Friday, March 1, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የገና በዓል ታሪካዊ  አመጣጥ

በጳውሎስ ካሱ

የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች በየዓመቱ በደማቅ (በተለየ የአሜሪካና አውሮፓ) ሁኔታ ከሚያከብሯቸው በዓላት አንዱ ገና ነው፡፡ የገና በዓል አከባበር በየአገሩ መጠነኛ  ልዩነት ቢኖረውም በየዓመቱ አዳዲስ  መሻሻሎች እየተደረገበት ደማቅነቱ እንደቀጠለ መጥቷል፡፡ ይህንኑ ተከትሎም የበዓሉን አጀማመርና ታሪክ ለማግኘት ብዙ ጥናቶች ተደርገዋል፡፡ የጥናቶቹ ግኝትም ብዙዎቹን እርግጥ ይህ በዓል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነውን? ብለው እንዲጠይቁ ሲያደርግ ብዙዎቹን ግን በዓሉን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ለማድረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በመጥቀስ ትክክለኛነቱን ለማሳየት ይሞክራሉ፡፡ የተቀሩት ደግሞ  ትኩረታቸውን ከበዓሉ በሚገኘው ደስታ ላይ ብቻ በማድረግ የአያገባኝም አቋም ወሰደዋል፡፡  እርግጥ የገና በዓል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው? መልሱ በሚከተሉት የጥናት ግኝቶች ውስጥ ይገኛል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደው በእርግጥ በፈረንጆቹ ዲሴምበር 25 ወይም በኢትዮጵያዊያን ታኅሣሥ 29 ነውን? አዲስ ኪዳን ኢየሱሰ ክርስቶስ የተወለደበትን ቀን በትክክል አይናገርም፡፡ ከወንጌላቱ ሁሉ መጀመርያ እንደተጻፈ የሚታመነው የማርቆስ ወንጌል ከክርስቶስ ልደት በኋላ 65 .ም. የተጻፈ ሲሆን፣ ታሪኩን የሚጀምረው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ነው፡፡ ይህም የሚጠቁመው የመጀመርያዎቹ ክርስቲያኖች የክርስቶስን የልደት ቀን እንደማያውቁ ለማወቅም ፍላጎት እንዳልነበራቸው ነው፡፡ ይህም አንድ ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም፤ ክርስቶስ በዲሴምበር 25 ወይም ታኅሣሥ 29 ተወለደ ብሎ የጻፈው ማነው? እንዴትስ አወቀ? ታሪክ እንደሚናገረው ጌታ ተወለደ ተብሎ የሚታመንበትን ዓመት የወሰነው ዲዮኒሲየስ ኤግዚገስ (Dionysisus Exiguus) የተባለ የካቶሊክ መነኩሴ ነው፡፡ ክርስቶስ የተወለደበትን ዓመት ለመወሰን የተጠቀመው ቀመርም የሚከተለውን ይመስላል፡ 

  • በቅድመ ክርስትና ሮም ዓመታት የሚቆጠሩት ከአበ አርበ ኮንዲታ (ab Urbe Condita) ማለትም ሮም ከተመሠረተችበት ቀን ጀምሮ ነው፤ ይህም AUC ይባላል እንደኛ .ም. ማለት ነው፡፡ ስለዚህ 1 AUC ሮም የተመሠረተችበትን ቀን ይወክላል፡፡ 5 AUC የሮምን ግዛት አምስተ ዓመት ይወክላል ወዘተ.
  • ዲዮኒሲየስ የሮማው ቄሳር አውግስጦስ 43 ዓመታት ከገዛ በኋላ በቄሳር ጢባርዩስ ተተካ የሚለውን ታሪክ አምኖ በመቀበል ቀመሩን በዚህ ላይ መሥርቷል፡፡
  • በሉቃስ ውንጌል ምዕራፍ 3 ቁጥር 1 እና 2 ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ 30 ዓመት ሲሞላው የጢባርዩስ 15 የንግሥ ዓመት እንደሆነ ተመልክቷል፡፡
  • ኢየሱስ ክርስቶስ በጢባርዮስ ዘመነ መንግሥት 30 ዓመቱ ከሆነ በቄሳር አውግስጦስ አገዛዝ ሥር 15 ዓመት ኖሯል ማለት ነው (ይህም የኢየሱስን ልደት በአውግስጦስ 28 የሥልጣን ዓመት ላይ ያደረገዋል)፡፡
  • አውግስጦስ የነገሠው 727 AUC ነው፡፡ እዚህ ላይ ተመሥርቶ ዲዮኒሲየስ የክርስቶስ ልደት 754 AUC ነው ብሎ ደመደመ፡፡ 

መጽሐፍ ቅዱስ በሉቃስ 15 ላይ ክርስቶስ የተወለደው በሄሮድስ ዘመነ መንግሥት እንደሆነ ይናገራል፡፡ ታሪክ እንደሚናገረው ደግሞ ሄርድስ የሞተው 750

AUC ነው፡፡ ይህም ዲዮኒሲየስ ክርስቶስ ተወለደ ካለበት አራት ዓመታት ቀደም ብሎ ማለት ነው፡፡ ዩሴፍ ፊትዝመየር የተባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮፌሰር ይህ የዲዮኒሲየስ ቀመር የተሳሳተ እንደሆነና በዚሁ ቀመር ላይ የተመሠረተው ክርስቶስ የተወለደው 1 .ም. (የክርስቲያኖች ዓመት መጀመርያ ተብሎ ከሚታመንበት ዓመት) ነው የሚለው እምነትም የተሳሳተ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ አንደ ፕሮፌሰሩ ጥናት ክርስቶስ የተወለደው ሰፕቴምበር (መስከረም) 11 ክርስቶስ ተወለደ ተብሎ ከሚታመንበት ዓመት 3 ዓመት ቀደም ብሎ ነው፡፡ በማን እንደተጻፈ የማይታወቀውና Depaschg Computus  በመባል የሚታወቅና ከክርስቶስ ልደት በኋላ 243 .ም. በሰሜን አፍሪካ እንደተጻፈ የሚታመን ጽሑፍ ክርስቶስ በፈረንጆቹ ማርች 28 እንደተወለደ ይናገራል፡፡ ከሊመንት የተባለ የአሌክሳንደሪያ ሊቀ ጳጳስ ደግሞ 215 .ም. በጻፈው ጽሑፍ ውስጥ  ክርስቶስ ኖቨምበር (ኅዳር) 18 አንደተወለደ እንደሚያምን ገልጿል፡፡ ከተደረጉ ጥናቶች አንዱም እንኳን ክርስቶስ ዲሴምበር 25 ወይም ታኅሣሥ 29 ተወለደ የሚል የለም፡፡ ይህም እነዚህ ቀናት የክርስቶስ ልደት ነው የሚለው እምነት ከየት መጣ የሚለውን ጥያቄ ያስነሳሉ፡፡ የገና በዓል፣ የገና ዛፍና የገና አባት ወዘተ. አንድ ላይ የነበሩና በአንድ ጊዜ የመጡ ጉዳዮች ሳይሆኑ በየዘመናቱ የተጨመሩ ነገሮች ናቸው፡፡

የገና በዓል አመጣጥ

ድሮ ሰዎች ፀሐይ አምላክ ናት ብለው ያምኑና ያመልኳት ነበር፡፡ ክረምት የሚመጣውም ፀሐይ ስትታመም ወይም ስትደክም ነው ብለው ያምኑ ነበር፡፡ በምድራችን በሰሜን ንፍቀ ክበብ አካባቢ አጭር የሚባለው ቀን የሚውለው እ.ኤ.አ. በዲሴምበር (ታኅሣሥ) 21 ወይም 22 ነው፡፡ ይህንንም ጊዜ የክረምት ሶልስቲስ ይሉታል (ፀሐይ የድካሟ የመጨረሻ ደረጃ ላይ የምትደርስበት ማለት ነው)፡፡ ፀሐይ ከመጨረሻ ድካሟ በኋላ ወደ ቀድሞ ጥንካሬዋ ስለምትመለስ ይህ ወቅት በልዩ ሁኔታ ይከበር ነበር፡፡ ይህ በዓል በተለያዩ አገሮች በተለያየ ሁኔታ ይከበር ነበር፡፡ ለምሳሌ ግብፃውያን ራ ብለው የሚጠሩት ፀሐይን እንደ ኮፍያ ያጠለቀ አምላካቸውን የሚያስቡበትና የሚያከብሩበት በዓል ሲሆን፣ የጥንት ሮማውያን ደግሞ ሳተርን የሚሉትን የእርሻ አምላክ ለማክበር በዓሉን ሳቱርናሊያ (Saturnalia) ብለው ያከብሩ ነበር፡፡ ቀጥሎ የሚመጣውን አረንጓዴነት በማሰብም ቤተ መቅደሳቸውንና ቤታቸውን በአረንጓዴ ዕፀዋት ያስጌጡ ነበር፡፡

ለዛሬው ገና ዋና መሠረቱ የሮማ አረማውያን ሳቱርናልያ የሚባለውና ከዲሴምበር (ታኅሣሥ) 17 እስከ 25 የሚቆይው የአንድ ሳምንት ሕግ አልባ ክብረ በዓል ነው፡፡ በዚህ ሳምንት የሮማ ፍርድ ቤቶች በሙሉ ይዘጉ ነበር፡፡ የሮማ ሕግም በዚህ ሳምንት ውስጥ ንብረት ያጠፋም ሆነ ሰው ያቆሰለ እንደማይቀጣ ይደነግጋል፡፡ ሳምንት የሚቆየው በዓል የሚጀምረው  የሮማ ባለሥልጣኖች የሮማውያን ጠላት ብለው የሚሰይሙትና የመጥፎ መንግሥት ጌታን የሚወክለውን ሰው/ሰዎች ከመረጡ በኋላ ነው፡፡ እነዚህ የሚመረጡት ሰዎች ምንም ጥፋት ያላጠፉ ንፁኃን ሰዎች ነበሩ፡፡ እያንዳንዱ የሮማ ማኅበረሰብ የየራሱን የሮማውያን ጠላት ይመርጥና ሳምንቱን ሙሉ እነዚህን ንፁኃን ሰዎች ከመጠን በላይ እንዲበሉ፣ እንዲጠጡና እንዲዳሩ ያስገድዷቸዋል፡፡ ሮማውያኑም በዓሉን  የሚያከብሩት ከመጠን በላይ በመብላት፣ በመጠጣት፣ በመዳራትና በመዋጋት ነበር፡፡ በበዓሉ የመጨረሻ ቀንም ማለትም ዛሬ የክርስቶስ የልደት ቀን ነው ተብሎ በሚታመንበት ዲሴምበር 25 እነዚህን ሳምንቱን ሙሉ የተሰቃዩ ንፁኃን ወንዶችና ሴቶች በመግደል ሮማውያን  ጠላቶቻቸውን እንዳጠፉ በመቁጠር ይኩራሩ ነበር፡፡ 

ሉሲያን (Lucian) የተባለ የግሪክ ታሪክ ጸሐፊና ባለቅኔ በጊዜው የሳቱርናልያ በዓል በግሪክ እንዴት ይከበር እንደነበር ሲጽፍ እንደ ሮማውያኑ ሰዎችን ከመሰዋት በተጨማሪ ከቅጥ ያለፈ መጠጥ ወይም ስካር፣ እርቃን ሆኖ ከቤት ቤት እየሄዱ መዝፈን (እንደ ኢትዮጵያውያን እንቁጣጣሽና ሆያ ሆዬ) ሴቶችን መድፈርና ሌሎች የልቅ ወሲብ ድርጊቶችና በሰው ቅርፅ የተሠሩ ብስኩቶችን መብላት (እነዚህ ብስኩቶች አሁንም በገና ወቅት በእንግሊዝና በጀርመን ይዘጋጃሉ) የበዓሉ ዋና ገጽታዎች እንደነበሩ ገልጿል፡፡

