Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በገሐዱ ዓለም የጠፋው በምናብ ይምጣ እንጂ!

ሰላም! ሰላም! እስኪ ደግሞ እንደተለመደው የሆድ የሆዳችንን እንጫወት። የበዓል ሰሞን ስለሆነ እንጂ የዘንድሮ ሆድ እንኳን ተርፎት የሚያወራው የሚፈጨው ምን አለው? ለዚህም መሰለኝ ብዙዎቹ ወገኖቼ ነገር ሲገባቸው ‹‹ሆድ ይፍጀው›› እያሉ የሚያልፉት። ‹‹ማርክስና ኤንግልስ ልዩ ምልዕክታቸውን ‘እጅ’ አድርገው ለወዝአደሩ መበልፀግ ሲጮኹ የነበረው . . . ›› እያለ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ይህንኑ ሲደጋግምብኝ ሰነበተ። እኔ ደግሞ፣ ‹በዚህ ዘመን የተቀላቀለ ርዕዮተ ዓለም የሚያራምዱ ስለበዙ አርፈህ ተቀመጥ፤›› አልኩት፡፡ ኑሮ ጫናውን የሚደጋገምብን አንሶ፣ ነገርና ዓረፍተ ነገር ሲደጋገምባችሁ እስኪ አስቡት። ‹‹ምንድነው የምትለኝ? እስኪ ግልጽ አድርገው?›› ስለው፣ ‹‹ሁሉም ዜጋ በተቀራራቢ የሀብት ልዩነት ማደግ ስለሚችልበት ሥርዓት ነው የማወራህ፤›› እያለ ስለ‘ሶሻሊዝም’ እና ‘ኮሙዩኒዝም’ ይነዘንዘኝ ጀመረ።

‹‹ደሃው ጀርባው መጉበጡ ሀብታሙም እያደር ወደ ላይ መተኮሱ የነፃ ገበያ ሥርዓት መገለጫ ከሆነ በአፍንጫችን ይውጣ፤›› እያለ ክፉኛ ሲብሰለሰል ከረመ። ታዲያ አንዳንድ በአብዮቱ ዘመን እላይ ታች ሲሉ ያልተሳካላቸው ሰዎች ሲሰሙት፣ ‹‹ይህቺ ጠጋ ጠጋ ዕቃ ለማንሳት ነው። እባክህ ለእኛም አልተሳካ!›› ሲሉት፣ እንደ እኔ ምኑንም የማያውቅ አልፎ ሂያጅ ደግሞ፣ ‹‹ወንድሜ ምናለበት አርፈህ ብትቀመጥ? እኛም አርፈን መበዝበዛችንን ብናጣጥም?›› ሲለው ሰነበተ። እንግዲህ ልባም ከሆናችሁ እዚህች ምስኪን አገር የተመቻቸውና ያልተመቻቸው ሰዎች ልዩነት በደንብ የሚታያችሁ አሁን ነው። የደከመውና የታከተው ‘ዓይቶ እንዳላየ’ የሚባል ጥበብ ከእንጀራ ይልቅ ዕድሜ ሲያረዝምለት፣ ትኩሱን ወጣት ብስጭትና ተስፋ መቁረጥ ዕድሜውን ወደሚያሳጥርበት የሱስ ዋሻ ሲመራው ማስተዋል ግድ ይላችኋል። ድሮስ ከዚህ ውጪ መሰንበት ምን ፈየደልን አትሉም? ወይም የባሰ አለና አገርህን አትልቀቅ የማለት ምርጫው የእናንተ ነው!

 ሸሽቶ ላይሸሽ ርቆ ላይርቅ የመኖርን እንቆቅልሽ ስንገፋ እንከርማለን። አቤት! ምን የማንገፋው የተራራ ዓይነት አለ? የሕይወት ግዴታ ነውና ግድ ይለናል፡፡ እኔም ቁጭ ብዬ ‹‹እህህ. . .›› ከማለት እያልኩ ስኳትን አይደክመኝም። በሳምንቱ መጀመርያ አንድ አዲስ የገባ ያለጠፈ ‘ላንድክሩዘር’ ለማሻሻጥ እንዴት ስቃዬን እንዳየሁ አይነገርም። መጀመርያ ‘ለመሆኑ ይኼን ውኃ የመሰለ ‘ላንድ ክሩዘር’ ማን ሊገዛ ይችላል?’ ብዬ ስጠይቅ ፈጥነው የታሰቡኝ በሥልጣናቸው አማካይነት የሚበለፅጉ አንዳንድ ሹማምንት ናቸው። እንጀራ ነውና ልቤ ጮቤ እየረገጠ አቅራቢያዬ ወዳለ አንድ ተቋም መጓዝ ጀመርኩ። ይኼኔ አንድ ደላላ ወዳጄ መንገድ ላይ አግኝቶኝ፣ ‹‹ተሸጠ እንዴ?›› ብሎ ስለመኪናው ሲጠይቀኝ እንዳልተሸጠ ነግሬው ወዴት እየሄድኩ እንደሆነ አስረዳሁት። ‹‹አይ አንበርብር ሞኙ። እንዴ በፊት ለፊት በር ገብተህ ልታሻሽጥ ታስባለህ? ያውም በዚህ በዓይነ ቁራኛ በሚያስተያይበት ዘመን?›› ሲለኝ ምን ነክቶኝ ነው ብዬ መለስ አልኩ። የባለሥልጣኖቻችን የሀብትና የንብረት ምዝገባ ግልጽነት አለመኖር አሳሳቢ መሆኑን የባሻዬ ልጅ ያጫወተኝ ትዝ አለኝ። እኔም ይኼንን ለዚሁ ወዳጄ ባነሳለት፣ ‹‹ከቴም የሀብት ምዝገባ? ኧረ ተወኝ አንተ ሰውዬ! ምናለበት ተፈጥሮ የቸረችንን አየር እንዳያቋርጡብን ብትፀልይ?›› ብሎ ወደሚቸኩልበት ጉዳዩ ጥሎኝ ፈረጠጠ።

ያው እንደምታውቁት ውስጣችን ምን ቢቋጥር አርፎ ለመቀመጥ ሕይወታችን አትፈቅድልንምና ስንሮጥ እንውላለን። ‘የሚሮጡት ብዙዎች የሚሸለሙት ጥቂቶች’ ሲባል ያልሰማ አለ? አንዳንዶች በአርባ ቀን ዕድል እያማረሩ ሲቆዝሙ፣ ዕድል መኖሩን የማያውቁት ደግሞ ላባቸውን ጠብ አድርገው ጣዕረ ሞት ከሚመስለው ኑሮ ጋር ይተናነቃሉ፡፡ የደላቸው ደግሞ የተኙበትና ጎዝጉዘው የተቀመጡበት ሥፍራ ድረስ በረከቱ ይፈስላቸዋል፡፡ ‹‹የገንዘብ ማተሚያ ማሽን መኝታ ቤታቸው ውስጥ የተከሉ አሉ እንዴ የሚያሰኝ ጊዜ ላይ ነው ያለነው፤›› ያለኝ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ አስቤ አስቤ እኔ ቆቁ አንበርብር ምንተስኖት ማን ዘንድ የሄድኩ ይመስላችኋል? ለነገሩ አገሩ በሙላ በቻይና ተወሮ ከእነሱ ውጪ ማን ዘንድ እሄዳለሁ? ከቀናት በፊት አንድ ቻይናዊ መኪና ሲያፈላልግ ተገናኝተን ስለነበር የሚሠራበት ‘ሳይት’ ቀጥ ብዬ ሄድኩ። በሥራ ተጠምዶ ወዲያ ወዲህ ሲል አላናግረኝ ማለቱን ያየ አንድ የእኛው ሰው የቀን ሠራተኛ ወደኔ ተጠጋና ቆመ። የእኛ ነገር በአገራችንም በሰው አገርም የሚቀናን መቀጠር እንጂ መቅጠር አይደለም። ኧረ ሥራ ተገኝቶ ሠርቶ ማደሩም ወግ ነው። ይኼው የቀን ሠራተኛ ቀስ ብሎ ተጠግቶኝ፣ ‹‹አይዞህ ጠጋ ብለህ ጥራና አናግረው። አማርኛ አቀላጥፎ ይናገራል፤›› አለኝ። ማስጠንቀቂያ! ዘንድሮ ሰው መልኩና ፀባዩ ብቻ ሳይሆን ቋንቋውም አልያዝ አልጨበጥ ብሏል።

አደራችሁን አይሰማኝም ብላችሁ ፈረንጅ ማማት ይቅርባችሁ እላለሁ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት። ‘የመናገር ነፃነት በተረጋገጠበት ዘመን ሰማኝ አልሰማኝ ምን አስጨነቀኝ?’ የምትሉ ካላችሁ ቻይናውያን የታላቁ የኮሙዩኒስት ፓርቲ ልጆች መሆናቸውን በጊዜ ልብ ብትሉ የሚሻል ይመስለኛል። ገባችሁ? የገባችሁ እባካችሁ ያልገባቸውን አስረዱልኝ? አመሰግናለሁ! ‹‹ለመሆኑ እንዲህ በአጭር ጊዜ ቋንቋችንን ለማጥናት የሚያጣድፋቸው ነገር ምን ይሆን?›› ብዬ ጠየቅኩት። ልጁ የወሬ ሱሱን ለማርካት ሲቁነጠነጥ መቆየቱን ከአነጋገሩ እያስተዋልኩ ተገረምኩ። ‹‹ቀን ይኼው እንደምታያቸው እነሱም ላባቸውን እያፈሰሱ ሲያሠሩን፣ ሲያስቆፍሩንና ሲያስንዱን ይውላሉ። ሲመሽ እኛ አገር ሥራ አልተለመደም። እንደ ታዳጊ አገር ሳይሆን እንደ አደገ አገር መዘባነን ያስመኘናል። ታዲያ ያኔ ምን ይሥሩ? ቋጣሪ ሆነን ያስመረርናቸውን ‘ቺኮቻችንን’ ለማደን በምሽት ሲወጡ በምን ይግባቡልህ?›› ሲለኝ፣ የወደፊቱ ‹‹ኢትዮ ቻይኒዝ›› ትውልድ ውልብ አለብኝ። ጉድ ነው አትሉም? አቤት ያኔ ተቀላቅሎ የሚበላውና የሚጠጣው ዓይነት ቅልቅል ብዛቱ? ያኔ ስምን የሚያወጣው እውነትም ‹‹መልዓክ›› መሆን ይገባዋል።

በዚሁ ስሜት ውስጥ ሳለሁ ራሴን እንዲህ ስል ጠየቅኩት። ‘ቻይና እየሠራችልን ነው እየረዳችን?’ በነገራችን ላይ እንዲህ ያለ መንታ ጥያቄ ሲገጥማችሁ እንደ ድሮው አንዱን መምረጥ አይሠራም። እንዴት ሆኖ ይሠራል? እስኪ ስታስቡት በዚህች ተለዋዋጭ ዓለም ምን ወጥ ነገር ኖሮ ነው ወጥ መልስ የምንመልሰው? ሳይንስ እንኳ ዓይኑን በጨው አጥቦ ትናንት እውነት ያለውን ዛሬ ሐሰት ብሎ እየሸመጠጠን አይደል እንዴ? እሱስ አንደኛውን መረጃውን ይዤ ነው ይላል። ሌላ ሌላው ነገር ነው እንጂ። ለምሳሌ ‘ኢትዮጵያ እያደገች ነው ወይስ እያደግኩ ነው እያለች?’ ብትባሉ መልሱ ሁለቱንም ነው። አያድርስና ‘እንዴት?’ ባይ አፋጣጭ ከገጠማችሁ ‘ለአንዳንዶች አድጋለች ለአንዳንዶች አድጌያለሁ ትላቸዋለች’ ብላችሁ መመለስ ግዴታ ሆኗል።

ሌላ ምሳሌ፣ ‘አፍሪካ እየሠራች ነው እያወራች?’ ተብላችሁ ብትጠየቁ አሁንም ‘ሁለቱንም!’ ብላችሁ መመለሳችሁን አደራ። መቼም ለዚህ እንዴት? ባይ አስጨናቂ ጠያቂ የሚኖረው አይመስለኝም። ምክንያቱም አኅጉራችን የአኅጉራት ቁጥር ማሟያ እንጂ ሌላ እንዳልሆነች ሁሉም ጠንቅቆ የሚያውቀው ጉዳይ ስለሆነ ነዋ። የአፍሪካ ኅብረት ተጎልቶ አውሮፓ በአፍሪካ ምድር ላይ ምን እየሠራች እንደሆነ እናውቃለና፡፡ ‹‹አይ ዘመን! ሁሉም በተናጠል የሚሮጥበት ጊዜ!?›› ይላሉ ባሻዬ እንዲህ ነገርን በነገር እያነሳን ስንጫወት። እናም ቻይና እየሠራችልን ነው እየረዳችን ብዬ ጠይቄ ራሴው ለራሴው ‘ሁለቱንም’ ስል መለስኩኝ። ሁሉንም ነገር ‘እንዲህ ነው! የለም እንዲያ ነው!’ ለማለት እየከበደን ሲመጣ ግርም አይላችሁም? ለነገሩ እውነትና ሐሰቱ፣ ዘይትና ውኃው ተቀላቅሎና ተመሳስሎ እየኖረ ነጥሎ ጠይቆ ነጥሎ መመለስ ቢከብደን ምን ይገርማል? ምንም!

 በቆምኩበት የሄድኩበትን ረስቼ ስለቅልቅልና ሚስቶ ሳስብ ሆዴ ክፉኛ ጮሆ አነቃኝ። ውስጤ አንጀት የሚያርስ አሪፍ ምግብ መብላት አማረው። ‘አማረኝ’ ማለት የሁላችንም ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ከሆነ ውሎ አድሯል። ድሮስ? ድሮማ ኃላፊነቱ የተወሰነ የእርጉዝ ሚስቶቻችን ብቸኛ ምልክት ነበረ። አንድ የሰማሁትን ቀልድ ጣል ላድርግላችሁ። ሁለት ባልና ሚስቶች ትንሽ ቀደም ባለው ጊዜ የመጀመርያ ልጃቸውን ሊወልዱ ሚስት እርጉዝ ነበረች፡፡ ተኝተው በእኩለ ሌሊት ሚስት ባሏን ትቀሰቅስና ‹‹ክትፎ አማረኝ!›› ትለዋለች። ተሯሩጦ ከየትም ከየትም ብሎ አምጥቶ ያበላታል። ለሁለተኛውም ልጅ እንዲሁ። ዘንድሮ ነው አሉ ሚስት ሦስተኛዋን አርግዛ (ኑሮ ምን ቢከብድም ወልዶ መክበድ የሚቆም አይመስልም) እኩለ ቀን ላይ ‹‹ክትፎ አማረኝ!›› ስትለው፣ ‹‹አሁንስ እኔንም አምሮኛል!›› ብሏት አረፈው! ባልም ሚስትም በአምሮት ተሰቃይተው የሚወልዱት ልጅ ትንሽ ከፍ ሲል በአምሮት ዙሪያ ምን ይል ይሆን? አደራ ደግሞ አንበርብር ጠይቆናል ብላችሁ ወልዶ ለመስማት እንዳይከጅላችሁ። መቼም የዛሬ ሰው ጥያቄ መመለስን በሽልማት ለምዶ ለመሸለም የማይሆነው ነገር የለም። 

ቶሎ ብዬ ጉዳዬን ለመጨራረስ ስላሰብኩ ሥራውን አቋርጦ እንዲያነጋግረኝ ቻይናውን በዓይኔ ጠቀስኩት። አጠር ወፈር የሚለው ቻይናዊ በትንንሽ ዓይኖቹ አፍጥጦ ሊያየኝ እየሞከረ ከቀረበኝ በኋላ እንዳስታወሰኝ ነገረኝ። እውነትም የአማርኛ ቃላት አደራደሩ ግሩም ነው። እኔማ ከሩቅ ምሥራቅ ሳይሆን ከመንዝ አካባቢ የመጣ ነበር የመሰለኝ፡፡ የመጀመርያ ቀን በሩቁ ስለተያየን በደንብ አልተዋወቅንም እንጂ መገረሜ ቀደም ብሉ ይታወቅ ነበር። ወዲያው የመጣሁበትን ጉዳይ ስነግረው ከታች ብቻ ታጥቆ እጅጌዎቹን ወገቡ ላይ ያሰረውን ቱታ ወዲያው ፈትቶ አወላለቀና ‹‹አሁኑኑ አሳየኝ!›› አለኝ። ወስጄ ከባለቤቱ ጋር አገናኝቼው መኪናውንም ካየ በኋላ ስልክ ቁጥሬን ተቀብሎ ተመልሶ ወደ ሥራው ሄደ።

 እኔም ምሳዬን ልበላ ቤቴ ጎራ አልኩ። ውዷ ማንጠግቦሽ ቡናውን አቀራርባ ወጡን ሞቅ ሞቅ አድርጋ የጎዳደለው እንዳያስታውቅ ያለውን በባለሙያ እጇ አጣፍጣ ሠርታ ጠበቀችኝ። እውነት ለመነጋገር እኮ የሌለንን ስናስብ ያለንን ማጣፈጡን ከረሳነው ዘመን የለንም። ስለባቡር እያሰብን ታክሲና አውቶቡሱን በፍጥነት ማቀራረቡን፣ ስለዓባይ ግድብ እያሰብን በየአካባቢያችን እየፈነዱ ያስቸገሩንን ትራንስፎርመሮች መጠጋገንን፣ ስለማኅበር ቤት ግንባታዎች እያለምን የኮንዶሚኒየም ቤቶች የኪራይ ዋጋ ንረትን ማቃለልን (ባለቤትነቱንማ እርሱት)፣ ወዘተ. አቅቶናል፡፡ መቀየር፣ ማሻሻል፣ ማስታገስ የሚባል ነገር አላውቅ ብለናል። ‘ብልጥ ልጅ እየበላ ያለቅሳል’ እንዲሉ እኛስ የያዝነውን ይዘን ብናለቅስ አይበጀንም ትላላችሁ? ከማንጠግቦሽ ጋር ስለውሎና ሥራ እያወራን ቆየንና ድንገት ዓይኔ ወደ እግሯ ተመለከተ። ባዶ እግሯን ወዲያ ወዲህ ስትካለብ መዋሏን ያን ጊዜ አስተዋልኩ። ‘ወይ ዕዳ! አሁን አፍ አውጥታ ጫማ ግዛልኝ ማለት ከብዷት ነው? በአሽሙር መነገሩ ይሆን?’ እያልኩ ሳወጣ ሳወርድ ቆይቼ፣ ‹‹ማንጠግቦሽ! አሁን እኔን ለማሳጣት ነው እንዲህ የምትሆኝው? ምናለበት በግልጽ ጫማ ግዛ ብትይኝ?›› ስላት ከት ብላ ሳቀችብኝ፡፡ ከዚያም ‹‹አይ አንተ? የቁልቢው ስለት ስላለብኝ ነው አዲስ ጫማ ፈልጌ አይደለም፣ አንተንም ለማሳጣት አይደለም፤›› ብላ መልሳ መላልሳ መሳቋን ቀጠለች።

የወጪ ነገር እንዳንገፈገፈኝ ታዝባኛለች መሰለኝ? እኔም ማንም ሰው የፈቀደውን እንደፈቀደው የማመንና የማግኘት መብት እንዳለው ጠንቅቄ ስለማውቅ ስለተሳለችው ስለት አስጨንቄ ሳልጠይቃት ቀረሁ። ‹‹ጉዳያችንን ሁሉ ከእግዜሩ ጋር አዛምደን መኖራችን እንዴት ጠቅሞናል መሰለህ አንበርብር? ለብዙ ጥፋትና ስህተት ሰፊ ትዕግሥት ያገኘነው ከየት ይመስልሃል?›› የሚሉኝ ባሻዬ ናቸው። እኔም አንዳንዴ ‘እውነታቸውን እኮ ነው ባሻዬ። ሰው የሰው ብቸኛ ተስፋው ቢሆን ኖሮ በዚህ መጨካከንና ለራስ ብቻ ማሰብ በገነነበት ጊዜ ምን ይውጠን ነበር?’ እላለሁ። እውነት ምን ይውጠን ነበር? አንዳንዴ እኮ ፈጣሪ የሰጠንን አየር ቆጣሪ ሊያስገቡለት የሚፈልጉ እንዳሉ ሳስብ ‹‹እባብ ልቡን ዓይቶ እግር ነሳው›› የሚለው አባባል ይመስጠኛል፡፡ 

እስኪ እንሰነባበት። ስልክ ቁጥሬን ቢቀበለኝም የውኃ ሽታ ሆኖ የቀረውን ቻይናዊ እየተጠባበቅኩ በጎን ሌሎች ተባራሪ ሥራዎችን ስሠራ ውዬ አደርኩ። አንድ ቀን አመሻሽ ላይ ከባሻዬ ልጅ ጋር የተለመደው ግሮሰሪያችን ልንሰየም በሩ አጠገብ ከመድረሳችን የጥሪ ድምፅ ሰማን። ከአስፋልቱ ጠርዝ ቻይናው የገዛውን  ‘ላንድክሩዘር’ መኪና አቁሞ በሰው ሲያስጠራኝ አየሁት። ‘ከመቅረት መዘግየት’ እያልኩ ስጠጋው ጋቢና ጠይም ዓሳ መሳይ ኢትዮጵያዊት ‹‹ልዕልት›› መቀመጧን ጨምሬ ታዘብኩ (ከባለትዳር እንዲህ ይጠበቃል? ሃሃሃ)፡፡ ቆንጆ መኪና ባለበት ቆንጆ ሴት አልጠፋ ያለችበት ምክንያት ግን ምን ይሆን? ብላችሁ ሞኝነቴ ገዝፎ ይታያችኋል፡፡ መኪናውን ገና የዚያን ቀን መቀበሉንና ዝም ያለኝ አውቆ እንደሆነ በተቀላጠፈ አማርኛው አስረድቶኝ ሞቅ ያለ ‘ኮሚሽኔን’ ሸጎጠልኝ።

ከባሻዬ ልጅ ጋር ወደ ግሮሰሪው ተያይዘን ዘለቅንና ቢራችንን አዘን ወግ ጀመርን። ‹‹አየህልኝ ቻይናን?›› ስለው፣ ‹‹ምን ታደርገዋለህ? ቁመታቸው ቢያጥርም ልባቸው ግዙፍ ነው፤›› ሲል ተሳሳቅን። ‹‹ለመሆኑ ዕድገታችን ከ11 በመቶ ወደ ታች ዝቅ ማለቱን ሰምተሃል?›› አለኝ ከተቀዳው ቢራ እየተጎነጨለት። እኔም እንዳልሰማሁ ስነግረው፣ ‹‹ለነገሩ ሰማህ አልሰማህ ዋናው ማደጉ ነው። አነሰም በዛም አድገናል ነው ጨዋታው!›› ብሎኝ ልገምተው ባልቻልኩት የሐሳብና የትካዜ መስመር ጭልጥ ብሎ ተጓዘ። ‘አነሰም በዛም አድገናል!? ወይ አማርኛ?’ እያልኩ በገዛ ሐሳቤ ውስጥ ጭልጥ ብዬ ጠፋሁ። በሐሳብ ባህር ውስጥ ሆኜ የደጋገምኩት ቢራ ሞቅታ መፍጠር ሲጀምር ምቾት ውስጥ ያለሁ አስመሰለኝ፡፡ እንጀራ የሚባለው ነገር ከላይ ታች የሚያካልበኝን ረስቼ ለራሴ በፈጠርኩት የምቾት ባህር ውስጥ ሰጠምኩ፡፡ ‹‹አንዳንዴም በዋልድባ ይዘፈናል›› ያለው ማን ነበር? በገሐዱ ዓለም ያጣነውን ምቾት በምናብ ስናመጣው እንዴት ይመቻል? አንዳንዴ እኮ ነገር ስልችት ሲል ምቾትን መመኘት የመሰለ ነገር የለም፡፡ ያው የበዓል ሰሞን ስለሆነ ሁላችንንም ምችት ይበለን! መልካም ሰንበት!   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት