Sunday, February 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርየልማት ሥራዎች ተገቢውን ጥበቃ ይደረግላቸው

የልማት ሥራዎች ተገቢውን ጥበቃ ይደረግላቸው

ቀን:

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በወረዳ ሦስት የሕዝብ ተሳትፎና የልማት ጽሕፈት ቤት በታኅሳስ መባቻ በተጻፈ ደብዳቤ ለልማት ሥራዎች ድጋፍ እንድናደርግ ተጠይቀናል፡፡ እኛም በበኩላችን በግላችንም ሆነ በድርጅታችን ስም ለአገራችን ልማት የሚውል የገንዘብ ዕርዳታ እስካሁን ስናደርግ ቆይተናል፡፡ በተጨማሪም በየዓመቱ ከምናገኘው ገቢ ላይ ከፍተኛ ታክስ በመክፈል ላይ እንገኛለን፡፡ ለወደፊቱም ቢሆን ከእነዚህ ተግባራት ወደ ኋላ አንልም፡፡

ሆኖም በተሰበሰበው ገንዘብ አንዳንድ የሚመሠገኑ የልማትና የፀጥታ ሥራዎች ቢከናወኑም፣ የተሠሩትን የልማት ሥራዎች በሚገባ አጠናቆ መጨረስና ተንከባክቦ መያዝን በተመለከተ በእናንተ በኩል ከፍተኛ ድክመትን ወይም ግድ የለሽነትን እናያለን፡፡ ስለዚህም የምናዋጣው ገንዘብ አብዛኛው በከንቱ እየባከነ መሆኑን ከቁጭት ጋር እንረዳለን፡፡ ለምሳሌ በከፍተኛ ገንዘብ የተሠሩ የእግር መንገዶችን እንመልከት፡፡ አንደኛ፣ ጥርት ብለው ሳይጠናቀቁና በየምክንያቱ በተለይም በመብራት ኃይል መሥሪያ ቤት የሚቆፈሩት አደገኛ ጉድጓዶች እንኳን ተደፍነው ሳያልቁ ለመመረቅና ሥራችሁን ለማወጅ ትቸኩላላችሁ፡፡

ሁለተኛ፣ እነዚህ በሕዝብ ገንዘብ በከፍተኛ ወጪ የተሠሩት የእግር መንገዶች እንጨት ሲፈለጥባቸው፣ ጎሚስታ ሲሠራባቸው፣ ከፍተኛ ክብደት ያላቸው የጭነት መኪናዎች ሲሰባብሯቸው፣ አሸዋና ጠጠር ሲራገፍባቸው፣ መኪናዎች ሲታጠቡባቸውና እግረኛውን ሲያሰቃዩና ለአደጋ ሲያጋልጧቸው በእናንተ በኩል ምንም ዓይነት አጥጋቢ መከላከል ስታደርጉ አትታዩም፡፡

ሌላ ምሳሌ ሰሞኑን በሰማያዊ ቀለም የተጻፉ የመንገድ ስሞችና የቤት ቁጥሮች የሚመስሉ ሰሌዳዎች በየመንደሩ ተተክለዋል፡፡ ስለአጠቃቀማቸውም ሆነ ስለአስፈላጊነታቸው ለነዋሪዎች የተሰጠ ማብራሪያ የለም፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ አብዛኞቹ አርጅተው መወዳደቅ ጀምረዋል፡፡ ይህ በእኔ ግምት ከፍተኛ የገንዘብ ብክነት ነው፡፡ ተጠያቂ ሰው መኖርም አለበት፡፡ እነዚህን የመሳሰሉትን ችግሮች ለመፍታት በሬዲዮ ማስታወቂያ ማውጣቱ ብቻ በቂ አለመሆኑን አይተናል፡፡ ምክንያቱም ምንም እንኳን አልፎ አልፎ ደንብ አስጠባቂዎች በየመንገዱ ሲዘዋወሩ ብናይም፣ እነዚህ ችግሮች ያለአንዳች ከልካይ አሁንም ሲፈጸሙ እናያለን፡፡

መፍትሔው ከባድ አይመስለኝም፣ ለምሳሌ አንዱ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው በየመንገዱ እየተዘዋወሩ የሚቆጣጠሩና አጥፊዎቸን በከፍተኛ ገንዘብ የሚቀጡ ቡድኖች (እነሱንም ቢሆን የሚቆጣጠር ሰው ያስፈልጋል) ማሠማራት ነው፡፡ ከሚከላከሉት ብክነት አንፃር ይህ ብዙ ወጪ የሚያስወጣ አይመስለኝም፡፡
ይህ ሳይደረግ እየቀረ ከግል ጉዳዮቻችን ላይ እየቀነስን ለአገር ልማት የምናዋጣው ገንዘብ በዚህ ዓይነት ሲባክን በዓይናችን እያየን ለምንስ እናዋጣለን?  በእርግጥ ታክስ መክፈል የእኛ ግዴታ ነው፡፡ ነገር ግን በፍቃደኝነት ለልማት የምናዋጣው ገንዘብ በትክክል ሥራ ላይ መዋሉን በተግባር ማሳየት ደግሞ የእናንተ ግዴታ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ሁላችንም ግዴታችንን ከተወጣን አገራችንን በጋራ እናለማለን፡፡

 (አክሊሉ ኪዳኑ፣ ከአዲስ አበባ)

***

ብሔራዊ ባንክና የወቅቱ ፈተናዎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለሚዲያ ዝግና መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ያልሆነ ተቋም ነው የሚል ወቀሳ በበርካታ የሚዲያ አካላት ይቀርብበታል፡፡ በቅርቡም ሜቴክ በገፍ ከባንክ እየወሰደ ሲረጨው ስለነበረው ብርና የውጭ ምንዛሪ ብሔራዊ ባንክ የሚለው ካለ ለማጣራት የሞከረ የሬዲዮ ጣቢያ ሙከራው ከንቱ መቅረቱን ሲያማርር ሰምተናል፡፡ የፋይናንስ ሴክተሩን የሚመለከቱ ማናቸውም ጉባዔዎች በተካሄዱ ቁጥር ተናጋሪዎቹ እንደ አሁኑ ድፍረት ሲሰማቸው በግላጭ፣ ቀደም ባለው ጊዜ ደግሞ በሽፍንፍን ማብጠልጠላቸው የተለመደ ነገር ከሆነ ቆይቷል፡፡ ሰሞኑን የሆነውንና ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነውም በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ባንኩን አስመልክቶ በሦስተኛው የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ፎረም ወቅት ተሰጡ ተብለው የቀረቡት መረር ከረር ያሉ ትችቶች ናቸው፡፡ በዕውኑ ብሔራዊ ባንክ አለን ብሎ እስከሚጠየቅ ድረስ በጉባዔው መብጠልጠሉን በዚያ የታደሙ ሁሉ ታዝበዋል፡፡ የሚያሳዝነው ነገር ግን በተለያዩ አካላት በቃልም ይሁን በጽሑፍ የሚሰነዘሩ ትችቶችን የባንኩ ኃላፊዎች የማይሰሟቸው ብቻ ሳይሆን፣ ተናጋሪዎቹን ቢችሉ ለመበቀል የማይመለሱ መሆኑ ነው፡፡ በሚዲያ ፊት ቀርቦ መረጃ ወይም ማብራሪያ መስጠት በራስና በሚሠሩት ሥራ መተማመን በሚነሱት የተቃውሞዎች ነጥቦች ላይ ሰፊ ዕውቀትና መረጃ መያዝ በቂ ዝግጅት ማድረግንም ይጠይቃል፡፡ ያለፉት ዘመናት ያሳዩት ነገር የባንኩ ሹመኞች ሥራቸውን ከዕይታ ተሰውረው የሚሠሩ እንጂ በአደባባይ ወጥተው የሚከተሉትን ፖሊሲ ለማስረዳትም ሆነ ለመከላከል የሚችሉ ያለመሆናቸውን ነው፡፡

አገሪቱ ከገባችበት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና በዚህ የተነሳ በኢኮኖሚ ላይ ከተፈጠረው ችግር በተጨማሪ፣ ባንኩ በልማት ባንክ በኩል ለተመረጡ ሴክተሮች እንዲውል ከባንኮች በግድ ሰብስቦ እንዲሰጥ ከተደረገውና ሆን ተብሎ በተዘረጋ የምዝበራ መረብ እንደወጣ ከቀረው ገንዘብ በስተቀር፣ መንግሥት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ስለሚገኝበት አሳሳቢ ሁኔታ የተረዳ አይመስልም፡፡

ባንኩ በሃያ ምናምን ዓመታት ውስጥ የገንዘብ ኢንዱስትሪው ለውጭ ኢንቨስተሮች በሚከፈትበት ጊዜ ለሚያጋጥመው ሥራ ራሱን ካለማዘጋጀቱ በተጨማሪ፣ የአገር ውስጥ ባንኮችም ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ አስቦ የሠራው ሥራ መኖሩ አይታይም፡፡ ይኼ ነው የሚባል ውጤት ላላሳዩት የመንግሥት ፕሮጀክቶች የውጭ ምንዛሪ እየዛቀ ከማሳቀፍ ውጪ፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ ውጤታማ ሥራ አልሠራም፡፡ የራሱንና የሴክተሩን የሰው ኃይል ልማት በማሻሻል እንዲሁም የክፍያ ሥርዓቱን በማሻሻል ረገድ የሚያስመሠግን ሥራ አልሠራም፡፡ ለራሱ እንኳ የሚሆን ደህና ሕንፃ የለውም፡፡ ግማሹን ከንግድ ባንክ ቀሪውን ከቀድሞው የሞርጌጅ ባንክ እየነጠቀ ባለብዙ አሮጌ ቤቶች ሆኗል፡፡ የዩኒሳ ግቢንም ተቀብሎ ምን እየሠራበት እንደሆነ ባይታወቅም፣ የውኃ ኢንስቲትዩት ተማሪዎች ነን ያሉ ሰዎች ከግቢው አስወጥቶናል በማለት ለትምህርት ሚኒስቴር መክሰሳቸውን ከመገናኛ ብዙኃን ሰምተናል፡፡

አገራዊውን ለውጥ ተከትሎ የመንግሥት ተቋማት መሪዎች ሹም ሽር እየተደረገ ባለበት ሁኔታ ለረዥም ዓመታት ባንኩን በገዥነትና በምክትል ገዥነት ያገለገሉትን ኃላፊዎች መንግሥት አንስቷል፡፡ ይሁን እንጂ ከዋናው ሥራ ላይ የተነሱትን ገዥ መልሶ የጠቅላይ ሚንስትሩ አማካሪና ይባስ ብሎ የባንኩ የቦርድ አባል አድርጎ ሾሟቸዋል፡፡ በአንድ ቦታ ላይ ዓመታትን ለመቀመጥ ዕድል ያገኙት የባንኩ ገዥ ባንኩን ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሳደግ ሰፊ ዕድል ነበራቸው፡፡ ያለመታደል ሆኖ የባንኩ በብዙ መለኪያዎች የኋሊት እንዲሄድ እከሌ የሚባል የኢኮኖሚም ሆነ ሌላ ባለሙያ የሌለበት የባለሙያ ድርቅ ያጠቃው ባዶ ድርጅት አድርገውት ተሰናብተዋል፡፡

ባንኩ እንደ ብዙ ማዕከላዊ ባንኮች ራሱን ችሎ የገንዘብ ፖሊሲዎችን እየቀረፀ በሥራ ላይ የሚያውል ሳይሆን፣ ሥራውንና ድርጅታዊ ነፃነቱን እርግፍ አድርጎ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለመሪ የፖለቲካ ድርጅቱ የኢኮኖሚ አማካሪዎች በመተው፣ ከላይ የተጣለበትን ውሳኔ በማስፈጸም ላይ የተጠመደ እንደነበረ አሁንም አንፃራዊ ነፃነቱን ያላስከበረ መሆኑን ብዙ የመስኩ ባለሙያዎች የሚያነሱት እውነት ነው፡፡

ገዥውንና ምክትላቸውን ያነሳ መንግሥት የቀሩትን ሁለት ምክትል ገዥዎች በነበሩበት በማቆየት የመረጠበት ምክንያት ደግሞ የበለጠ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ምክንያቱም ሁለቱ ሰዎች በተመደቡባቸው ቦታዎች የሚመጥን ልምድና ዝግጁነት የሌላቸው መሆኑ በግልጽ የሚታወቅ በመሆኑ ነው፡፡ ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለቆየን ሁሉ በሙያቸው ከፍ ካለ ደረጃ የደረሱትንና በአመራራቸውም አንቱ የተባሉትን የባንክ ኢንዱስትሪው የሚያከብራቸውን አቶ ጌታሁን ናናን በወቅቱ የነበሩት ገዥ ያነሱበት ምክንያት እስካሁን እንቆቅልሽ እንደሆነ ነው፡፡ የበለጠ አስገራሚው የሆነው ደግሞ በምትካቸው ያመጧቸው ግለሰብ አብዛኛውን ሕይወታቸውን በንብረትና በሰው ኃይል ማኔጅመንት ላይ ያሳለፉ መሆናቸው ነው፡፡

እንዲያውም በቦታቸው እንዲቆዩ አጋጣሚው ከፈቀደላቸው ዕድገት ግለሰቦች ይልቅ ከቦታቸው የተነሱት ኃላፊዎች የሚፈለገውን ያህል ውጤታማ አይሁኑ እንጂ ሙሉ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን እንዲሁም ዕውቀታቸውን በባንኩ ማዋላቸውን ባንኩን የሚያውቁ ሁሉ የሚስማሙበት ሀቅ ነው፡፡

የባንኩ ዋነኛ ኃላፊነት የሆነው የገንዘብ ፖሊሲ የመቅረፅ ሥራ የሚሠራው የምክትል ገዥ ቦታ እስካሁን ባዶ ነው፡፡ አዲሱን እንግዳ ገዥ ማን እያማከራቸው እንደሚሠሩ የሚያውቀው አንድዬ ብቻ ነው፡፡ እርግጥ ነው በችሎታ ሳይሆን በዘር ኮታ ሥልጣን በሚታደልበት አገር ለገዛ ህሊናቸውና ለሙያቸው እንዲሁም ለመርህ የሚቆሙ ሰዎችን ማግኘትና መሾም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈተና እንደሚሆን ከእስከዛሬው ልምድ መገመት ቀላል ነው፡፡ ይሁን እንጂ ባንኩ የተሸከመውን ኃላፊነት ለሚገነዘብ ሰው አሁን ባለበት ሁኔታ እንዲቀጥል ማድረግ አገርን ውድ ዋጋ ማስከፈሉ አያጠያይቅም፡፡ የካፒታል ገበያ እንዲቋቋም እስካሁን እሹሩሩ እየተባለ ያለው የባንክ ሴክተሩም መከፈቱ እንደማይቀር የአደባባይ ሚስጥር ሆኗል፡፡

እነዚህ ሁሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እንዲመራና እንዲያስተባብር የሚጠበቅበት ባንክ ግን፣ ከገባበት ጥልቅ እንቅልፍ የነቃ አይመስልም፡፡ ጊዜው የጋረጠውን ፈተና የሚገነዘቡ መፍትሔም ለማምጣት ብቃት፣ ዕውቀት፣ ፍላጎት፣ ያላቸው አንቱ የተባሉ መሪዎችን ከየትም ፈልጎ በባንኩ ቁልፍ ቦታዎች ላይ በፍጥነት ማስቀመጥ ይዋል ይደር የማይባል ጉዳይ ነው፡፡ ሞልቶ ከተረፈው ኢትዮጵያዊ ባለሙያ መካከል የቀደመውን ወንዝ ያላሻገረ የአባልነት መለኪያ አሽቀንጥሮ በመጣል፣ ለባንኩም ለአገሪቱም የሚመጥኑ ሰዎችን መሾም ለተጀመረው አገራዊ ለውጥ ፋይዳው ከፍ ያለ ስለሆነ ይህንኑ ጠቅላያችን እንዲያስቡበት ማስታወስ እንሻለን፡፡

(ከምንተስኖት ዓብይ ዘገየ፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በጦርነቱ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ የመገንባቱ ውጥን

በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል በሦስት ዙር ተካሄዶ በነበረው ጦርነት ምክንያት...

በርካታ ሰዎችን እያጠቁ የሚገኙት የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች

ትኩረት የሚሹ የትሮፒካል /ሐሩራማ በሽታዎች በአብዛኛው ተላላፊ ሲሆኑ፣ በዓይን...

ስለአገር ኢኮኖሚ ማሰብ የነበረባቸው ጭንቅላቶች በማያባሩ ግጭቶች ተነጥቀዋል!

አገራችን ኢትዮጵያ ውጪያዊና ውስጣዊ ፈተናዎቿ መብዛት ብዙ ዋጋ እያስከፈላት...