Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹በውትድርና ዘመኔ በራስ ሕዝብ ላይ ጭካኔ የተሞላበት ዘግናኝ ጥቃት ተፈጽሞ ያየሁት በምዕራብ...

‹‹በውትድርና ዘመኔ በራስ ሕዝብ ላይ ጭካኔ የተሞላበት ዘግናኝ ጥቃት ተፈጽሞ ያየሁት በምዕራብ ወለጋ ነው››

ቀን:

የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ

በኤርትራ ድንበር የሠፈረውን ሠራዊት የማንቀሳቀስ ተግባር እንዲቆይ ተወስኗል ብለዋል

የመከላከያ ሠራዊቱን የውጭ ኃይሎች አሳንሰው እንዲገምቱት የሚያደርግ ማንቋሸሽ እንዲቆም አሳስበዋል

በአሁኑ ወቅት በምዕራብ ወለጋ የተፈጠረውን ፖለታካዊ መነሻ ያለው የፀጥታ ችግር በተመለከተ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስተያየታቸውን የሰጡት የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ፣ ‹‹በውትድርና ዘመኔ አይቼው የማለውቀው ጭካኔ፤›› ሲሉ ለፓርላማው ገለጹ።

የመከላከያ ሚኒስቴርን የ2011 ግማሽ ዓመት የሥራ ክንውን ሪፖርት ለማቅረብ ከመከላከያ ሚኒስትሯ አይሻ መሐመድ (ኢንጂነር) ጋር በመሆን ሰኞ ታኅሳስ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በምክር ቤቱ የተገኙት ጄኔራል ብርሃኑ፣ የታጠቁ ኃይሎችን ትጥቅ በማስፈታት ረገድ መከላከያ ሠራዊቱ ምን እያደረገ እንደሆነ ማብራራያ እንዲሰጡ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ነው በምዕራብ ወለጋ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት እንደተፈጸመ የተናገሩት።

ለአንድ ሕዝብ ነፃነት የሚታገል ኃይል በሚታገልለት ሕዝብ ላይ ጭካኔ የተሞላበት ዘግናኝ በደል እንዴት ሊፈጽም ይችላል? በማለት ጥያቄ በማንሳት፣ ‹‹ለረጅም ዓመታት በውትድርና አገልግያለሁ፣ እንዲህ ዓይነት ጭካኔ በወለጋ ከተፈጸመው በስተቀር አይቼ አላውቅም፤›› ብለዋል።

‹‹በምዕራብ ወለጋ የተፈጸመውን ጭካኔ በቅርቡ በቪዲዮ ምሥል ጭምር ታዩታላችሁ፤›› ሲሉም ተናግረዋል።

ባል ታስሮ ሚስት የምትደፈርበት፣ ሕዝብ ተጨንቆ በጉድጓድ የተደበቀበት፣ በርካታ ሰዎች ታግተው የተገኙበት፣ የመንግሥት ተሽከርካሪና የጦር መሣሪያ በሙሉ የተዘረፈበት እንደነበር ገልጸዋል።

‹‹የመከላከያ ሠራዊቱ ወደ ወለጋ ሲገባ ያገኘነው ጉድ ዘግናኝ ነው፤›› ሲሉ ያጋጠመውን ሁኔታ ተናግረዋል።

በወለጋ የተከሰተውን የማስተካከል ሥራ የክልሉ ፀጥታ ኃይል እንጂ የመከላከያ ሠራዊቱ መሆን እንዳልነበረበት፣ ነገር ግን ችግሩን የፈጠሩት በአካባቢው የተሰማሩ ታጣቂዎች በሰላማዊ መንገድ ሊታገሉ የመጡ ናቸው እንዳትነኳቸው በመባሉ የክልሉ የፀጥታ ኃይል ሽባ ሆኖ መገኘቱንም ተናግረዋል። ጄኔራል ብርሃኑ የክልሉ የፀጥታ ኃይል ኃላፊነቱን በወቅቱ እንዳይወጣ ‹‹እንዳትነኳቸው›› የሚለውን ትዕዛዝ ማን እንዳስተላለፈ አልገለጹም።

የመከላከያ ሠራዊቱ ከተሰማራ በኋላ ችግሩ እየተፈታ እንደሆነ የአካባቢው ነዋሪዎችም ከተደበቁበት እየወጡ ሠራዊቱን ‹‹አድኑን›› በማለት መናገር መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ከባኮ አካበቢ አንስቶ መንቀሳቀስ የማይቻል እንደነበር ነገር ግን ሠራዊቱ ከገባ በኋላ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ መጀመሩን፣ ሸሽተው ወደ አዲስ አበባ የገቡ ባለሀብቶችም ወደ አካባቢው በመመለስ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

ከወለጋ በተጨማሪ የመከላከያ ሠራዊቱ በበርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች በፀጥታ ሥራ ላይ ተጠምዶ የቆየባቸው የተለያዩ ጊዜያት እንደነበርም አውስተዋል።

በተለይ በጅግጅጋ ተፈጥሮ የነበረው አገር የማፍረስ አዝማሚያ እንደነበረው፣ ነገር ግን ሠራዊቱ በጥንቃቄና ያላንዳች ኪሳራ የነበረውን ሁኔታ መቀልበስ እንደቻለ ተናግረዋል።

በሐዋሳ በሁለት ብሔሮች መካከል የተፈጠረውን ግጭት የመከላከያ ሠራዊቱ ባይገባ ኖሮ ማንም ሊፈታው የማይችልበት ደረጃ ላይ ይደርስ እንደነበር፣ እንዲሁም በቅርቡ በሞያሌ የተከሰተውን ግጭት ከክልሉ መንግሥት ጋር በመሆን በአጭር ጊዜ በጥንቃቄ መፍታት መቻሉን አስታውቀዋል።

የመከላከያ ሠራዊቱ ሞያሌ በመግባት የትጥቅ እንቅስቃሴውን መቀልበስ ይቻል እንጂ፣ ፖለቲካዊ ውሳኔ የሚጠይቅ በመሆኑ የሚመለከተው የፖለቲካ አመራር ሊሠራበት እንደሚገባ አስረድተዋል።

የኤርትራ ድንበር ላይ ሰፍሮ የነበረው የመከላከያ ሠራዊት በሁለቱ አገሮች መካከል ሰላም መውረዱን ተከትሎ ሰሞኑን ከአካባቢው እንዲንቀሳቀስ ሲደረግ በአካባቢው ሕዝብ መታገቱን፣ ሠራዊቱ በማንኛውም ጊዜ በየትኛውም ቦታ የመንቀሳቀስ መብት እያለው የተፈጸመውን ተግባር በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡ ከምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ ተነስቶ ነበር።

 ለጥያቄው ማብራሪያ የሰጡት ጄኔራል ብርሃኑ ከኤርትራ ድንበር በመንቀሳቀስ ላይ የነበረው የመከላከያ ሠራዊት ዕገታ ተፈጽሞበታል በሚል የቀረበው ጥያቄ አገላለጹ ተገቢ ባለመሆኑ ማስተካከያ ሊደረግበት እንደሚገባ በመጠቆም፣ ‹‹ማንም እሳት የሚተፋ የመከላከያ ሠራዊትን ሊያግት አይችልም፣ እንቅስቃሴውን የማቆየት የሕዝብ ጥያቄ ነው የቀረበው፤›› ሲሉ መልሰዋል።

 ከክልሉ መንግሥት ውጪ የሆኑ ሥጋት እየፈጠሩ መኖር የለመዱ ‹‹ነጋዴዎች›› ሕዝቡ ላይ የወረራ ሥጋት በመጫር የተፈጠረ አጋጣሚ እንደነበር ገልጸዋል።

ከውጭ ሊመጣ የሚችል የወረራም ሆነ ማንኛውንም ሥጋት ወይም እንቅስቃሴ የሚተነትነውና የመቀልበስ ኃላፊነትም የተጣለበት የመከላከያ ሚኒስቴር መሆኑን የገለጹት ጄኔራል ብርሃኑ፣ ‹‹የወረራ ሥጋት አለመኖሩን በምክር ቤቱ ፊት አረጋግጣለሁ፤›› ብለዋል።

ሕዝቡ ወጥቶ እየጠየቀ ሠራዊቱ ጥሎት ሊሄድ ስለማይችል፣ ሠራዊቱን የማንቀሳቀስ ዕቅድ እንዲከለስና ሠራዊቱ ባለበት እንዲቆይ መደረጉን አስረድተዋል።

ሠራዊቱ እንዳይንቀሳቀስ ወጣቶችና ሕፃናት ወደ መንገድ እንዲወጡ የተደረገው ከክልሉ መንግሥት ዕውቅና ውጪ መሆኑን ከክልሉ መንግሥት ጋር በመነጋገር እንደተገነዘቡ ያስረዱት ጄኔራሉ፣ ጊዜ ይወስድ ይሆናል እንጂ ይኼንን ሴራ የትግራይ ሕዝብ መገንዘቡ አይቀርም ብለዋል። በመከላከያ ሠራዊቱና በሠራዊቱ አመራሮች ላይ ሰፊ የሆነ ስም የማጥፋትና ሠራዊቱ አገርን መከላከል የማይችል የሚሊሻ አቅም እንኳን እንደሌለው በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ የተከፈተው ዘመቻ፣ በፍጥነት ሊቆም እንደሚገባ አሳስበዋል።

ይህ ድርጊት የውጭ ጠላቶች ሠራዊቱን አሳንሰው እንዲገምቱ የሚያደርግ በኢትዮጵያዊ ሊነገር የማይገባ እንደሆነ፣ ዓላማው ግን አገር የማፍረስ ዕቅድ ያነገቡ ጥቂቶችን በዚህ መንገድ የማገዝ ድርጊት ሊሆን ስለሚችል ምክር ቤቱ እንዲገነዘበው ጠይቀዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