 አራተኛው ክፍለ ዘመን የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እነዚህን አረማውያን አባል ለማድረግ በማሰብ ክርስትናን ከተቀበሉ በኋላም ሳቱርናልያን ማክበር መቀጠል እንደሚችሉ በማሳመን የክርስትናን እምነት እንዲቀበሉና ሳቱርናልያና ወደ ቤተ ክርስቲያን ይዘው እንዲገቡ ፈቀዱላቸው፡፡ ሆኖም ሳቱርናልያንና ክርስትናን የሚያገናኛቸው አንድም ነገር አልነበረም፡፡ ይህን ችግር ለመፍታትና ሳቱርናልያን ክርስቲያናዊ  ለማስመሰል የወቅቱ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሳቱርናልያን የመዝጊያ ቀን (ዲሴምበር 25) የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ቀን ብለው  በመሰየም በዓሉ እንዲቀጥል አደረጉ፡፡ ሳቱርናልያም ክሪስማሰ (ገና) ተባለ፡፡ የሚያሳዝነው እነዚህ የስመ ክርስቲያን መሪዎች በበዓሉ ይዘት ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ ለማድረግ አለመቻላቸው ነው፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ይህ ‹‹የክርስቶስ ልደት ቀን›› የሚከበረው ልክ እንደ ሳቱርናልያ በመጠጣት፣ በመዳራትና፣ በራቁት የጎዳና ላይ ዳንስ (የክሪስማሰ ካሮል መሠረቱ ይኼ ነው) ነበር፡፡

ኢንከሪዝ ማዘር የተባሉ አሜሪካዊ 1687 ዓ.ም. ባሳተሙት ጽሑፍቸው ላይ ‹‹ዲሴምበር 25 የክርስቶስ የልደት ቀን ነው ብለው ማክበር የጀመሩት ክርስቲያኖች ቀኑን የሚያከብሩት ክርስቶስ በዚህ ቀን ተወልዷል በሚል እምነት ላይ ተመሥርተው አልነበረም፡፡ የአረማውያኑ ሳቱርናልያ የሚከበረው በተመሳሳይ ወቅት ስለነበረ በዓሉ ወደ ቤተ ክርስቲያን አንዲገባ ፍቃደኛ ስለሆኑ ብቻ ነበር፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡ በዚሁ ግልጽ የሆነ አረማዊ መሠረቱ ምክንያት ቀደም ባሉት ጊዜያት በአንዳንድ አክራሪዎች ዘንድ የገናን በዓል ማክበር በሕግ የተከለከለ ነበር፡፡

አንዳንድ አፀያፊ የሳቱርናልያ አከባበር ገጽታዎች በጥንቷ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አማካይነት 1466 ዓ.ም. አንደ አዲስ አንዲከበሩና ዕውቅና እንዲያገኙ እንደተሞከረ አንዳንድ የታሪክ ምንጮች ይጠቅሳሉ፡፡ ለምሳሌ 1466 ዓ.ም. የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ ሁለተኛው ጳውሎስ የሮማን ዜጎች  ለማስደሰት ሲል አይሁዶች እርቃናቸውን በጎዳና እንዲሮጡ ማድረግ እንደጀመረ የታሪክ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ሩጫውን ከባድ  ለማድረግና ሕዝብን የበለጠ ለማሳቅ ሲባልም ሯጮቹ ከመጠን በላይ እንዲመገቡ ይደረግ እንደነበር እነዚሁ ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡ ጳጳሱም  ከሕዝቡ ጋር ተቀምጦ በሩጫው ይስቅ እንደነበር ተዘግቧል፡፡ ዛሬ ‹‹የክርስቶስ ልደት›› እየተባለ የሚከበረው በዓል መሠረቱ ይኼ ነው፡፡ 

