Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየኤሌክትሮኒካዊ ውል ሕግጋት ወዴት አሉ?

የኤሌክትሮኒካዊ ውል ሕግጋት ወዴት አሉ?

ቀን:

በውብሸት ሙላት

ከቀናት በፊት የምሥራቅ አፍሪካ የኤሌክትሮኒካዊ ንግድ ሥራ ማዕከል (East Africa E-Commerce Center) አዲስ አበባ ላይ ሊከፈት እንደሆነ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በዜናነት ተላልፏል፡፡ ምንም እንኳን ሊገነባ ታስቦ የነበረው ኬንያ ላይ ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ አዲስ አበባ እንዲዛወር ተወስኗል፡፡ የሚያስገነባውም ዓለም አቀፉ የፖስታ ድርጅት ኅብረት እንደሆነ ተገልጿል፡፡ የንግድ ማዕከሉም በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሥራ ዕድል ሊፈጥር እንደሚችልም እንዲሁ ተጠቁሟል፡፡

 ኤሌክትሮኒካዊ ዘዴን በመጠቀም መገበያየት ከተጀመረ ዓመታት አልፈዋል፡፡ በርካታ አገሮችም ይህን ሁኔታ በማጤን የሕግ ማዕቀፋቸውን በማሻሻል ለአገልግሎት ሰጪውም ለተገልጋዩም የሕግ ጥበቃ አድርገዋል፡፡ ኢትዮጵያም ይህንን ጉዳይ ዘግይታም ቢሆን የዛሬ ስድስት ዓመት ገደማ የሕግ ማዕቀፍ ለማውጣት ሽር ጉድ ስትል እንደነበርም የተለያዩ መግለጫዎችንም በኮሙዩኒኬሽንና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አማካይነት ስትሰጥ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ይሁን እንጂ ክፍያና ፊርማን ከሚመለከቱ የተወሰኑ ብጥስጣሽ ሕግጋት በስተቀር ለዘርፉ የሚመጥን ጥቅል ሕግ እስካሁን አላወጣችም፡፡ ኤሌክትሮኒካዊ የግብይት ሥርዓቱ ግን እየሰፋና እየጨመረ ነው፡፡ እንደውም በአፍሪካ ከሚገነቡት አራት ትላልቅ የኤሌክትሮኒካዊ የንግድ ሥራ (የግብይት) ማዕከል አንዱ አዲስ አበባ ላይ ሊገነባ ነው፡፡ ለኤሌክትሮኒካዊ የንግድ ሥርዓት የኢትዮጵያ ዝግጁነት እየተሻሻለ ቢሄድም በብዙ ዘርፍ አሁንም ጭራ ናት፡፡ ከእነዚህ መካከል የሕግ ማዕቀፉ አንዱ ነው ብቻ ሳይሆን የባሰበትም ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሕግ ማኅበረሰብን እየቀደመ መምራት ይጠበቅበታል፡፡ ይህን ማድረግ ካልተሳካለት ደግሞ ከማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካ ለውጥና መሻሻል ጋር አብሮ መሄድ አለበት፡፡ በሁለቱም መልክ መጓዝ ያልቻልንባቸው ሁኔታዎች ግን በርካታ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የኤሌክትሮኒክስ የንግድ ሥርዓትን ለማሳለጥ የሚረዳ፣ ተዋዋይ ወገኖች ፍትሐዊ ግንኙነት እንዲኖራቸው የሚያግዘውን ኤሌክትሮኒካዊ ውል ጉዳይ ሕግ አውጪው አሁንም እንደዘነጋው ነው፡፡  የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛው ይኼው ነው፡፡ በመሆኑም ትኩረት የተደረገው ውል የሚደረገው በኤሌክትሮኒክ በሚሆንበት ጊዜ የሕጋችን ሁኔታ ምን እንደሚመስል ወርድና ቁመቱን ጠቅለል ባለ መልኩ ማሳየት ነው፡፡ ወርድና ቁመት ከሌለውም ይኼንኑ መጠቋቆም ነው፡፡

ለመንደርደሪያ ያህል

የመዋዋል ነፃነት ለውል መሠረቱ በመሆኑ፣ በዋናነት ውል ግለሰባዊ ግንኙነትን የሚገዛና ለተዋዋዮች ፍልጎት ስለሚገብር ለአዳዲስ የሕግ አሠራሮች ምንጭ ይሆናል፡፡ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ያስገኛቸው በረከቶች ለውልም ፀበለ ፃዲቅ ማቃመሱ አልቀረም፡፡ በዘመነ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተዋዋዮችን ቦታ ሳይገድባቸው፣ አካላዊ መተያየት ግድ ሳይሆንባቸው፣ አገር አካለው ወንዝና ተራራ አቋርጠው መጓዝ ሳይጠበቅባቸው በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ወይም ኮምፒውተራቸው አማካይነት የትም ሆነው ከሌላ ወገን ጋር ውል መግባት እንደውሉም መፈጸም ተዘውትሯል፡፡ የውልነት አቋም ያላቸው ስምምነቶች ተቀባይነት፣ አስገዳጅነትና ተፈጻሚነት ውጤት ይኖራቸው ዘንድ በሕግ የተቀመጡ ዝቅተኛ መሥፈርቶችን አሟልተው መገኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የፍትሐ ብሔር ሕግም አንድ ውል ሕጋዊ ውጤት እንዲኖረው በአራት ጎራ የተመደቡ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ይጠበቅበታል፡፡ በአንድ በኩል ተዋዋዮቹን የሚመለከቱ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ውል የሚደረግበትን ነገርና ውሉ የተደረገበትን ፎርም ይመለከታል፡፡ ተዋዋይ ወገኖች ውል ለማድረግ አዕምሯዊ ብቃት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከዕድሜ፣ ከአዕምሯዊ ጤንነትና አንዳንዴም ውሉን ለመገንዝብ የሚረዱ አካላዊ ጤንነትንም እንዲኖር ሕግ ይጠይቃል፡፡ ሕጉ ይህን መፈለጉ ጥበቃ ሊያደርግላቸውና በሌላ ወገን ያልተመጣጠነ ጥቅም እንዳይያዝባቸው ነው፡፡ ውል በሚደረግበትም ጊዜ ተዋዋይ ወገኖች በአዕምሯቸው የፈለጉትን (ሳይጭበረበሩ፣ ሳይሳሳቱና ሳይገደዱ ወዘተ.) በትክክል በውሉም ላይ እንዲፈጸም ሕግ አንዳንድ ለጥበቃ የሚያገለግሉ መለኪያዎችን አስቀምጧል፡፡

 ሰው ውል የመዋዋል ነፃነት ቢኖረውም ለነፃነቱ ገደብ መኖሩ አይቀርም፡፡ መዋዋል የሚቻለው ሕጋዊ የሆኑ፣ በሰው ልጅ ችሎታና አቅም ሥር የሆኑ፣ ሞራልን የማይጥሱ እንዲሆኑ ሕግ ይፈልጋል፡፡ ከዚህ ባለፈም ውሎችን እንዴት መደረግ እንዳለባቸው ነፃነቱ የተዋዋዮቹ ቢሆንም፣ አንዳንድ ጉዳዩችን ግን በምን መልኩ መደረግ (ለምሳሌ በጽሑፍ) እንዳለባቸው ሕግ አስቀድሞ ሊወስን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ውል በባህሪው ለለውጥ የተጋለጠ ነውና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘመን ውል የማድረግ ችሎታ፣ ስምምነት፣ የውል ጉዳይና ፎርምን በሚመለከት ተጨማሪ ዝቅተኛ መሥፈርቶችን ማስቀመጥ ከአንድ አገር ሕግ አውጪ የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው፡፡

እንዳለመታደል ሆኖ የኢትዮጵያ ሕግ አውጪ ግለሰባዊ ግንኙነቶችን የሚመለከቱ ሕግጋትን አጥንቶ የማማሻል ፍላጎትም አቅምም የጎደለው ይመስላል፡፡ በዚያው በጃንሆይ (በአፄ ኃይለ ሥላሴ) እንደወጡ አሁንም አሉ፡፡ በጎነቱ እንኳን በዚያን ዘመን ጥሩ ሕግጋት ወጡ፡፡ በዚያን ወቅት ያልወጡ እንደ ዓለም አቀፍ የግለሰብ ሕግ፣ የማስረጃ ሕግና አስተዳደር ሕግ ወዘተ. በደርግም ይሁን በኢሕአዴግ ዘመን ሊፀድቁ አልቻሉም፡፡ ያኔ እንደተጀመሩ አሁንም ያው በጅምር ላይ ናቸው፡፡ በረቂቅ ሕግነት ዘመናትን አሳለፉ፡፡

ኤሌክትሮናዊ ንግድ ሥራ (ግብይት)

‹‹ንግድ ሥራው የሚለው ሐረግ በእንግሊዝኛው ‹‹Commerce›› የሚለውን ለመተካት ነው፡፡ ንግድ ሥራን ወይም ግብይትን ኢንተርኔትና መሰል መሠረተ ልማቶችን በመጠቀም ሲከናወን ኤሌክትሮኒካዊ ንግድ ሥራ ይሆናል፡፡ ንግዱ የሚሠራበት (የሚከናወንበት) ሌላው ምኅዳር መሆኑ ነው፡፡ ከምናየው ገሃዳዊው ዓለም በትይዩ በቆመው ምናባዊው (Cyber) ምኅዳር ግብይት፣ ንግድና ውል ይደረጋል፡፡ በቀላል አገላለጽ ከመርካቶ፣ ከሰኞ ገበያ፣ ከእዳጋ ዓርቢ ከአራዳና ፒያሳ ሱቆች ኮምፒውተርንና ስልኮችን በመጠቀም የቦታና የጊዜ ገድብም ቀጠሮም የሌለበት የግብይትና የንግድ ሥራ ነው፡፡

ዓለም አቀፉ ኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት (Organization for Economic Co-operation and Development/OECD) ኤሌክትሮናዊ ንግድ ሥራን ብያኔ ሲሰጥ ‹‹ድርጅቶችም ይሁኑ ግለሰቦች የሚከናውኗቸው የንግድ እንቅቃሴዎች ኤሌክትሮናዊ ሒደቶች፣ መረጃ የማስተላለፍ ክንዋኔዎች ከያዙ የመረጃ ዓይነቶቹ ጽሑፍም፣ ድምፅም ምስልም ቢሆኑ ኤሌክትሮኒካል ንግድ ሥራ ይባላሉ፡፡ የንግድ ሥራን የሚያሳልጡና ሥርዓት የሚያስይዙ ተቋማትንና ሒደቶችንም በሚመለከት በኤሌክትሮኒክ የንግድ ሥራ መረጃ መለዋወጥንም ያካትታል፡፡ ይኼም ድርጅታዊ ሥራ አመራር፣ የንግድ ድርድርና ውል፣ የሕግና ደንብ ማዕቀፍን፣ የክፍያ ሥርዓትና የግብር ጉዳይንም  ያካትታል፤›› በማለት ሰፋ ያለ ትርጓሜ አስቀምጧል፡፡

ከዚህ ለየትና ጠበብ ባለ ሁኔታ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድና ልማት ጉባዔ (United Nations Conference on Trade and Development/ UNCTAD) ኤሌክትሮኒካዊ ንግድ ሥራ ትርጓሜ አስቀምጧል፡፡ ኤሌክቶኒካዊ ንግድ ሥራ አለ ለማለት ‹‹ግብይት የሚደረገበትን ሸቀጥ ወይም አገልግሎት ኢንተርኔትን መሠረት አድርጎ ትዕዛዝ ከተሰጠ በቂ ነው፡፡ ርክክቡና ክፍያው ኢንተርኔትን መሠረት ባያደርጉና ከእዚያ ውጪ ቢከፈሉም ኤሌክትሮኒካዊ ንግድ ሥራ ግን አለ፤›› ይላል፡፡

 ከላይ በተገለጹት በሁለቱ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተሰጡት ብያኔዎች ቢኖሩም ከእነዚህ ለየት ባለ መልኩ ደግሞ ኤሌክትሮኒካዊ የሚያሰኘው የግድ ኢንተርኔት ብቻ ሳይሆን ስልክም፣ ከተለያዩ ቦታዎች ሰዎችን በቀጥታ ውይይት ማድረግ የሚቻልባቸው ቴሌቪዥኖችና ኤሌክትሮኒክ መልዕክቶችንም ያካትታል የሚሉም አሉ፡፡ አንዳንድ አገሮች  (ለምሳሌ አሜሪካ) ኤሌክትሮኒካዊ ንግድ ሥራ አንድ አንድ የግብይት ማከናወኛ ዓውድ ይቆጥሩታል፡፡ ሌሎች አገሮች (ለምሳሌ አውስትራሊያ) ደግሞ ኤሜይልና የመዝናኛ አገልግሎቶችንም በመጨመር ኤሌክትሮኒካዊ ንግድ ሥራ ምድብ ሥር ያካትቷቸዋል፡፡ ስለዚህም የሚተዳደሩበትን የሕግ ማዕቀፍ ከትርጓሜያቸው ተነስተው ይቀርፃሉ የተፈጻሚነቱን ወሰንም ዱካ ያበጁለታል፡፡

ኤሌክትሮኒካዊ ውል

ኤሌክትሮኒካዊ ውል በአንፃሩ አንድ ውል መብትና ግዴታ ለመፍጠር ወይም ለማሻሻል ወይም ቀሪ ለማድረግ ኤሌክትሮኒካዊ የግንኙነት ዘዴን በመጠቀም ሲከናወን ኤሌክትሮኒካዊ ውል ተብሎ ሊጠራ ይችላል፡፡ ስለሆነም ውልን በኤሌክትሮኒክ ዘዴ መፍጠርና የመፈረም ተግባር ነው፡፡  በኢሜይል፣ በኤሌክትሮኒክና የእርስ በርስ መረጃ ልውውጥ ዘዴ (Electronic Data Interchange/EDI)፣ በኢንተርኔት አማካይነት የሚደረግ ሸመታ (Online shopping) ወዘተ. ኤሌክትሮኒካዊ ውሎች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሮኒካዊ ውሎች ሕግጋት ሁኔታ

በአጠቃላይ የውል ጉዳዮችን የሚመለከተውና አሁንም በሥራ ላይ ያለው ሕግ በ1952 ዓ.ም. የወጣው የፍትሐ ብሔር ሕግ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ከእዚህ ውጭ ሌሎች ምንም ዓይነት ሕግጋት የሉም ማለት አይደለም፡፡ እንደ ንግድ ዓይነቱ ወይም እንደ ግብይት አፈጻጸሙ አንዳንድ ቁርጥራጭ ሕግጋት መኖራቸው ሀቅ ነው፡፡ ለምሳሌ የምርት ገበያ ሕጉ፣ የብሔራዊ የክፍያ አዋጅና የኤሌክትሮኒክ ፊርማ አዋጅ ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

ይሁን እንጂ መሠረታዊ የኤሌክትሮኒክ ውል ባህሪያትን ታሳቢ በማድረግ የወጣ ጥቅል ሕግ የለም፡፡ ኤሌክትሮኒካዊ የንግድ ሥራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ ቢሄድም ሕጉ ከተግባሩ ገና ውራ እንደሆነ ነው፡፡ እስኪ አንዳንድ የውል መሠረታዊ ገጽታን እያነሳን በፍትሐ ብሔር ሕጉ ላይ የተቀመጡት ድንጋጌዎች በኤሌክትሮኒክ የሚፈጸሙ ውሎችን ለማስተዳደር ብቃት ይኖራቸው ከሆነ እንፈትሻቸው፡፡

ኤልክትሮኒካዊ ውል ለመዋዋል

የፍትሐ ብሔር ሕጉ ውልን ‹‹ንብረታቸውን የሚመለከቱ ግዴታዎችን ለማቋቋም ወይም ለመለወጥ ወይም ለማስቀረት ባላቸው ተወዳዳሪ ግንኙነት በሁለት ወይም በብዙ ሰዎች መካከል የሚደረግ ስምምነት ነው፤›› በማለት አንቀጽ 1675 ላይ ብያኔ አስቀምጧል፡፡ ይህ ጥቅል ብያኔ አንድ ውል መርካቶም ይፈጸም ሾላ ገበያ፣ ፒያሳ በሚገኝ ሱቅ ውስጥም ይሁን ኢንተርኔትን ተጠቅሞ ገዥ ከአማዞን/ኢቤይ ሁሉንም በጥቅል የሚመለከት ድንጋጌ ነው፡፡ ዋናው ነገር ንብረት የሚመለከት እስከሆነ፣ ግዴታን ለመፍጠር ወይ ለማሻሻል ወይ ለማስቀረት በማሰብ የሚደረግ ስምምነት መኖሩ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ አንቀጽ በመቀጠል ስንጓዝ ይህንን ጥቅል ብያኔ ነፍስ የሚዘሩበትን ሌሎች ድንጋጌዎችን እናገኛለን፡፡

ከላይ ከተገለጸው ብያኔም ይሁን የትኛውም የውል ጽንሰ ሐሳብ በተዋዋዮች መካከል ስምምነት መኖርን ታሳቢ ያደርጋል፡፡ ስምምነት የምትለው ቃል ግልጽና ቀላል ብትመስልም ቅሉ ወደ ነባራዊው ዓለም ይዘናት ስንጓዝ እጅግ አነታራኪ የመሆን ነገር የታወቀ ነው፡፡ ለንትርክ የተጋለጠችበት ምክንያትም ብዙ ናቸው፡፡ በልማዳዊውና መደበኛው የውል ሥርዓት የሚታወቀው ተዋዋዮች ፊት ለፊት ይተያያሉ፡፡ የሚዋዋሉበት ጉዳይ ላይ አስቀድመው ድርድር ያደርጋሉ፡፡ ከዚያም በደረሱበት ስምምነት መሠረት ውል ይገባሉ፡፡ በኤሌክትሮኒካዊ ውል ግን ተዋዋዮች እንኳንስ ፊት ለፊት መተያየት ቀርቶ ፍፁም ማን ማን እንደሆነ ላይተዋወቁ ይችላሉ፡፡ ድርድር ማድረግም አልተለመደም ይልቁንም እዚያው ኢንተርኔት ላይ የተገለጸውን መቀበል ነው፡፡ ውል ሲደረግም ምስክሮች አይኖሩም፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው የፍትሐ ብሔር ሕግ ደግሞ እንዲህ ዓይነቶቹን ሁኔታዎች ከግምት በማስገባት አልተሻሻለም፡፡ እስኪ እንደው የሁኔታውን አሳሳቢነት ለመረዳት ያህል የተወሰኑ ነጥቦችን እናንሳ፡፡ ከተዋዋዮች ውል የመግባት ችሎታ (Capacity) እንጀምር፡፡ በመቀጠል ተጨማሪ አራት አስረጂዎችን እንጨምራለን፡፡

በፍትሐ ብሔር ሕጉ ማንም ሰው በሕግ ፊት ውጤት ያለው ተግባር የማከናወን ብቃት እንዳው ግምት/ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች የሚያደርጓቸው ግንኙነቶች፣ የሚፈጽሟቸው ተግባራት በሕግ ፊት ውጤት ላይኖራቸው አስገዳጅ ላይሆኑም የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩን አይዘነጋም፡፡ ዕድሜና የአዕምሮ ጤንነት ሁኔታ ከግምት ይገባሉ፡፡ ድርጅቶች ከሆኑ ሥልጣን ባለው አካል የተመዘገቡ ወይም በሕግ የተቋቋሙ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ስለሆነም ውል በሚደረግበት ጊዜ እንዲህ ዓይነት ቅድመ ሁኔታዎችን ተዋዋዮች ማወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለምሳሌ አንድ የአምስት ዓመት ሕፃን ልጅ አንድ በሬን ለአንድ ሰው በአምስት መቶ ብር ቢሸጥለትና ገዥውም በርካሽነቱ ተደንቆ በደስታ በሬውን ወደ ቤቱ ይዞ ቢሄድና በማግሥቱ የልጁ እናት/አባት መጥተው ውሉ እንዲፈርስ ቢጠይቁ መፍረሱ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ገዥውም የሻጩን ሕፃንነትና የአዕምሮ አለመጎላመስ እያወቀ እንደገዛ ይወሰዳል፡፡

አንድ የአሥር ዓመት ሕፃን ልጅና ሌላ ጎልማሳ በኢንተርኔት ወደሚያደርጉት ግብይት እንምጣ፡፡ ይህ ሕፃን ልጅ የአባቱን የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት ቁጥር በቃሉ ይዞ የፈለገውን ግዥ ፈጽሞ ከአባቱ የባንክ ሒሳብ ላይ ተቆርጦ እንዲከፈለው አደረገ እንበል፡፡ በሌላ አገላለጽ ልጁ ራሱ ለሻጩ ዋጋውን በሞባይል ስልክ አስተላለፈ፡፡ የሚሸጠውን ነገር ያየው ከፌስቡክ ላይ ነው እንበል፡፡ በፌስቡክ የተዋወቁት ሻጭና ገዥ ግብይቱን ፈጸሙ፡፡ የተሸጠውን ነገርም በፖስታ ቤት ለመላክ ተስማምተዋል፡፡ የሕፃኑ ልጅ (ገዥ) አባት በሁኔታው ተበሳጭቶ ውሉ እንዲፈርስ ለመጠየቅ ቢከጅል፣ የኢትዮጵያ የፍትሐ ብሔር ሕግ የሚመለከተው የሻጭና ገዥን የዕድሜ ሁኔታ ብቻ ስለሆነ ይቻላል በማለት መደምደም ይቻላል፡፡ ነገር ግን በኤሌክትሮኒካዊ ዘዴ ውል ለመዋዋል ምን ምን ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት እንዳለበቸው ሕጉ ምንም የሚለው ነገር ስለሌለ፣ ለተዋዋዮች ግንኙነት ራስ ምታት ነው፡፡ ውሉ ሊፈርስ የሚችለው ሁለቱም ተዋዋዮች ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸሙ ሲሆን ነው፡፡

ኤሌክትሮኒካዊ ውሎች የአገር ድንበር ስለማይገድባቸው (በተለይ ዓለም አቀፍ የክፍያ ሥርዓት ለምሳ ማስተር ካርድ ዓይነት) ይህ ድምዳሜ ሁልጊዜም እውነት ነው ማለት አይቻልም፡፡ የተለያዩ አገሮች ላይ ሆነው ለሚደረጉ ውሎች በምን መንገድ ሊፈታ እንደሚችል በመፍትሔነት የሚያገለግል ዓለም አቀፍ የግለሰብ ሕግ (Private International Law or Conflict of Laws) የለንም፡፡ እዚህ ላይ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉና የፍርድ ቤቶችን ሥልጣን ለመወሰን የወጡ አዋጆች ላይ ያሉ ዓለም አቀፍ የግለሰብ ሕግን በሚመለከት የተሰጡ ውሳኔዎች እንዴት ዕውቅና እንደሚሰጣቸውና የትኞቹ ፍርድ ቤቶች እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችን አከራክሮ የመወሰን የሥረ ነገር ሥልጣን እንዳላቸው የተደነገጉ አንቀጾች መኖራቸውን በመዘንጋት አይደለም፡፡ ይህ ሕግ ያላቸው አገሮች እንኳን ኤሌክትሮኒካዊ የንግድ ሥራና ውል እየተስፋፉ ሲመጡ ለማሻሻል ተገደዋል፡፡ በአጭሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ ከሌላ አገር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር የሚደረጉ ኤሌክትሮኒካዊ ውሎችን በሚመለከት የውል ይፍረስልኝና እንደውሉ ይፈጸምልኝ ወዘተ. ዓይነት ጥያቄዎች ቢነሳ የኢትዮጵያዊ ሕግ ምላሹ ‹‹እንጃ አላውቅም እንደ ፍጥርጥርህ፣ እንደገባህ ተወጣው፤›› ከማለት የተሻለ አይደለም፡፡

ውል የመዋዋል ችሎታን በሚመለከት አንድ ነጥብ እንጨምር፡፡ ይኼውም ከውል ተዋዋዮች አንደኛው ወይም ሁለቱ ድርጅቶች ናቸው እንበል፡፡ ማንኛውም ድርጅት ውልና ሌሎች ሕጋዊ ውጤት ያላቸውን ተግባራት ለመፈጸም ሕጋዊ ሰውነት (Legal Personality) ሊኖራቸው እንደሚገባ የታወቀ ነው፡፡ ኤሌክትሮኒካዊ ግብይት የሚፈጸመው በመካነ ድር (Website) በሚሆንበት ጊዜ አገልግሎት ፈላጊው ‹‹ገዝቻለሁ›› ወይም ‹‹ተቀብያለሁ›› ወይም ‹‹ተስማምቻለሁ›› ከማለት ያለፈ ስለ ሕጋዊ ሰውነት መኖር አለመኖሩ ማረጋገጫ ላይኖረው ይችላል፡፡ ካልሆነም የሐሰት ማረጋገጫ ድረ ገጹ ላይ ሊያሳይ ይችላል፡፡

እንደ ውሉ ሳይፈጸም የቀረ ጊዜ በፍርድ ቤት እንደ ውሉ ይፈጸምልኝ አለበለዚያም ካሳ ይከፈለኝ ብሎ ዳኝነት ለመጠየቅ ጣጣው ብዙ ነው፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት አገልግሎት ሰጪዎች ኢንተርኔትን በመጠቀም አገልግሎት ለመስጠት ማሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎችን በመወሰንና በማስፈጸም ሸማቹን ጥበቃ ለማድረግ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ኢትዮጵያ የላትምና፡፡

ሁለተኛው ማሳያ ከፈቃድ (መስማማት/Consent) ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ተዋዋዮች ውል ከመፈጸማቸው በፊት ሊዋዋሉበት ስለሚፈልጉት ጉዳይ በምን ሁኔታና እንዴት ሆኖ ብሎም ምን ዓይነት መብት እንደሚያሰገኝ ምን ግዴታ እንደሚያመጣ መስማማት አለባቸው፡፡ ስለሆነም በነፃ ፈቃዳቸው፣ ሳይጭበረበሩና ስህተት ሳይኖር ውል መደረግ አለበት፡፡ ካልሆነ ግን በህሊናቸው ያሰቡት ነገር በትክክል በውሉ አልተገለጸም ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በመካነ ድር አማካይነት የሚፈጸሙ ውሎች፣ በክፍያ ማሽኖች የሚደረጉ ክፍያና ግብይቶች ስህተት (Contractual Error or Mistake) ተፈጽሟል የሚባለው ምን ሲሆን እንደሆነና እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥም ማስጠንቀቂያ እንዴት እንደሚሰጥ ወዘተ. ግልጽ የሕግ ድንጋጌ መኖር አለበት፡፡ ለምን ቢሉ በኢሜይል ወይም በሌላ ኤሌክትሮኒካዊ ዘዴ የሚሰጡ ማስጠንቀቂያዎችን የኢትዮጵያ ሕግ አያውቃቸውምና፡፡

ሦስተኛው ማሳያ የፍርድ ቤት ሥልጣን ጉዳይ ነው፡፡ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ ላይ እንደተገለጸው ከውል ይፈጸምልኝ ወይም ይፍረስልኝ ጋር በተገናኘ የዳኝነት ሥልጣን የሚኖረው ውሉ የተደረገበት ወይም የሚፈጸምበት አካባቢ የሚገኝ የወረዳ/የመጀመርያ ደረጃ ወይም ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህም መነሻነት የየትኛው ክልል ሥልጣን አለበለዚያም የፌዴራል ፍርድ ቤት ሥልጣን እንደሆነ መለየት ይቻላል፡፡ ኤሌክትሮኒካዊ ውሎች ሲሆኑ ውሉን ሲዋዋሉ የት ቦታ ሆነው እንደተዋዋሉ እንኳን ለማስረዳትም ከባድ የሚሆንበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ የሚፈጸምበትም እንዲሁ፡፡ ለአብነት ውል የተደረገው በኢሜይል አማካይነት ከሆነ ላኪውና ተቀባዩ (ማለትም ኢሜይሉ የተላከበትና የተነበበት) የት ሆነው እንደተለዋወጡ ማስረዳቱ አዳጋች ነው፡፡

አራተኛው ጉዳይ ውል እንደ ሕግ ሆኖ የሚፀናው በተዋዋቹ መካከል እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ኤሌክትሮኒካዊ ውሎች በተለይም ኢንተርኔት ላይ የተመረኮዙ ከሆኑ በተዋዋቹ መካከል አገልግሎቱን ማለትም የኢንተርኔት ግንኙነቱን የሚሰጥ ሌላ ተጨማሪ አካል የመኖር ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ለምሳሌ ‹‹ኔትወርክ›› መኖርን የሚፈልጉ የባንክ አገልግሎቶች አሉ፡፡ ይህንን የ‹‹ኔትወርክ›› አገልግሎት የሚያቀርበው ኢትዮ ቴሌኮም አለ፡፡ አንድ ሰው የኤቲኤም ማሽን ተጠቅሞ በጨረታ ላሸነፈው ሥራ ገንዘብ አስተላለፈ፡፡ ይሁን እንጂ በኔትወርክ ችግር ምክንያት ክፍያው በሻጩ የባንክ ሒሳብ ውሉ ላይ በተገለጸው ሰዓት ሳይሆን ዘግይቶ ስለደረሰ ውሉ ቢፈርስ፣ ከተዋዋቹ ባለፈ የባንኩና የኢትዮ ቴሌኮም ኃላፊነት ምን ሊሆን እንደሚችል ሕግ ሊኖር ይገባል፡፡ 

ለማጠቃለል ያህል ኤሌክትሮኒካዊ ውሎችን በሚመለከት ከተሠራው ይልቅ የሚቀረው እጅግ ብዙ ነው፡፡ በኤሌክትሮኒካዊ ዘዴ የሚደረጉ ግንኙነቶችና ግብይቶች ከዕለት ወደ ዕለት ዓይነታቸውም መጠናቸውም እየተበራከተ ነው፡፡ በዚህ ዘዴ ለሚደረጉ የንግድም ይሁን ሌላ ግብይቶች ተገቢ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ ማውጣት ከሕግ አውጪው የሚጠበቅ ነው፡፡ እርግጥ ሕዝቡ እየጠበቀ ሕግ አውጪው ሕግ ባያመጣም፡፡ ያም ሆኖ ግን ስለዘገየ ይቅር የሚባልበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ የችግሩን አሳሳቢነት የትየለለሌ ምሳሌዎችን በማቅረብ ማስረዳት ይቻላል፡፡ ለጊዜው ይኼው በቂ ነው፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...