Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የባንኮች ካፒታል መጠን ከ85 ቢሊዮን ብር በላይ ደረሰ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ያሉት 18ቱ ባንኮች የካፒታል መጠን በአሥር በመቶ አድጎ 85.7 ቢሊዮን ብር መድረሱን ብሔራዊ ባንክ ይፋ አደረገ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ሪፖርት መሠረት፣ የ18ቱ ባንኮች ካፒታል ከ85.7 ቢሊዮን ብር ሲያስመዘግብ፣ ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ድርሻ 60.1 በመቶ እንደሆነ ከሪፖርቱ መመልከት ተችሏል፡፡ የንግድ ባንክ ካፒታል መጠን 43.85 ቢሊዮን ብር ሲያስመዘግብ፣ የልማት ባንክ ደግሞ ከ7.6 ቢሊዮን ብር መድረሱን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ የንግድ ባንክ ካፒታል የአገሪቱ ባንኮች በጠቅላላው ካፈሩት አጠቃላይ ካፒታል ውስጥ የ51.1 በመቶውን ድርሻ እንደያዘ ያሳያል፡፡

16ቱ የግል ባንኮች ዓምና ያስመዘገቡት የካፒታል መጠን 34.22 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ይህም ከጠቅላላው የባንኮች ካፒታል ውስጥ 39.9 በመቶ ነው፡፡ ሁሉም ባንኮች በ2010 ሒሳብ ዓመት የደረሱበት የካፒታል መጠን ከ2009 አንፃር በ7.8 ቢሊዮን ብር ጨምሯል፡፡ ካቻምና ባንኮቹ የነበራቸው የካፒታል አቅም 77.96 ቢሊዮን ብር እንደነበር ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

ከግል ባንኮች ከፍተኛውን ካፒታል በማስመዝገብ ከተጠቀሱት ውስጥ አዋሽ ባንክ 4.2 ቢሊዮን ብር፣ ዳሸን 3.7 ቢሊዮን ብር፣ አቢሲኒያ 3.26 ቢሊዮን ብር፣ ወጋገን ባንክ 3.19 ቢሊዮን ብርና ኅብረት ባንክ 2.57 ቢሊዮን ብር በየፊናቸው አስመዝግበው ነበር፡፡ የመንግሥት ባንኮች በበኩላቸው ዓምና የደረሱበት የካፒታል መጠን ከካቻምናው አንፃር ሲታይ የ1.5 ቢሊዮን ብር ብቻ ጭማሪ ነበረው፡፡ በ2009 ዓ.ም. ሁለቱ የመንግሥት ባንኮች የነበራቸው የካፒታል መጠን 50.1 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ በአንፃሩ 16ቱ የግል ባንኮች በ2009 ዓ.ም. በጠቅላላው የነበራቸው ካፒታል 27.78 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ በ2010 መጨረሻ ግን ወደ 34.22 ቢሊዮን ብር ከፍ ብሏል፡፡

ይህም የግል ባንኮች በአንድ ዓመት ውስጥ ካፒታላቸውን በ6.4 ቢሊዮን ብር ማሳደግ መቻላቸውን አመላክቷል፡፡ እነዚህ ባንኮች ግን በ2010 መጨረሻ ላይ ከሕዝብ ያሰባሰቡት የተቀማጭ ገንዘባቸው መጠን 730 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ 18ቱም ባንኮች የቅርንጫፎቻቸውን ቁጥር 4,757 ማድረሳቸውም ተጠቅሷል፡፡ ባንኮቹ በ2010 ዓ.ም. 500 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈታቸው የ18ቱም ባንኮች ቅርንጫፎች ብዛት 4,757 መድረሱን ብሔራዊ ባንክ አመላክቷል፡፡ ከተከፈቱት ቅርንጫፎች ውስጥ 1,452 የንግድ ባንክና የልማት ባንክ ናቸው፡፡

ከ2010 ዓ.ም. ከተከፈቱት ውስጥ በርካታ ቅርንጫፎችን በመክፈት ወጋገን ባንክ ቀዳሚ ሆኗል፡፡ ባንኩ በ2010 ዓ.ም. 69 አዳዲስ ቅርንጫፎችን ከፍቷል፡፡ ዳሸን ባንክ 66፣ ንግድ ባንክ 65፣ አንበሳ ባንክ 52፣ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ 45፣ አዋሽ ባንክ 43 ከፍተዋል፡፡ ቡና ባንክ 33፣ አቢሲኒያ 31 ቅርንጫፎችን በመክፈት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ንግድ ባንክ ያሉት የቅርንጫፍ ባንኮች ቁጥር 1375 ሲሆን፣ 16ቱ የግል ባንኮች የከፈቷቸው ቅርንጫፎች ብዛት 3‚275 ደርሷል፡፡ በዚህም በአገሪቱ ካሉት ቅርንጫፎች ውስጥ 68.8 በመቶው የግል ባንኮች ድርሻ ሆኗል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች