Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉጭሮ ለማፍሰስ ሳይሆን የፈሰሰውን ለመልቀም እንትጋ!

ጭሮ ለማፍሰስ ሳይሆን የፈሰሰውን ለመልቀም እንትጋ!

ቀን:

በሳሙኤል ረጋሳ

ከወራት በፊት የኢትዮጵያ ህልውና ከባድ ሥጋት ላይ ወድቆ ነበር፡፡ የሥጋቱም መነሻ በመንግሥትና በሕዝብ መሀል የነበረው ቅራኔ የመጨረሻው ጫፍ በመድረሱና ሕዝቡ በተለይ ወጣቱ ወደ አመፅ ጭምር መግባቱ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሕወሓት መራሹ ኢሕአዴግ በውስጡ በነበሩ ወጣት ኢሕአዴጎች ወሳኝ ትግልና በሕዝቡ ድጋፍ ከሥልጣኑ ዘወር እንዲል ተደርጓል፡፡ የአዲሱ አመራር ራዕይና የተግባር እንቅስቃሴ በውጭም በውስጥም ለነበሩ ኢትዮጵያውያንና ተቋማዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ብሩህ ተስፋን የፈነጠቀ ነበር፡፡ አገሪቱም ከአደጋ ተርፋ የሰላም ዘመን መምጣቱን ያበሰረ ነው ተብሎ ነበር፡፡

አሁን ያለው ዋና ጥያቄ የታሰበው ሰላም መጣ ወይ? ሕዝቡስ ከሥጋቱ ዳነ ወይ? አገሪቱስ ከመከፋፈልና ከመፈራረስ የአደጋ ሥጋት ወጣች ወይ? የሚሉትንና ሌሎች ሕዝቡን ምቾት የሚነሱትን ጥያቄዎች ቆም ብሎ ማጤን ያስፈልጋል፡፡ የማንፈልጋቸውንና ሊመሩን አይገባም ያልናቸውን ሰዎች ካገለልንና አሁን ያሉትን አመራሮች የምንደግፍ ከሆነ (ሕዝቡ ድጋፉን በተግባር ስላላየ) እየፈጠርናቸው ያሉት ችግሮች ከየት መጡ? የፀጥታው ሁኔታ ከበፊቱ እጅግ የወረደ በመሆኑ የአንድና የሁለት ሰዎች ሞት ትልቅ ዜና በነበረበት አገር፣ በመቶ የሚቆጠሩ ዜጎቻችን በተለያዩ አካላት ሲጨፈጨፉ የማይገርመን ሆነናል፡፡ ከአቅም በላይ በሆነ ረሃብ ካልሆነ በቀር በጦርነትና በፖለቲካ በአገር ውስጥ መሰደድ ወይም መፈናቀል ባልነበረበት አገር፣ ሚሊዮኖች ሁከትና ብጥብጥ አላኖር ብሏቸው ቀያቸውንና ንብረታቸውን ጥለው ተሰደዋል፡፡ ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ ጫፍ መታወቂያ ሳይኖረው ቢሻው በእግሩ ቢሻው በትራንስፖርት መዘዋወር የዕለት ጉዳይ በነበረበት አገር፣ ከአንድ ወረዳ ወደ ሌላ ጎረቤት ወረዳ ደርሶ መመለስ ዕድለኛነት ሆኗል፡፡ በሰላም ተምሮ መግባትና በሰላም ሠርቶ መብላት አስተማማኝ አልሆነም፡፡ በዚህ ከቀጠልን የወደፊት ዕድላችን ምን እንደሚሆን መገመት አይከብድም፡፡ የልጆቻችንንም ተስፋ ከዚህ አንፃር መታየት አለበት፡፡ መጪውን ጊዜ የሚሠራው የአሁኑ ትውልድ ነው፡፡ ያለንበትን ዘመን የሠሩት ደግሞ ቀዳሚዎቹ ትውልዶች ናቸው፡፡ እስከ ዛሬ የነበሩት ቀዳሚዎቹ ለእኛ አገራችንን ከእነ ችግሯም ቢሆን በነፃነት አስረክበውናል፡፡ እኛ ደግሞ ሲሆን ችግሯን ቀርፈን አገሪቱን በነፃ ማስረከብ መቻል አለብን፡፡ አሁን እየተጓዝንበት ያለው መንገድ ተስፋን የሚያጭር ሳይሆን የክፉ ቀን መቃረብ ምልክት ነው፡፡ ሰላምን ለማውረድ ሳይሆን አዳዲስ ቅራኔዎችን በመፍጠር ተጨማሪ አደጋን ለማስከተል የሚተጉ በጣም በርካታ ወገኖች አሉን፡፡

