Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናለህዳሴ ግድቡ ግንባታ 98.7 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉ ተገለጸ

ለህዳሴ ግድቡ ግንባታ 98.7 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉ ተገለጸ

ቀን:

ለኃይድሮሊክ ስትራክቸር ሥራው የ126 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈረመ

የዛሬ ሰባት ዓመት ገደማ ግንባታው የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የፕሮጀክትና የፋይናንስ አስተዳደር፣ እንዲሁም ወለድና የእርጅና ወጪ ጨምሮ በአጠቃላይ 98.7 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ተናገሩ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህዳሴ ግድቡ ግንባታና አጠቃላይ ሁኔታዎችን የተመለከተ ሪፖርት እንዲቀርብለት ባዘዘው መሠረት፣ ሚኒስትሩና የሥራ ባልደረቦቻቸው ሐሙስ ታኅሳስ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. በምክር ቤቱ ተገኝተው ሪፖርታቸውን በማቅረብ ለተነሱላቸው ጥያቄዎችም ተጨማሪ ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል።

ሚኒስትሩ ባቀረቡት ሪፖርት የህዳሴ ግድቡ ግንባታ በአሁኑ ወቅት ለደረሰበት ደረጃና ለተሠሩ ሥራዎች ወጪ በተደረገው ፋይናንስ መካከል ከፍተኛ ልዩነት እንደሚስተዋል ገልጸው፣ በአጠቃላይ ለግንባታ 74.5 ቢሊዮን ብር ወጪ ቢደረግም የፕሮጀክት አስተዳደር፣ የፋይናንስ አስተዳደር፣ የወለድና የዲፕሪሴሽን (depreciation) ወጪዎችን አጠቃሎ የተፈጸመው ክፍያ 98.7 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስረድተዋል።

ግድቡን ለመገንባት ከተመረጡ ኩባንያዎች ጋር የተፈጸመውን የሥራና የክፍያ ውል፣ እንዲሁም እስካሁንወጪ የተደረገውን ክፍያ ዘርዝረው አቅርበዋል።

 በዚህም መሠረት የሲቪል (የግንባታ) ሥራዎችን ለማከናወን ከተመረጠው የጣሊያን ኩባንያ ሳሊኒ ጋር በተገባው ውል መሠረት ለሚያከናውናቸው ሥራዎች 21.4 ቢሊዮን ብርና 1.47 ቢሊዮን ዮሮ ለመክፈል ውል መገባቱን፣ በዚህም መሠረት ኩባንያው ከተጣለበት የግንባታ ኃላፊነት ውስጥ 82 በመቶውን መፈጸሙንና ለዚህም ከአጠቃላይ የግንባታ ክፍያ ውል 81.6 በመቶው እንደተከፈለው አስረድተዋል።

 የኃይድሮ ሜካኒካልና የብረት ስትራክቸር ሥራዎችን ለመሥራት የተመረጠው የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ጋር የተገለጹትን ተግባራት ለመፈጸም በአጠቃላይ የ25.6 ቢሊዮን ብር ውል መገባቱን፣ ከተሰጡት አጠቃላይ ሥራዎች ውስጥ የፈጸመው 23 በመቶውን ብቻ እንደሆነ ነገር ግን ከአጠቃላይ ክፍያው 16.8 ቢሊዮን ብር እንደተከፈለው ገልጸዋል።

 የህዳሴ ግድቡ ባለቤትን በመወከል ግንባታውን እንዲቆጣጠር ከተመረጠው አማካሪ ኩባንያ ለሚሰጠው አጠቃላይ አገልግሎት 242.9 ሚሊዮን ብርና በውጭ ምንዛሪ 120.5 ሚሊዮን ዮሮ ለመክፈል ውል እንደተፈጸመ፣ እስካሁን ለሰጠው አገልግሎትም  40 ሚሊዮን ብርና 33.4 ሚሊዮን ዩሮ መከፈሉን አስረድተዋል።

 ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚይዘው ውኃ በሚተኛበት ሥፍራ የሚገኘውን ቁጥቋጦ ለመመንጠር 5.1 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ክፍያ ለመፈጸም ለሥራው ከተመረጠው ሜቴክ ጋር ውል መፈጸሙን፣ ከዚህ ውስጥ 2.5 ቢሊዮን ብር ወይም 50 በመቶ ክፍያ መፈጸሙን ተናግረዋል። በሜቴክ የተከናወነው የምንጣሮ ሥራ 26.6 በመቶ ያህል ብቻ መሆኑ በአየር ካርታ ሥራ ባለሙያዎች መረጋገጡን አስረድተዋል። በውጭ ምንዛሪ ለመክፈል በተገባው ውል መሠረት ለሳሊኒ 1.28 ቢሊዮን ዩሮ መከፈሉንና ክፍያው በተፈጸመበት ወቅት የምንዛሪ ተመኑ በአንድ ዩሮ 22.5 ብር እንደነበር አስታውቀዋል።

በአጠቃላይ የግድቡ ግንባታ ለማጠናቀቅ ከተገባው የክፍያ ውል ውስጥ እስካሁን 74.55 ቢሊዮን ብር እንደተከፈለ፣ ነገር ግን ከላይ በተገለጹት ተጨማሪ የወጪ ዓይነቶች ምክንያት አጠቃላይ ክፍያው 98.7 ቢሊዮን ብር መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የህዳሴው ግድብ ግንባታ አፈጻጸም በአሁኑ ወቅት የሚገኝበት 65.5 በመቶ መሆኑን፣ የተከፈለውና የቀረው ግንባታ ከሚያስፈልገው ወጪ አንፃር ሲመዘን መንግሥት ፕሮጀክቱን ለመገንባት የተከተለው መንገድ ከጅምሩ ትልቅ ስህተት መሆኑን ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

ይህ ስህተትም ዋናውንና ውስብስብ የሆነውን የኃይድሮ ሜካኒካል ሥራ እውቀቱም ሆነ ልምዱ ለሌለው ሜቴክ መስጠቱ እንደሆነ ሚኒስትሩ አስረድተዋል። በዚህም ምክንያት ሁለት ጉዳቶች በአገሪቱ ላይ መድረሳቸውን ጠቁመዋል።

 አንደኛው ጉዳት በሜቴክ ምክንያት ግንባታው በመዘግየቱ ከፍተኛ ተጨማሪ ወጪ አገሪቱ እንድታወጣ መዳረጉ ሲሆን፣ ሌላው ግንባታው ባይዘገይ ኖሮ በቅድሚያ ወደ ኃይል ማመንጨት ሥራ ከሚገቡት ሁለት ተርባይኖች ሊገኝ የሚችለውን 740 ሜጋ ዋት የኃይል አቅርቦት በመታጣቱ የመጣ ጉዳት መሆኑን አስረድተዋል።

የፕሮጀክቱን ሁለት ተርባይኖች ወደ ኃይል ማመንጨት ሥራ ለማስገባት አስፈላጊው የማፋጠን ሥራዎች ታቅደው እንዲተገበሩ እየተሠራ እንደሆነ፣ ከሁለት ዓመት በኋላ በታኅሳስ ወር 2013 ዓ.ም. ለማመንጨት ታቅዶ አስፈላጊው ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ሙሉ የግዱቡ ግንባታ በታኅሳስ 2015 ዓ.ም. ይጠናቀቃል ተብሎ መታቀዱንም አክለው ገልጸዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በአብዛኛው ያነሷቸው ጉዳዮች፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ጨምሮ እንዴት ችግሩን መቅረፍ እንዳልቻሉና ለተገለጹት ችግሮች ሁሉ እንዴት ሜቴክ ብቻ ተጠያቂ ይሆናል፣ እንዲሁም ለተፈጸመው በደል ሕጋዊ ተጠያቂነት ሊኖር እንደሚገባ በሚሉት ዙሪያ ያጠነጠኑ ነበሩ።

ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ የችግሩ መንስዔ የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ከባለቤቱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ውጪ በሆነ የተለየ አደረጃጀት ሥር በመዋቀሩ መሆኑ ገልጸዋል፡፡ ራሱን በቻለ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት መሪነት ትዕዛዞችን ከኤሌክትሪክ ኃይል ቦርድ ጽሕፈት ቤት እየተቀበለ እንደሚፈጽም፣ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ አልፎ አልፎ ለሚኒስቴሩ ሪፖርት እያደረገ ሲከናወን መቆየቱን አስረድተዋል። ከፕሮጀክቱ ባለቤት ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር የነበረው ግንኘነት የላላ እንደነበርና ከክፍያ ጉዳዮች ውጪ ግንኙነት እንዳልነበረው አስረድተዋል።

የግድቡን ግንባታ ሒደት የሚመለከቱ ሪፖርቶች በሚስጥር ተይዘው የሚቆዩበት አሠራር እንደነበረም ጠቁመዋል፡፡

ከአሁን በኋላ እንዲህ ዓይነቱ አሠራር እንደማይኖርና ማናቸውም ፕሮጀክቱን የሚመለከቱ ጉዳዮች በግልጽ ይፋ እንደሚደረጉ ያስታወቁት ሚኒስትሩ፣ ፕሮጀክቱ ሕዝብ እንደተመኘው እንደማይቀርና የሕዝቡን ዓመኔታ ለመመለስም እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ፓዎር ቻይና ከተሰኘው ኩባንያ ጋር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የኃይድሮሊክ ስቲል ስትራክቸር ግንባታ ለማከናወን የ125.6 ሚሊዮን ዶላር የግንባታ ስምምነት መፈራረማቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ የኮንትራት ስምምነቱ የተከናወነው የውኃ መቀበያ አሸንዳዎችንና የመቆጣጠሪያ በሮችን እንዲሁም 11 ኃይል ማመንጫ ተርባይኖችን የዲዛይን፣ የአቅርቦት፣ የገጠማ፣ የፍተሻና የሙከራ ሥራዎች ለማከናወን እንደሆነ በፊርማ ሥነሥርዓቱ ወቅት ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ  አብርሃም በላይ (ዶ/ር)ና በኢትዮጵያ የፓዎር ቻይና ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ቲያን ስምምነቱን መፈራረማቸው ታውቋል፡፡ ወሳኝ የተባሉት የግድቡ የብረታብረት ሥራዎች እ.ኤ.አ. በጁን 2020 ይጠናቅቃሉ የተባለ ሲሆንአጠቃላይ የግድቡ ግንባታም እ.ኤ.አ. በ2022 ተጠናቆ መንግሥት እንደሚረከበው ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...