ኢትዮጵያዊው ወጣቱ የረዥም ርቀት ሯጭ ሰሎሞን ባረጋ ዓምና በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ፍጻሜ በብራሰልስ በ5000 ሜትር የዓለም ምርጥ ሰዓትን 12፡43.02 በማስመዝገብ ከማሸነፉም በላይ የዓለም ከ20 ዓመት በታች ሪከርድን መጨበጡ ይታወሳል፡፡
ኢንተርናሽናል አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) ባለፈው ሳምንት አጋማሽ በድረ ገጹ ይፋ እንዳደረገው እ.ኤ.አ. በ2019 አንፀባራቂ አትሌቶች ይሆናሉ ካላቸው ስምንቱ መካከል የተጠቀሰው ሰሎሞን ባረጋ ነው፡፡
በ2008 እና 2009 ዓ.ም. በዓለም ከ20 እና ከ18 ዓመት በታች ሻምፒዮና ስኬታማ የነበረው ሰሎሞን ዘንድሮም ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮናም ችሎታውን እንደሚያሳይና የዓለም ክብረ ወሰንንም ሊያሻሽል እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
ዓምናም ከምርጥ አምስት አትሌቶች ውስጥ ተካትቶ የነበረው ሰሎሞን ዘንድሮ የ5000 ሜትር የዓለም ክብረ ወሰንን ለመስበር ማቀዱን ለሚዲያዎች መናገሩ አይዘነጋም፡፡
‹‹የራሴን ፈጣን ሰዓት የማሻሻል ዕቅዴ ግቡን መቷል፡፡ አሁን ደግሞ የማልመው የ5000 ሜትር የዓለም ክብረ ወሰንን ማሻሻል ነው፤›› ሲል መናገሩን ኢትዮ ላይቭ ሶከር በዘገባው አስታውሷል፡፡
የዓምናው የሰሎሞን ስኬት ከርሱ ባሻገር በፎቶውም ተንፀባርቋል፡፡ በ2010 ዓ.ም. በተለያዩ የአትሌቲክስ መድረኮች በተደረጉ ውድድሮች በፎቶ ጋዜጠኞች ከተነሱት ምርጥ 70 ፎቶዎች መካከል በተደረገ ውድድር በአንደኛነት የተመረጠው የሰሎሞን ባረጋ ፎቶ መሆኑም ይታወቃል፡፡ ከመም (ትራክ) ውድድር ውጪ በሚታወቅበት የአገር አቋራጭ ውድድር ባሸናፊነት ሲያጠናቅቅ የተነሳው ፎቶ ነበር አንሺውን ስፔናዊው ፍሊክስ ሳንቼዝ ያሸለመው፡፡
የደቡብ ፖሊስ ባልደረባ የሆነው ሰሎሞን በተጎናፀፈው ስኬት ባለፈው ጳጉሜን የኢንስፔክተርነት ማዕረግ ማግኘቱ ይታወሳል፡፡