- Advertisement -

በየዕለቱ የሕዝባችንን መሞትና መሰደድ ሳይገርመንና መፍትሔ ሳናበጅለት ብናነሳውም ምንም ፋይዳ የለውም፡፡ ነገር ግን ሕዝብን ከፍተኛ ስሜት ውስጥ ከቶ ሊያጨራርስ የሚችል ትኩስ አጀንዳ ቀርፀን ወደ ሕዝቡ እንደ ጥሩ ነገር እናስተላልፋለን፡፡ ኢሕአዴግ በብሔር ፖለቲካ መረዘን እያልን እኛም ያንኑ ተከትለን የበለጠ ጠንካራ መርዝ ወጣቱን እየጋትነው ነው፡፡ አሁን ሁሉም ፖለቲከኛ ነኝ ባይ የሚያስበውን የተወሰነውን የሕዝብ ክፍል በቀቢፀ ተስፋ አደናግሮ የራሱን ደጋፊ በማፍራት የተሻለ ኃይል በመያዝ ለሥልጣን መብቃትን ነው፡፡ አንዱ የሕዝብ ክፍል በብሔርም ሆነ በሌላ ከተያዘ ሌላው ደግሞ ያልተያዘ አካባቢን ፈልጎ በክፉ መንፈስ በማነሳሳት የግሉ ለማድረግ መጣር የዘመኑ ፋሽን ሆኗል፡፡ በማኅበራዊና በመደበኛ ሚዲያዎች፣ የስፖርት ሜዳዎችን ጨምሮ ሁሉም ሕዝብን ሊያገናኙ በሚችሉ ዘዴዎች፣ ሕዝብን በሕዝብ ላይ ለማሳመፅ በተቻለ መጠን እየተሠራ ነው፡፡ አንዱ ሳይሳካ ሲቀር ሌላው ይሞከራል፡፡

አገር የሕዝብና የመሬት ድምር ነው፡፡ አሁን ያልተመቸውና የተበደለው ሰው ብቻ ሳይሆን መሬቱም ነው፡፡ ከባህሮቿ ርቀናል፡፡ ሐይቆቿን አድርቀናል፡፡ ወንዞቿን አድርቀናል፡፡ የተፈጥሮ ዛፎቿን ጨርሰን አገሪቱን ራቁቷን አስቀርተናል፡፡ አፈሯን ቦርቡረንና መርዘን ልማቷን አምክነናል፡፡ አራዊቶቿንና አዕዋፏቷን በጥይትና በጭስ ፈጅተንና አስደንብረን ወደ ጎረቤት አገር አብርረናቸዋል፡፡ ለዚች አገር ህልውና ሲል ከሩቅና ከቅርብ ከመጣው ጠላት ጋር ተናንቆ የሞተን ቀዳሚ ትውልድ ረስተን፣ ዛሬ እኛው ያራቆትናትን አገር እንደ ቅርጫ ሥጋ ተቃርጠን ለየራሳችን ለማድረግ እየተፋጀን ነው፡፡ እስካሁን ድረስ የጨመርንላት ልማት የደረስንበት ስኬት የለም፡፡ የጨመርነው ነገር አለ ከተባለ እንኳ በየዓመቱ ቁጥሩ በሚሊዮን የሚጨምር ደሃ ሕዝብ ነው፡፡ ሰላም የምንነሳትን አገር ለመግዛት እንጣላለን፡፡

