በአጭር የተከረከሙት ፀጉራቸው ብዙም ሽበት አይታይበትም፡፡ ጎስቋሏ ፊታቸው ግን እርጅና የተጫጫናቸው አስመስሏቸዋል፡፡ ከወለሉ የመስኮት ያህል ከፍታ ያለውን በር እንደተደገፉ ውጭ ውጭውን ያያሉ፡፡ ዕይታው የደከመው ዓይናቸው ግን ወዳጆቻቸውን እንኳን አይለይም፡፡ በስማቸው እየጠሯቸው ለሰላምታ እጃቸውን ለዘረጉላቸው ሰዎች አፀፋውን ቢመልሱም ማን መሆናቸውን አላወቁም፡፡ ከተቀመጡበት መዝጊያውን ተደግፈው እንደ መነሳት እያሉ እንግዶቻቸው ወደ ውስጥ እንዲገቡ ጋበዙ፡፡
ወደ ጎን አንድ፣ ወደ ኋላ ደግሞ ሁለት ሜትር ስፋት ያለው የወ/ሮ ሻሼ አንተሉል ቤት እንኳንስ እንግዶቹን ሊያስተናግድ የሚቆሙበት ጥግ እንኳን የለውም፡፡ እንግዶቻቸውም እንግባ ሳይሉ ከደጅ ተቀመጡ፡፡ የወ/ሮ ሻሼ ቤት ከሁለት ዱካ በላይ የሚይዝ ቦታ የለውም፡፡ ስለዚህ ሁለት ሰው ቁጭ ካለ ተደርቦ የሚገባ ሌላ ሦስተኛ ሰው በተሳፋሪ አውቶብስ ውስጥ ተደርቦ እንደገባ መንገደኛ ይቆማል እንጂ መቀመጫ ማግኘት የማይታሰብ ነው፡፡
ከአንድ ሰው በላይ መያዝ የማይችለው አልጋቸው ከመሬት ከፍ ብሎ ተቀምጧል፡፡ ሥሩ እንደ መጋዘን የማይፈልጓቸውን ዕቃዎች ማጎሪያ ነው፡፡ አልጋው ማታ ማታ መኝታ ቀን ቀን ደግሞ የዕቃ ማስቀመጫ ጭምር ነው፡፡
እትዬ ሻሼን የሚያጫውተው ወጣት የልጅ ልጃቸው ሚሊዮን አንበርብር ነው፡፡ እሳቸው ከተቀመጡበት በመዝጊያው ተቃራኒ የተሸጎጠው ምጣድ ሰምቷል፡፡ ከአክንባሎው ሥር የሚወጣው የትኩስ እንጀራ እንፋሎት መፈናፈኛ የሌላትን ጎጆ አውዷል፡፡ የወ/ሮ ሻሼን የድህነት ኑሮና የተሻለ ኑሮ ያላቸውን ዜጎች የሚያመሳስላቸው የትኩሱ እንጀራ መዓዛ ነው ያስብላል፡፡ በበርበሬ ብሉኝ የሚል ትኩስ እንጀራ የያዘ ሰፌድ አልጋው ላይ ይታያል፡፡ ወ/ሮ ሻሼ ደካማ ናቸው፡፡ ምጣድ ላይ እንጀራ ማስፋት፣ ማንሳትም የሚችሉ አይመስሉም፡፡ እንጀራውን የሚጋግረው ጅንስ ሱሪውን ዝቅ አድርጎ የታጠቀው፣ በአንዱ ጆሮው ላይ ኤርፎን ያንጠለጠለው ሚሊዮን መሆኑን ለማወቅ ጊዜ ወሰደብን፡፡ ሚሊዮን እንጀራ ጋግሮ እስኪጨርስ ወ/ሮ ሻሼ ስለ ኑሯቸው ያወጉን ገቡ፡፡
ወ/ሮ ሻሼ ጨው በረንዳ አካባቢ ከሚገኘው መንደር ለ40 ዓመታት ያህል መኖራቸውን እንጂ ዕድሜያቸው ምን ያህል እንደሆነ በውል አያውቁም፡፡ ‹‹70 ይሁን 80 ስንት ዓመት እንደሆነኝ የት አውቄ?›› አሉ ድህነት ያጎሳቆለው ሰውነታቸውን ገምግመው በዕድሜ ማምሻው ላይ እንደሚገኙ በመገመት፡፡