የገና ዛፍ፣ የገና ስጦታዎች አመጣጥና የገና አባት

ልክ እንደ በዓሉ ሁሉ የገና ዛፍ፣ ስጦታና የገና አባት መሠረታቸው  አረማውያን ናቸው፡፡

የገና ዛፍ

ከሳቱርናልያ ተከታዮች ጋር በገፍ ወደ ቤተ ክርስቲያን ከገቡትና ልማዳቸው ክርስቲያናዊ ከተደረገ አረማውያን መካከል የአሸይራ (Asheira) አምላኪዎች ይገኙበታል፡፡ የዛፎች አምልኮ የቆየ ነው፡፡ በቅድመ ክርስቶስ ዘመን አህዛብ በተለይ ትላልቅና ዓመቱን ሙሉ አረንጓዴ እንደሆኑ ለሚቆዩ ዕፀዋት ልዩ ትርጉም ይሰጧቸውና ያመልኳቸው ነበር፡፡ እርኩሳት መናፍስትን፣ አስማተኞችን፣ በሸታን የመሳሰሉትን ይከላከሉ ብለው ስለሚያምኑ ቅርንጫፎቻቸውን እየቆረጡ በበራቸው ላይ ወይም በቤታቸው ውስጥ ይሰቅሉ ነበር፡፡ አይሸራውያን አንደ ብዙ  አረማውያን በደን ውስጥ ያሉ ትላልቅ ዛፎችን ያመልኩ የነበረ ሲሆን ምሳሌዎቻቸውን (ቅርንጫፎቻቸውን) ወደ ቤታቸው በማምጣት ያስጌጧቸው እንደነበረና አነዚህም ቅርጫፎች እርኩሳት መናፍስትን ይከላከላሉ የሚል እምነት እንደነበራቸው ታሪክ ይጠቁማል፡፡ ልክ  እንደ ሳቱርናልያ  ልማዶች  ይህም ልማድ የክርስትና ስም ተሰጥቶት ቤተ ክርስቲያን ገባ፡፡ 

የገና ስጦታዎች አመጣጥ

በቅድመ ክርስትና ሮም ቄሳሮች በሳቱርናልያ በዓል  ወቅት የተናቁ ተገዥዎቻቸው  መስዋትና ስጦታ እንዲያመጡላቸው ያስገድዱ ነበር፡፡ በኋላ ላይም ይህ ግዴታ በሕዝቡ መካከል ተሠራጭቶ እንደ መልካም ልማድ ተቀባይነት ስላገኘ በሳቱርናልያ በዓል ወቅት ሕዝቡ ስጦታ መለዋወጥ ጀመረ፡፡ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንም ይህንን ልማድ ቅዱስ ኒኮላስ ይሰጥ ነበር ከሚባለው አፈ ታሪካዊ ስጦታ ጋር በማያያዝ ክርስቲያናዊ አደረጋቸው፡፡

የገና አባት

19 ክፍለ ዘመን በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ‹‹ቅዱስ›› የሚል ማዕረግ የተሰጠው 270 .ም. በቱርክ እንደተወለደ በቱርክ ሊቀጳጳስ እንደነበረና ታኅሣሥ 6፣ 345 .. እንደ ሞተ የሚነገርለት ኒኮላስ የተባለ ሰው አለ፡፡ ኒኮላስ 325 .ም. በተደረገው የኒቅያ ጉባዔ ላይ ከተገኙ ሊቀጳጳሶች አንዱ አንደ ነበር የታሪክ ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡ 1087 .ም. ለኒኮላስ ከፍተኛ  አክብሮት የነበራቸው መርከበኞች አጽሙን ከቱርክ ወደ ጣሊያን ወስደው ቤሪ በተባለች ስፍራ በሚገኝ መቅደስ ውስጥ አስቀመጡት፡፡ ቀደም ብላ በዚህ መቅደስ ውስጥ የነበረችው ለሕፃናት ስጦታ ትሰጣለች የሚል ታሪክ ያላት ኢፊፋበያ የተባለችው የአረማውያን አማልክትም ከመቅደሱ ተወግዳ በኒኮላስ ተተካች፡፡ ኒኮላስም መቅደሷንም ታሪኳንም ወረሰ፤ ቦታውም የኒኮላስ አምላኪዎች  መሀከል ሆነ፡፡ የኒኮላስ ተከታ በየዓመቱ ታኅሣሥ 6 ሲያከብሩ ስጦታ ይለዋጡ ነበር፡፡ የኒኮላስ አምልኮ በሰሜን እየተስፋፋ በጀርመን አረማውያን ተቀባይነት አገኘ፡፡ እነዚህ የጀርመን አረማውያን ዋደን የተባለ  ነጭ ፂም ያለውና በዓመት አንድ ጊዜ በሰማይ ውስጥ በፈረስ እንደሚጋልብ የሚነገርለት አምላክ ያመልኩ ነበር፡፡ ለዚህ አምላክ የተፈጠረው  ታሪክ ሁሉ ለኒኮላስ ተሰጠ፡፡ ቀደም ብላ እንዳደረገችው አረማውያኑን ለመሳብ ብላ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የኒኮላስን አምላኪዎች ተቀብላ ታሪኩንም ውነት ነው ብላ በማስተማር ስጦታ ከታኅሣሥ 6 ይልቅ በታኅሣሥ 25 እንዲሆን ማስተማር ጀመረች፡፡ የስፓኝ ስሙ ሳንታ ክላውስ (Santa Claus) የበለጠ ዕውቀና እያገኘ መጣ፡፡ አዳዲስ የፈጠራ ታሪኮች ተጨመሩለት፡፡ 1931 ዓ.ም. የኮካ ኮላ ኩባንያ በሠራው ማስታወቂያ ላይም ሳንታ ቀይ ፀጉራም ልብስ የለበሰ ነጭ ፂም ያለው ወፍራም ሰውዬ ሆኖ ቀረበ፡፡ ይህ ሳንታም ሊቀ ጳጳስ፣ የአረማውያን አምላክና የንግድ ማስታወቂያ ሆኖ እስከ ዛሬ ቀጥሏል፡፡ 

የገና በዓል ብዙ ደጋፊዎች ያሉት በዓል ነው፡፡ ደጋፊዎች በሦስት ይከፈላሉ፡፡ የመጀመርያዎቹ በዓሉ መጸሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው በዓል ነው ብለው የሚያምኑ ናቸው (ከልባቸውም ይሁን ከአፋቸው)፡፡ ሁለተኛዎቹ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ባይኖረውም የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ እውነት እስከሆነ ድረስ ልደቱን ማክበሩ ክፋት የለውም ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡ ሦስተኛው አካል የሚከራከረው በዓሉ ለንግድና ቤተሰቦችን/ሰዎችን በማቀራረብ  ካለው ጠቀሜታ አኳያ ነው፡፡ 

ይህንን የባዕድ አምልኮ ክርስቲያናዊ ቀለም እየቀቡ መቀጠል ትክክል ነውን? አንድ ታሪክ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ስለተለጠፈበት ብቻ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሊሆን ይችላልን? መልሱ አይደለም ነው፡፡ ክርስቲያኖች የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ወደዚህ ዓለም መምጣት እያሰቡ በማንኛውም ቀንና ወር እግዚአብሔርን ማመስገን ይገባናል አንጂ የጌታን ልደት ከማንኛውም ቀንና ወር ጋር ማያያዝና ማክበር እንዲሁም የአረማውያንን ልማድ ክርስቲያናዊ ቀለም ቀብቶ መለማመድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም፡፡ ይህንንም ማድረግ እግዚአብሔርን  ማስቆጣትና ማሳዘን ብቻ ሳይሆን ራስን አግዚአብሔር ለሰው ልጅ ካዘጋጀው የክብር ሕይወት ማግለል ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው   [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles