Friday, September 22, 2023

የመከላከያ ሠራዊቱ የሪፎርም ሥራዎች ክንውንና ውስጣዊ የፀጥታ ችግሮችን የመፍታት ተልዕኮ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የመከላከያ ሚኒስቴር በተቋሙና በሠራዊቱ ላይ ሁለንተናዊ የሪፎርም ሥራ እያከናወነ መሆኑን፣ ይኼንንም አስመልክቶ ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑ ተግባራትን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ታኅሳስ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ሪፖርት አቅርቧል።

ሪፖርቱን በዋናነት ያቀረቡት የመከላከያ ሚኒስትሯ አይሻ መሐመድ (ኢንጂነር) እና ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ሲሆኑ፣ ሌሎች የሚኒስቴሩ አመራሮችም ማብራሪያዎች ሰጥተዋል።

ተቋማዊ አደረጃጀት

የተቋሙን ተልዕኮ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመወጣት የሚያስችል ተቋማዊ ሪፎርም በማዘጋጀት ወደ ሥራ ለማስገባት ከተከናወኑ ሥራዎች መካከል ትልቅ ትኩረት በመስጠት ከተከናወኑ ተግባራት አንዱ፣ የሠራዊቱን ማቋቋሚያ አዋጅ የማሻሻል ሥራ መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡ በሥራ ላይ የነበረውን አዋጅ በመፈተሽ ከተቋሙ የሪፎርም ሥራ ጋር ተያይዞ ሠራዊቱ አሁንና ወደፊት ሊወጣው ከሚችለው ተልዕኮና ግዳጅ አንፃር በመቃኘት፣ ከ20 በላይ የሚሆኑ አንቀጾች እንዲሻሻሉና አዳዲስ ሐሳቦች እንዲካተቱ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

በዚህ መሠረት ሠራዊቱ እስካሁን ከነበረው የምድርና የአየር ኃይል አደረጃጀት በተጨማሪ ሌሎች ኃይሎችን ይዞ እንዲደራጅ የማድረግና ተጨማሪ ዝርዝር የማሻሻያ መነሻዎችን በማካተት፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንዲፀድቅ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡

የተሻሻለው አዋጅ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት መሆኑን፣ በሠራዊቱ ኑሮና የሰው ኃይልን በማብቃት ረገድም ጉልህ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይታመናል ሲሉ በሪፖርታቸው አመልክተዋል፡፡ ተግባራዊ እየተደረገ ላለው ተቋማዊ አደረጃጀት ማሻሻያ አገራዊና ተቋማዊ የደኅንነት ሥጋት ትንተና፣ በተለያዩ ወቅቶች የመከላከያ አደረጃጀቶችን በማየት በመገምገምና ጠንካራ ደካማ ጎኖቻቸውን ለይቶ ተሞክሮ መውሰድ፣ እንዲሁም የሌሎች አገሮች ወታደራዊ አረጃጀቶች ጥናታዊ ግምገማ እንደ ግብዓት መወሰዱን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት ለአደረጃጀት ማሻሻያው መርሆዎችና አቅጣጫዎች ተቀምጠውለት የተቋሙን ቀጣይና የወደፊት ተልዕኮ መሠረት ያደረገ ሆኖ፣ በየደረጃው እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በማዕከል የሚገኙ ክፍሎች ማለትም የዋና መምርያዎች፣ የዋና ዳይሬክቶሬቶችና የማዕከሎች፣ እንዲሁም የዕዝ አደረጃጀቶች ፀድቀው በሥራ ላይ እንዲውሉ የተደረገ መሆኑን፣ ሌሎች ቀሪ በተዋረድ ያሉ አደረጃጀቶችም ከክፍሎች ጋር በመነጋገር በተጠናከረ መንገድ እየተሠሩ እንደሚገኙና በአሁኑ ወቅትም ተቋማዊ የማሻሻያ ሥራው በማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ እንደሆነ ሪፖርት አድርገዋል፡፡

በተጨማሪም ተቋሙ አሁን ያለውንና በቀጣይ ሊኖረው የሚችለውን ተልዕኮ መሠረት ያደረገ የዕዝ ስታፍ፣ የእግረኛና የሜካናይዝድ ክፍለ ጦሮች፣ የብርጌድና የሻለቃ አደረጃጀትና የሰው ኃይል ስታንዳርድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በሪፎርሙ መሠረት እንደ አዲስ ከሚደራጁት ኃይሎች መካከል የልዩ ዘመቻዎች ኃይል አደረጃጀት በመከላከያ አዛዦች መማክርት ደረጃ ውይይት ተደርጎበትና አስፈላጊው ግብዓት ተካቶበት መፅደቁን፣ የባህር ኃይል አደረጃጀት እንደ አዲስ የሚደራጅ በመሆኑ ከመንግሥት በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት የባህር ኃይሉን ለማደራጀት የሚያስችሉ የተለያዩ አገሮች ተሞክሮዎች፣ እንዲሁም የቀድሞ የባህር ኃይል አባላትን አቅም በመጠቀም የዝግጀት ሥራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የባህር ኃይል ለማደራጀት የተለያዩ አገሮች ተሞክሮን ለመውሰድ የሚያሽችሉ ጉብኝታዊ ግምገማዎች በመካሄድ ላይ እንደሚገኙ የጠቀሱት ሚኒስትሯ፣ እስካሁንም ወደ ፈረንሣይና ኬንያ በማቅናት የሁለቱን አገሮች ባህር ኃይሎች በመጎብኝት ተሞክሮ እንደተወሰደ ገልጸዋል።

የብሔር ተዋፅኦ በሠራዊቱ

ከላይ የተገለጹት የአደረጀጀት ሥራዎች ከተሠሩ በኋላ ብቃትንና ብሔራዊ ተዋፅኦን ግምት በማስገባት በወጣው መሥፈርት መሠረት፣ በየደረጃው የአመራሮች ምደባ በማከናወን ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን ሚኒስትሯ አይሻ መሐመድ ተናግረዋል፡፡

ብሔራዊ ተዋፅኦን የማመጣጠን ተግባርን በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ፣ ባለፉት ዓመታት የሠራዊቱን ብሔራዊ ተዋፅኦን የማመጠን ሥራ ችግር እንደነበረበት ተናግረዋል።

የሠራዊቱን የብሔር ተዋፅኦ ለማመጣጠን ይሞከር እንደነበር፣ ነገር ግን ከልብ ታምኖበት ባለመሠራቱ ችግር ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል። የሠራዊቱ የታችኛው ክፍል ላይ የብሔር ተዋፅኦ ጉዳይ ችግር እንዳልነበረ ያወሱት ጄኔራል ብርሃኑ፣ መሠረታዊ ችግር የነበረው የሠራዊቱ ከፍተኛ አመራር ላይ የነበረው የብሔር ተዋፅኦ ምጥጥን እንደነበር ገልጸዋል።

ከሠራዊቱ መሰናበት የነበረባቸው ከፍተኛ አመራር መኮንኖች ጦርነት ስለነበረ ወይም ጦርነት ሊከሰት ይችላል በሚል ግምት የጡረታ ጊዜያቸውን ጨርሰው እንዲቆዩ በመደረጉ፣ ከታች ወደ አመራርነት ማደግ የነበረባቸው የሠራዊቱ አባላት ማደግ ሳይችሉ መቆየታቸውን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት በሠራዊቱ የመዋጋት አቅም ላይ ጉዳት በማያስከትል ሁኔታ የአመራሩን ብሔራዊ ስብጥር ከምንጊዜውም በተሻለ ሁኔታ ለማመጣጠን እንደተሞከረ፣ ነገር ግን ምጥጡኑን በስድስት ወራት ወስጥ መቶ በመቶ ለማሳካት እንደማይቻል ገልጸዋል።

ሚኒስትሯ በበኩላቸው ሙያዊ ሥነ ምግባርና ሞራልን በመጠበቅ፣ በአሠራርና በመመርያ ብቻ ሥራን በማከናወን ተጠያቂነትን ማስፈን፣ ግልጽ፣ አሳታፊና የኃላፊነት መንፈስ ለመውሰድ የሚያስችል ከሐምሌ 2010 ዓ.ም. የማዕረግ መቆያ ጊዜያቸውን የሸፈኑና የማዕረግ መመልመያ መሥፈርቱን ያሟሉትን በመለየት፣ መንግሥት የፈቀደላቸው ቀጣዩን የማዕረግ ዕድገት እንዲለብሱ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

