Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በቀረጥ ነፃ ብዝበዛ

በየግብይት ሥርዓቱ ውስጥ የሚካሄዱ በርካታ ሸፍጦችና ወንብድናዎች ተበራክተዋል፡፡ የመንግሥት ሹማምንት ሳይቀር በንግድ መስመሮች ውስጥ በስውር እየተሳተፉና ከነጋዴዎች ጋር ‹‹በኔትወርክ›› እየተመሳጠሩ ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ያለርኅራሄ የአገር ሀብት አባክነዋል፡፡

ሸማቾችም ያለፍዳቸው እንዲሸከሙ የሚገደዱት ያልተገባ ዋጋ ጭማሪ ከብዙ ምክንያቶች መካከል በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ ባንሰራፉ ሥውር ደባዎች የሚጣሉባቸው በመሆናቸው ነው፡፡ ጥራቱን ያልጠበቀ ምርት ያለ ምንም ይሉኝታ በማስመጣት ገበያውን በሚያጨናንቁ አስመጪዎች ተግባር ስናዝን ቆይተናል፡፡ በግብይቱ ውስጥ የሚፈጸሙ ያልተገቡ ተግባራትን ወደ ሕጋዊ መስመር ለማስገባት ያለው ተነሳሽነትና ቁርጠኝነትም ከፉከራ ብዙም ፈቅ አለማለቱ ሌላኛው ችግር ነው፡፡ ሕገወጥ ነጋዴዎች አባሪና ተባባሪ ስላላቸው፣ ለምን ይህንን ፈጸምክ ብሎ የሚቆነጥጣቸው ባለመኖሩ ጭምር ያሻቸውን ያደርጋሉ፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር የጀመረውን እንቅስቃሴ የሚደግፈው አቻ መሥሪያ ቤት መኖር አለበት፡፡ ሸቀጦችን ከዋጋ በታች እንደሸጡ በማስመሰልና ሲገዙም ከፍተኛ ወጪ እንዳወጡ በማጭበርበር (አንደር ኢንቮይሲንግ፣ ኦቨር ኢንቮይሲንግ) የገቢና ወጪ ንግዱን እንዳሻቸው የሚያሽከረክሩ ‹‹ነጋዴዎች›› በተግባራቸው ልክ ሊቀጡና ሊወነጀሉ ይገባቸው ነበር፡፡ በመንግሥት ይህ ባለመደረጉ፣ ተገቢው ቁጥጥር ስለሌለ፣ ይልቁንም አስመጪዎች የትኞቹ እንደሆኑና ላኪዎችም እነማን እንደሆኑ መንግሥት አጣርቶ እያወቀው በደረሰኝ የማጭበርበር ተግባር ተንሰራፍቶ መታየቱ አስገራሚ ነው፡፡ በዚህ ሳቢያ ከአገር የሚሸሸው ገንዘብ ምን ያህል እንደሚሆን እየገመትን ግምታችን የሚያደርሰን ድምዳሜና መላምት ላይ በመንተራስ የጉድ አገር ማለታችን አይቀርም፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት የአገርን ሀብት ከማሸሽ ባሻገር፣ በገበያው ውስጥ የሚፈጥረው ውጣውረድ ለአገር ዕድግትም ሆነ ለሕዝቡ ኑሮ  ደንቃራ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ሁሉንም ጎድቷል፡፡ የጥራቱን ጉዳይ ለፈጣሪ እንተወውና በተጭበረበረ  ዋጋ ወደ አገር የሚገባው ዕቃ በገበያው እንዳሻው ወደ ላይ ከሚሰቀልበት ምክንያት አንዱ በተጭበረበረ ደረሰኝ የተነሳ እንደሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ድርጊቱ ረቀቅ ያለም ነው፡፡