ተወልደው ያደጉት ጎጃም አካባቢ ሲሆን፣ ወደ አዲስ አበባ የመጡት በአጋጣሚ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ከባለቤታቸው ጋር ሲጣሉ ልጃቸውን በሆዳቸው እንደያዙ ወደ አዲስ አበባ ኮበለሉ፡፡ አዲስ አበባ የመጡት ግን የሚያውቁት ዘመድ ኖሯቸው ሳይሆን ምንም ሠርተው ሊያድሩ የሚችሉባት ከተማ ስለመሰለቻቸው ነበር፡፡
እንደ መጡ ቅድስት ማርያም አካባቢ ሰው ቤት ተቀጥረው መሥራት ጀመሩ፡፡ ጎጃም ጥለውት ከመጡት ባላቸው ያረገዙትንም እዚሁ ወለዱ፡፡ ልጃቸው ዛሬ 40 ዓመት ሞልቶታል፡፡ ሌሎች ልጆችም ወልደዋል፡፡ ወ/ሮ ሻሼ ሰው ቤት ተቀጥረው እየሠሩ፣ በትርፍ ሰዓታቸው ደግሞ ቃሪያና ሽንኩርት ጉልት እየቸረቸሩ ልጆቻቸውን ከነልጅ ልጆቻቸው ቀጥ አድርገው ነበር የሚያስተዳድሩት፡፡
መተንፈሻ በሌላት በጠባቧ ጣሪያ ሥር ብዙ ልጆች አድገዋል፡፡ ጠባቧ ክፍል ልጆቻቸው ከነ ልጆቻቸው አብረው የሚያድጉባት ጉደኛ ቤት ነች፡፡ 40 ዓመት ሆኖታል የሚሉት ልጃቸው ሳይቀር ልጆቹን ይዞ በዚህች ክፍል ውስጥ ይኖራል፡፡ ጎኗ አንድ ሜትር የማትሞላው አልጋ ወ/ሮ ሻሼንና ሚሊዮንን ታሳድራለች፡፡ ቀሪዎቹ ወለሉ ላይ ያገኙትን አንጥፈው ተጠጋግተው ያድራሉ፡፡
ትልቁ ልጃቸው ግን ሕመም ስለጠናበት ቀዝቃዛ ወለል ላይ ተጠጋግቶ ማደር አልሆነለትም፡፡ ስለዚህም ቀን ቀን እናቱ ቤት እየዋለ ማታ ማታ ማደሪያውን ይፈልጋል፡፡ እንደ አቅሙ የሚሠራው የቀን ሥራ ለማደሪያው የሚሆነውን አምስት ብር አያሳጣውም፡፡ ምግብና ሌሎች ወጪዎቹን የሚችሉት ግን ደካማዋ ወ/ሮ ሻሼ ናቸው፡፡ ሁለቱ ልጆቻቸው ከሞቱ ቆይተዋል፡፡ ‹‹ልጆቼ ጦር ሜዳ ሳይሆን እዚሁ ነው የሞቱት፤›› አሉ ራሳቸውን ተጠያቂ በማድረግ፡፡
አንድ ብርጭቆ ሻይ ጠጥተው እንደዋዛ የሚከፍሉት ስምንት ብር ለወ/ሮ ሻሼ ትልቅ ወርኃዊ ወጪ ነው፡፡ ‹‹ዕድሜዬን የጨረስኩት እዚህ ሠፈር ነው፤›› የሚሉት ወይዘሮዋ ሱቅ ለምታህለው የቀበሌ ቤት በወር ስምንት ብር ከሃምሳ ሳንቲም እንደሚከፍሉ ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት አስተያየት ተደርጎላቸው በወር የሚከፍሉት ወደ አራት ብር ከሃያ አምስት ሳንቲም ዝቅ ተደርጎላቸዋል፡፡
በጉብዝናቸው ወቅት መላ ቤተሰቡን ያስተዳድሩ የነበሩት አቅመ ደካማዋ ባልቴት ቤት ከዋሉ ቆይተዋል፡፡ ጉልበታቸውም ዛል፣ ዓይናቸውም ደከም፣ ጆሯቸውም አሻፈረኝ ብሏል፡፡ እንዲያም ሆኖ ቤተሰባቸው አልተበተነም፡፡ እትዬ ሻሼ ግን የሚከፈላቸው ጡረታ፣ ወይም አለሁ የሚላቸው በየጊዜው ገንዘብ እየቆረጠ ከችግራቸው የሚገላግላቸው ዘመድ የላቸውም፡፡ ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ ደሃ ቢሆኑም የሚያሳድራቸው መላ ግን አላጡም፡፡
የወ/ሮ ሻሼ ቤት ባረጀ ማዳበሪያ የተሠራ ኮርኒስ አለው፡፡ ኮርኒሱ ለቤቱ ድምቀት እንዲሆን የተሠራ ሳይሆን ሌላ የተለየ ሚና አለው፡፡ በመግቢያው ጎን ባለው ግድግዳ ላይ ኮርኒሱን ሽቅብ ሰንጥቆ የሚገባ መሰላል ቆሟል፡፡ መሰላሉ እንደ ሁለተኛ ቤት የሚቆጥሩት ቆጥ መወጣጫ ደረጃ ማለት ነው፡፡ ገና ሲነኩት የሚወላገደውን መሰላል በመላ በዘዴ አድርገን የዶሮ ማደሪያ ወደ ምታክለው ቆጥ አጮለቅን፡፡
ያረጀው የጭቃ ግድግዳ ላይ የተቀባው ሎሚ መሳይ ቀለም እንዳይሆኑ ሆኗል፡፡ በአንድ በኩል እንደ መጨቅየት ሲል በሌላ ደግሞ ቀለሙ ረግፎ ስሱን የጭቃ ምርጊት ያሳያል፡፡ በቀጫጭን ማገሮች ላይ የተዘረጋው የቆርቆሮ ንጣፍም ሙሉ ለሙሉ ዝጓል፡፡ በኮርኒሱና በጣሪያው መካከል ያለው ርቀት ከግማሽ ሜትር አይበልጥም፡፡ ከማዳበሪያው ኮርኒስ አናት ላይ ያረጁ የሳር ፍራሾች ተዘርግተዋል፡፡ ሁለት ያረጁ ቡራቡሬ ብርድ ልብሶችም ይታያሉ፡፡ ለማፅዳትም ሆነ ለማንጠፍ የማይመች በመሆኑ የተሰናዳ ነገር የለም፡፡ አቧራም ውጦታል፡፡
በዚህ ቆጥ ውስጥ ሲጠጡ የሚያመሹ ወዛደሮች ውድቅት ላይ እስከ አሥር ብር እየከፈሉ ያድራሉ፡፡ ገበያው በሚደራበት ቀን በአንድ ጊዜ እስከ አምስት ሰዎች፣ ሲጠፋ ደግሞ ሁለት ሰዎች ያድሩበታል፡፡ የወ/ሮ ሻሼ ብቸኛ ገቢም ይኸው ማደሪያ ነው፡፡ ኑሮ የማይገፉት ጋራ ለሆነበት ወዛደር የወ/ሮ ሻሼ ሕይወት የቡርዥያ ነው፡፡ የማይደረስበት የድሎት ዓለም፣ የባለጊዜ ኑሮ ነው፡፡ ለወ/ሮ ሻሼ ግን የመኖርና ያለመኖር ወይም ጎዳና ልመና የመውጣትና ያለመውጣት የክብር ጉዳይ ነው፡፡ የቀጣዩን ቀን ወጪ የሚሸፍኑበት ገንዘብ እስኪያገኙ በራቸውን አይዘጉም፡፡ ሰክሮ የሚወላገድ ወዛደር ገብቶ ቆጡን እስኪሞላ ቁጭ ነው፡፡
ቆጡ ሞልቶ በሩ ቢዘጋም ሰላም እንቅልፍ ይተኛሉ ማለት አይደለም፡፡ ጥምቢራው እስኪዞር የጠጣ ድንገት ከቆጡ ወርዶ በር ከፍቼ ካልወጣሁ ይላል፡፡ መከልከል አይቻልም በሩን በርግዶ ሲወጣ ወለሉ ላይ የተኙት በተከፈተው በር የሚገባው ንፋስ ቀጥታ ያገኛቸዋል፡፡ በሩ በተከፈተና በተዘጋ ቁጥር ሽው እያለ የሚገባው ንፋስ እንቅልፍ ሲነሳቸው ከላይ ሽንት የሚለቅባቸውም አለ፡፡
‹‹በተኛንበት ፊታችን ላይ ከላይ ሽንት የሚፈስብን ጊዜያት አሉ፡፡ እንዲህ የሚያደርጉት ወጥቶ ለመሽናት አቅሙ የሌላቸው ሰካራሞች ናቸው፤›› አለ ሚሊዮን፡፡
የወ/ሮ ሻሼ መተዳደሪያ አብዛኞቹ የሠፈሩ ነዋሪዎች መተዳደሪያም ነው፡፡ መተንፈሻ የሌላትን አንድ ክፍል በእንጨት ርብራብ ቆጥ ሠርተውላት መኖሪያ ቤትም ቤርጎም ያደርጓታል፡፡ ግላዊ ሕይወት የሚባል ነገር የለም፡፡ የአንድ ቤተሰብ አባላት ከፊሉ አልጋ ላይ የተቀረው መሬት አንጥፎ በጋራ ያድራል፡፡ ቆጣቸውን የሚከራዩ ወዛደሮችም በፍቅር አብሮ እንደሚኖር ቤተሰብ የሳር ፍራሽ ተጋርተው ያሸልባሉ፡፡
ሰክሮ ውድቅት ላይ የሚረብሸው፣ ከላይ ሽንቱን የሚለቅባቸው ቢኖርም ብቸኛው የገቢ ምንጭ ነውና አለማከራየት አማራጫቸው አይደለም፡፡ በተለይ አድጎ ለቁም ነገር የበቃ ልጅ ካላደረሱ፤ አምስትና አሥር ብር እስከከፈላቸው ድረስ ቤታቸውን ከፍተው ቆጥ ላይ ለሚያሳድሩት እንግዳ ጀርባቸውን አይሰጡም፡፡ ሚሊዮን ግን ለወይዘሮ ሻሼ ተስፋ ሆኗቸዋል፡፡
ሚሊዮን ተወልዶ ያደገው እዚሁ ቤት በአያቱ እጅ ነው፡፡ እናቱ በሕይወት ብትኖርም ያሳደጉት በአንፃራዊ ዕይታ ከእሷ የተሻለ ኑሮ የሚኖሩት አያቱ ወ/ሮ ሻሼ ናቸው፡፡ ነፍስ ሲያውቅ ጀምሮ ጠባቧን ክፍል ከእንግዶች ጋር ይጋሯታል፡፡ ሌሊት በተኙበት ፊታቸው ላይ የሚፈሰው የሰካራም ሽንት ቢያስመርረውም ተስፋ አላስቆረጠውም፡፡ በአቋራጭ ከችግራቸው የሚላቀቁበትን ዕድል ሊያመቻችም አልወሰነም፡፡ በትምህርቱ ገፋበትና በመምህርነት ተመረቀ፡፡
ወ/ሮ ሻሼና መላው ቤተሰባቸው የሚኮራበት አንድ ንብረትም ኖራቸው፡፡ ሚሊዮን ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ ሲመረቅ የተነሳቸውና በኩራት ግድግዳ ላይ የሚሰቅሏቸው ፎቶ ግራፎች ኖራቸው፡፡ ምንም እንኳ ፎቶ ግራፎቹ የተሰቀሉት በዕቃ መካከል ቢሆንም የዘመናት የልፋት ውጤት ነውና ዋጋው በቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ ከድህነት ወለል በታች ለሆነው ለቤተሰቡ ሕይወት የለውጥ ጭላንጭልም ነው፡፡
ሚሊዮን የአያቱ ልጅ ነው፡፡ ከአባቱም ከወላጅ እናቱም የሚቀርበው አያቱን ወ/ሮ ሻሼን ነው፡፡ ቤቱ ውስጥ ከሚኖሩት መካከል በዕድሜ ትንሹ እሱ ነው፡፡ የሚተኛውም እንደ ትንሽነቱ ከአያቱ ጎን ነው፡፡ አያት እንዳሳደገው ግን ቀበጥ አይደለም፡፡ ያለበትን የድህነት ዓለም ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ መቀየርም ይፈልጋል፡፡ በሆነው ባልሆነው ከመበሳጨት ይልቅ ነገ የተሻለ ነገር ይዞ እንደሚመጣ ያውቃልና ተኝቶ አያድርም፡፡
ትምህርቱን በሚማርበት ወቅትም በጎን እንደ ጓደኛው የሚቆጥራቸውን አያቱን በሥራ ያግዛል፡፡ ቡና ያፈላል፣ ወጥ ይሠራል፣ እንጀራም ይጋግራል፡፡
ተመርቆ የማስተማር ሥራ የጀመረው ዘንድሮ ነው፡፡ አሁንም ድረስ ከሥራ መልስ አያቱን ደፋ ቀና ብሎ በሥራ ያግዛል፡፡ ሊጠይቁት የሚመጡ ጓደኞቹንም ቡና አፍልቶ ምሣ ሠርቶ የሚያስተናግዳቸው እሱ ነው፡፡ ከመላ ቤተሰቡ መካከል ጥሩ ሥራ ሲይዝ እሱ የመጀመርያው ነው፡፡ እሱ መመኪያቸውና ተስፋቸው ብቻ አይደለም፡፡ የጥንካሬ ተምሳሌታቸው ጭምርም ነው፡፡
በወር የሚያገኛትን እየቆጠበ ቁም ነገር ላይ ያውላል፡፡ የተጣራ ሁለት ሺሕ ብር እጁ ላይ ይገባል፡፡ አንዱን ሺሕ ዕቁብ ይጥላል፡፡ በተቀረው ወ/ሮ ሻሼ የጎደላቸውን ይሞላል፣ የራሱን ልዩ ልዩ ወጪዎች ይሸፍናል፡፡ ደመወዝ መብላት እንደ ጀመረ የገባው ዕቁብም ደርሶታል፡፡ ቤታችን ውስጥ ቢኖር ብሎ ከልጅነቱ የተመኘውን ቡፌ ገዝቶ ጠባቧን ክፍል አጨናንቋል፡፡ የኤሌክትሪክ ምጣድም የገዛው በቅርቡ በወጣለት ዕቁብ ነው፡፡
ሰፊ የምግብ ጠረጴዛ የምታክለው የወ/ሮ ሻሼ ቤት ብፌና ምጣድ ሲገባባት መተንፈሻ ብታጣም የልጅነት ምኞቱን ዕውን ለማድረግ የቦታ ጥበት ምክንያት አልሆነም፡፡ ወ/ሮ ሻሼ ላለባቸው የልብ ሕመም የሚታዘዝላቸውን መድኃኒትም የሚገዛው ዕቁብ ጥሎ ከሚተርፈው ገንዘብ አብቃቅቶ ነው፡፡ ‹‹አሁን እኔ ደርሻለሁ እግዜር የተመሰገነ ይሁን፤›› ይላል በየቀዳዳው የሚወረውራት ደመወዙ ለእነሱ ብዙ ነገር ማለት እንደሆነች ሲገልጽ፡፡
ከኛ የባሰ ኑሮ ያለው ስንት አለ ሲሉ ባላቸው ነገር ለመፅናናት የሚሞክሩት እንደ ወ/ሮ ምሕረት ኑረዲን ቤተሰብ ያሉ በባሰ ድህነት ውስጥ የሚገኙትን ተመልክተው ነው፡፡ ወ/ሮ ምሕረት የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ሞክራ ስላልተመቻት የልጆቿን ቁጥር መመጠን አልቻለችም፡፡ በ32 ዓመቷ አራት ልጆች ወልዳለች፡፡ የመጀመርያ ልጇ ዕድሜዋ 14 ሲሆን፣ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ነች፡፡ ሁለተኛ ልጇ አሥር፣ ሦስተኛው ሦስት ዓመት፣ የመጨረሻው ደግሞ ገና አንድ ዓመቱ ነው፡፡
ይህ ነው የሚባል ገቢ የላትም፡፡ አባትየው ያስተዳድራቸው የነበረው ሸንኮራ እየሸጠ ነበር፡፡ ባደረበት ሕመም ሕይወቱ ካለፈ ስምንት ወሩ ነው፡፡ ወ/ሮ ምሕረትና ልጆቿ ገና ሐዘናቸው አልወጣላቸውም፡፡ ስለ አባታቸው ማውራት ሲጀምሩ ሳግ ይተናነቃቸዋል፡፡ ወ/ሮ ምሕረት በዚህ ዕድሜዋ አባት የሞተባቸውን ልጆች ለማሳደግ የምታደርገው ትግል የሞት ሽረት ያህል ብርቱ ነው፡፡
በወይዘሮዋ ፊት እልህ፣ ቁጣ፣ ብስጭት ይነበባል፡፡ ሁሉም ነገር ለእሷ እልህ አስጨራሽ ትግል ነው፡፡ የልጆቿን ፍላጎት ማሟላት ሳይሆን በሕይወት የማቆየት ትግል፡፡ ትንሽ ነገር ቱግ የሚያደርጋት በትንሹ በትልቁ የምትከፋ ፈጣሪ ፊቱን ያዞረባት አድርጋ ራሷን የምትቆጥር ናት፡፡ ታላቅ ታናሹን እንዲጠብቅ ግድ ነው፡፡ ከዚያ ውልፍት ያሉ ሲመስላት ቁጣዋ መከራ ነው፡፡
ወ/ሮ ምሕረት እንደ ወ/ሮ ሻሼ የቀበሌ ቤት የላትም፡፡ የምትኖረው አነስተኛ ሱቅ የምትመስል ጠባብ ቤት ውስጥ ተከራይታ ነው፡፡ ማድ ቤት ለሚመስለው የጭቃ ቤት በወር 900 ብር ትከፍላለች፡፡ የምትተዳደረው ቆሎ ቆልታ በመሸጥ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በየሰው ቤት ተዘዋውራ ልብስ በማጠብ የተሻለ ገቢ ታገኝ የነበረ ቢሆንም የመጨረሻ ልጇን ከወለደች በኋላ ተንቀሳቅሶ መሥራት ችግር ሆነባት፡፡ ሕፃኑን አስቀምጣ መሥራት አልቻለችም፡፡ ታላላቆቹ ትምህርት ቤት ስለሚሄዱ የሚጠብቀውም የለውም፡፡ አዝላው ማጠብ ብትችልም ሕፃን የያዘችን ሴት ለማሠራት ፈቃደኛ የሆነ አላገኘችምና ቤት መዋል ብቸኛ አማራጯ ሆነ፡፡
ልጆች ከትምህርት ቤት ሲመለሱ ጠብቃ ሕፃኑን ጥላላቸው ተዘፍዝፎ የዋለ ባቄላና ሽምብራ ከከሰል ማንደጃ ጋር ይዛ ወደ አስፓልት ትሮጣለች፡፡ እስከ ምሽት የተወሰነ ከቸረቸረች በኋላ ትመለሳለች፡፡ የምታገኘው ግን የልጆቿን ጉሮሮ ለመሸፈን እንኳን የሚበቃ አይደለም፡፡ ቁርስ ሳይበሉ ከቤት የሚወጡባቸው ቀናት ብዙ ናቸው፡፡ የምትቋጥርላቸው ምሳም የለም፡፡
ችግሯን የተመለከቱ ‹‹የራጉኤል ሠፈር ልጆች›› የምትላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች የድንች መጥበሻ ማሽን ገዝተው ሰጥተዋታል፡፡ ይህም ተጨማሪ ገቢ ሆኗታል፡፡ ልጆቿ ወደ ትምህርት ቤት ከመውጣታቸው በፊት ቀደም ብላ ወጥታ መንገድ ላይ ብስኩት ትሸጣለች፡፡ በአንድ ጠዋት በ25 ብር የምትገዛውን ዱቄት ብስኩት አድርጋ እየጠበሰች በ45 ብር ታጣራዋለች፡፡ የልጆቿ የትምህርት ቤት መግቢያ ሰዓት እንዳይረፍድባቸው ብን ብላ ወደ ቤት ትመለሳለች፡፡ ደግማ ወደ ሥራ የምትወጣው ልጆች ከትምህርት ቤት ከተመለሱ ከ11 ሰዓት በኋላ ነው፡፡ ግማሽ ኪሎ የሽምብራ፣ አንድ ኪሎ የአተር፣ አንድ ኪሎ የባቄላ ቆሎ በቀን ሽጣ ታድራለች፡፡ ቆሎ ስትሸጥ በቀን ከ30 እስከ 40 ብር ታተርፋለች፡፡
በአጠቃይ በቀን የምታገኘው ገንዘብ የልጆቿን ቀለብ ለመሸፈን የሚበቃትም አይደለም፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ በየወሩ የሚጠበቅባት 900 ብር የቤት ኪራይ አለ፡፡ የቤት ኪራይ እንድትከፍል የሚጠበቀው ወር በገባ በስምንተኛው ቀን ነው፡፡ ብትቸገርም አከራዮቿ ከአንድ ቀን በላይ አይታገሷትም፡፡ ከሁሉ በላይ የቤት ኪራይ ነገር እንደሚያሳስባት ትናገራለች፡፡
ኑሮ ለወ/ሮ ምሕረት በሕይወት ለመቆየት የሚደረግ ትግል፣ ውጥረት የበዛበት ዓለም ነው፡፡ በገጿ ላይ የሚነበበው ጭንቀት ኑሮን የማሸነፍ እልህ ነው፡፡ ፈገግታ የራቀው ገጿ የፈካው ‹‹እንዲህ በይ እንዲህ ሁኚ›› የሚላት ፎቶ ጋዜጠኛ ከፊቷ ሲቆም ነው፡፡ ትርጉም የሌለው የሚመስለው ሕይወቷ፣ ከድህነት ጋር ትግል የገጠመችበት ኑሮዋ ለአፍታ የሰው ትኩረት ቢስብ፣ በካሜራ እናስቀረው ቢሏት ተደብቆ የኖረው ጥርሷ አልከደን አለ፡፡ ፊቷን ሸፍና እፍረት የተቀላቀለበት ሳቅ ሳቀች፡፡
እንዲህ ያሉ የራጉኤል አካባቢ ድሆችን ባላቸው አቅም የሚረዱት የዚያው አካባቢ ነዋሪዎች ያላቸውን በማዋጣት ነው፡፡ እንዲህ ባለ ተግባር የሚሳተፉ ሰዎች እግዚአብሔር አብ ዘቅዱስ ራጉኤል የተሰኘ ማኅበር አቋቁመዋል፡፡ የአገርህን እወቅ ማኅበር ሆኖ የተቋቋመው በ1995 ዓ.ም. እንደነበር የሚናገሩት የማኅበሩ ሰብሳቢ አቶ አለባቸው ምሥጋናው፣ ቆይቶ ማኅበሩ ዓላማውንም ስያሜውንም ለውጦ በበጎ አድራጎት ተግባር መሰማራቱን ይናገራሉ፡፡
30 አባላት ያሉት ሲሆን፣ 200 የሚሆኑ ታዳጊዎችን ያስተምራሉ፡፡ ተንቀሳቅሰው መሥራት የማይችሉ እንደ ወ/ሮ ሻሼ ያሉ ሰዎችን ከተቻለ በገንዘብ፣ ካልሆነ ደግሞ ገቢ ሊያስገኝላቸው የሚችሉ አጋጣሚዎችን ይፈጥሩላቸዋል፡፡ ለምሳሌ ወ/ሮ ሻሼን ለመርዳት ያሰቡት ወዛደሮች የሚያድሩበትን ቆጥ የተመቸ አድርጎ በመሥራት ነው፡፡ ትኩረት አድርገው የሚሠሩት ግን ተማሪዎች ላይና እንደ ወ/ሮ ምሕረት ባሉ ተንቀሳቅሰው መሥራት በሚችሉ የማኅበረሰቡ ክፍሎች ላይ እንደሆነ አቶ አለባቸው ይናገራሉ፡፡
‹‹ችግሩ ያለው ያልሞቱ ያልዳኑ ሰዎች ላይ ነው፡፡ ሰዎች ሊሞቱ ሲሉ የሚያልፋቸው የለም ቋፍ ላይ የደረሱትን ግን ማንም ሰው ዞር ብሎ አያያቸውም፤›› የሚሉት አቶ አለባቸው ምንም የሌላቸው ነገር ግን ለልመና ያልወጡ ሰዎችን መርዳት ላይ ማኅበሩ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያሉትን ሰዎች ለመርዳት የሚያደርጉት ጥረት ካለው የተረጂው ቁጥር አንፃር እዚህ ግባ የሚባል አልሆነም፡፡ እስካሁን 2,000 ሰዎችን መድረስ ቢችሉም መርካቶ አካባቢ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ከዚህ በብዙ እጥፍ ይበልጣሉ፡፡ የማኅበሩ አባላት የሚያደርጉት ርብርብም እንደየአቅማቸው የተወሰነ ነው፡፡
ይረዳሉ ብሎ ከተረጂ ስም ዝርዝር መሀል እንዲገቡ የተደረጉ እንኳ ዙር ሳይደርሳቸው ብዙ ይቆያሉ፡፡ በማኅበሩ አባላት መካከል የሆኑት አቶ ገዛኸኝ ሮበሌ ያለውን ችግር ሲያስረዱ ‹‹ከኔ ቤት ፊት ለፊት አቶ በቀለ የሚባሉ አንድ አዛውንት ይኖሩ ነበር፡፡ የሚተዳደሩት ወፍጮ ቤት እየሠሩ በሚያገኙት ነበር፡፡ እርጅና ሲጫናቸው ቤት ውስጥ ቀሩ፡፡ የሚኖሩትም ብቻቸውን ስለነበርና ይህ ነው የሚባል ገቢ ስላልነበራቸው፣ የሚኖሩበትም ቤት በላያቸው ላይ ሊፈርስ ሲደርስ ማኅበራችን ሊረዳቸው በዕቅድ ያዛቸው፡፡ ነገር ግን ቤቱን ፈጥኖ ለማደስ አልቻልንም፤›› ይላሉ፡፡ የአካባቢው ነዋሪ ምግብ እያቀረበላቸው አንዳንድ የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ እያደረገ ትንሽ ከቀዩ በኋላ አቶ በቀለ ቤታቸው ሳይታደስ ሕይወታቸው አለፈ፡፡ አጋጣሚው አባላቱን ያስቆጨ ነበር፡፡ እንዲህ ያሉት ክስተቶች ማኅበሩን ሌሎች በጎ ፈቃደኞች እንዲያግዙት ማድረግ የግድ እንደሆነ፣ በተቻለ መጠንም ማኅበረሰቡ እንዲያውቃቸው ማድረጉ ወሳኝ እንደሆነ ተስማምተው ተልዕኮውን የማስተዋወቅ ሥራ መጀመሩን አቶ ገዛኸኝ ይናገራሉ፡፡ አቶ አለባቸው፣ እንዲህ ባለ አስከፊ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ግለሰቦችን ለመርዳትም ለማኅበሩ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ሳይሆን ለጋሾች የተመረጡ ተረጂዎችን እንዲደግፉ እንፈልጋልን ብለዋል፡፡