የኢትዮጵያ የባህል ፖሊሲ የአገሪቱን ባህል ለተቀረው ዓለም በስፋት ለማስተዋወቅ የሚያስችሉ በባህል እኩልነትና የጋራ ጠቀሜታ ላይ የተመሠረቱ ጠንካራ አገራዊ፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶች መፍጠር እንደሚገባ ያመለክታል፡፡
ኢትዮጵያ ባህልን አስመልክቶ የገባቻቸውንና ለወደፊቱም የምትገባውን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ግዴታዎች ለመወጣት አስፈላጊው ትኩረት እንደሚደረግም ያሳያል፡፡
የኢትዮጵያን ባህል ለማስተዋወቅ ከፖሊሲው አንዱ አካል የባህል ልውውጥና ግንኙነት ቢሆንም ግዘፍ ነሥቶ የሚታይበት ነገር ውስን መሆኑ ይወሳል፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ ከ30 ከሚበልጡ የአፍሪካ፣ የእስያ፣ የአውሮፓና የላቲን አሜሪካ አገሮች ጋር የባህልና ቱሪዝም ስምምነቶችን ተፈራርማለች፡፡ ስምምነቶቹን እንደየ አገሮቹና አንደ ስምምነቶቹ ዓይነቶች የየራሳቸው አፈጻጸሞች አሏቸው፡፡ በተለያዩ የባህል ዘርፎች የትብብር መርሐ ግብሮች እየተዘጋጁ አቅም በፈቀደ መጠን ተግባራዊ የሚደረጉ ናቸው፡፡
ከተለያዩ አገሮች ጋር የባህል ስምምነት ቢኖርም የተወሰኑ አገሮች ተወስደውና ዓላማ ተደርገው ወቅታዊ ሁነቶች በሚኖሩበት ጊዜ ትኩረት እየተሰጠ ተሳትፎ ይደረጋል እንጂ ስምምነት ባለበት አገር ሁሉ ለመሥራት የአቅም ውስንነት እንዳለ ይወሳል፡፡
ባህልን አስመልክቶ ከተለያዩ አገሮች ጋር የሚደረጉት ግንኙነቶች የየአገሮቹን ባህልና ሥነ ጥበብ በሚገልጹ ኤግዚቢሽኖችና ፕሮግራሞች መሳተፍና በኢትዮጵያም በማዘጋጀት ነው፡፡ በነባሩ ልምድ ኢትዮጵያ በእስያ፣ በናይጄሪያ፣ በሴኔጋል በተዘጋጁ የአፍሪካ የጥበብና የባህል ፌስቲቫሎች እንዲሁም የባህል ሙዚቃ ቡድኖችም በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በአፍሪካ አንዳንድ አገሮች እየሄዱ ይሳተፋሉ፡፡
አገራዊ ባህልን ለማስተዋወቅ ከትላልቅ ስብሰባዎች ይልቅ የባህል መገለጫ የሆኑትን ቁሳዊ ባህሎች ማሳየት ባህልን የማስረፅ ኃይሉ የጎላ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ለማሳየት በተደጋጋሚ የሚታዩት የፋሽን ትርዒት፣ ቡና ማፍላትና ጭፈራን ነው፡፡
የባህል ኦሊምፒያድ
ኦሊምፒክና ባህል ቁርኝት አላቸው፡፡ እርስ በርሳቸውም ይገላለጣሉ፡፡ የኦሊምፒክ ተሳታፊ አገሮች ባህላዊ መለያም የሚታይበት ነው፡፡
ተናፋቂውና ተወዳጁ ኦሊምፒክ የአራት ዓመት ቀጠሮውን አጠናቆ ካለፈው የሪዮ ኦሊምፒክ አርማ የተቀበለችው ቶኪዮ የ2020ውን 32ኛ ኦሊምፒያድ ለማስተናገድ አሥራ ስምንት ወራት ቀርቷታል፡፡ የዓለምን ሕዝብ ያላንዳች ልዩነት የሚያስተሳስረውና በባህላዊ መድረክ የሚታጀበው የኦሊምፒክ ጨዋታ ከ200 በላይ አገሮች የሚውጣጡ ከ11 ሺሕ በላይ አትሌቶች ከነባህላዊ መገለጫዎቻቸው ጋር እንደሚገኙ ይጠበቃል፡፡ ቶኪዮን በባህላዊ ገጽታ ጠቢባኑ (አርቲስቶች) በኦሊምፒኩ ብቻ ሳይሆን በፓራሊምፒክ ጭምር ለማድመቅ ዝግጅታቸውን ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡
‹‹የቶኪዮ 2020 ባህላዊ ኦሊምፒያድ›› የሚሰኘው የባህል ክብረ በዓልን ልዕልና ለማጎናፀፍ አዘጋጁ ተቋም ከጥቅምት 2009 ዓ.ም. (ኦክቶበር 2016) ጀምሮ እየሠራ መሆኑን የኦሊምፒኩ ድረ ገጽ ዘግቦታል፡፡
ተካፋይ አገሮች በኦሊምፒኩ መንደር የየራሳቸው ባህላዊ መገለጫዎች እንደሚያቀርቡም እየተናገረ ነው፡፡
አምስት ቢሊዮን የዓለም ሕዝብ የሪዮ ኦሊምፒክን ቴሌቪዥን ጨምሮ በልዩ ልዩ መንገዶች የሚከታተል ቢሆንም ዕድለኞቹ የሪዮን ምድር የሚረግጡት ጎብኚዎች ከኦሊምፒክ የመስተንግዶ ቤቶች የሚያጣጥሙት ሁነት ያህል አይሆንም፡፡ የአፍሪካ አህጉር ጨምሮ ሠላሳ አገሮች የራሳቸው ቤት እንደሚኖራቸው አረጋግጠዋል፡፡ ባህላቸውንና ታሪካቸውን መስህቦቻቸውንም ጭምር ያስተዋውቁበታል፡፡
ቤቶቹ የኦሊምፒክ የክብር አካል ሆነው መከሰት የጀመሩት በቤጂንግና ቀጥሎም በለንደን ኦሊምፒክ ጊዜ ነበር፡፡ ቤቶቹ እንግዶችን እንደቤታቸው የሚቆጥሩበት ዓይነት ምቾትን ያጎናፅፋቸዋል፡፡
እንግዶች የየአገሩን ባህላዊ ምግብ የሚያጣጥሙበት፣ በየሙዚቃው ዘና የሚሉበት በዓውደ ርዕይ ልምድ የሚለዋወጡበት፣ እንደየአገሩ አቀራረብ የተለያዩ ጨዋታዎች ውድድሮች የሚፈጠሩበት እንደሚሆን ተጠብቋል፡፡
ኢትዮጵያ በቶኪዮ ባህላዊ ኦሊምፒያድ ትሳተፍ ይሆን?
ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት በፊት ራሷን የምታስተዋውቅበት አዲስ መለያ (ብራንድ) አስቀድማ በጀርመን፣ ቆይታም በአዲስ አበባ ማድረጓ ይታወሳል፡፡ በመጀመርያ በእንግሊዝኛው “Land of Origins” (ላንድ ኦፍ ኦሪጅንስ) ቆይታም በአማርኛ ‹‹ምድረ ቀደምት›› መለያዬ ነው ብላለች፡፡
ይሁን እንጂ ይህን አዲሱን መለያዋንና ሌሎች ጓዞቿን ባለፈው የሪዮ ኦሊምፒክ በኦሊምፒክ መንደር በአፍሪካ ቤት (Africa House) ለማስተዋወቅ አልታደለችም፡፡ እ.ኤ.አ. በ2012 ለንደን ባዘጋጀችው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች፣ በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አጋፋሪነት በባህላዊ ኦሊምፒክ ተሳትፋ ራሷንም አስተዋውቃ ነበር፡፡ አፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የራሷ ጎጆ ተዘጋጅቶላት ከተሳተፉት አገሮች መካከል የኢትዮጵያ መቀመጫ በርካታ ተመልካችና ልዩ አድናቆት ማግኘቱ በተለይ በኦሊምፒክ መንደር ውስጥ የኢትዮጵያ ቀን በታላቅ ሁኔታ መከበሩ በወቅቱ ተዘግቦ ነበር፡፡
በአፍሪካ ሐውስ የኢትዮጵያ መቀመጫም ልዩ አድናቆትና ተመልካች አግኝቷል፡፡ በኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩልም አትሌቶችን የማስተዋወቅ የባህልና የሙዚቃ ሥራ ቀርቧል፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ የልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ መካነ መቃብር በመጎብኘትና ማንነትን በማሳወቅ ረገድ ልዩ ልዩ ሥነ ሥርዓቶች ተካሂደዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኤምባሲ በሃይድ ፓርክ በተዘጋጀው የኢትዮጵያ ቀን፣ ባህላዊ ምግብና የቡና ሥነ ሥርዓት፣ ሙዚቃና ዳንስ ያካተተ የምሳ መሰናዶ እንዲሁም በገናናው አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥነው ‹‹ጽናት›› ፊልም ለዕይታ በቅቶ ነበር፡፡
በሪዮ ኦሊምፒክ በዓለም በቡና ምርት ቀዳሚ የሆነችው ብራዚል ከመካሄዱ አንፃር የቡና መገኛዋ ኢትዮጵያ የቡና ሥነ ሥርዓቱን ጨምራ ልዩ ልዩ ባህላዊና ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊም መገለጫዎቿን በአፍሪካ ጎጆ ውስጥ ለማዘጋጀት አልታደለችም ነበር፡፡
ኦሊምፒክን በሚያዘጋጁ አገሮች ሥነ ጥበብ፣ ባህልና የፈጠራ ሥራ የሚታዩባቸው ክብረ በዓላትም ይዘጋጃሉ፡፡ ከሐምሌ 17 ቀን 2012 ዓ.ም. 32ኛውን ኦሊምፒያድ የምታስተናግደው የጃፓን ቶኪዮ ከተማ የባህል ኦሊምፒያድን በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ታከብራለች፡፡
የ2020 የባህል ፓራሊምፒያድም ከነሐሴ 19 ቀን እስከ ጳጉሜን 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ የሚዘልቅ ነው፡፡ በባህል ኦሊምፒያድ ጥላ ሥር ሙዚቃ፣ ዳንኪራ፣ እይታዊ ጥበብ (ሥነ ሥዕል)፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ቴአትርና ፊልም ተካትተዋል፡፡
የመጀመርያው የኦሊምፒክ ጨዋታ በግሪኳ ከተማ ኦሊምፒያ የተከናወነው ከ2700 ዓመታት በፊት በ776 ዓመት ቅድመ ክርስቶስ ነበር፡፡ ኦሊምፒያ የአገሪቱ የስፖርትና ባህል ማዕከል በመሆኗ ከጅምሩ ምርጥ አትሌቶችና ምርጥ ኪነ ጠቢባን (አርቲስቶች) መናኸሪያና መወዳደሪያ ነበረች፡፡
በ1886 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 1894) ፈረንሳዊው ባሮን ፒየር ደኩበርቲን የዘመናዊ ኦሊምፒክ እንቅስቃሴን ሲመሠርቱ አዲሱ የኦሊምፒክ ጨዋታ የጥንቱን የግሪክ ትውፊት መቀጠልና ባህል የኦሊምፒክ እንቅስቃሴ ሁለተኛው ምሰሶ ሆኖ ከስፖርት እኩል መጓዝ እንዳለበት የወሰዱት አቋም ነበር፡፡
የኦሊምፒክ ቻርተር እንደሚለው የኦሊምፒክ ጨዋታን የሚያስተናግዱ አገሮች ባህላዊ ፕሮግራሞች እንዲያዘጋጁና የአገሪቱን ባህልና ትውፊት ማስተዋወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የኦሊምፒክ ባህልና ትምህርት ለማስተዋወቅ በሺዎች በሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በጎ ፈቃደኞች ለኦሊምፒኩና ለፓራኦሊምፒክ ጨዋታ ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1949 ዓ.ም. (እ.ኤ.ኡ. 1956) በሜልቦርን ኦሊምፒክ መካፈል የጀመረች ቢሆንም ቀደም ሲል በ1916 ዓ.ም. የወቅቱ አልጋ ወራሽ ልዑል ራስ ተፈሪ መኰንን ከ11 መሳፍንትና መኳንንት ጋር በፓሪስ ኦሊምፒክ ስታዲየም በባህላዊ ልብስ የክብር እንግዳ ሆነው ተገኝተው ነበር፡፡ ከ1984ቱ (እ.ኤ.አ. 1992) የባርሴሎና ኦሊምፒክ ጨዋታ በስተቀር (የአውሮፓ ሱፍ እንዲለብሱ ተደርገዋል) በሌሎቹ ኦሊምፒያዶች የተለያዩ የባህል አልባሳት ለብሰው በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በመገኘት አገራቸውንና ባህላቸውን ማስተዋወቃቸው ይታወሳል፡፡