በደረሰኝ ለማጭበርበር ብሎም ሆነ ብሎ ዋጋን በማዛባት ለሚገኝ ርካሽ ጥቅም ምቹ ከሆኑት መካከል ከቀረጥ ነፃ ማበረታቻ ቁልፍ ሚና አለው፡፡ መንግሥት የቀረጥ ነፃ ማበረታቻ ሲያወጣ፣ ዓላማው ለኢኮኖሚው ማደግ፣ ለሕዝብ ጠቃሚነት የሚያግዙ የኢንቨስትመንት ተግባራትን እደጉ በርቱ ለማለት እንደሆነ ይታመናል፡፡ በማበረታቻው ተበረታተው በሚያከናውኗቸው የንግድ ሥራዎች ለዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ፣ የነዋሪዎችን አማራጮች የሚያሰፉ፣ አሮጌውን በአዲስ አሠራር ተክተው ኑሮን የሚያቀሉ ፕሮጀክቶችን ለማገዝ ከሚል መነሻ የሚሰጥ ማበረታቻ ነው፡፡ ማበረታቻው ግን የሚፈለገውን ውጤት አምጥቷል ማለት አይቻልም፡፡ በትክክል ሥራ ላይ ውሏል ወይ? ብለን ብንፈትሽ ጉድ እንደምንጎለጉል ከሰሞኑ ገቢዎች ጫፍ ጫፋቸውን የነካካቸው ዕርምጃዎች ያመላክቱናል፡፡

ከቀረጥ ነፃ ማበረታቻዎች ብቻም ሳይሆኑ፣ ለውጭ ባለሀብቶች የሚሰጡ የተጋነኑ የታክስ ዕፎይታዎችም ጭምር ካስገኙት ጥቅም ይልቅ የውጭ ምንዛሪ ገቢ በማሸሽ ጉዳት ማስከተላቸውን በአፍሪካ ላይ የተካሔደውና በቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ የሚመራው ከፍተኛ የጥናት ቡድን ያወጣው ሪፖርት፣ ኢትዮጵያም የዚህ ዓይነቱ ሰለባ እንደሆነች ከጥቂት ዓመታት በፊት ይፋ አውጥቶ ነበር፡፡ ሰምቶ የሚተገበር አካል ጠፋ እንጂ፣ በርካታ አሃዛዊ መረጃዎችም ኢትዮጵያን ጨምሮ በእንዲህ ያለው ማበረታቻ ሰበብ የደረሰባቸው ጉዳት ተመላክቶ ነበር፡፡

ግሎባል ፋይናንሺያል ኢንተግሪቲ እንዳሰኘው ያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ባወጧቸው መረጃዎች መሠረት ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ከኢትዮጵያ የሸሸው ገንዘብ ከ30 ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ ስለመሆኑ ያመላክታሉ፡፡ የታቦ ምቤኪ ተቋም ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. እስከ 2010 ባለው ጊዜ ውስጥ፣ በአሥር ዓመታት በአማካይ አሥር ቢሊዮን ዶላር እንደሸሸባት ሲያስታውቅ፣ ይህም 13 ዓመታት የፈጀባትን የህጻናት ሞት ቅነሳ በሁለት ሦስተኛ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለመቀነስ ያስችላት እንደነበር ተንትኗል፡፡  

ከቀረጥ ነፃ የገባ ዕቃ ግምቱ ምን ያህል ነው የሚለው ሒሳብ ቢሠራ፣ ምን ያህል ለመንግሥት ገቢ ሊሆን የሚችል ምን ያህል ገንዘብ እንደቀረ መገመት አያዳግትም፡፡ መገመት ብቻም ሳይሆን፣ የገቢዎች ሚኒስቴር በትንሹ በዓመት ከ14 ቢሊዮን ብር ያላነሰ የቀረጥ ገቢ በታክስ እፎይታ ምክንያት እንደሚያጣ ማስታወቁ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ቀረጥ ከሚከፈልባቸው ዕቃዎች ባልተናነሰ ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ ዕቃዎች ገበያ ውስጥ ያላቸውን ድርሻ ካሰላን፣ የአገራችን የግብይት ሥርዓት ምን ያህል በችግር እንደተበተበ ያመለክተናል፡፡

የቀረጥ ነፃ ዕቃዎችን በማስገባት ከታለመላቸው ዓላማ ውጪ ያውላሉ የሚባሉት ተራ ነጋዴዎች ወይም ባለሀብቶች አይደሉም፡፡ ደህና ስም ያላቸው ተቋማትና ግለሰቦች፣ ባንክ ዋስትና የሚሰጣቸው ወፍራም ‹‹አልሚዎች››ም ተሳታፊ መሆናቸው፣ ለኢትዮጵያ ደሆች ይበልጥ መራቆትና ወደፊት ሊመጣ ይችላል ተብሎ በተሰፋ ለሚጠበቀው የባለሀብቶች አስተዋጽኦ አብዛኛው ሕዝብ ተጨማሪ ታክስ እንዲከፍል የሚያስገድድ አሠራር መሆኑ የታወቀ ነው፡፡

በቅርቡ የገቢዎች ሚኒስቴር ይፋ እንዳደረገው ቁጥሩ ሁለት ሺሕ የማይሞላ ነዋሪ በሚገኝባት የአፋር ክልሏ የገጠር ከተማ አባላ ውስጥ 52 ባለኮከብ ሆቴሎች እንገነባለን በሚል መነሻ ከቀረጥ ነፃ የገቡ የተለያዩ የግንባታና መሰል ዕቃዎች ሁኔታውን ይበልጥ ያሳዩናል፡፡ በዚህች ትንሽ ከተማ ባለ ኮከብ ሆቴል ቀርቶ ደረጃ ያለው ቪላ ቤት አልተገነባም፡፡ ይህ የሚያመለክተው በቀረጥ ነፃ ስም ምን እየተሠራ እንደነበር ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ችግር ሥር እየሰደደ መጥቷል፡፡

በእንዲህ ያለው እኩይ ተግባር በርካቶች የራሳቸውን ሀብት አደልበዋል፡፡ ከቀረጥ ነፃ ያስገቡትን ሸቀጥ ገበያው ውስጥ እንዳሻቸው መልቀቃቸው በሕጋዊ መንገድ ቀረጥ ተከፍሎበት የገባውን ዕቃ በቂጡ ቁጭ እያደረጉ ገበያውን እንደሚያመሳቅሉትም እንረዳለን፡፡

በዚያች ሚጢጢ ከተማ ውስጥ ይገነባሉ ለተባሉት ሆቴሎች ከቀረጥ ነፃ ሸቀጦችን ያስገቡት ሰዎች እንዲህ ያለውን አድራጎት ለብቻቸው ሆነው ፈጽመውታል ብሎ ማመን ሞኝነት ነው፡፡ በከተማዋ የተፈጸመው ጉድ እንደ ምሳሌ ቀረበ እንጂ ስንቱ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ነው ያለ ቀረጥ ስንታ ስንቱን ዕቃ ያለገደብ እየቸበቸበ ስንጥቅ አትርፎ፣ አገር አራቁቶ የሚንደላቀቀውን ቤቱ ይቁጠረው፡፡ ከቀረጥ ነፃ መብት ለሕገወጥ ንግድ ሰበብ ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡ ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ ምርቶች ለተፈቀደላቸው ዓላማ ስለመዋላቸው ማረጋገጥ እስካልተቻለ ድረስ በርካቶች እጃቸውን እያስረዘሙ መቀጠላቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

እንዲህ ያለውን ተግባር ለመቆጣጠር ይመስላል ከሰሞኑ ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ ምርቶችን ለጊዜው እንዲቆሙ ለማድረግ እንቅስቀሴ ተጀምሯል፡፡ በዚህ ረገድ መንግሥት ሊወስደው ያሰበው ዕርምጃ ተገቢ ቢሆንም፣ ጤነኛውን ከዋልጌው የሚለይበትን አሠራር መዘርጋት ይኖርበታል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት