የኦሮሚያ ክልል ኦነግ ክልሉን ከማመስ ድርጊቱ እንዲቆጠብ አሳስቧል
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ተከፈተብኝ ያለው ጦርነት እንዲቆም፣ የኦሮሞ ሕዝብና ሰላም ወዳዶች ሁሉ በመንግሥት ላይ ጫና እንዲያደርጉ ባወጣው መግለጫ ጠየቀ።
ኦነግ ሰኞ ታኅሳስ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው፣ “ኦነግ በመራው የኦሮሞ ሕዝብ የነፃነት ትግልና ሕዝባችን (በተለይም ቄሮ) በከፈለው ውድ መስዋዕትነት ኢሕአዴግ ተገዶ ለሰላም ጥሪ መልስ እንዲሰጥ በመደረጉ፣ ላለፉት ስምንት ወራት ለሁሉም የሚጠቅም የሰላም መስኮት ዕድል የተከፈተ ወይም የተፈጠረ መስሎ ነበር። ኦነግም መታደሱንና ለሰላም ዝግጁነቱን ከተናገረው የኢሕአዴግ መንግሥት ጋር በሰላም አብሮ ለመሥራት ከስምምነት ደርሷል፡፡ ሁሉንም ወገኖች በሰላማዊ መንገድ አብሮ ለመሥራት በሚያስችል ሥርዓት ውስጥ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማበርከት ወስኖ፣ በኢትዮጵያ መንግሥትና በኦነግ መካከል የነበረውን ጦርነት ለማቆም የጋራ ውሳኔ ላይ ደርሰዋል፤” ሲል ወደ አገር ቤት የገባበትን መንገድ ገልጿል።
ይሁን እንጂ እስካሁን ኢሕአዴግና የመንግሥት ሥርዓቱ ከፀረ ዴሞክራሲ አቋምና አካሄዱ ፈቀቅ ባለማለቱ፣ እውነተኛ መስዋዕትነት የከፈሉ ወገኖች ለውጡን ለማሳካትና ሥርዓቱንም ለማሻሻል ተሳታፊ ሊሆኑ አለመቻላቸውን አስታውቋል፡፡ በመሆኑም በሥርዓቱ የሚካሄዱ አፈናዎች፣ እስራት፣ ግድያና ሌሎችም የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዛሬም ድረስ እንደቀጠሉ ናቸው ሲል ይከሳል።
በማከልም በተደጋጋሚና በስፋት የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች አባላት ሳይቀሩ በኦነግና በኦሮሞ ነፃነት ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻና ፕሮፓጋንዳዎች እያካሄዱ ናቸው ብሏል፡፡ በኦነግና በመንግሥት መካከል የተደረሰው ስምምነት እንዳይተገበር ሆን ተብሎ የኦነግ ከፍተኛ አመራር አዲስ አበባ ከገባበት ዕለት ጀምሮ፣ በርካታ የተለያዩ ዓይነት እንቅፋቶችን በመፍጠር፣ እንዲሁም ኦነግ ጽሕፈት ቤቶቹን ከፍቶ በአግባቡ እንዳይንቀሳቀስና እንዳይሠራ ለማደናቀፍና ለመገደብ ደባዎች እየተፈጸሙ ነው ብሏል፡፡
ይህ ደግሞ ለአገሪቱ ሰላም በጎ አስተዋፅኦ የማይኖረው በመሆኑ በጊዜና በአግባቡ ለመፍታት፣ ብሎም ስምምነቱና ለውጡ መንገዱን እንዳይስት ማድረግ እንደሚገባ ያትታል።
በመሆኑም ሁሉም ሰላም ወዳድ ወገኖች በተለይ ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብ መንግሥት እያካሄደ ያለውን ጦርነት እንዲያቆም አስፈላጊ ጫና ማድረግ እንዳለበት፣ በኦነግና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል የተደረሰው ስምምነት በተለይ ደግሞ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትን በሚመለከት አሁን የተፈጠረውን አዲስ ሁኔታ ለማስታረቅና ለመፍታት በሚያስችል ሁኔታ፣ ሦስተኛ ወገን በሚገኝበት ስምምነቱ እንደ አዲስ ውይይት ሊደረግበት እንደሚገባ በመግለጽ ጥሪውን አቅርቧል።
ኦነግ ጥሪውን ያቀረበው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ኦነግ ክልሉንና የክልሉን ሕዝብ ሰላም ከማወክ እንዲታቀብ የሚያሳስብ መግለጫ ባወጣ ማግሥት ነው።
ክልሉ ባወጣው መግለጫ ኦነግ ከመንግሥት ጋር የደረሰውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ አለመተግበሩን በመጥቀስ፣ የኦሮሞን ሕዝብ ሊሰብሩ የሚፈልጉ ኃይሎች ፍላጎትን ተሸክሞ ለማሳካት በሚያደርገው እንቅስቃሴ የኦሮሚያ ክልል ሰላም እየደፈረሰ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
የኦሮሞ ሕዝብ ለውጡን ለማስቀጠል በጋራ እየተንቀሳቀሰ ባለበት በአሁኑ ወቅት ሰላማዊ ሕዝብ ውስጥ በመንቀሳቀስ አደጋ ማድረስ፣ ለሕዝቡ የቆመን የፀጥታ ኃይል መግደል፣ የጦር መሣሪያ በመዝረፍ ሁከት መፍጠር እንዲሁም ጉዳቱን እያወቁ፣ እያዩና እየሰሙ ኦሮሚያን የጦርነት አውድማ ለማድረግ አቅደው እንደሚሠሩ ኃይሎች “ኦሮሞ አገር መምራት አይችልም፣ የሽግግር መንግሥት ነው የሚያስፈልገው፤” በማለት ጭምር እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አስረድቷል።
ለአንድነትና ለሰላም ያለው አማራጭ ሕግን ማክበርና ማስከበር መሆኑን፣ ለዚህ ደግሞ መንግሥት ግዳጅ ስላለበት የሕግ የበላይነት ተከብሮ ሰላም እንዲሰፍን እየሠራ መሆኑንም ገልጿል።
ለዚህም ሕዝቡ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያደርግ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጥሪውን እንደሚያስተላልፍ አስታውቋል፡፡