የዛሬ 800 ዓመት የሠራነውን የላሊበላ ሕንፃ እንኳ ማደስ አቅቶን ፈረንጅ ገንዘብና ዕውቀት እንዲመፀውተን የዛሬው ትውልድ በልመና ላይ ነው፡፡ እህል የሚመረተው በአፈርና በውኃ በመታገዝ ነው፡፡ እኛ ግን ይኼን ግብዓትና ተፈጥሮአዊ ሁኔታ ከሚገባው በላይ ተሟልቶልን ሳለ፣ ፈረንጅ ቀለብ ካልሰፈረልን መኖር የማንችል ሆነናል፡፡ ፈረንጅ አገር እህል በፋብሪካ አይመረትም፣ ከሰማይም አይዘንብም፡፡ እኛ ወይ አመራረቱን አላወቅንም ወይም የጋረደብን ነገር አለ፡፡ ረሃብ ለምንድነው እኛን ለይቶ በቋሚነት የሚያጠቃን? ግርግር፣ ረብሻና እልቂት ለምንድነው ዘለዓለም የማያጣን? ማንኛውም አገር ችግር ሊገጥመው ይችላል፡፡ ሰላምም ሊያጣ ይችላል፡፡ ለዘለዓለም ግን አብሮት አይኖርም፡፡ እኛ ታሪካችን ሁሉ የጦርነትና የችግር ሆነ፡፡ እነዚህንና ሌሎች ተመሳሳይ ከእኛ ጋር ኖረው ያረጁትን ችግሮች ለመፍታት የቻለ መንግሥትም ሆነ ምሁር አልገጠመንም፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከነበረው የማረሻና የበሬ እርሻ አልወጣንም፡፡ ዛሬም ድረስ በወፍጮአችን በሁለት ድንጋይ መሀል እህል አስቀምጦ አንዱን በሌላ ማሸት አልቀረልንም፡፡

መሪዎቻችን ጨካኞች፣ ክፉዎችና ስግብግቦች በመሆናቸው ሥልጣን ከተቆናጠጡ በኋላ ሌት ተቀን የሚያስቡት ሕዝቡን የማሠልጠንና የማዘመን መንገድ ሳይሆን፣ ምን ብናደርገው ነው ሥልጣናችንን ሳይቃወም በመኃይምነት የሚገዛልን በሚል እሳቤ የተቃኘ ነው፡፡ መሪዎቻችን የሥልጣን ዕድሜያቸው ማብቃቱ ሲገባቸው፣ ሕዝብን በማናቆርና በማጨራረስ ከተጠያቂነት ለመዳንና ባሉበት ለመቀጠል በሚቻላቸው ሁሉ ይጥራሉ፡፡ ምክንያቶቹ ብዙ ናቸው፡፡ ሲፈልጉ እኛ የማናውቀው ታሪክና በደል ፈጥረው እንገነጠላለን ይሉና የማናውቀው ጦርነት ውስጥ ከተው ያጨራርሱናል፡፡ ከተቻለም ይገነጥሉናል፡፡ ሲፈልጉ የማናውቀውን ርዕዮተ ዓለም ከፈረንጅ ቀድተው ያመጡና የመንግሥተ ሰማያት መግቢያ ብቸኛ በራችን ነው በማለት ነውጥ ፈጥረው ካጨራረሱን በኋላ፣ ወደማናውቀውና ወደማንለምደው የአስተዳደር ዘይቤ ከተው መምከሪያ ያደርጉናል፡፡ ፊውዳሊዝም፣ ሶሻሊዝም፣ ካፒታሊዝም፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ…ወዘተ ምን ያልተሞከረብን አለ? ግን አንዱም አልሠራም፡፡ ሲሻቸው የእኛ ብሔር ሲጨቆን ኖሯልና አሁን ነፃነታችንን ማግኘት አለብን በማለት በስሜት እየነዱ ምንም ትርፍ ወደማያስገኝ ጦርነት ይከቱናል፡፡

