Monday, February 6, 2023

የኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ቆይታና ውጤቱ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኢትዮጵያ የዛሬ ሁለት ዓመት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በመሆን የተመረጠችው ታኅሳስ 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ነበር፡፡ በወቅቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት አባልነት ድምፅ ከሰጡ 190 አባላት አገሮች መካከል የ185 አገሮችን ድምፅ በማግኘት የተለዋጭ አባልነት መንበሩን ስትቆናጠጥ የነበረው ጥያቄ፣ ይህ አባልነት ለአገሪቱም ሆነ ለቆመችለት ዓላማ ምን ፋይዳ ይኖረዋል የሚል ነበር፡፡ በወቅቱም ይህን ያህል ድምፅ አግኝቶ መመረጥ እንደ ትልቅ ድል ሲወሳ ነበር፡፡

ረቡዕ ታኅሳስ 24 ቀን 2011 ዓ.ም. በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ የዚህን ከፍተኛ ድምፅ ምንነት ሲያስረዱ፣ ‹‹185 ድምፅ ማግኘት ቁጥር ብቻ ሳይሆን፣ ከፍ ያለ ይሁንታና የኃላፊነት ስሜት የሚተላለፍበት ነው፡፡ 185 አገሮች ለአገራችን በጎ አመለካከት እንዳላቸው ያመላከተ ነው፤›› ሲሉ ለላቀ ኃላፊነት የመታጨት ዕድል እንደሆነ ያብራራሉ፡፡

ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ተለዋጭ አባልነት ኢትዮጵያ በወቅቱ የአንድ ዓመት ዝግጅት ያደረገች ሲሆን፣ አምስት ግቦችን ለማሳካት በማለም ነበር የዛሬ ሁለት ዓመት ቀሪዎቹን 14 አባላት የተቀላቀለችው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት አምስት ቋሚ አባላት ያሉት ሲሆን፣ አሥር በየጊዜው የሚቀያየሩ ተለዋጭ አባላት አሉት፡፡ ኢትዮጵያ ሰንቃ ከገባቻቸው ዓላማዎች የመጀመርያው የአገሪቱን ጥቅምና ሐሳብ ማንፀባረቅ ሲሆን፣ ሁለተኛው የአገሪቱና የቀጣናውን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ የራስን ጥረት ማድረግ፣ ሦስተኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በተጠናከረ መንገድ ዘመኑን እየመሰለ ማስቀጠል መቻል፣ አራተኛ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በአፍሪካ ኅብረት መካከል በተለይም በአፍሪካ ኅብረት ፀጥታና ደኅንነት ምክር ቤትና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታና ደኅንነት ምክር ቤት ግንኙነት ማጠናከርና አምስተኛ ሽብርተኝነትንና አክራሪነትን መከላከል የሚሉ ናቸው፡፡

አገሪቱ እነዚህን ግቦች ለማሳካት በስድስት መርሆዎች ላይ መሠረት ያደረገ ሥራ ስታከናውን እንደነበር አምባሳደር ታዬ ያስረዳሉ፡፡ እነዚህም መርሆዎች ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችና የሰላምና ፀጥታ ማስከበር በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚታወቁ ሕጎችና መርሆዎች እንዲመሩ ማድረግ፣ የሚወሰዱ አቋሞችን ከአገሪቱ ፍላጎት ጋር ማጣጣም፣ ከሁኔታዎች ጋር የተዛመዱና ሚዛናዊ ማድረግ፣ በተቻለ አቅም ገለልተኛ የሆነ አቋም መያዝ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር መርሆዎችን ማክበርና ማስከበር፣ በአፍሪካ ኅብረት የተወሰኑ ውሳኔዎችን በምክር ቤቱ ማንፀባረቅና ዓለም አቀፍ የሰላምና ፀጥታ ችግሮችን መፍታት የሚቻለው በባለ ብዙ ወገን እንጂ በተናጠል አለመሆኑን አቋም መያዝ የሚሉ ሲሆኑ፣ ቆይታው ውጤታማ እንዲሆን ትልቅ አስተዋፅኦ ያደረገ ዝግጅት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በቆይታው ምን ትርፍ ተገኘ?

እንደ አምባሳደር ታዬ ገለጻ፣ ኢትዮጵያ በፀጥታው ምክር ቤት በምታራምዳቸው መርሆዎች፣ በቆይታዋ የወሰደቻቸው አቋሞችና ያንፀባረቀቻቸው ጉዳዮች ዘላቂ ወዳጅ ለማፍራትና ለገጽታ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበራቸው፡፡ አገሮች በሚያንፀባርቋቸው አቋሞች የሚመዘኑባቸውን ዕርምጃዎች የሚወስዱ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ትልቅ የዲፕሎማሲ ትርፍ አግኝታለችም ይላሉ አምባሳደር ታዬ፡፡ ‹‹የተመኘነውም ይኼንኑ ነበር፤›› ሲሉም እርካታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በዘለለ ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ትርፎችንም እንዳገኘችና ቆይታዋ ውጤታማ እንደነበር የአምባሳደር ታዬን ሐሳብ ባለሙያዎች ይስማሙበታል፡፡ ከሪፖርተር ጋር የስልክ ቆይታ ያደረጉት የሰላምና ደኅንነት ምርምር ባለሙያ አቶ አበበ ዓይነቴና የጂኦ ፖለቲካ ተንታኝና ባለሙያ አቶ ልዑልሰገድ ግርማ የኢትዮጵያ ቆይታ በደምሳሳው ሲታይ ውጤታማ እንደነበር የሚስማሙ ሲሆን፣ የተገኘውን ውጤት ማስቀጠል ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡

‹‹በአጠቃላይ ከብዙ ዓመታት በኋላ የተገኘ ዕድል በመሆኑና ኢትዮጵያም ለዚህ መብቃቷ በራሱ ስኬት ቢሆንም ኢትዮጵያ ከረዥም ጊዜ እንቅፍል የነቃችበት ወቅት በመሆኑ፣ ይህ አገር ውስጥ በጊዜው በነበረው ሰላምና የኢኮኖሚ ዕድገት የተገኘ ፀጋ ነበር፤›› የሚሉት አቶ አበበ፣ በእርግጥም የኢትዮጵያ ቆይታ ስኬታማ ነበር ይላሉ፡፡

አቶ አበበ ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ቆይታ በአጠቃላይ ሲታይ ስኬታማ ነው ቢባልም፣ በተናጠል እያንዳንዱ አገራዊና ቀጣናዊ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ተነስተው ቢታዩ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ፡፡

በተመሳሳይ አቶ ልዑልሰገድ ኢትዮጵያ የፀጥታ ምክር ቤት አባል በነበረችበት ወቅት በዓለም እንደ አጠቃላይና እንደ ቀጣና በተለይ ችግሮች የታዩ እንደነበር በማስታወስ፣ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የነበራትን ግንኙነት ሰላማዊ ለማድረግ የወሰደችው ርቀትና ካሁን ቀደም በኤርትራ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ትወተውት የነበረች አገር ተለውጣ ማዕቀቡ እንዲነሳ ማድረጓ ትልቅ ዕርምጃ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹ይህ በዚህ የሚቆም ብቻ ሳይሆን ለሌላውም አካባቢ የሚሠራም ነው፤›› ሲሉ የዕርቁን ፋይዳ ጉልህነት ያስረዳሉ፡፡

ከኤርትራ ጋር የተደረገው ዕርቅ እንደ አገር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለኢትዮጵያ ትልቅ ከበሬታን ያስገኘ ነበር ያሉት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ፣ የኤርትራ ማዕቀብ እንዲነሳ ለማድረግ ለቀጣናው የሚኖረውን ፋይዳ ያለማሳለስ በማስረዳት ማዕቀቡን ማስነሳት ብቻ ሳይሆን ቅቡልነትን እንዲያገኝ ሰፊ ሥራ መሠራቱን ያብራራሉ፡፡

‹‹የኢትዮጵያና የኤርትራን ግንኙነት ወደ ኋላ መመለስ የማይቻል ነው፡፡ ወደ ኋላ መመለሱ በምንም ሁኔታ ቅቡልነትን ሊያገኝ አይችልም፡፡ የተለያዩ አገሮች በኢትዮጵያ የተደረገው ለውጥ ከላያችን ላይ ተከምሮ የነበረን መርግ ነው ያራገፈልን ብለዋል፡፡ በየወሩ የሚቀያየሩ የፀጥታ ምክር ቤት ፕሬዚዳንቶች መሸከም ከምንችለው በላይ ሙገሳን ሲያደርጉልን ነበር፤›› ሲሉም አምባሳደር ታዬ ዕርቁ ምን ያህል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትኩረት ያገኘ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ እንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት መውጣቷን ተከትሎ ይፈጠራል ተብሎ በተሠጋው የድጋፍ መቀነስ ምክንያት በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ተልዕኮ (አሚሶም) ዕድሜ ያጥራል ተብሎ የነበረ ቢሆንም እንዲቀጥል መደረጉ፣ አልሸባብ እንዲዳከምና የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት እየተንገዳገደ ቢሆንም እንዲጠነክር ማገዝ፣ ደቡብ ሱዳን ምንም እንኳን አሁንም አስተማማኝ ሁኔታ ላይ ባትሆንም የተሻለ አቋም ላይ እንድትገኝ ለማድረግ የተደረገ ጥረትና ኢትዮጵያ በቆይታዋ ያገኘቻቸው መድረኮች ተጠቅማ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶቿን ማጠናከር መቻሏ፣ ተጨማሪ ስኬቶች እንደሆኑ አቶ ልዑልሰገድ ያስረዳሉ፡፡

አምባሳደር ታዬ ተመሳሳይ ዕይታ ያንፀባረቁ ሲሆን፣ ይህ ቆይታ በተለይ በሰላም ማስከበር ኢትዮጵያ ባከናወነቻቸው ተግባራት ዕውቅና ያገኘችበት ነው ይላሉ፡፡ በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ተነስቶ ዕርቅ መፈጠሩ፣ በሱዳን ኢቢዬ ግዛት ዓለም አቀፍ ሆኖ የቆየ ችግርን ለመፍታት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ኃይል ቆይታ እንዲራዘምና የኢትዮጵያ አስተዋፅኦ ጉልህ እንዲሆን በማድረግ ረገድ፣ በሱዳን ዳርፉር ተሰማርቶ የሚገኘው ኃይል ውጤታማ እንዲሆን በማድረግ፣ በሶማሊያ፣ በብሩንዲ፣ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ በመካከለኛው ምሥራቅና በእስያ ሰላም እንዲመጣ የተሠሩ ሥራዎች እጅግ ከፍተኛ ውጤት ማስገኘት የቻሉ ናቸው ይላሉ፡፡

ችግር በተፈጠረባቸው አካባቢዎች የሰላም አስከባሪ ኃይል ማሰማራት የመጨረሻው አማራጭ መሆኑን በማመን የመከላከል ስትራቴጂና ሥልት በማስተጋባት አስተዋፅኦ መደረጉን በማስረዳት፣ ኢትዮጵያ በቆይታዋ 560 በይፋ የተመዘገቡ ንግግሮችን በማድረግ አቋሟን እንዳንፀባረቀችና ቢያንስ በቀን ሁለት ጊዜ በሚደረገው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ሰፋ ያለ አስተዋፅኦ መደረጉን አምባሳደር ታዬ ያስረዳሉ፡፡

‹‹በእነዚህ ዓመታት እንደ አገር ትልቁ ስኬት ነው የምንለው ከኤርትራ ጋር የተደረገው የሰላም ስምምነት ነው፡፡ ዓለማችን እ.ኤ.አ. በ2018 ከጎበኟት ጥቂት በጎ ነገሮች የሚጠቀስ የመጀመርያው ነው፤›› ሲሉም አምባሳደሩ በተደጋጋሚ ትልቅ ውጤት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰላም ማስከበር ውጤታማ የሆነው በኢቢዬ የተሰማራው ጦር በብዛት የኢትዮጵያ ጦር ያለበት መሆኑን፣ የሰላም ማስከበር የውኃ ልክ መሆን የቻለ ተልዕኮ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

የቆይታው ፈተናዎች

የተባበሩት መንግሥታት የባለ ብዙ ወገን (Multi Lateral) ግንኙነት ትልቁ አካል ሲሆን፣ የጋራ ችግሮችን በጋራ የመፍታት መርህን ይዞ የሚሠራ ዓለም አቀፍ የትብብር መድረክ ነው፡፡ የጋራ ችግሮችን በግል አቅም፣ በግል ጥረት ከመፍታት ይልቅ፣ በጋራ መፍታት ዘላቂ መፍትሔ እንደሚያመጣም ታምኖበት የተደረገ ስብስብ ነው፡፡

ሆኖም ኢትዮጵያ በፀጥታ ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በነበረችባቸው ሁለት ዓመታት ይህ የባለ ብዙ ወገን ችግር አፈታት መርህ ተቀባይነቱ እየቀነሰ፣ አገሮች ባላቸው አቅምና ተስማሚነት ለጉዳዮች መፍትሔ ወደ መሻት ያዘነበሉበት ነበር፡፡ ይህ የኢትዮጵያ የሁለት ዓመታት ቆይታ ዋና ፈተና እንደነበርና ሌሎች ፈተናዎች ከዚህ የሚመነጩ እንደነበሩ አምባሳደር ታዬ ይናገራሉ፡፡

‹‹ዋናው ፈተና በባለ ብዙ ወገን ግንኙነት ላይ የነበረው ዕምነት መቀነስ ነው፡፡ በተናጠል የሚፈቱ ችግሮች ቢኖሩም ዘላቂነት አይኖራቸውም፡፡ ይህ በኢራን የኑክሌር ጦር መሣሪያ ስምምነት መፍረስ የታየ ነው፡፡ ይኼንን ማስታመም ፈተና ነበር፤›› ሲሉ ይህ ምን ያህል ቆይታቸውን ከባድ እንዳደረገባቸው አምባሳደር ታዬ ያወሳሉ፡፡

ይህ ፈተና እየጎላ መጥቶ ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ያልታየ የጂኦ ፖለቲካ ክርክር ሳይሆን በጭብጥ ጉዳዮች ላይ እንኳን ልዩነቶች እየታዩ መምጣታቸውን በመጥቀስ በአየር ንብረት፣ በሰላም ማስከበር አስፈላጊነት፣ በስደተኞች ጉዳይ፣ በኬሚካል ጦር መሣሪያዎች፣ ወዘተ. አከራክረው የማያውቁ ጉዳዮች አከራካሪ ሆነው መከሰታቸውን ይመለከታሉ፡፡ በተለይ ይህ ቋሚ በሆኑ አባላት መካከል ፈተና ስለነበር፣ ያለ ብዙ ትዕግሥት ውሳኔ ማግኘት እንደማይቻል መመልከታቸውን አስረድተዋል፡፡

ሌላው ፈተና ካሁን ቀደም አጀንዳ ተቀርፆ ይቀርብ የነበረ ቢሆንም፣ ድንገቴ አጀንዳዎች እየቀረቡ በልዩ ጉዳዮች ላይ መወያየት እየበዛ መምጣቱን በማስታወስ፣ ይህ አገሮችን አቋም ለመያዝ ከባድ እንደሚያደርግባቸው ያስረዳሉ፡፡ ይህ አሠራር በፀጥታ ምክር ቤት አጠራር ኤኦቢ (Under any other Business) እየተባለ እንደሚጠራና አስጨናቂ እንደነበረም ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የፀጥታ ምክር ቤቱ በሰላምና በደኅንነት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ቢያደርግም፣ ሁሉንም ጉዳዮች የምክር ቤቱ  አጀንዳዎች የማድረግ አዝማሚያ እየሰፋ መምጣቱንም አክለዋል፡፡

መጪው ጊዜ ምንን ይዟል?

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ለሦስተኛ ጊዜ ተለዋጭ አባል የሆነችበትን የሁለት ዓመታት ቆይታ ታኅሳስ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. አጠናቃለች፡፡ በዚህ መሀል የፀጥታው ምክር ቤት ፕሬዚዳንት በመሆን ለአንድ ወር ያገለገለችው ኢትዮጵያ፣ ካገኘቻቸው ስኬቶች ቀጣይነትና አፍሪካ እንደ አኅጉር እየጠየቀች ካለችው የሁለት አገሮች የፀጥታ ምክር ቤት ቋሚ አባልነትና የሁለት አገሮች ተለዋጭ አባልነት ላይ የሚኖራት ድርሻን በሚመለከት ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ አበበ፣ ኢትዮጵያ በአባልነት ስትመረጥ ዓለም የመተማመኛ ድምፅ (Vote of Confidence) እንዲሰጣት በማስመር ማስቀጠሉ ቀላል እንደማይሆን ይናገራሉ፡፡

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. እስከ 2011 በቀጣናው የነበረውን ሰላም የማስከበር ሚና በብቸኝነት እየተወጣች መቆየቷን ያስታወሱት አቶ አበበ፣ ሌሎች የዓለም አገሮች ከ2008 የኢኮኖሚ ቀውስ በኋላ ትኩረት መስጠታቸውንና የባህር ላይ ውንብድናን ከኢኮኖሚያቸው ችግር ጋር በማቆራኘት ለመዋጋት መውጣታቸውን አስታከው ሰላም ማስከበርን እንደያዙት ያስረዳሉ፡፡

‹‹ይኼንን ስኬት ማስቀጠሉ ላይ ነው ትልቁ ጥያቄ፡፡ ማስቀጠል እንችላለን ወይስ አንችልም? ማስቀጠል ካልቻልን የአንድ ወቅት የሁለት ዓመታት ቆይታ ታሪክ ሆኖ ነው የሚቀረው፤›› ይላሉ፡፡

‹‹ቀድሞ ከመመረጥ ጀምሮ የነበረው ስኬት የተመዘገበው በውስጥ በነበረን ሰላምና መረጋጋት ነው፡፡ አሁን ቀጣይነት ያለው ለውጥ ካላመጣን እየተፈጠሩ ያሉ ክፍተቶች የፀጥታ ምክር ቤት ቋሚ አባልነት ይቅርና እንደ አገር ለመቀጠልም የህልውና ጥያቄ የሚያስነሱ ናቸው፤›› ሥጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡

‹‹አሁን ባለው የዓለም አስተዳደር መልክና የቀጣናው የጂኦ ፖለቲካ ሁኔታ እንዳንወድቅ ሆነን ማስቀጠል እንችል ይሆን?›› ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡ ‹‹እንደ አገር የህልውና ጥያቄ ውስጥ እየገባን ነው፤›› በማለት፡፡

በስፋት የነበረው ጥያቄ ልማቱ ፍትሐዊ ሆኖ ይዳረሳል አይዳረስም? የዴሞክራሲ ምኅዳሩ ይስፋ ወይስ አይስፋ ሲሆን፣ አሁን ይህ ጥያቄ የአገር ህልውና ጉዳይ ሆኖ መምጣቱን አቶ አበበ ይናገራሉ፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ትልቅ አገር በመሆኗ የተፈናቀሉ ጎረቤቶችን በሙሉ እያስጠለለች ትገኛለች በማለት፣ ‹‹የእኛ ሰው ቢፈናቀል የት ነው የሚሄደው?›› ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡

ይሁንና አቶ ልዑልሰገድ አሁን በአገሪቱ እየታየ ያለው ዴሞክራሲን የማስፋት ሥራ ሰፊ ትኩረት ያገኘ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ይህም ዓለም አቀፍ ትኩረትን ያመጣ ክስተት ነውም ይላሉ፡፡

ነገር ግን እሳቸውም የአገሪቱ የውስጥ ችግር ውስብስብ እየሆነ መምጣቱን  ያምናሉ፡፡ ከውጫዊ ፍላጎት ጎን ለጎን የውስጥ ሁኔታን ማሻሻልና ማጠናከር ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

ለዓለም አቀፍ ተሰሚነት የውስጥ ጥንካሬ ወሳኝ መሆኑን አምባሳደር ታዬ ያምናሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ሦስት ዓመታት የነበረው አመፅና ብጥብጥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የነበራቸው ቆይታ ፈታኝ እንዳደረገው በማስረዳት፣ ‹‹ኢትጵያ ቀድሞ በነበረው በጎ ስም አስተዋፅኦ ነበር እንጂ ትርምስ በተፈጠረ ቁጥር እንደ ቁብ የሚቆጥር የለም፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹በቆይታችንም መናኛ አገር ሳንሆን አቋም ያለን መሆናችንን ያስመሰከርንበት ነው፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ቋሚ አባል ለመሆን ተፎካካሪ አገሮች ሊኖሩባት ስለሚችሉ ታሪኳን በማጉላት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባትም አቶ ልዑልሰገድ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካኒዚም አቀንቃኝ ብትሆንም ይኼንን በጉልህ ስታቀነቅነው አትታይ፤›› የሚሉት አቶ ልዑልሰገድ፣ የነበሩትን የመሪነት ሚናዎች ማስቀጠልም ያስፈልጋል ይላሉ፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -