Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየልደቱ በዓልና የተንፀባረቀው አገራዊ መልዕክት

የልደቱ በዓልና የተንፀባረቀው አገራዊ መልዕክት

ቀን:

ምዕራባዊውን የጎርጎርዮሳዊ ቀመር በሚከተሉት አገሮች የሚገኙ ክርስቲያኖች ገናን ካከበሩ ከአሥራ ሦስት ቀናት በኋላ ነበር ምሥራቃዊውን የዩልዮስ ቀመር የሚከተሉት አገሮች ክርስቲያኖች የእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ከትናንትና በስቲያ ያከበሩት፡፡

ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ግብፅ ታኅሣሥ 29 (ኪያክ 29) ባሉት የራሳቸው አቆጣጠር መሠረት በዓለ ልደቱን ሲያከብሩት፤ ሩሲያ፣ ዩክሬን፣ ጆርጂያ፣ መቄዶንያ፣ አዘርባጃን፣ ሰርቢያ፣ እስራኤል፣ ቤላሩስ፣ ቱርክ፣ ሞንቴኔግሮ፣ ካዛክስታን፣ ሞልዶቫ፣ ወዘተ ‹‹ዲሴምበር 25›› ባሉት ቀን (በጎርጎርዮሳዊ ቀመር ጃንዋሪ 7) በተመሳሳይ በዓሉን አክብረዋል፡፡

የኦርቶዶክስ አገሮች የሚባሉት እነ ሩሲያ (ከዓለም ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች 39 በመቶ በሩሲያ ይገኛሉ)፣ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮችና መካከለኛ ምሥራቅ ቤተ ክርስቲያኖች የሚከተሉት የጁሊያን ካላንደር (ከግሪጎሪያን ካላንደር በፊት የነበረ መደበኛ ቀመር) በመሆኑ ነው ከምዕራቡ የክብረ በዓል ቀን የተለዩት፡፡

ጥቂት የኦርቶዶክስ አገሮች ግሪክን ጨምሮ፣ ቆጵሮስና ሮማንያ የጁሊያን ካላንደር እ.ኤ.አ. በ1923 ከልሰው ልደትን በምዕራቡ ቀመር ዲሴምበር 25 ላይ ነው ያከበሩት፡፡

የኢትዮጵያ እህት ቤተ ክርስቲያኗ ኮፕቲክ በአዲሱ የግብፅ የአስተዳደር ዋና ከተማ ከካይሮ 45 ኪሎ ሜትር ርቀት ያስገነባችውና በመካከለኛው ምሥራቅ ግዙፍ የተባለው የልደተ ክርስቶስ ካቴድራል በመረቀችበት በዓሉን ኪያክ 29 ቀን 1735 ዓመተ ሰማዕታት ስታከብር፣ በእኩለ ሌሊቱ ሥርዓተ ቅዳሴ ፕሬዚዳንት አብድልፈታህ አልሲሲ ተገኝተዋል፡፡ በአዲሱ ካቴድራል ምረቃ ላይም ዲስኩር አሰምተዋል፡፡

በሩሲያም እንደ ሁሌው ፕሬዚዳንቷ ቭላድሚር ፑቲን በቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ በሚገኘው የመድኃኔ ዓለም ብርሃነ መለኮት ካቴድራል ተገኝተው በእኩለ ሌሊት በመገኘት አስቀድሰዋል፡፡ በትውፊት ሲተላለፍ እንደኖረው ከቤተ ክርስቲያኒቱ አቅራቢያ ለልደቱ ክብርም መድፉንም ተኩሰዋል፡፡

ሰኞ ታኅሣሥ 29 በዓለ ልደቱ በተከበረባት ኢትዮጵያም ለየት ያለ ሥርዓት የተፈጸመባት የላሊበላ ከተማ ናት፡፡ በሁሉም የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ሌሊቱን ማኅሌት ተቆሞ ቅዳሴ እንዳበቃ የበዓል ፍጻሜ ቢሆንም፣ በላሊበላ ግን ከዚህ በተጨማሪ ታኅሣሥ 29 ቀን ማለዳ ላይ ‹‹ቤዛ ኩሉ›› የተሰኘው ክብረ በዓል ተፈጽሟል፡፡ 

ከአሥራ አንዱ ውቅር አብያተ መቅደሳት አንዱ በሆነው በቤተ ማርያም ዙሪያ የቤዛ ኩሉ (የዓለም መድኅን) ዝማሬ ካህናቱ ከጋራ ዲያቆናቱና ምዕመናኑ ከሥር ሆነው በመዘመርና በማሸብሸብ ሴቱ በዕልልታ፣ ወንዱ በጭብጨባና በሆታ አክብረውታል፡፡

በላሊበላ ያለው የገና በዓል አከባበር የካህናቱ ረባዳ መሬትና ጋራ ላይ መሆን ትርጉም አለው፡፡ መሬት ላይ ያሉት የእረኞችና ማሜ ጋራ ላይ ያሉት ደግሞ የመላዕክት ምሳሌዎች መሆናቸውን ያሳያል፡፡

በቤዛ ኩሉ ዝማሬ ትርዒት ላይ የሚሳተፉት ካህናት የሚለብሷቸው አልባሳትና የሚይዟቸው ንዋያተ ቅድሳት ከወትሮው ለየት ያሉ ናቸው፡፡

መምህር ዓለሙ ኃይሌ ስለዚሁ ሲያብራሩ እንዲህ ይላሉ፣ ‹‹የወርቅ፣ የብር፣ የሐር፣ ወዘተ ንዋያተ ቅድሳት የያዙና ልብስ ተክህኖ የለበሱ ካህናት ከማሜ ጋራው ላይ ተሠልፈው ይቆማሉ፡፡ በውስጥ ጥንግ ድርብ የታጠቁ፣ ከላይ ካባ የደረቡ፣ አለቃ ወዳሾች፣ ርዕሰ ደብሮች፣ ቀኝና ግራ ጌቶች፣ ከውስጥ የሐር ቀሚስ ያጠለቁ፣ ከላይ ቀይ ጃኖ (ሻማ) ያሸረጡ ልጅ እግር ደብተሮች መደዳውን ይደረደራሉ፡፡ በግራ እጅ የብር መቋሚያ በተጌጠ መሐረብ ተይዞ ትከሻ ላይ ያርፋል፡፡ በቀኝ እጅ የብር ፀናፅል ይያዝና በሠልፍ ይቆማል፡፡ ሌሎች መዝሙሮችና ደብተሮች ደግሞ በዚሁ ዓይነት ከታች ከማሜ ጋራው ሥር ክብ ሠርተው ይቆማሉ፡፡ ከዚያ እየተቀባበሉ ‹‹ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ›› (ዛሬ የዓለም መድኅን ተወለደ) እያሉ ያዜማሉ፡፡ ይህ የማይለወጥ ሁሌም ያለ ሥርዓት ነው፡፡

የልደቱ በዓልና የተንፀባረቀው አገራዊ መልዕክት

 

ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ገናን በዓል በላሊበላ ለማክበር የሚጓዙት ምዕመናንና ከዓለም ዙሪያ የሚመጡት ዑደተኞች (ቱሪስቶች) ብዛት ከፍ ያለ ነው፡፡

በላሊበላ በገና ዕለት ከተሰሙት የታቦት ዜማዎች የሙገሳ ቃል ግጥሞች ይገኙበታል፡፡

‹‹ማር ይዘንባል ማር

ከእመቤቴ በር

ማር ይዘንባል ማር፤

አልጋ ባልጋ ነው መንገዱ

ቅዱስ ላሊበላ ወዳንተ ሲሄዱ

ቀና ነው አሉ መንገዱ፤

ታየኝ ክብርሽ

እመቤቴ ያሉሽ››

እያሉ ነጋሪት (ከበሮ) እየመቱ ምሥጋና በዜማ በልደት ቀን እያቀረቡ እያጨበጨቡ እልል እያሉ ይጨፍራሉ፡፡ ሁሌ እንደሚዘመረው ምዕመኑ ኪነ ሕንፃውን እያወደሱ የዘመሩት ቃል ግጥምም አላቸው፡፡

‹‹ቅዱስ ላሊበላ የላስታው ደብር

ውስጡ አረንጓዴ ነው ባህር

ቅዱስ ላሊበላ የመጥረቢያው እንኳ እጄታ የለው

ከቶ እንዴት አድርጎ ሠራው?

ከቶ እንዴት አድርጎ አነፀው?››

የመሪዎች መልዕክት

የእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አስመልክቶ በዋዜማው የክርስትና ሃይማኖት መሪዎችና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ለሕዝበ ክርስቲያኑና ለኅብረተሰቡ ከበዓሉ አከባበር ባሻገር ከአገሪቱ ሰላም አኳያ መልዕክታቸውን  አስተላልፈዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ወፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በመልዕክታቸው ለመንግሥት ማሳሰብያን፣ ለሕዝቡ ደግሞ ምክርን ለግሰዋል፡፡ እንዲህም አሉ፡- ‹‹መንግሥት ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች በማሳተፍና በማወያየት፣ የአገሪቱን ሰላምና አንድነትን እንዲያረጋግጥ፣ የዜጎችን ደኅንነትና ሰላም በመጠበቅ የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብር እናሳስባለን፡፡

‹‹ሕዝቡ በአጠቃላይ በተለይም ወጣቱ ትውልድ፣ ተረጋግቶና ሰከን ብሎ በማሰብ ለአገር አንድነት፣ ለሰላም መጠበቅና ለሰው ልጆች መብት መከበር በአንድነት እንዲተጋ በአጽንዖት እንመክራለን፡፡››

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስም በበኩላቸው እንዲህ ብለዋል፣ ‹‹ሰላም ለመንፈሳዊና ሥጋዊ እንቅስቃሴ ዋነኛ ዋስትና ነው፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ ከምንም በላይ ሰላም እንዲሰፍን መሥራት ይገባዋል፡፡ በተጨማሪም ዘረኝነትን በመፀየፍ ያለ ምንም መለያየት በአገራችሁ መኖር አለባችሁ፡፡ ቤተሰቦችም ልጆቻቸውን ከዘረኝነት የፀዱና በአንድነት የሚያምኑ በማድረግ ማሳደግ ይገባቸዋል።››

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ፕሬዚዳንት ቄስ ዮናስ ይገዙም በመልዕክታቸው እንዲህ አስገንዝበዋል፣ ‹‹የክርስቶስን የልደት በዓል ስናከብር አብሮነቱን፣ ፍቅሩንና ይቅርታውን እያሰብን መሆን ይገባል። ዴሞክራሲ፣ ልማትና ብልፅግና እንዲመጣም ሁሉም ይህን ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡››

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት ማሰሪያ ላይ የሚከተለው ይገኝበታል፡- ‹‹ፈጣሪ አገራችንን የምናሳድግበትንና ራሳችንም ለታላቅነት የምናበቃበትን ዕድል ሰጥቶናል፡፡ እንደ ቤተልሔም ሰዎች ስንዘናጋ፣ እንደ ሄሮድስ ሾተል ስንሞርድ፣ እንደ ሊቃውንተ አይሁድ በትንሽ በትልቁ ስንጨቃጨቅ፣ እንደ ዘመኑ ሰዎች ስንከፋፈል፣ እንደ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ሥልጣንና ጥቅም ቀረብን ብለን በኩርፊያ ስናምፅ፣ ዕድሉ እንዳያልፈን፡፡

‹‹እንደ እረኞችና እንደ ሰብዓ ሰገል አውቀን እንጠቀምበት፡፡ የሚጠበቅብንን አድርገን የሚገባንን እናግኝ፡፡ ታሪክ ማለፉ ላይቀር ወቀሳና ከሰሳን ለትውልድ አናስተላልፍ፤ እኛ በሌሎች እንደተማርነው ሁሉ፣ ሌሎችም ነገ በእኛ መማራቸው አይቀርምና፡፡››

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...