የጂኦግራፊያዊ አቀማመጣችንን፣ የሃይማኖት ልዩነቶቻችንን ሁሉ ሳይቀር በምናባቸው የሚፈጥሩትን ልዩነት በውስጣችን በማስረፅ አብሮ የኖረ ሕዝብ ጎራ ለይቶ እንዲፋጅ ያደርጉታል፡፡ በተለይም በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ሁሉም ነገር የፖለቲካችን ነፀብራቅ ሆኗል፡፡ ፖለቲካችን ደግሞ ቅኝቱ በሙሉ የሚያራርቅና የሚያጨራረስ ነው፡፡

በአገራችን ሁሉም ሰው ሥልጣን መያዙን እንጂ ለሥልጣን ብቁ መሆኑንና አለመሆኑን አያገናዝብም፡፡ ሁሉንም ነገር ለመፈጸምና ለሥልጣን ለማብቃት ፖለቲከኛ መሆንና በፖለቲካ ሥራ ውስጥ ማለፍ ብቻውን ለሥልጣን የሚያበቃ አይደለም፡፡ አገርን ለመምራት የራሱ የሆነ የተለየ ክህሎት በተጨማሪ ያስፈልገዋል፡፡ ትዕግሥተኝነት፣ አስቦ መናገር፣ ሁሉንም በእኩል ማየት፣ የሰውን ሐሳብ ማዳመጥ፣ ሊደርስ የሚችል አደጋን ገምቶ በቅድሚያ መፍትሔ ማስቀመጥ፣ የመሳሰሉትንና ሌሎችንም ብቃት ይጠይቃል፡፡ እነዚህ ብቃቶች ደግሞ በካድሬነት ወይም በዶክተርነት ብቻ የሚገኙ ሳይሆኑ፣ ከውልደቱ እስከ ዕድገቱ ባዳበረው ሰብዕናና በተፈጥሮም ጭምር የሚገኙ ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት ወጣቶቻችን ማወቅ የሚገባው ተምረው ሥራ መያዝ ብቻ ሳይሆን፣ ለወደፊቱ አገሪቱን ተረክበው አንድነቷን ጠብቀው በሰላም ሊመሩ እንዲችሉ ከቀድሞዎቹ መሪዎች የተለየ አዲስ ሰብዕና መላበሳቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡ ምክንያቱም የዚህች አገር መጥፊያዋም ሆነ መዳኛው ያለው በተተኪው ትውልድ እጅ በመሆኑ ነው፡፡ እነዚህን ወጣቶች አቅጣጫ የሚያሳያቸው፣ በቂ ተሞክሮና ዕውቀት ያለው ቀና የሆነ ቀዳሚ ትውልድ ሊመራቸው ሊያስተምራቸው ይገባል፡፡ አሁን ያለው ወጣት ተወልዶ ያደገው በኢሕአዴግ ሥርዓት ውስጥ ነው፡፡ ስላለፈው ዘመን የአገሪቱ ታሪክ፣ ስለሕዝቦቿ አንድነትና የጋራ ትውፊቶቻችን እንዲያውቅ አልተደረገም ብቻ ሳይሆን አልተፈለገም፡፡ በአንፃሩ በትምህርት ቤትም በውጭም ልዩነቶቻችን እንዲጎሉና እንዲበዙ ሆኗል፡፡ በአገርና በብሔር መሀል ያለው ልዩነትና አንድነት ሳይነገረው አገርን ጠልቶ ብሔሩን እንዲያስቀድም ነው የተማረው፡፡ ኢሕአዴግ ይኼ ሲከተለው የነበረውና ያስተማረው መንገድ ስህተት መሆኑን አምኗል፡፡ ነገር ግን ይኼ ስህተት በወቅቱ በአዕምሮአችን እንዲሰርፅ የተደረገው በጣም በጥልቀት ነው፡፡ በመሆኑ ይኼ ስህተት የሆነው አስተምሮ በአዕምሮአችን ውስጥ ፅኑ መሠረት በመያዙ በቀላሉ ልንገላገለው አልቻልንም፡፡ የምንጓዝበት መንገድም ትክክል ይመስለናል፡፡ የምናምነውና የምናነበው በቂ ሰነድ የለንም፡፡ ቢኖርም መጻሕፍትን ማንበብና ሰነዶችን የመመርመር ባህል ጨርሶ ጠፍቷል ወደሚባልበት ደረጃ እየደረስን ነው፡፡ ዋና የመረጃ ምንጮቻችንን ፌስቡክና ካድሬዎች የሚመስሉን በርካቶች ነን፡፡ ይኼን ክፍተት የተረዱ በርካቶች ወጣቶችን በማባበልና በመለማመጥ ለተሳሳተ ዓላማቸው ማስፈጸሚያነት የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ነው፡፡ አሁን ባለው ወጣት ትውልድ በመጀመርያ አገሪቱን በማስቀጠል ላይ እንተማመንና እንሥራ፡፡ አፍራሽ ዝንባሌዎችን እንለያቸው፡፡ አንዴ ካመለጠን ልንመልሰው ወደማንችል ስህተት አንግባ፡፡ አንድ የሁላችንም የሆነ የጋራ መንገድ እንዲኖረን መንግሥትና ሕዝብ ሚናቸውን ይወጡ፡፡ አገራዊ ችግር አገራዊ መፍትሔ ያስፈልገዋል፡፡ መለያየታችን ደካማ ያደርገናል፡፡ ለጠላቶቻችን የምንመቸው ደግሞ ደካማ ሆነን ስንገኝ ነው፡፡

በአሁኑ ዘመን አንድ አገር ደካማ የሚሆነውና የሚፈርሰው ከውጭ በሚመጣ ወራሪ ኃይል አይደለም፡፡ አሁን በእኛ አገር እየተሞከረ እንዳለው የእርስ በርስ ግጭትን በመፍጠር እርስ በርስ በማጠፋፋት ነው፡፡ አንድ አገር ከሌላው ጋር የሚያደርገው ጦርነት ቀርቷል፡፡ አሁን አንድን አገር ለማሸነፍም ሆነ ለማፍረስ ቀላልና ወጪ ቆጣቢ የሆነው አስተማማኝ መንገድ ሕዝቡን እርስ በርሱ ማጫረስ ነው፡፡ ይኼ አስተማማኝና በጣም ውጤታማ መሆኑን እንደ የመንና ሶሪያ ካሉ አገሮች መረዳት ይቻላል፡፡ እነዚህ አገሮች ከማንኛውም ኃይል ከሚባል አገር ጋር ጦርነት ገጥመው ቢሆን ኖሮ የሚያገኛቸው ጉዳት በምንም መመዘኛ ከአሁኑ ጋር የማይወዳደርና ቀላል ነበር፡፡ የመከራና የጦርነቱ ዘመንም ይኼን ያህል አይረዝምም ነበር፡፡

እስካሁን በነበረው ሁኔታ መሪዎቻችን አልተጠነቀቁልንም፡፡ አገሪቱን ከማዳንና ሕዝቡን ከመጠበቅ ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም ሲያሳድዱ ነው የኖሩት፡፡ ብዙዎቻችን የምንታለለው መሪ ሲባል ከሁላችንም በተሻለ አገሪቱን የሚወድ ይመስለናል፡፡ አንድ ተራ ዜጋ ከመሪው የበለጠ አገሩን ሊያፈቅር ይችላል፡፡ እነሱ የሚፈለጉት አገርን ለማስተዳደር የተሻለ ብቃትና ተነሳሽነት ይኖራቸዋል በሚል እሳቤ ነው፡፡ ይኼ እሳቤም ብዙ ጊዜ ስህተት እንደሆነ ዓይተናል፡፡ ስንት አዋቂ ተሸፍኖ ባለበት አገር ነው የማይገባቸውን ቦታ ይዘው የማይገባቸውን ሀብት የሰበሰቡት፡፡

የወደፊቱን መገመት ቢከብድም የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት እስካሁን ካየናቸው ሁሉ ለሕዝቡ የተሻለ ፍቅር፣ ክብርና በጎ ጥረት እንዳለው መገመት አይከብድም፡፡ የአገሪቱን ሰላም ለማስጠበቅ በትዕግሥትና በጥበብ እየተደረገ ያለው አካሄድ የሚያበረታታ ነው፡፡ ምናልባትም ዶ/ር ዓብይ ወደ ሥልጣን ባይመጡና ሌላ ሰው ተመርጦ ቢሆን ሊደርስ የሚችለውን ዕልቂትና ሁከት እናስበው፡፡ አንዳንድ ሰዎች አሁንም ቢሆን ሞቱ አልቀረልንም በማለት የሚማረሩ አሉ፡፡ ነገር ግን አሁን ያለው ሁኔታ ከጅምላ ፍጅት አድኖ ወደ ተቆጠበ ግድያ መልሶናል፡፡ ሕዝቡም እየተፈጸመ ያለውን ችግር በትዕግሥት የተቀበለው፣ መንግሥት ያለውን ቀናነትና አገራዊ ስሜት በማየት ነው፡፡ ወደፊትም የመንግሥት ጥረት እስከቀጠለ ድረስ ሕዝቡ በዚሁ መንፈስ እንደሚቀጥል ይገመታል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ከዚህ መንግሥት በተሻለ ዴሞክራሲያዊ መብታችንን ጠብቆ በትዕግሥት የሚመራን ያለ አይመስልም፡፡ ሁልጊዜ ችግሮችን ለመፍታት የምንሞክረው በኃይል ወይ በፍቅር ነው፡፡ ባለህሊና ሰው በፍቅር፣ ባለክፉ አዕምሮ ደግሞ በኃይል ችግራቸውን ለመፍታት ይሞክራሉ፡፡ የህሊና መሠረቱ በጎና ሚዛናዊ የሆነ አስተሳሰብ ተግባር ነው፡፡ ህሊና እንዲኖረን ተገቢው የሞራል፣ የትምህርትና አዎንታዊ የሆነ አካባቢያዊ ዕውቀት ያስፈልገናል፡፡ ህሊና ቢሶች ላይም እነዚህን ግብዓቶች በመጨመር ህሊና ልንፈጥርላቸው እንችላለን፡፡

አሁን ያለውን መንግሥት በግልጽ እየተቃወሙ ያሉት የትግራይ ክልላዊ መንግሥት አመራሮች ብቻ ይመስላሉ፡፡ እነሱ ወደ ሰላም ለመምጣት የሚያስቸግራቸው ነገር ምንድነው? ከዚህ በፊት በተደረገው የመቀሌ ሰላማዊ ሠልፍ ላይ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ሲናገሩ፣ ከሕወሓት ውጪ ያሉትን አመራሮች እነሱ ማርከው ያመጡዋቸው በመሆኑ ስለነሱ ስሜት እንደሌለቸው ገልጸዋል፡፡ ይኼ የትዕቢትና የጀብደኝነት አነጋገር ነው፡፡ ለወደፊት በአጭር ጊዜ ውስጥ የተፈጠረው ክፍተት በሰላማዊ መንገድ ተፈትቶ ሰላማችንን እንመልሳለን ስንል፣ የበለጠ ውጥረት መፍጠር ተገቢ አይደለም፡፡ ክፉ ዶሮ ‹‹ባልበላውም ጭሬ አፈሰዋለሁ›› አለች አሉ፡፡ ባለህሊናዋ ዶሮ ደግሞ ‹‹እንኳንስ ላፈስ የፈሰሰ እለቅማለሁ አለች›› ይባላል፡፡

ሁሉም ነገር አሁን ባለበት ረግቶ አይቀርም፡፡ ጊዜ ሲያልፍ የሚያስቆጨንን ነገሮች አንሥራ፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ አምቦ ከተማው ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ በመንግሥት ሥራ ላይ ነበር፡፡ ችግሮች እንዳይፈጠሩ በዚያ አካባቢ ካየኋቸው አጋጣሚዎች ጥቂቱን ልግለጽ፡፡ አምቦ አካባቢ አገራዊ ወይም አካባቢያዊ የሆነ ችግር ሲመጣ ‹‹ለሚያልፍ ዘመን›› የሚል አባባል አላቸው፡፡ ይኼ የኦሮሚኛ አባባል መሠረተ ሐሳቡ በክፉ ቀን ያለ ጥፋታቸው ለጥቃት የተጋለጡና ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ወገኖችን ከክፉ ዘመን በህሊናዊ ድጋፍ መታደግ ነው፡፡ ይኼ አባባል ጊዜ ሲያልፍ የሚያስከትለውን መተዛዘብና አብሮ ለመኖር ያለውን ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት ሁኔታዎችን ለመፈጸም ወይም ላለመፈጸም የሚረዳ እሳቤ ነው፡፡ ከማውቃቸው በርካታ አብነቶች ሁለቱን እነሆ፡፡

ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከክፉ ዘመን ሁሉ የከፋው ክፉ ዘመን የደርግ የቀይ ሽብር ዘመን ነው፡፡ የቀይ ሽብር ወቅትን ለዚህ ትውልድ ማስረዳት እጅግ ከባድ ነው፡፡ ካልኖሩት በቀላሉ አይገባም፡፡ በእነዚህ የመከራና የግፍ ዘመናት ከአምቦ በስተቀር በሁሉም የአገሪቱ ከተሞች ወጣቶች ያለ ፍርድ በግለሰቦች ፍላጎት እየተረሸኑ አስከሬናቸው በየአደባባዩ ተጥሎ ዝናብና ፀሐይ ሲፈራረቅበት ይውል ነበር፡፡ አምቦ ግን በቀይ ሽብር አንድም ሰው አልተገደለም፡፡ አምቦ ከዚህ ጉድ ያመለጠችው ገዳይ ካድሬና አጥፊ ሳይኖር ቀርቶ አይደለም፡፡ በወቅቱ የአገር ሽማግሌዎች በ‹‹ለሚያልፍ ዘመን›› ብሂላቸው ማንንም ሰው ማጋለጥና መጠቆም የሚባለውን የእርስ በርስ መጠፋፊያ ዘዴ ዝግ እንዲሆን አጥብቀው ውስጥ ውስጡን ስለሠሩ ነው፡፡ አዎ ሕዝብም አልጠቆመ፣ ዘመኑም አለፈ፣ ወጣቱም ከሞት ተረፈ፡፡

ሌላው አብነት ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን እንደመጣ መላ አገሪቱን ለማረጋጋትና ለመቆጣጠር ከብዶት ነበር፡፡ ስለዚህም የመንጋ ፍርድን እንደ መፍትሔ መጠቀም ጀመረ፡፡ ሕዝብን እያስወሰነ ዕርምጃ ያስወስድ ነበር፡፡ በዚህ መሠረት አሥራ አንድ ወጣቶች ሕዝብ በተሰበሰበት ስታዲየም ለፍርድ ቀርበው ካድሬዎች ባደረጉት ከፍተኛ ቅስቀሳ ወጣቶች እንዲገደሉ ተወሰነባቸው፡፡ ወደ መገደያ ሥፍራ ቀርበው የሞት ቅጣት ሊፈጸምባቸው ሲል ከሕዝቡ መሀል አንዱ ተጨማሪ ሐሳብ አቀርባለሁ ብሎ ዕድል ከተሰጠው በኋላ፣ ‹‹ለሚያልፍ ዘመን›› ብለን ልጆቻችንን ራሳችን አናስገድልም በማለት ሰፊ ንግግር አደረገ፡፡ በግለሰቡ ንግግር ልባቸው የተነካው ተሰብሳቢዎችም ወዲያው በጭብጨባና በፉጨት ከመቀመጫው ተነስተው ግድያውን ስለተቃወሙ ወጣቶቹ ከሞት ተረፉ፡፡

ስለዚህ ከዚህ ዘመን ብዙ እንማራለን፡፡ የሚገርመው ነገር ይኼ ዘመን ሲያልፍ በትዕግሥትና በጥበብ ማለፍ የሚገቡን ብዙ ነገሮች እንደነበሩ እናያለን፡፡ ግን ለሚያልፍ ዘመን የማያልፍ ክፉ ሥራ ብንሠራ መጪው ጊዜ በሙሉ የፀፀት፣ የቁጭትና የአደጋ ይሆንብናል፡፡ ስለዚህ ጭራ የምታፈሰዋን ዶሮ ሳይሆን የፈሰሰውን የምንለቅም እንሁን፡፡ አብዛኛው ሕዝብ በቄሮና በቀሬ ዘመን ይኼ አስተሳሰብ የቀረ ነው ቢልም፣ እርሾው እንዳልጠፋ ምልክቶቹ አሉ፡፡ ይኼ አካባቢ በአሉታዊም ሆነ በአዎንታዊ የፖለቲካ ተፅዕኖ ሥር ካሉ የአገሪቱ ክፍሎች አንዱ ነው፡፡ ሆኖም ግን በዚህ ሁሉ አስቸጋሪና ምስቅልቅል ጊዜም ቢሆን በአካባቢው በርካታ ችግሮች ተፈጥረዋል፡፡ ነገር ግን በጣም የሚገርመው በዚህ ሒደት ውስጥ ከሌላ አካባቢ በመጡ ወይም የሌላ ብሔረሰብ አባላት በሆኑ ነዋሪዎች ላይ የደረሰ የመገደል፣ የመገለል ወይም የማስወጣት ዕርምጃ የተወሰደበት የለም፡፡ እንደ ቀድሞው አብረው ይኖራሉ፡፡ ማኅበራዊ ግንኙነታቸውም አልላላም፡፡ ይኼ ማለት ግን አካባቢው በሙሉ ፍቅርና ሰላም ነው ማለት አይደለም፡፡

በአሁን ጊዜ ሁላችንም ለአገራችን ከሁሉም በፊት የምንመኝላት ሰላም ነው፡፡ ሰላምን ለማግኘት ደግሞ ፍቅር መቅደም አለበት፡፡ ፍቅር በሌለበት ሰላም ምኞት ብቻ ስለሚሆን አይታሰብም፡፡ ቀደም ሲል በመላ አገሪቱ በሕዝብ መሀል የነበረውን ፍቅር አጠናክሮ ለማስቀጠል ሳይሆን፣ ቅራኔዎችን የሚፈጥሩና የሚያሰፉ ቡድናዊ አስተሳሰቦች በሕዝብ ውስጥ እንዲሰርፁ በመደረጉ ነው ፍቅር የጠፋውና ቅራኔ ያሰፋው፡፡ ፍቅር ባለመኖሩ ደግሞ ሰላም ሊኖር አልቻለም፡፡

እንግዲህ የብሔራዊ ዕርቅ መሠረት ሐሳብ ፍቅርን በመመለስ ሰላምን ማስከተል በመሆኑ፣ መንግሥት እየሄደበት ያለው የብሔራዊ ዕርቅ ጉዳይ ሁሉም ሊደግፈው የሚገባ ነው፡፡ ለዚህ አፈጻጸም ሲባል የሚቋቋመውን ኮሚሽን አባላት በጥንቃቄ መሰየም አለባቸው፡፡ አሁን እንደምናየው ሹመት የካድሬዎች ስብስብ ወይም ለባለሥልጣናቱ ቀረቤታ ስላላቸው ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ለሴቶች፣ ለወጣቶች፣ ለብሔረሰብ፣ ለሃይማኖት…ወዘተ ኮታ ሰጥተን ያለ ተገቢነት ነገሮችን ሁሉ መልሰን ጥሬ እንዳናደርግ እንጠንቀቅ፡፡ አሁንም ለዚህ ሥራ ጭረው የሚያፈሱትን ሳይሆን፣ የፈሰሰ የሚለቅሙትን በመብራት ፈልገን ማግኘት አለብን፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...