በማያያዝም ከሰባት እስከ አሥር ዓመታት አገልግሎታቸውን የጨረሱ፣ ለማዕረግ ምልመላ የሚሰጠውን የሳይኮሜትሪክ መመዘኛ ፈተና ማለፍ ያልቻሉ፣ በትምህርት ደረጃቸው ምክንያት ማደግ የማይችሉ፣ ሁለት ጊዜ ከማዕረግ ዕድገት የታገዱና በተለያዩ ምክንያቶች በአጠቃላይ 7,017 የሠራዊቱ አባላት ባለፉት ስድስት ወራት እንዲሰናበቱ መደረጉን ገልጸዋል።

ወታደራዊ ዝግጁነትን ማረጋገጥ

የጦርነት አደጋን ለመግታት ወይም የሚያጋጥም አደጋን በአጭር ጊዜና በአነስተኛ ኪሳራ ለመጨረስ የሚያስችል ዝግጁነት ማረጋገጥን በተመለከተ፣ የአገሪቱን የአየር ክልል በአስተማማኝ ለመጠበቅና ተገቢውን የአየር ድጋፍ ለመስጠት የተዋጊና የትራንስፖርት አውሮፕላኖችንና ሔሊኮፕተሮች ፍተሻ፣ እንክብካቤና ጥገና፣ እንዲሁም የአየር መከላከል አቅም ዝግጁነት የማረጋገጥ ሥራዎች እንደተሠሩ ሚኒስትሯ በሪፖርታቸው አመልክተዋል፡፡

በአውሮፕላኖችና በሔሊኮፕተሮች፣ እንዲሁም በአየር መከላከያ ትጥቆች ላይ የመከላከያ ጥገናና ዕድሳት በማድረግ ወደ ኃይል የመመለስ ሥራም መከናወኑን፣ የአብራሪዎችን የውጊያ አቅም ለማሳደግ የሚያስችሉ በተዋጊና በትራንስፖርት አውሮፕላኖችና ሔሊኮፕተሮች የበረራ ልምምዶች መደረጋቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ሠራዊቱ የታጠቃቸውን የሜካናይዝድ መሣሪያዎች በአግባቡ በመያዝና በመንከባብ መሣሪያዎቹ የአገልግሎት ብቃታቸውን ጠብቀው እንዲቆዩ ለማስቻል፣ የተለያዩ ብልሽት የነበረባቸው ከቀላል እስከ ከባድ የጦር መሣሪያዎችና ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች ተጠግነው ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

በትጥቅነት የተያዙና በክምችት የሚገኙ የአየርና የስፔስ (ህዋ) ክልከላዎችን ለማድረግ የማዕከል ምደባና የግንባር ቀደም ማዘዣ ጣቢያዎች በዳታ ሊንክና በዩኤቪ በማስተሳሰር፣ ሚስጥራዊነቱን የጠበቀ ፈጣን የመረጃ ልውውጥ እንዲኖራቸው መደረጉንም አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጋር በመቀናጀትም በኢትዮጵያ የአየር ክልል የሚደረጉ የአየር ትራፊክ እንቅስቃሴዎችን መቆጣጠር መቻሉንና በቀጣይም በመረጃ ልውውጥ ያሉትን ከፍተቶች ለመቅረፍ በጋራ እየተሠራ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡

የቅኝት ራዳሮችንና የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን በመጠቀም በአየር ክልል የተደረጉ በረራዎችን በተመለከተ ክትትል መደረጉን፣ የአገሪቱን የአየር ክልል ለመቆጣጠር የአየር መከላከያ አቅሞች ከአየር መቃወሚያ መሣሪያዎች ጋር በማስተሳሰር የራዳር ሽፋኑን ማስፋት እንደተቻለ ሚኒስትሯ ለምክር ቤቱ ገልጸዋል፡፡ የአየር መከላከያ ምድብተኞችን ሙያዊ አቅም ለማሳደግም ለአዳዲስ ምድብተኞች በራዳሮች የደረጃ ሁለት ሥልጠና፣ እንዲሁም የኢግላና የስትሬላ ሙያተኞች ከረዳት ወደ ዋና ተኳሽነት ለማሳደግ የሚያስችል ሥልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በሶማሊያ መሽጎ የሚገኘው የአሸባሪው አልሸባብ ቡድን በአገሪቱ ተሰማርቶ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ አደጋ ለማድረስ በዝግጅት ላይ እያለ፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በአጭር ጊዜ ዝግጅት ወደ ደሎ በመንቀሳቀስ በሥፍራው ከሚገኝ ምድር ኃይል ጋር በመረጃ በመቀናጀት በወሰደው ዕርምጃ በጠላት ሰው ኃይልና የጦር ቁሳቁሶች ላይ ከባድ ኪሳራ ማድረስ መቻሉንም አውስተዋል፡፡ ይህ ዘመቻም አየር ኃይሉ በአስቸጋሪ የመሬት ገጽታ በተለይም ጥቅጥቅ ባለ ጫካ ከባቢ ውስጥ የመሸገ ጠላትን በመለየት፣ ዒላማ ውስጥ እንዴት ማስገባት እንደሚቻልና አቧራማ በሆነ አካባቢ እንዴት ማረፍ እንደሚቻልም ከፍተኛ ልምድ ማግኘት እንዳስቻለው አስረድተዋል፡፡

ወቅታዊ የውስጥ የፀጥታ ችግሮች

ወቅታዊ የአገር ውስጥ ችግሮችን ለመቀልበስ ከሌሎች ከሚመለታቸው የፀጥታ አካላትና የክልል መስተዳድሮች ጋር የመከላከያ ሠራዊቱ አብሮ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

ሕገወጥ የጦር መሣሪያና የሰው ዝውውርን ለመቆጣጠርና ለመከላከል በቂ የሰው ኃይል በመመደብ በቀንና በሌሊት የቅኝት፣ የክትትልና የሥምሪት ሥራዎችን ሲከናወኑ መቆየታቸውንና እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎችን ለመቆጣጠር በተደረገ ጥረት ልዩ ልዩ የጦር መሣሪያዎችና ተታኳሾች፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ ማቴሪያሎች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጭ ለመውጣት የሞከሩ ግለሰቦችም እንደተያዙ ጠቁመዋል፡፡ ወደ አዲስ አበባ የገቡ የተለያዩ ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎችና ተተኳሾች ከፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ በቀረበው ጥያቄ መሠረት2 የመሣሪያዎቹን ዓይነትና ሥሪት የመለየት ሥራ እንደተከናወነ ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚታዩትን ግጭቶች ከማኅበረሰብ ጋር በማቀናጀት የመረጋጋት ሥራዎችን ሠራዊቱ ኮማንድ ፖስት አቋቁሞ እያከናወነ እንደሚገኝ የገለጹት ሚኒስትሯ፣ በዚህም በአንዳንድ ክልሎች አጎራባች ቀበሌዎች በተነሱ የጎሳ ግጭቶች የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ የማድረግና የማረጋጋት ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት የሰጡት ጄኔራል ብርሃኑ፣ በክልሎች ውስጥ ከክልሎች የአስተዳደር ወሰኖች ጋር በተገናኘ የሚነሱ የፀጥታ መደፍረሶችን ለመፍታት በዋናነት በፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ወይም ከመከላከያ ውጭ ባሉ የክልልና የፌዴራል የፀጥታ አካላት መሆን እንደነበረበት ጠቁመዋል። የክልል የፀጥታ ኃይሎች ብሔርን ወይም ጎሳን ወግነው እየተሠለፉ በመሆኑ ማኅበረሰቡ መከላከያ እንዲሰማራ መፈለጉ ተገቢ እንደሆነና ይህም ለሠራዊቱ ክብር በመሆኑን የጠቆሙት ጄኔራል ብርሃኑ፣ በዚህ ሁኔታ ሠራዊቱ በየቀበሌው ተበትኖ የክልል የፀጥታ አካላትን ሚና እንዲወስድ ማድረግ የአገር መከላከል ሚናውን እንዲዘነጋና ሠራዊቱን የሚያዳክም መሆኑን አስረድተዋል።

አሁን የመከላከያ ሠራዊቱ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ውስጣዊ የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታት በሥራ የተወጠረበት ጊዜ መሆኑን የገለጹት ጄኔራል ብርሃኑ በቤኒሻንጉል፣ በምዕራብ ወለጋ፣ በሞያሌ፣ በአማራ ክልል በጎንደር ከቅማንት ጋር በተያያዘ፣ በሐዋሳ፣ በጅግጅጋና በሌሎች የተለያዩ አካባቢዎች የፀጥታ ሥራ ላይ መሰማራቱን ተናግረዋል።

እነዚህን ኃላፊነቶች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሠራዊቱ የሕይወት መስዋዕትነት እየከፈለ በመፈጸም ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

 ‹‹በአንዳንድ አካባቢዎች የወደቁ የሠራዊቱ አስከሬኖችንና ቁስለኞችን በሔሊኮፕተር እየለቀምን ለአጸፋ ጥቃት ሳንተኩስ ነው የምንሠራው፤›› ሲሉ ያለውን ችግር ውስብስብነት ገልጸዋል።

 የተፈጠሩትን የፀጥታ ችግሮች ለመፍታት መከላከያ እንዲገባ ባይደረግ እንደሚመረጥ የተናገሩት ጄኔራሉ፣ መከላከያ በገባባቸው አካባቢዎች በሙሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ የፀጥታ ችግሮችን በጥንቃቄ እየፈታ መሆኑንና ከሠራዊቱ አቅም በላይ የሚሆን የፀጥታ ሥጋት አለመኖሩን አስረድተዋል። ነገር ግን መከላከያ የፀጥታ ሥራ ውስጥ እንጂ የፖለቲካ ሥራ ውስጥ ሊሳተፍ የማይችል በመሆኑ፣ የፖለቲካ አመራሩ ለችግሩ ፖለቲካዊ መፍትሔ በፍጥነት ማበጀት እንደሚገባው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

 በሌላ በኩል ሚኒስትሯ ወይዘሮ አይሻ የሠራዊቱን ኑሮ ለማሻሻል እየተደረገ ያለውን ጥረት አመላክተዋል። የሠራዊቱን ኑሮ ማሻሻልን በሚመለከት አየተተገበሩ ናቸው ካሏቸው መካከል በተደራጀና በጠንካራ ክትትል አመጋገብን መምራት፣ በተወሰኑ አካባቢዎች የሠራዊቱን የውኃ አቅርቦት ለማሟላት በጀት መድቦ የውኃ ጉድጓዶች በማስቆፈር አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ይገኙበታል። የሠራዊቱን ኑሮ ደረጃ በደረጃ ለማሻሻል በተያዘው አቅጣጫ መሠረትም ወታደራዊ አልባሳት በመንግሥት ወጪ እንዲቀርቡ የማድረግ፣ የአሃዶች የመጠለያ ችግሮችን ለማቃለል እንቅስቃሴ መጀመሩን፣ በሁሉም ክፍሎች የሬጅመንት መመገቢያ፣ የክፍለ ጦር ስታፍ፣ የሬጅመንት ኮማንድ፣ የሻምበልና የጋንታ መኖሪያ ቤቶች፣ እንዲሁም ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውሉ በርካታ ቤቶች ተሠርተው አገልግሎቶች እንዲሰጡ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

አሠራሩ በሚፈቅደው መሠረትም የሠራዊቱ ቤተሰቦች ማግኘት ያለባቸው መብቶችን ማሟላት፣ የኢኮኖሚ ጥቅም እንዲያገኙ በየአካባቢው የሚገኙ የሠራዊቱ መዝናኛ ክበቦችንና መደብሮችን ተደራጅተው እንዲይዙና በተመጣጣኝ ዋጋ ለሠራዊቱ አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ አቅም በፈቀደው ሁሉ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -