዳደሩ በመሆኑ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ ከአገሪቱ የእንስሳት ሀብት ውስጥ የአማራ ክልል ድርሻ 29 በመቶ ገደማ ስለመሆኑም አቶ መላኩ አጣቅሰዋል፡፡ ሆኖም ዘርፉን በአግባቡ መጠቀም መቻል ከክልል አልፎ አገራዊ ፋይዳው እንደሚጎላ ሲያነሱም፣ ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ እጥረት መፍትሔነቱን በማውሳት ነው፡፡

መንግሥት አብዝቶ ከሚታትርበት የጨርቃ ጨርቅና ሌላው አምራች ኢንዱስትሪ ባልተናነሰ የእንስሳት ሀብት ለኢኮኖሚው የጎላ ሚና እንደሚኖረውም ይቀሳሉ፡፡ ሲያብራሩም፣ ‹‹ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው 97 በመቶ ከውጭ በሚመጣ ግብዓት የሚንቀሳቀስ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የእንስሳት ሀብትን በመጠቀም የሚሠራ ኢንዱስትሪ ግን አብዛኛውን ግብዓት የሚያገኘው ከአገር ውስጥ በመሆኑ፣ ለግብዓት ብዙም የውጭ ምንዛሪ  ስለማያወጣ የተጣራ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማስገኘት ዘርፉ ያለው ዕድል ትልቅ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

የሥራ ዕድል በመፍጠርና በቀላሉ በርካቶችን በማሠልጠን በሰፊው ለማሰማራት የሚቻልበት ዘርፍ ከመሆኑ ባሻገር፣ ከዚህ በሚያያዝ ያስቀመጡት ነጥብ ለተለያዩ የልማት ሥራዎች በሚል ሰበብ ከቦታቸው የሚነሱ አርሶ አደሮች የሚከፈላቸውን ካሳ ከእንስሳት ሀብት ጋር በተያያዙ ሥራዎች ላይ እንዲያውሉት ማድረግ የሚቻልበት ዕድል ስለመኖሩም አቶ መላኩ ይናገራሉ፡፡ የሥጋና የእንስሳት ተዋጽኦ የወጪ ገበያን በተመለከተ ግብፅ፣ ሱዳን፣ ጂቡቲና እንደ ሳዑዲ ዓረብያ ያሉ አገሮች ከፍተኛ የገበያ መዳረሻ ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድልም ተነስቷል፡፡ ‹‹ግብፆች ከአውስትራሊያ ሥጋ ያስመጣሉ፡፡ ሳዑዲ ዓረብያ ከብራዚል ዶሮና እንቁላል ያስመጣሉ፡፡ እነዚህ አገሮች ምርቶቹን በቀላሉ እንዲያገኙ ለማስቻል እንደ ኢትዮጵያ ቅርባቸው የሚገኝ አገር የለም፡፡ ከፍተኛ ገበያ በቅርባችን ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡

እንደ ውጭ ገበያው ሁሉ በአገር ውስጥም ሰፊ የገበያ ዕድል እንዳለ ያስረዱት አቶ መላኩ፣ ከአገሪቱ ዕድገትና ከሕዝቧ ብዛት አንፃር በቂ የእንስሳት ተዋጽኦ ሊቀርብ ባለመቻሉ በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል የሚታየው ልዩነት እየጎላና እየተስፋፋ መምጣቱን ያወሳሉ፡፡ ለአብነትም የአንድ እንቁላል ዋጋ ወደ አምስት ብር ማሻቀቡ ተመልክቷል፡፡

በሌሎች አገሮች የእንቁላል ዋጋ ከኢትዮጵያ ባነሰ ዋጋ እንደሚሸጥ ጠቅሰዋል፡፡ እንቁላል ብቻ ሳይሆን፣ የሥጋም ሆነ የዶሮ ዋጋ ከሌሎች አገሮች አኳያ ሲታይ በኢትዮጵያ ውድ ነው፡፡ ምክንያቱም አቅርቦቱ እንደልብ ስለሌለ ነው፡፡ በዚህ ሳቢያም ትላልቅ ሆቴሎችና እንደ አየር መንገድ ያሉ ድንበር ዘለል የንግድ ተቋማት ዶሮና ሌሎችንም የግብርና ምርቶች ከውጭ  በገፍ ያስገባሉ፡፡ በመሆኑም በእንስሳት ሀብት ላይ ትኩረት መስጠት የተትረፈረፈ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማስገኘት ባይችል እንኳ፣ የውጭ ምንዛሪ ወጪን ለመቀነስ ያለው አቅም ትልቅ እንደሆነ በማመላከት የትኩረት ያለህ ብለዋል፡፡

የጥራት ተወዳዳሪነት

 እንዲህ ያሉ ያልተነኩ ጠቀሜታዎች ቢኖሩትም ዘርፈ ብዙ ችግሮችም የከበቡት ስለመሆኑ አቶ መላኩ በሰፊው አብራርተዋል፡፡ ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃን በሚያሟላ ደረጃ የእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦን ሳያቋርጡ በጥራትና በብዛት ማምረት አለመቻል አንደኛው ችግር ነው፡፡ የቁም እንስሳት የኮንትሮባንድ ንግድ መጧጧፍም አገሪቱን የውጭ ገቢ በማሳጣት ዘወትር የሚጠቀስ ነው፡፡ የእንስሳት በሽታም አሉታዊ ድርሻው የጎላ ነው፡፡ በ2009 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ በኮንትሮባንድ ንግድ ምክንያት ሶማሌላንድ 4.5 ሚሊዮን፣ ጂቡቲ 2.5 ሚሊዮን እንስሳትን ለውጭ ገበያ ማቅረባቸውን ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ምርምር ማዕከል ያወጣውን መረጃ አቶ መላኩ አጣቅሰዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአንፃሩ ባለፈው ዓመት ወደ ውጭ የላከቻቸው የቁም እንስሳት ብዛት 750 ሺሕ ይገመታሉ፡፡ ማዕከሉ በዘርፉ የሠለጠነ የሰው ኃይል በብዛት ማፍራት ላይ ፈጣን ዕርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ እያሳሰበ ይገኛል፡፡

የቁም እንስሳት ወጪ ንግድ መቀዛቀዝ

የቁም እንስሳት ላኪዎች ለሚያቀርቧቸው ትልልቅም ሆኑ አነስተኛ ቁመና ላላቸው ሰንጋዎች በእኩል ግምት 600 ዶላር በቅድሚያ ክፍያ እንዲያስገቡ በብሔራዊ ባንክ መጠየቃቸው ለእንስሳት የወጪ ንግድ እንቅፋት ከሚባሉት ውስጥ አንደኛው ነው፡፡

በባህር ዳርና ገንዳ ውኃ የኳራንቲን ጣቢያዎች፣ የተሟላ ማቆያ ሳይኖር የኳራንቲን ሠርተፍኬት የተሰጣቸው እንስሳት ብቻ የይለፍ ፈቃድ እንዲያገኙ የሚያስገድድ ጥብቅ መመርያ መቀመጡ፣ የቁርጥ ግብር የሚጠየቅበት አሠራር ኢፍትሐዊነቱ በመብዛቱ ተዋናዮቹ የሥራ ዘርፍ እንዲቀይሩ እያስገደዳቸው መምጣቱ ተገልጿል፡፡

ከሱዳን ጋር በሚደረገው የቁም እንስሳት ግብይት ወቅት ስለሚታየው ችግርም ተብራርቷል፡፡ የሱዳን መንግሥት በዶላር አዘዋዋሪዎች ላይ የሚያደርገው ጥብቅ ቁጥጥር፣ የሱዳን መገበያያ ገንዘብ የመግዛት አቅሙ መቀነሱ፣ የሁለትዮሽ የኳረንታይን ስምምነትን በሱዳን በኩል አለመከበሩ፣ በኮንትሮባድ የሚወጡት ጊደሮች፣ ጥጆችና ላሞች በወረደ ዋጋ ስለሚቀርቡ፣ ሕጋዊ የወጪ ንግዱ ላይ ተፅዕኖ መፍጠራቸው ተወስቷል፡፡

የሱዳን መንግሥት በሁለቱ አገሮች መካከል የተደረሰውን ስምምነት ባለማክበራቸው ምክንያት ባልታወቀ ሁኔታ ከኢትዮጵያ የሚሄዱትን እንስሳት እንዳይገቡ ተከልክሏል፡፡ በኮንትሮባንድ ይገባል የሚባለውን ጊደር፣ ጥጃና ላም በወረደ ዋጋ መግዛት የሚችሉበት ሰፊ ዕድል ስላቸው ሕጋዊው የእንስሳት የወጪ ንግድ መስመር እየተዳከመ መጥቷል፡፡ ወደ ሱዳን በሕገወጥ መንገድ የሚገባውን ከብት የሱዳን መንግሥት በኩል ክልከላ እንዲደረግበት አለመደረጉም ለችግሩ መባባስ ምክንያት ተደርጓል፡፡

ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የቁም እንስሳት ኮንትሮባንድ ንግድን ለመቆጣጠር ከዚህ ቀደም ያደርግ የነበረው ትብብር በመቆሙ ለችግሩ መባባስ ሌላው ሰበብ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በድንበር አካባቢ የሠፈሩ የሱዳን ወታደሮች ራሳቸውንም ሆነ አገራቸውን የሚጠቅም ነገር ግን ሕገወጥ የሆነ ተግባርን ከመከላከል መቦዘናቸው ማነቆ ከሆኑት የዘርፉ ችግሮች ውስጥ ሆኗል፡፡

በወረቀት የቀረው ፍኖተ ካርታ

ዘርፉን ለማበረታታት መንግሥት ሲሞክራቸው የነበሩ ጅምሮች ውጤት ሳያመጡ ቆይተዋል ያሉት አቶ መላኩ፣ ለ15 ዓመታት ዘርፉን ለመምራት ታስቦ የተዘጋጀው የእንስሳት ሀብት ፍኖተ ካርታ በጅምር የቀረ ውጥን ከመሆን እንዳላላፈ ያትታሉ፡፡ ከ2008 ዓ.ም. እስከ 2022 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ የእንስሳት ሀብትን በመጠቀም ከ7.6 ቢሊዮን ብር በላይ የሚጠይቁ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶች እንደሚካሄዱ፣ የአገሪቱን የሥጋ፣ የእንስሳት፣ የመኖ፣ የዶሮ፣ የወተትና የሌሎችም ውጤቶች በሚቀጥሉት 15 ዓመታት ውስጥ የት መድረስ እንዳለባቸው፣ ተለምዷዊ አመራረትን በአዳዲስ ዘይቤዎች በማሻሻል የአገሪቱን ሀብት ለመጠቀም ያለመ ነበር፡፡

በእንስሳት ሀብት ዘርፍ ምንም ኢንቨስትመንት ሳይካሄድ እስከ እ.ኤ.አ. 2028 ድረስ ቢቆይ፣ 42 በመቶ የሥጋ ወይም 1,213 ቶን የሥጋ አቅርቦት ችግር እንደሚፈጠር በፍኖተ ካርታው ተመልክቷል፡፡

እንዲህ ያሉ ሥጋቶችን ያመላከተው ፍኖተ ካርታው፣ በእንስሳ ሀብት ልማት ዘርፍ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ የሚያስፈልጉ ኢንቨስትመንቶችን ደልድሎ ነበር፡፡ ለወተት ሀብት 1.3 ቢሊዮን ብር፣ ለሥጋና ለወተት ሀብት ፕሮግራም 3.4 ቢሊዮን ብር፣ ለዶሮ ሀብት ልማት 2.4 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሚደረግ አመላክቷል፡፡

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የወተት ማቀነባበሪያዎች መገንባት በአምስት ዓመታት የወተት ማቀነባበሪያዎችን በማቋቋም በቀን አሥር ሺሕ ሊትር ወተት ማምረት እንደሚቻልም በዕቅዱ ተጽፏል፡፡ የወረቀት ነብር የሆነው ፍኖተ ካርታ፣ መልካም ዕድሎችን ከማመላከት በቀር መሬት አለመውረዱ የማቀድ እንጂ የማስፈጸም ብቃት እንደሌለ አመላካች የመንግሥት ችግር ሆኗል፡፡ አቶ መላኩ እንደጠቀሱት፣ የፌዴራል መንግሥቱ የ15 ዓመታት ፍኖተ ካርታ ሲያዘጋጅ፣ የአማራ ክልል በበኩሉ የአሥር ዓመት ፍኖተ ካርታ ለብቻው ማዘጋጀቱ የመናበብ ክፍተትንም የሚያሳይ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

የቆዳና ሌጦ ንግድ የቁልቁል ጉዞ

ከቆዳና ሌጦ ዋጋ መውደቅ ጋር ተያዞ አቶ መላኩ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ፣ መሠረታዊው ችግር የመሠረተ ልማት አለመሟላት ነው፡፡ በግዥ የተሰበሰበውን ጥሬ ቆዳና ሌጦ ወደሚፈልገው አካባቢ ወይም ፋብሪካዎች ለማድረስ ከባድ ፈተና እንደሚታይ አንስተዋል፡፡ በዚያም ላይ የጥራት ችግር ይታከልበታል፡፡ የቆዳና ሌጦ ዋጋ ለመውደቁ ሌላው ምክንያት የቆዳ ፋብሪካዎች በሚፈለገው መጠን የማይገዙ መሆናቸው ነው፡፡ በመሆኑም ቆዳ ነጋዴዎች ያለ አግባብ ቆዳ አከማችተው ለመጠበቅ ይገደዳሉ፡፡ አብዛኞቹም ተበላሽቶባቸው ለኪሳራ ሲዳረጉ ይታያሉ፡፡ ቆዳ አቅራቢዎቹ ፋብሪካዎቹ ስለማይገዟቸው ወደ ውጭ ለመላክ የተጣለው ከፍተኛ ታክስ እንዲሻሻልላቸው ጥያቄ እስከማቅረብ ደርሰዋል፡፡ ቆዳና ሌጦ እሴት ተጨምሮበት ወይም ወደ ምርት ተለውጦ ካልተላከ በቀር በጥሬ ቆዳና ሌጦ ደረጃ ወደ ውጭ እንዳይላክ ከፍተኛ ታክስ የተጣለበት ለአገር ውስጥ ፋብሪካዎች ፍጆታ እንዲቀርብ ታስቦ ነበር፡፡

የትኛውም የወጪ ንግድ ምርት ኤክሳይዝ፣ ቫትና ሌሎችም ታክሶች አይከፈልበትም፡፡ ቆዳና ሌጦን በጥሬው ወደ ውጭ መላክ ግን የ150 በመቶ ኤክስይዝ ታክስ ይጠየቅበታል፡፡ በዚህ ሳቢያ ቆዳ ነጋዴዎች ከሁለት ያጣ እየሆኑ እንደሚገኙ በየመድረኩ ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡

ድርቅና በሽታ

ድርቅ በመጣ ጊዜ የመጀመሪያ ተጠቂዎች እንስሳት መሆናቸው፣ የመኖ ዋጋ በየጊዜው መናር፣ በአገሪቱ ያሉት የመድኃኒት ፋብሪካዎች ሦስት ብቻ በመሆናቸው አብዛኛው መድኃኒት ከውጭ መምጣቱና በዋጋ መወደዱ ሌላው የዘርፉ ችግር ነው፡፡

የርቢ ላሞች፣ ጊደሮች ጥጆች መታረዳቸው፣ ከልማድ ባፈነገጠ መንገድ የሚወልዱ ጊደሮች፣ ጥጆችና ላሞች ለእርድ እየዋሉ በመምጣታቸው ዘራቸው እንዲጠፋ የሚያደርግ ተግባር እየተበራከተ መምጣቱም እንደ ባህር ከሰፋው የእንስሳት ሀብት ችግሮች ውስጥ ተነቅሷል፡፡ አቶ መላኩ እንዳሉት፣ ‹‹ላም የምትታረደው ከመከነች፣ ካረጀች፣ መውለድ ካቆመች በኋላ ነበር፡፡››

ችግሮቹ አያባሩም፡፡ አቶ መላኩም ይተነትናሉ፡፡ በ2004 ዓ.ም. የወጣው የሊዝ አዋጅም ለእንስሳት ሀብት ችግር የሆነበትን አግባብ አላጣም ነበር፡፡ ከብት ለማደለብ፣ ወተት ለማቀነባበርና ለሌሎችም ሥራዎች የሚሆን ቦታ የሚመራው በጊዜያዊ ሊዝ አሰጣጥ መሠረት ነው፡፡ ለእነዚህ ልማቶች ሥራዎች የሚፈቀደው ጊዜ ከ15 እስከ 20 ዓመታት ለሚቆይ እንጂ በቋሚ ሊዝ መሠረት ባለመሆኑ ባለሀብቶች የማይበረታቱበት ሆኗል፡፡

‹‹በዚህ መንገድ የሚሰጠውን ቦታ ማዘጋጃ ቤት ባስፈለገው ጊዜ ሊያስነሳህ ይችላል ማለት ነው፡፡›› ከዚህ በተጨማሪም ለእንስሳት ሀብት ልማት ተብሎ የተጠናና የተከለለ ቦታ አለመኖሩ ሌላው ችግር ነው፡፡ ነገር ግን ከታች እስከ ላይ ለኢንዱስትሪ ፓርክና ኢንዱስትሪ ፓርክ ይሆናል ተብሎ ቦታዎች እንዲከለሉ ሲደረግ፣ አንድም ቦታ ግን ከብት ለማደለብና ለመሳሰሉት አለመዘጋጀቱ ዘርፉን ጎድቶታል፡፡ አንዳንድ ቦታ በተወሰነ ደረጃ ቦታ ይዘጋጃል ቢባልም፣ ዘርፉን ለመለወጥ በሚያስችል በደረጃ ወይም ለትላልቅ ኢንቨስትመንቶች ቦታ የለም፡፡

ለእንስሳት ሀብት ተብሎ የተለየው መሬት አሰጣጥ ዘርፉን በእጅጉ መጉዳቱን ለማሳየት እንደ ምሳሌ ያነሱት በጊዜያዊ ሊዝ ተወስዶ ለሚሠራ ቢዝነስ ባንኮች ብድር የማይፈቅዱ መሆናቸውን ነው፡፡ በጊዜያዊ ቁሳቁሶች የታነፁ የእንስሳት ማቆያዎችና ሌሎችም መሠረተ ልማቶች ብሎም በውስጣቸው ያሉትን እንስሳት እንደ ዋስትና መያዝ ስለማይፈልጉ ብድር አይሰጡም በማለት የፋይናንስ ተቋማትን ተችተዋል፡፡

ከፋይናንስ ጋር የተያያዘው ሌላው ጉዳይ ለላኪዎች የውጭ ምንዛሪ ያስገኛሉ ተብሎ ስለሚታሰብ ለሚወሰዱት ብድር የሚጠየቁት ወለድ 8.5 በመቶ ገደማ ቢሆንም፣ የእንስሳት ሀብት በማልማት ለሚሠሩ ተበዳሪዎች ግን 17 በመቶ ወለድ እንዲከልፍሉ ይጠየቃሉ ያሉት አቶ መላኩ፣ ለእንስሳት ሀብት ፋይናንስ ስለማይቀርብ ልማቱ አዳጋች ሆኗል ብለዋል፡፡

በጥቅሉ የእንስሳት ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም ያላስቻለው ዘርፉን እንደ ኢንዱስትሪ ያለመመልከት ችግር ነው፡፡ ላም ራስዋን የቻለች ማሽን ነች፡፡ የእንስሳት ልማት ራሱን የቻለ ኢንዱስትሪ ነው ብሎ ከዚህ ጋር ተያይዞ ግንዛቤ ውስጥ ያልገባ ብለው ያመለከቱት ነጥብ፣ በአሁኑ ወቅት ለወተት ማቀነባሪያ፣ ለአግሮ ኢንዱስትሪ፣ ለሥጋ ማቀነባበሪያና ለመሳሰሉት ተብሎ ቦታ ይሰጣል፡፡ ለእነዚህ ማቀነባበሪያዎች ቦታ መስጠት መልካም ቢሆንም ላሞቹ በሌሉበት ወተት ማቀነባበሪያ መገንባት ትርጉም አይሰጥም ብለዋል፡፡ ሥጋ ሳይኖር ስለ ሥጋ ማቀነባበሪያ ይወራል ብለዋል፡፡ ስለዚህ በመጀመርያ ግብርናው ላይ ለሥጋ ማቀነባበሪያው የሚሆን የማደለቢያ ወይም ለወተት ማቀነባሪያው ስላለ ማሰብ ካልተቻለ አስቸጋሪ ነው፡፡

የመፍትሔ ሐሳቦችና ተወያዮች 

ይህ ጥናታዊ ጽሑፍ ሲቀርብ በተወያይነት በዘርፉ የተሰማሩ የክልል ነጋዴዎች ተገኝተዋል፡፡ የክልሉ ከፍተኛ ኃላፊዎችም የተገኙበት ሲሆን፣ አቶ መላኩ እንደ መፍትሔ ያስቀመጧቸው ሐሳቦች ነበሩ፡፡ አንዱ የ15 ዓመቱ ፍኖተ ካርታ በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውል ማድረግ፣ ለእንስሳት ሀብት ልማት በሊዝ የሚሰጠው ቦታን በሚላከት የተደነገገው አዋጅ እንዲሻሻል ማድረግ፣ በቆዳና ሌጦ የወጪ ንግድ ላይ የተጣለው ታክስ እንዲነሳና የመሳሰሉትን አንስተዋል፡፡

ከመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ግብት መፈጸሚያ ጣቢያዎች ጀምሮ፣ በእንስሳት ማቆያዎች፣ በሕክምና መስጫዎች፣ በኤክስፖርት ቄራዎችና በሌሎችም የአቅርቦት ሰንሰለቶችም ውስጥ እንስሳቱ በሚያልፉባቸው ሒደቶች ውስጥ ከየት ተነስተው የት እንደደረሱ ዱካቸውን የሚከታተለው ይህ ሥርዓት፣ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸው እንስሳት የጤንነት ደረጃዎች ስለማሟላታቸው፣ የሚላከው የሥጋ ምርትም ተገቢውን የጥራትና የጤንነት መሥፈርቶች ስለማሟላቱ ለማረጋገጥ የሚደረጉ መሠረተ ልማቶችን መገንባትም ተጠቅሷል፡፡

ከክልሉ የተሰጠው በዘርፉ የተሰማሩ ነጋዴዎች የተለያዩ አስተያየቶች ሰጥተዋል፡፡ የመኖ፣ የዝርያና የጥራት ችግር አለ፡፡ የገበያ ችግር መኖሩን ሁሉ ጠቁመዋል፡፡

አንድ እንቁላል 2.70 ብር የሚገዛን አጣን ያሉም አሉ፡፡ በዕለቱ ውይይት የታደሙ የዓለም የእርሻና ምግብ ድርጅት ተወካይ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ ለሰብል የተሰጠው ትኩረት ለእንስሳት ሀብትም አለመሰጠቱ ከዘርፉ መሠረታዊ ችግሮች ውስጥ የሚካተት ነው ብለዋል፡፡ ከዚህም ሌላ በዘርፉ የተደረጉ በርካታ የምርምር ሥራዎች ቢኖርም ይህንን መጠቀም አለመቻል ራሱ አንድ ክፍተት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዕለቱ የተካሄደውን ውይይት የመሩት የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ በውይይቱ በዘርፉ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ ይቻል ዘንድ ጉዳዩን ለክልሉ ካቢኔ እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች