Monday, November 28, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናየፀጥታ አስከባሪዎችን ኃይል አጠቃቀምና ተጠያቂነት የሚወስኑ ሁለት ሕጎች ለማውጣት ዝግጅት እየተደረገ ነው

  የፀጥታ አስከባሪዎችን ኃይል አጠቃቀምና ተጠያቂነት የሚወስኑ ሁለት ሕጎች ለማውጣት ዝግጅት እየተደረገ ነው

  ቀን:

  የአገሪቱ የፀጥታ አስከባሪዎች የኃይል አጠቃቀም፣ እንዲሁም ኃላፊነታቸውን በሚወጡበት ወቅት ለሚፈጽሟቸው ድርጊቶች የሕግ ተጠያቂነትና ቁጥጥር እንዲደረግባቸው የሚያስችሉ ሁለት አዋጆች በመረቀቅ ላይ መሆናቸው ተገለጸ።

  የሕግ ረቂቅ ሰነዶቹን በማዘጋጀት ላይ ያለው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች የድርጊት መርሐ ግብር ጽሕፈት ቤት ነው።

  የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ይበቃል ግዛው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የፀጥታ አስከባሪዎች ኃይል አጠቃቀም የመጀመሪያ ረቂቅ በአሁኑ ወቅት የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በቅርቡም ባለድርሻ አካላት በሚሳተፋት መድረክ ቀርቦ የበለጠ ለማዳበር ውይይት ይደረግበታል።

  የአገሪቱ ፀጥታ አስከባሪዎች የኃይል አጠቃቀም ቁጥጥር የሚደረግበት ወጥ የሆነና ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን የሚያሟላ ሕግ ባለመኖሩ፣ የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች መጠበቃቸውን ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ስለሆነ ረቂቅ ሕጉን ማዘጋጀትና በሕግ አውጪው እንዲፀድቅ ማድረግ አስፈላጊ እንዳደረገው አቶ ይበቃል ገልጸዋል።

  ረቂቅ ሕጉ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን መሠረት በማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን የገለጹት አቶ ይበቃል፣ በዋናነት የፀጥታ አስከባሪ ፖሊሶችም ሆኑ የማረሚያ ቤቶች የጥበቃ ሠራተኞች ኃይል መጠቀም የሚችሉት ምን ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥም እንደሆነ፣ በምን ሁኔታ ኃይል መጠቀም እንደሚቻልና እንደማይቻል የሚወስን እንደሚሆን አስረድተዋል።

  አሁን በሥራ ላይ የሚገኙ የፌዴራል ፖሊስ ማቋቋሚያና ማስፈጸሚያ ሕጎች ላይ የኃይል አጠቃቀምን የተመለከቱ ድንጋጌዎች ቢኖሩም፣ ተጠያቂነትን ለማስፈንና የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ለመጠበቅ የሚያስችል ደረጃ እንደሌላቸው፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን እንደማያሟሉ ተናግረዋል።

  ይህ የኃይል አጠቃቀም ሕግ ውይይት ተደርጎበት ከዳበረ በኋላ በቀጣዮቹ ሁለት ወይም ሦስት ወራት ውስጥ፣ በፓርላማ ፀድቆ ተግባራዊ እንዲሆን መታቀዱንም አስረድተዋል።

  ከዚህ ሕግ ዓላማዎች ጋር የሚቆም የፀጥታ ኃይሎች ተጠያቂነትን የሚወስን ሌላ የሕግ ሰነድ በመረቀቅ ላይ እንደሚገኝም አቶ ይበቃል ገልጸዋል።

  ሁለቱም ሕጎች የፀጥታ ኃይሎች የኃይል አጠቃቀም በሕግ ቁጥጥር እንዲደረግበትና ከኃይል አጠቃቀማቸው ጋር በተገናኘ ሕጋዊ ተጠያቂነት እንዲኖርባቸው የሚያስችሉ መሆናቸውን፣ በዚህም የዜጎች ሰብዓዊ መብት በበቂ ሁኔታ እንዲጠበቅና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመገንባት ሒደቱ እንዲሟላ የሚያስችሉ እንደሚሆኑ እምነታቸውን ገልጸዋል።

  በተለያዩ ጊዜያት በአገሪቱ ካጋጠሙ የፀጥታ ችግሮች ጋር በተገናኘ ፀጥታ አስከባሪዎች የወሰዷቸው የኃይል ዕርምጃዎች ሕጋዊና ተመጣጣኝ የኃይል ዕርምጃ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ምርመራዎች፣ የፀጥታ አስከባሪዎች ተመጣጣኝ ኃይል መጠቀማቸውን ድርጊቶችን እንዲመረምሩ የተቋቋሙ ኮሚቴዎች ሪፖርት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ ከእነዚህም መካከል በ1997 ዓ.ም. በምርጫ ማግሥት በአዲስ አበባ ተከስቶ ከነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ የፀጥታ ኃይሎች የወሰዱት የኃይል ዕርምጃ ተመጣጣኝ እንደነበረ ሪፖርት መደረጉ አይዘነጋም፡፡ በተመሳሳይ ከሁለት ዓመት በፊት በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች በወጣቶች ከተካሄዱ የፖለቲካ ተቃውሞዎችና ጋር በተያያዘ የፀጥታ ኃይሎች የወሰዱት የኃይል ዕርምጃ ተመጣጣኝ እንደነበረ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ይኸው ኮሚሽን በተመሳሳይ ወቅት በአማራ ክልል ከቅማንት የማንነት ጥያቄ ጋር በተገናኘ፣ ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር ፀጥታ አስከባሪዎች ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል መጠቀማቸውን ለፓርላማ ሪፖርት በማድረግ፣ በሕግ እንዲጠየቁም የውሳኔ ሐሳብ ማቅረቡ አይዘነጋም።

  የፀጥታ ኃይሎች የኃይል አጠቃቀምን በተመለከተ በተለያዩ ወቅቶች የተደረጉት እነዚህ ምርመራዎች የኃይል አጠቃቀሙ ተመጣጣኝ ወይም ተመጣጣኝ እንዳልነበረ ለመወሰን በመመዘኛነት የተጠቀሙት ግብዓት ምን እንሆነ፣ እንዲሁም ግብዓት የሆነው መመዘኛና መረጃ ተቀባይነት ብሎም የተደረሰበት ድምዳሜ ተዓማኒነት እስካሁን አከራካሪ ከመሆኑ ባለፈ፣ ከዜጎች ሰብዓዊ መብቶች መከበር ይልቅ ለፖለቲካዊ ግብ ትኩረት ያደረጉ ምርመራዎች እንደነበሩ በስፋት ይተቻሉ።

  ይህ በእንዲህ እንዳለ ዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ሰሞኑን ለፓርላማ ባቀረቡት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት የወንጀል ሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ፣ እንዲሁም የጦር መሣሪያ አያያዝና ቁጥጥር አዋጆችን የማርቀቅ ሒደት በመከናወን ላይ እንደሆነ ገልጸዋል።

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...