Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ ኤርፖርት ተርሚናል ማስፋፊያና የሆቴል ፕሮጀክቶች ሊመረቁ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አቪዬሽን ቡድን የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የመንገደኞች ማስተናገጃ ሕንፃ ማስፋፊያና ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ለማስመረቅ በዝግጅት ላይ  እንደሆነ ታወቀ፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ አቪዬሽን ቡድን ጋር የተቀላቀለው የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት፣ የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የመንገደኞች ማስተናገጃ ሕንፃ ማስፋፊያ ፕሮጀክት በ2007 ዓ.ም. መጀመሩ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የግንባታው ወጪ 250 ሚሊዮን ዶላር ተገምቶ የነበረ ቢሆንም፣ በሒደት በተጨመሩ ሥራዎች ምክንያት ወጪው ወደ 363 ሚሊዮን ዶላር አድጓል፡፡

የሕንፃው ንድፍ የተሠራው ሲፒጂ በተሰኘ የሲንጋፖር ኩባንያ ሲሆን፣ ግንባታውን የሚያካሂደው ሲሲሲሲ የተባለ የቻይና ኮንትራክተር ነው፡፡ የፕሮጀክት ክትትል ሥራውን ኤዲፒአይ የተሰኘ የፈረንሣይ ኩባንያ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ለፕሮጀክቱ የሚውል ብድር የተገኘው ከቻይና ኤግዚም ባንክ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ሦስት ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ በሁለት ኮንትራት ውሎች የታሰረ ነው፡፡

የመጀመርያ ክፍሉ የአዲስ አበባ ኤርፖርት ዋና የመንገደኛ ማስተናገጃ ሕንፃ የምሥራቅና ምዕራብ ክፍል ማስፋፊያ ነው፡፡ በሁለተኛ ውል የተፈረሙት የቪአይፒ ተርሚናል ግንባታና የአገር ውስጥ ተርሚናል ማስፋፊያ ሥራዎች ናቸው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2003 የተመረቀው ተርሚናል ሁለት በዓመት ስድስት ሚሊዮን መንገደኞች እንዲያስተናግድ ተደርጎ የተገነባ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት 11 ሚሊዮን መንገደኞች በማስተናገድ ላይ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት መጨናነቅ በመፈጠሩ በመንገደኞች ዘንድ ቅሬታ ፈጥሯል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ አበባን የአፍሪካ ቀዳሚ የአቪዬሽን መናኸሪያ ለማድረግ የነደፈውን ዕቅድ ለማሳካት፣ መጠነ ሰፊ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ማካሄድ አስፈላጊ እንደሆነ የአየር መንገዱ ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ኤርፖርት ዋና ተርሚናል 48,000 ካሬ ሜትር የወለል ስፋት ያለው ሲሆን፣ በማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ተጨማሪ 74,000 ካሬ ሜትር ወለል እየተገነባ ነው፡፡ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ዋና ኃላፊ አቶ ኃይሉ ለሙ (ኢንጂነር) ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የፕሮጀክቱ 1/3ኛ አካል የሆነው የምሥራቁ ክፍል ግንባታ ተጠናቆ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ የፕሮጀክቱ 2/3ኛ አካል የሆነው የምዕራቡ ክፍል ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ የሜካኒካል፣ የኤሌክትሪካል፣ የፍሳሽ፣ የአየር ማስተላለፊያና የእሳት መከላከያ መሠረተ ልማቶች ሥራ በመጠናቀቅ ላይ እንደሆነ አቶ ኃይሉ ተናግረዋል፡፡ የወለል ማንጠፍና ቀለም ቅብ ሥራ በመካሄድ ላይ ሲሆን፣ የመኪና ማቆሚያና የመዳረሻ መንገድ ሥራ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ የምዕራቡ ክፍል ግንባታ 80 በመቶ እንደተጠናቀቀና በአጠቃላይ የዋና ተርሚናሉ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ሥራ 83 በመቶ መገባደዱን አቶ ኃይሉ ገልጸዋል፡፡

ዋና ተርሚናሉ ገቢና ወጪ መንገደኞች የሚስተናገዱበት ምድርና ሁለት ፎቆች አሉት፡፡ ሁለት ኤስካሌተሮች፣ እያንዳንዳቸው 26 መንገደኛ የሚይዙ ስምንት አሳንሰሮች፣ የሻንጣ መቀበያና ማጓጓዣ መሣሪያና የእሳት መከላከያ መሠረተ ልማት ተመርተው በመገጠም ላይ ይገኛሉ፡፡ በማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ተጨማሪ 72 የመንገደኛ ማስተናገጃ መስኮቶችና 21 የመሳፈሪያ በሮች እንደሚገነቡ ታውቋል፡፡

የማስፋፊያ ሥራው ሙሉ በሙሉ የሚጠናቀቀው ሰኔ 2011 ዓ.ም. ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፕሮጀክቱን በቅርቡ በሚካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ወቅት ለማስመረቅ በዝግጅት ላይ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ይመርቁታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የፕሮጀክቱ ሁለተኛ ክፍል የቪአይፒ ተርሚናል ሲሆን፣ ግንባታው በመስከረም 2010 ዓ.ም. መጀመሩ ይታወሳል፡፡ በቀድሞ የኤርፖርት ጉምሩክ መጋዘን አካባቢ የሚገነባው ባለሁለት ፎቅ የቪአይፒ ተርሚናል የተለያዩ ሳሎኖች፣ የስብሰባና የኮክቴል አዳራሽ ይኖረዋል፡፡ የራሱ መኪና ማቆሚያ ሥፍራና መዳረሻ መንገድ (ከቦሌ ቀለበት መንገድ ተርሚናሉ ድረስ) እንደሚገነባለት ታውቋል፡፡

የመሠረትና የምድር ወለል ግንባታ ተጠናቆ ኮለኖች በመቆም ላይ እንደሆኑ የገለጹት አቶ ኃይሉ፣ የቪአይፒ ተርሚናሉ ግንባታ ከአንድ ዓመት በኋላ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል፡፡ የተርሚናል አንድ (የአገር ውስጥ በረራ ተርሚናል) ማስፋፊያ ሥራ በቅርቡ የተጀመረ ሲሆን፣ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ታውቋል፡፡

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ65 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያስገነባው ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ለማስመረቅ በዝግጅት ላይ እንደሆነ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመሠረተ ልማት ዕቅድና ልማት ሥራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም ተስፋዬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በ20,000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው ባለ ስምንት ፎቅ ሆቴል ግንባታ ተጠናቆ አስፈላጊ ዕቃዎችና መሣሪያዎች ተገጥመዋል፡፡

ስካይላይት ተብሎ የተሰየመው ሆቴል 373 የመኝታ ክፍሎች፣ ሦስት ምግብ ቤቶች (የቻይና፣ የኢትዮጵያና የአውሮፓ)፣ ሦስት ቡና ቤቶች አሉት፡፡ ከ2,000 በላይ እንግዶች የሚያስተናግድ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ እያንዳንዳቸው 30 ሰዎች የሚይዙ አምስት የስብሰባ ክፍሎች እንዳሉት አቶ አብርሃም ገልጸዋል፡፡ የስፓ፣ የጂምናዚየምና የማሳጅ አገልግሎት መስጫ፣ የጤና ማዕከል፣ የመዋኛ ገንዳ፣ አነስተኛ የጎልፍ መጫወቻ ሜዳ አካቶ ይዟል፡፡ የተለየ የቡና መሸጫ ካፌ፣ የአየር ትኬት መሸጫና የስጦታ መደብር ይኖረዋል ተብሏል፡፡

ትልቅ የምግብ ማዘጋጃ ማዕድ ቤት፣ የልብስ ንፅህና መስጫና ማቀዝቀዣ ክፍሎች ለአገልግሎት ዝግጁ ተደርገዋል፡፡ አምስት መቶ መኪኖች ማቆም የሚችል ሥፍራ መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡ የሆቴሉ ንድፍና ግንባታ ሥራ ያከናወነው አቪክ የተሰኘ የቻይና ኩባንያ ሲሆን፣ የፕሮጀክት ክትትል ሥራ የሚያከናውነው ስለሺ ኮንሰልት የተባለው አገር በቀል አማካሪ ድርጅት ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጪ 35 በመቶ የሸፈነ ሲሆን፣ 65 በመቶ የቻይና ኤግዚም ባንክ በብድር መልክ እንዳቀረበ ታውቋል፡፡

400 ያህል ሠራተኞች ተቀጥረው ሥልጠና እየተሰጣቸው እንደሆነ የገለጹት አቶ አብርሃም፣ ሆቴሉ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ ለ800 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡ ሆቴሉ ከኤርፖርት ማስፋፊያ ፕሮጀክት ጋር በአንድ ላይ ጥር 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ለማስመረቅ ታቅዷል፡፡

ሆቴሉ ጂኤስኤችኤም በተባለ የቻይና ሆቴል አስተዳደር ኩባንያ እንደሚተዳደር የገለጹት አቶ አብርሃም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ አበባን የቻይና መንገደኞች ዋነኛ መተላለፊያ የማድረግ ዕቅድ ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1973 ወደ ቤጂንግ በረራ የጀመረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት የቻይና አራት ከተሞች የሚበር ሲሆን፣ በሳምንት 36 በረራዎች ያደርጋል፡፡ በቀን በቻይናና አዲስ አበባ መሀል 4,000 ያህል ቻይናውያን መንገደኞች የሚያጓጉዘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ቻይናውያን የበረራ አስተናጋጆች አሠልጥኖ በማሰማራት በአዲስ አበባ ኤርፖርት ለቻይናውያን መንገደኞች መረጃ የሚሰጡ ቻይናውያን ሠራተኞች መድቦ እየሠራ ይገኛል፡፡ አዲስ በተገነባው ሆቴል ትልቅ የቻይና ምግብ ቤትና በቻይና ባህላዊ ሥዕሎችና ጌጣ ጌጦች የተንቆጠቆጡ ስድስት የተለዩ የቪአይፒ መመገቢያ ክፍሎች ክፍሎች ተዘጋጅተዋል፡፡

‹‹ዓላማችን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቻይናውያን ተጓዦችና ቱሪስቶች መሳብ ነው፤›› ያሉት አቶ አብርሃም፣ ይህ ማለት ግን በሌሎች ዜጎች ላይ አድልኦ ይፈጸማል ማለት እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሆቴል አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅታችንን እያጠናቀቅን ነው፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሆቴል ሥራ መግባቱ አንዳንድ ባለሆቴሎችን አላስደሰተም፡፡ ‹‹ገበያ ይሻማል› የሚል ሥጋት ፈጥሯል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓላማ ያሉትን ሆቴሎች ገበያ መሻማት እንዳልሆነ አቶ አብርሃም ገልጸዋል፡፡ ‹‹የእኛ ዓላማ ለደንበኞቻችን ከፍተኛ ጥራት ያለው ምርትና አገልግሎት ማቅረብ ነው፡፡ በቀን 400 ያህል መንገደኞች አዲስ አበባ በሚገኙ ሆቴሎች እናሳርፋለን፡፡ ስካይላይት ሥራ ሲጀምር 150 የሚሆኑትን በራሳችን ሆቴል ብናሳርፍ 250 የሚሆኑትን በሌሎች ሆቴሎች እናሳርፋለን፡፡ በስካይላይት የምናሳርፋቸው የጎልድ፣ የፕላቲኒየም አባሎቻችንንና በኢትዮጵያ ሆሊዴይስ በኩል ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ የምናመጣቸውን ቱሪስቶች ይሆናል፡፡ የሆቴሉ መገንባት የአየር ጉዞና የሆቴል አገልግሎት በፓኬጅ ለመሸጥ ይጠቅመናል፡፡ ገበያው ሰፊ በመሆኑ ለሁላችንም ይበቃብናል፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም ሆቴሉ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሁለተኛ ሆቴል ግንባታ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ ሁለተኛው ሆቴል የሚገነባው ከስካይላይት አጠገብ በሚገኝ 22,000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ነው፡፡ በ150 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚገነባው ሆቴል 637 የመኝታ ክፍሎች እንደሚኖሩትና የሆቴሉን ንድፍና ግንባታ የሚያካሂደው አቪክ ኩባንያ እንደሆነ ታውቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የንድፍ ሥራው በመከናወን ላይ እንደሆነ የገለጹት አቶ አብርሃም፣ ግንባታው ከሦስት ወራት በኋላ እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት አምስት ዓመታት የኤርፖርት ማስፋፊያ ፕሮጀክቱን ሳይጨምር 550 ሚሊዮን ዶላር የፈጁ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እንዳካሄደ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች