ሊጉ በራሱ እንዲተዳደር ተወሰነ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አዲሱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተቋሙን ኃላፊነት ሲረከብ ‹‹አስፈጽማለሁ›› ብሎ ቃል ከገባቸው ዕቅዶች መካከል በፌዴሬሽኑ ለዓመታት ሲንከባለል የቆየውን የተዝረከረከ አሠራር ከዘመኑ ጋር ሊራመድ የሚችል የአሠራር ሥርዓት (ሪፎርም) ማድረግ አንዱ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ታኅሣሥ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ የሪፎርሙ አንድ አካል የሆነውን የጽሕፈት ቤት ዋና ኃላፊ ቅጥር ፈጽሟል፡፡
በአቶ ኢሳያስ ጅራ የሚመራው አዲሱ ካቢኔ በፌዴሬሽኑ የሚጠበቀውን አደረጃጀት ዕውን ለማድረግ ሁሉን አቀፍ የስትራቴጂ ዕቅድ እንዲዘጋጅ ማስጠናቱ ይታወሳል፡፡ በገለልተኛ ሙያተኞች አማካይነት የተዘጋጀው ስትራቴጂክ ዕቅዱ የባለድርሻ አካላትን አስተያየት በግብዓትነት አካቶ ከተጠናቀቀ በኋላ እንዲተገበር ሲጠበቅ በመዘግየቱ ለምን የሚል ቅሬታና ትችት ሲያስተናግድ ቆይቷል፡፡
አመራሩ ባደረገው መደበኛ ስብሰባ በተቋሙ በየደረጃው የሚገኙ ኃላፊነቶችንና የሥራ ክፍሎች በአዲሱ አደረጃጀት መሠረት ምደባና ቅጥር እንዲፈጸም ውሳኔ ላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡ በዚሁ መሠረት በዋና ጸሐፊነት ኢያሱ መርሐጽድቅ (ዶ/ር) ሲቀጠሩ፣ በቦታው የቆዩት አቶ ሰሎሞን ገብረሥላሴ ደግሞ ዝቅ ብለው ምክትል ጸሐፊና የእግር ኳስ ልማት ኃላፊነት መመደባቸው ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል ለዓመታት ፌዴሬሽኑንና ክለቦችን ሲያወዛግብ የቆየው ‹‹ሊጉን በባለቤትነት የማስተዳደር ጥያቄ›› ዕልባት ለመስጠት ሊጉን በባለቤትነት እንዲያስተዳደር በሚቋቋመው አካል ዝርዝር አሠራር ላይ ለመምከር፣ የአሥራ ስድስቱ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የመጨረሻውን ውይይት ጥር 7 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል እንዲያደርጉ ጥሪ መደረጉን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