Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልገና እና ትውፊቱ

ገና እና ትውፊቱ

ቀን:

በየዓመቱ ከሚከበሩት በዓላት አንዱ የእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ የገና (ልደት) በዓል ነው፡፡ የዘንድሮው በዓል የ2011ኛው ዓመቱ ነው፡፡ ሰኞ፣ ታኅሣሥ 29 ቀን 2011 .. የገና በዓል በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ግብፅ እና በመካከለኛው ምሥራቅና በምሥራቅ አውሮፓ ባሉት ኦርቶዶክሳውያን አገሮች በነሩሲያም ይከበራል፡፡ 

የጁሊያን ቀመር የሚከተሉት ምሥራቅ ኦርቶዶክሳውያን ገናን ሲያከብሩ ዕለቱን ዲሴምበር 25፣ 2018 ብለው ሲሆን፤ ኢትዮጵያና ኤርትራ ታኅሣሥ 29 ግብፅ (ኮፕቲክ) ደግሞ ኪያክ 29 ብለው ያከብሩታል፡፡ 

16ኛው ምዕት ዓመት ከጁሊያን ካላንደር ተከልሶ የተዘጋጀውን የግሪጎሪያን ካላንደር የተከተሉት ምዕራባውያን ደግሞ በእነርሱ ዲሴምበር 25 ባሉት ከ13 ቀናት በፊት ታኅሣሥ 16 ቀን አክብረውታል፡፡ በዓሉ አንድ ሆኖ የቀኑ ልዩነት የተፈጠረው መሬት ፀሐይን ለመዞር የሚፈጅባት ጊዜ በምሥራቆች 365 ቀን 6 ሰዓት ነው በማለታቸው ምዕራቦች ደግሞ 365 ቀን 5 ሰዓት 48 ደቂቃ 46 ሰከንድ ነው በሚል ልዩነት በመፈጠሩ ነው፡፡ 

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ዮም ተወልደ ቤዛ ኵሉ ዓለም (የዓለም ቤዛ ዛሬ ተወለደ) እያሉ ኢትዮጵያውያኑ በደማቅ ሥነ ሥርዓት በዓሉን እያከበሩ ነው፡፡ የዛሬውን በዓለ ልደት ለማክበር በመንፈቀ ኅዳር የጀመሩትን ጾም 44 ቀኖች አሳልፈዋል፡፡ 

ያለም ሁሉ መድኃኒት 
ተወለደ በበረት፣ 
እያሞቁት እንስሳት 
ብርሃን ሆነ በዚያች ሌት 
ሲዋዥቡ መላዕክት 
ደስ አሰኙ ለኖሩት፤ የሚለው ኅብረ ዝማሬ የበዓሉ መገለጫ ነው፡፡

በሁሉም የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት፣ ሌሊቱ ማሕሌት ተቁሞ ቅዳሴ እንዳበቃ፣ የበዓል ፍፃሜ ቢሆንም፣ በተለይ በላሊበላ ግን በተጨማሪ በዕለቱ ጧት ላይ ቤዛ ኵሉ የተሰኘው ክብረ በዓል ከአለት ከተፈለፈሉት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በአንዱ በቤተ ማርያም ካህናቱጋራና መሬት ላይ ሆነው ያከብሩታል፡፡ 

ምዕመናን ባለፈ የአገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ትኩረት የሚስብ ዓቢይ ትርዒት ነው፡፡ የላሊበላው ቤዛ ኵሉ አከባበር ተምሳሌታዊ ነው፡፡ ማሜ ጋራ ላይ ያሉት የመላዕክት ምሳሌ፣ መሬት ላይ ያሉት ደግሞ የእረኞች ምሳሌ ሆነው ዝማሬውን በሆታና በዕልልታ ያጅቡታል፡፡ የክርስቶስ ኢየሱስን መወለድ መጀመርያ ያወቁ እረኞች በመሆናቸው በአገር ቤት ትውፊቱ እየተነገራቸው የሚያድጉት እረኞች በተለየ ሁኔታ ያከብሩታል፡፡ 

የበዓለ ልደት ማሕሌቱ በካህናት በሚቀጥልበት ሌሊት ሊቃውንቱ ልደቱን አስመልክተው በየአጥቢያው በቅኔ ማሕሌት ዙርያ ቅኔውን ይዘርፉታል፡፡ አንዱ፣ ከሰባት አሠርታት በፊት ሊቁ አለቃ ለማ ኃይሉ ወልደ ታሪክ በግዕዝ የተቀኙትና ወደ አማርኛ የተመለሰው ይሄ ነበር፡፡

ፍጡራን ሁሉ፣ ሐሳባቸውን በፈጣሪያቸው ይጥሉ ዘንድ በሕገ ልቡና ተነግሯል፡፡ 

ዛሬ ከልማዱ ሥራ ፈጣሪ አረፈ፡፡ የተረፈ የልጁን ድህነት መዋረድ በጎል (በረት) ሲያይ 
የመንግሥት ዙፋን እንዳይሻ የወርቅ ልብስ እንዳይሻ አሳቡን ከድንግል ማርያም ላይ ጣለ፡፡

የገና ዛፍ

አብዛኛውን ጊዜ ሲነገር እንደሚሰማው የገና ዛፍ ልማድ ባዕድና ምዕራባዊ ምንጭ እንደሆነ ተደርጎ ነው፡፡ ነገር ግን በብሪቲሽ ሙዚየም ውስጥ የሚገኘው 13ኛው ምዕት ዓመት ብራና (መጽሐፍ) እንደሚያስረዳው፣ 512 .. የነበረው የሶሪያ ንጉሠ ነገሥት አናስታሲዮስ ቀዳማዊ በሰሜናዊቷ ሶሪያ በቱር አብዲ ከተማ፣ የቅዱስ ገብርኤል ገዳምን ባሠራበት ጊዜ ካቀረባቸው መባዎች አንዱ ዛፍ ነበር፡፡

‹‹. . . ሁለት ትልልቅ ዛፎች በተዋበው የመቅደሱ ግራና ቀኝ እንዲቆሙ አደረገ፡፡ በቅርንጫፎቹም ላይ የብርሃን ምልክቶች ተደረጉ፡፡ እንያንዳንዱ ዛፍ አንድ መቶ ሰማንያ ትናንሽ አምፑሎችና ሃምሳ የብር ጌጦች ከላይ እስከታች ተጌጡ፡፡ መስቀሎች፣ ወርቅ፣ ብር ወይም መዳብ፣ እንዲሁም ቀይ እንቁላሎች፣ እንስሳት፣ አዕዋፋት፣ ደወል. . . የዛፉ አካል ሆኑ፡፡››

በግሪክ የተሰሎንቄ አሪስቶትል ዩኒቨርሲቲ የቢዛንታይን አርኪዮሎጂ ፕሮፌሰር የነበሩት ኮንስታንቲን ካሎኪርስ፣ Sacred Trees and the Eastern Origin of the Christmas Tree በተሰኘው ጥናታቸው እንዳሰናዱት፣ በክርስቲያን ቲኦሎጊያና አምልኮ ውስጥ ዛፍ የሚያመለክተው፣ የገነትን ዛፍ (መልካምንና ክፉውን የሚለይ የዕውቀት ዛፍ) ነው፡፡ የተጌጡ ዛፎች (ሞዛይክ ዛፎች) በቀዳሚው ዘመን ኒቆፖሊስ በሚገኘው ቅዱስ ድሜጥሮስ ገዳም፣ በኤጲረስና በተለያዩ ቦታዎችም እንዲሁ ነበሩ፡፡

በካታኮምቡ በሕይወት ዛፍ (ዕፀ ሕይወት) የተመሰለው ክርስቶስ ነው፡፡ ፈኒክስም (የወፍ ዓይነት) በዘላለማዊነት ተመስላለች፡፡ የወይራ ዛፍም የብሉይና ሐዲስ ኪዳኖች ተምሳሌት ሆኗል፡፡

በመጀመርያዎቹ የክርስትና አራት ምዕት ዓመታት፣ የገና በዓል ከጥምቀት ጋር ጃንዋሪ 6 ቀን ይከበር ነበር፡፡ በግሪክ የተለያዩ አካባቢዎች በዓሉ ሲከበር በአብያተ ክርስቲያናቱ መካከለኛ ቦታ በብርቱካን የተጌጡ ሁለት ዛፎችን ያቆሙ ነበር፡፡ ሜትሮፖሊታን ሂሮቴዮስ ቫላኮስ The Feasts of the Lord: An Introduction to the 12 Feasts and Orthodox Christology በሚለው መጽሐፋቸውም እንዲህ አመሥጥረውታል፡- የገና ዛፍ፣ የዕውቀት ዛፍን ይበልጡንም የሕይወት ዛፍን እንድናስታውስ ያደርገናል፡፡ ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ጋር ተያይዟልና፤ በዐቢይ ፍሥሐ የምናከብረውም የሕይወት ዛፍ በበረት ከድንግል ማርያም በመወለዱ ነው

ከዓመታት በፊት የሶሪያ ኦርቶዶክስ ቅዱስ ኒቆላስ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የሆኑት አባ ዳንኤል Christmas Tree … Pagan???- In Defense of the Christmas Tree በሚል ርዕስ አንድ መጣጥፍ አስነብበው ነበር፡፡ ከበርካታ ዓመታት በፊት በገና ሰሞን በአንድ ቴሌቪዥን ሃይማኖታዊ ፕሮግራም ሲተላለፍ ቀልባቸውን የወሰደው፣ የውይይቱ ርዕሰ ጉዳይ ከበዓል ጋር በተያያዘ የአንዳንድ ልማዶች አዝማሚያ በተለይም በወጣቶች ዘንድ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ የሚመለከት ነበር፡፡

አባ ዳንኤል እንዳሉት፣ ተወያዮቹ የአዲሱ ዘመን (New Age) መንፈሳዊነት አደገኛነትን በተመለከተ ቢስማሙም ከመሃል አንዱ ተወያይ ያነሳው የገና ዛፍም እንዲሁ ከፓጋን (አሕዛብ) የተገኘ ነው፤ የሚለው ነጥብ ግን አስደንግጧቸዋል፡፡ ዕውን የገና ዛፍ የፓጋን ነው? ከልጅነታችን ጀምሮ የልደት በዓል በመጣ ቁጥር ስናከብር የምናደርገው የገና ዛፍ መሠረቱ በእርግጥ ከፓጋን ነው? የሚለውን አስተያየት መረመሩና ፈጽሞ አይደለም፤ መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፤ በማለት ማስረጃ እየጠቀሱ እንዲህ ጽፈውታል፡፡

ብዙዎች እንደሚገነዘቡት፣ የገና ዛፍ ወደ አሜሪካ የዘለቀው ከጀርመን በተሰደዱ ዳያስፖራዎች ነው፡፡ ግን የዛፉ ምንጭ ከየት መጣ? ተወያዮቹ እንዳሉት ከፓጋኒዝም ነው? የገና ዛፍ መሠረት ከቀደምት ጀርመኖች አይደለም፤ በጥንታውያን ክርስቲያኖች ትውፊት በሥርዓተ ቅዳሴ ውስጥ የነበረና ከጊዜ በኋላ የደበዘዘ ነው፡፡ በመካከለኛው ዘመን ከቅዳሴ በፊት ወይም በኋላ በምዕራብ አውሮፓ አብያተ ክርስቲያናት ይከናወን ነበር፡፡ በተለይም ከሰሙነ ሕማማትና ትንሣዔ ምስጢር ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ ቆይቶም ከታዋቂ ቅዱሳን ጋርም መዛመድ ጀመረ፡፡ በታላላቅ ካቴድራሎች ዐውደ ምሕረት መንፈሳዊ ትርዒቱ (Liturgical dramas) ይቀርብ ነበር፡፡ አንዱ ትርዒት እንደምዕራባዊቷ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት፣ በገና ዋዜማ በሚከበረው የአዳምና ሔዋን በዓል ዕለትም ይቀርብ ነበር፡፡

የገነት ትርዒት (The Paradise play) በገነት ውስጥ በነበረው የአዳምና ሔዋን ታሪክ ላይ የተመሠረተና ከገነት ዛፍ፣ ወይም ከዕውቀት ዛፍ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህም የገነት ዛፍ በጀርመናውያን ዘንድ የታወቀና የተለመደ ሆኗል፡፡ በመሠረቱ ዛፎቹ የሚሸበርቁት በብስኩት ሲሆን ቁርባንን የሚያስታውስ ነው፡፡ ቆይቶ ግን ልዩ ልዩ ጣፋጮች ተኩት፡፡

የእኛ የገና ዛፍ የተገኘው ከፓጋንጥድ’ (Yule) ዛፍ ሳይሆን በአፕል በተጌጠውና ዲሴምበር 24 ቀን (ታኅሣሥ 28) በአዳምና ሔዋን በዓል ቀን ከሚደረገው የገነት ዛፍ ነው፡፡ የገና ዛፍ መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው፤›› በማለት ያለጥርጥር በአጽንዖት ይናገራሉ፡፡

ኢትዮጵያ እና የገና ዛፍ

በኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ጥድን ቆርጠው የገና ዛፍን በማዘጋጀት በዓሉን እያከበሩ ይገኛሉ፡፡ እንደ አውሮፓው ቅኝት ሁሉ፣ እዚህም ከፓጋን (አሕዛብ) ሥርዓት የተወረሰ ነው ብለው የሚያምኑ ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡

የገና ዛፍ 20ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ ሩብ ውስጥ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቤተ መንግሥት እንደነበረ የሰነድ ማስረጃ ቢኖርም ለአገሪቱ መነሻ ነው ብሎ መደምደም ግን ሊያስቸግር ይችላል፡፡

ስለገና ዛፍ መሠረትም ምናልባትም በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ውስጥ ካሉ ትውፊቶች ጋር ሊዛመድ የሚችልበት ነገር እንዳለ አንዳንድ ጽሑፎች፣ ድርሳኖች ይጠቁማሉ፡፡ታላቁ ሊቅ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በተዘጋጀው ‹‹መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ›› ውስጥ በለሶን የሚል ቃል እናገኛለን፡፡

ዕፀ አእምሮ [የዕውቀት ዛፍ] የገነት በለስ፤ አዳምና ሔዋን ፍሬውን በልተው ቅጠሉን የለበሱት፣ ኋላም የልደት ዕለት በታምራት መልአክ አምጥቶላት ዳግሚት [ሁለተኛዋ] ሔዋን ለልጇ ለዳግማይ አዳም [ኢየሱስ] ያለበሰችው፤ በማለት በለሶንን ይፈቱታል፡፡ ከቅዱስ ያሬድ ድጓ (የዜማ መጽሐፍ) የልደት ምንባብ ከደነቶ እሙ ቈጽለ በለሶን [እናቱ የበለሶን ቅጠል አለበሰችው] በማለትም አክለውበታል፡፡ሥላሴ ቅኔያቸውም እንዲህ አፍታተውታል፡፡

በለሰ ገነት ለአዳም ወሔዋን መቲሮቶሙ

መንክረ ልደት አምላከ መንገሌሆሙ ሰሐበ፤

ወገብርኤልሀ ዜናዌ ቀጸበ፤

እንተ ከመ ዝሰ ግብር እምከመ ለአዳም ተውህበ

ወረከበት ሔዋን ዘኢተረክበ፤

ካዕበ ይስሐብ ኀቤሆሙ አበ

ለበለስ ይምትርዎ ካዕበ፡፡

የቃል በቃል ፍችውም እንዲህ ነው፡፡ የገነትን በለስ አዳምና ሔዋን መቁረጣቸው ወደነርሱ ሳባቸው፣ አስደናቂ የሆነውን የአምላክ መወለድ ወደነርሱ ሳበ፡፡ የምሥራች ነጋሪን ገብርኤልንም የጠቀሰው እርሱ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ነገር ምሥጢር ለአዳም እንደተሰጠ ሔዋንም ያልተገኘውንና ያልተመረመረውን ምሥጢር አገኘች፡፡

ታላቁ ኢትዮጵያዊ የስድስተኛው ምዕት ዓመት ቲኦሎጂያን ቅዱስ ያሬድ እንዳተተው፣ በእንተ ልደቱ ለክርስቶስ አድባር ኮኑ ኅብስተ ሕይወት፤ ወዕፀወ ገዳምኒ ፈረዩ አስካለ በረከት፤ ወማየ ባሕርኒ ኮነት ሐሊበ ወመዓረ፡፡ ማለትም ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ተራሮች የሕይወት እንጀራ ሆኑ፤ የበረሃ ዛፎችም የበረከት እሸትን አፈሩ፤ የባሕር ውኃም ወተትና ማር ሆነች ይላል፡፡

በምዕራብም ሆነ በምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት እንዳለው ሁሉ፣ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም በአንዳንድ ዓበይት በዓላት እንደ ሆሣዕና፣ ስቅለት፣ ያሉት ከቅዳሴ በኋላ የሚደረጉ ሥርዓቶች አሉ፡፡ አንዱ በበዓለ ስቅለቱ ከስግደት በኋላ የሚደረገው በወይራ ቅጠል ካህናቱ፣ ‹‹ይኸን ያህል ስገድ›› እያሉ የሚያደርጉት ጥብጠባ ይጠቀሳል፡፡ ሊቃውንቱ ስለ በለሶን፣ ስለገና ዛፍ አንድምታ አፍታተው እንደሚገልጹት ይጠበቃል፡፡

የሶርያው ካህን አባ ዳንኤል እንደጻፉት፣ ገና ታላቁ ምሥጢረ ሥጋዌ የሚከበርበት ነው፡፡ በዚያም ምሥጢር እግዚአብሔር ቃል፣ ሰው ሆነ (ቃል ሥጋ ኮነ)፡፡ በእኛም ዘንድ አደረ እንዲል፡፡ አባ ዳንኤል በጽሑፋቸው አያይዘውም፣ በገና ዛፋችሁ ተደሰቱ ብለው አሳረጉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...