Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ፍሬን የሌለው አንደበት በዛ እኮ!

ሰላም! ሰላም! ያው በየሳምንቱ አዳዲስ ነገር ፍለጋ ላይ የሚያሰማራን ኑሯችን ስንቱን ያሰማናል መሰላችሁ? ባሻዬ ሰሞኑን በአንድ ወቅት በከተማው ስለተወራው ከመቃብሯ ስለተፈናቀለች ሴት ወሬ ተጠምደው ባገኙኝ ቁጥር ሲነዘንዙኝ ሰነበቱ። “በቤትና በመሬት ጉዳይ ብንፈናቀልም የምንፈናቀለው በልማት ስም በቁም ሳለን ብቻ ይመስለኝ ነበር፤” ይሉኛል በድርጊቱ መገረማቸውን ከመፈናቀል ጎን ለጎን አያይዘው። ባሻዬ ከወዲሁ ስለመቃብራቸው ጉዳይና ስለሥነ ሥርዓቱ የጻፉት ኑዛዜ አንድ መጽሐፍ ይወጣዋል እየተባለ አንድ ሰሞን በሠፈሩ ስማቸው ይብጠለጠል ነበር። “የዘንድሮ ሰው እንዲህ ብሎ በማውራቱ እንደማዝነው በሌላ በምንም አላዝን አንበርብር!” አሉኝ አንድ ቀን። “እንዴት ባሻዬ?” ብላቸው፣ “አብዛኛው ሰው በቁም ሳይደላው የሚያልፍ ነው። ታዲያልህ በቁሙ ቤት መሥራት አቅቶት እኔ ዘላለማዊ እንቅልፍ ተኝቼ ስለማርፍበት የመቃብር ቤቴ ስጨነቅ ያሽሟጥጠኛል። አመድ በዱቄት ይስቃል ማለት ነው እኮ!” ሲሉኝ ‘ቆሜስ ይሁን ሞቼ ካልደላኝ ምን ዋጋ አለው?’ የሚል አንድምታ ያለው ጨዋታቸው ማረከኝ። ለነገሩ ልጣቸው የተራሰ፣ ጉዱጓዳቸው የተማሰ በሌላ በኩል ያምሱናል፡፡ ዕድሜ የማያስተምራቸው ጉዶች!

ታዲያ አንዳንዱ ደረስኩ ባይ ወግና ሥርዓት የማያውቅ የዘመኑ ሰው ‘ፋስት ፉድ’ በለመደበት ቀብርም በ‘ፋስት ሙድ’ ካልተጠናቀቀ እያለ እነ ባሻዬን ሲያስቸግራቸው ስታዩ ጉድ ያሰኛችኋል። በቀብርና በለቅሶ በሚጠፋው ጊዜ የማንደሰተው እኔና ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነን፡፡ በአንድ ጀንበር የተኖረበትን የአባቶች ልማድ ካልሻርን ብለው የሚጋጩ ዘመነኞችን ስናይ ደግሞ እንበሳጫለን። ከግልብ ማወቅ ልግምነት እንደሚቀድም ማን ቢነግረን ልብ እንል ይሆን!? ዘመናዊነትን የዕውቀት ቁንጮ አድርገው ለማሳየት የሚመፃደቁ አንዳንዶች የያዙትን ዘመናዊ ሞባይል ስልክ አጠቃቀም አለማወቃቸውን ስትረዱ ‹‹ድንቄም›› ማለታችሁ አይቀርም፡፡ አለባበስ፣ ፀጉር አቆራረጥ፣ አካሄድ፣ አነጋገር፣ ወዘተ ብቻውን ምን ይረባል? በላዩ ላይ ዕውቀት ካልታከለበት ባዶ ጉራ ምን ይረባል? ብቻ ተውት አዛውንት ተብዬዎችም ብሶባቸዋል፡፡

 ሰሞኑን እንደሰማችሁት ለዓመታት ከሚያዛጉበት ኤርትራ በሰላም ገብታችሁ ተፎካከሩ ተብለው የመጡ ነውጠኞች፣ ከእንቅልፋቸው የቀሰቀሳቸውን መንግሥት አሻፈረኝ ብለው ነፍጥ ሲወለውሉና ሲወራጩ፣ ምነው የእኛ በቁም ማንቀላፋት ትንሳዔ አግኝቶ ልክ ባስገባናቸው አያስብልም? “ለአገራችን ትንሳዔ መነሳሳታችን ከወሬ በዘለለ ቢሆን ምን ነበረበት?” ስለው የባሻዬን ልጅ፣ “ነበር ምን ዋጋ አለው! የእናት አገር ፍቅር በትርጉም አልባ የእርስ በርስ ጥላቻና መናናቅ አከርካሪው ተመታ እንጂ!” ቢለኝ ክው አልኩ። መቼም አንድ ነገር ሰምቼ ሌላ የሚጎተተው ነገር እየበዛብኝ ተቸግሬላችኋለሁ። ነገር ሰንጣቂ የሚባለው እንደሱ ዓይነቱ ይሆን? አንዳንዱ የተማረ የሚባለው ግን በአብዛኛው ለምን ይሆን ነገር ሰንጥቆ ሲያበቃ ከመልካሙ ነገር ይልቅ ቅንነት የጎደለው ነገር ላይ ሲያተኩር የምንታዘበው? “የአገር ፍቅር ዕውን አንተ በምትለው መንገድ አከርካሪው ከተመታ ዛሬ ምን ተካው ትላለህ ታዲያ?” ስለው “የሥልጣን ቅዠት ነዋ። ጨዋታው ሁሉ ሥልጣንና ገንዘብ ብቻ ሆነ እኮ?” አለኝ ጣቶቹን ብር እንደሚቆጥር እያንቀሳቀሰ፡፡ “የሕይወት ቁም ነገሩ በሥልጣንና በገንዘብ እየተተመነ ሲመጣ የአገር ነገር ያሳዝናል። ይኼው ንቅዘት ላያችን ላይ ድሩን እየደጋገመ ያደራል። እናማ አገር ካለችበት ይህን ከመሰለ የዘቀጠ ሁኔታ ወጥታ የትንሳዔ ዘመን እንዲመጣላት ሲፈለግ፣ የሚሠራላት ሳይሆን የሚያወራላት በዝቶ አረፈው፤” ሲለኝ “ኧረ ከወሬ ማን ይገላግለን?” አልኩ። ተረታችንስ ‹‹ለወሬ የለው ፍሬ›› አልነበር? ይኼም ‹‹ድሮ ቀረ›› እንዳይባል እንጂ? እንዳይባል ደግሞ በጥባጩ ከታሪክ የማይመረው የድሮው ነው፡፡

ባሻዬ እንደነገርኳችሁ እንዲህ እንዲህ ላለው ተዓምር መሰል ወሬ መናኸሪያ ናቸው። ማለቴ ያው ከዕድር ሰዎቻቸው ጋር እንዲህ ዓይነት ወሬ ካገኙ ቁጭ ብለው ሲሰልቁ ነው የሚውሉት። ታዲያ ሲያገኙዋችሁ እናንተም የመቀላቀል ግዴታ ይኖርባችኋል። በተረፈ የምትሠሩት ሥራ ወይም የምትሄዱበት ቀጠሮ ለእሳቸው ምንም ነው። በነገራችን ላይ እንዲህ ያሉ ሰዎች እኮ ጥቂት አይደሉም። ለምሳሌ ጣደፍ ጣደፍ እያላችሁ ስትጓዙ እጃቸውን በሁለቱ የጃኬት ኪሳቸው ከተው ጅንን እያሉ የሚጓዙ የምታውቋቸው ሰዎች ያጋጥሟችኋል። ዘንድሮ አክብሮ ሰላምታ የሚሰጥ ሰው እንደሚናቀው ሌላ የሚናቅ ሰው ጠፍቷል፡፡ ከአንገታችሁ ጎንበስ ብላችሁ ሰላምታ ትሰጡና መጓዝ ልትቀጥሉ ስትሉ፣ “አንተን አይደል እንዴ ስፈልግ የነበረው?” ይሏችኋል። ክንዳችሁን ጨብጦ በያዘው በደህና ቀን ብዙ ጠቅልሎ በጎረሰ እጃቸው እያሳመሙ። “የአንዳንዱ ሰው እኮ የመዳፍ ስፋት የድሮ እህል መሥፈሪያ ነው የሚያክለው፤” ይላሉ ባሻዬ። ባሻዬን በኖሩበት ዘመን እንዲህ ያለ ንፅፅር ሲያቀርቡ፣ ልጃቸው በበኩሉ፣ “የእኔ ትውልድ ደግሞ ችግሩም መፍትሔውም ወረቀት ላይ ሆኖበት፣ የሚበጀውን በምርጫ ሰበብ የሐሜትና የአሉባልታ ፍጆታ ያደርገዋል፤” ይላቸዋል ልዩነቱ በደንብ እንዲገባቸው። ሁሉም በመሰለው መንገድ የሚፈልገውን ሲናገር እኔ ሥራዬ ማዳመጥ ብቻ ነው!

‹‹የምግብ ጥያቄ በተመለሰበት አገር የታደለ የሚባለው ናሳ መርጦት ጠፈርን ያሳየው ሰው መሆን አለበት። በእኛ አገር ደግሞ በደህና ቀን እህል በገፍ ሲሠፈር ያየው ነው ብንል አንሳሳትም፤›› የሚለኝ የባሻዬ ልጅ ነው። ይህቺ ይህቺ ደግሞ ትጥፋን እንዴ? ድህነትና የምግብ እጥረት ከዚህ ውጪ እንድናስብ ስለማይፈቅዱ ዕድል በዚህ ቢፈታ አንገረም። እናም ስለዚያ ስላስቆማችሁ ሰው ስጨርስላችሁ፣ የባጥ የቆጡን ወሬ ሊያወራችሁ ሲፈልግ በአንዴ ሥራ አጥ አድርጓችሁ ያርፋል። እናንተ የሚጠብቃችሁ ሥራ ወይም ጉዳይ ጊዜ አይሰጥም፡፡ ይኼ ወጠምሻ ደግሞ እንቅ አድርጎ ይዞአችሁ፣ ‹‹እንዴት ነው እባክህ? ጠፋህ እኮ?…..›› እያለ ማውራት ይጀምራል፡፡ ወደ ሥራችሁ እንደምትቸኩሉ ስትነግሩት፣ ‹‹ምን ከዘንድሮ ጠብ የማይል ሥራ የተሠሩትን ሕንፃዎችና መንገዶች እየዞሩ ማየት ይሻላል፤›› እያለ ሲስቅ፣ ከጤነኛ ጋር እየተነጋገራችሁ መሆኑን ትጠራጠራላችሁ፡፡ በምግብ ነው ወይስ በመድኃኒት እንዲህ ሰፊ የሀብታም እርሻ መስሎ የሚንቀሳቀሰው ማለታችሁም አይቀር፡፡ ብቻ አያጋጥም ነው፡፡ ካጋጠመ ግን የዘመኑን ነውጠኛ ፖለቲከኞች ወይም አክቲቪስቶች ተርታ ሊሆን ይችላል፡፡

ባሻዬ የስምተኛው ሺሕ ምልክት የሚሉት ሰሞነኛ ጨዋታ አምጥተዋል። ምን መሰላችሁ? ሁሉም ነገር በሺሕ መተመን፣ መጠራትና መቆጠር ከጀመረ እንደ ባሻዬ አባባል በቃ የስምንተኛው ሺሕ ምልክት እሱ ነው። እስኪ ጥቀሱ ሲባሉ ‘የጤፍ ዋጋ፣ የቤት ኪራይ ንረት፣ የበዓል ገበያ፣ ጉቦ፣ የሕዝብ ብዛት . . .’ እያሉ ብዙ ይዘረዝራሉ። እኔም ሳዳምጣቸው እቆይና ሁሌም የማይዘሉትን ‘ጉቦ’ “ደግሞ እሱ ምኑ ይሆን በመሠረታዊ ምልክትነት ያስቆጠረው?” ብዬ ግራ ገብቶኝ እጠይቃለሁ። “አይ ልጅ አንበርብር! ጉቦማ መቼም ቢሆን አብሮን የሚኖር ባላንጣ ደባላችን ነው። ትተን ማስተው ስላልቻልን እንደ መብት በየመሥርያ ቤቱና በየጉራንጉሩ የሚጠየቀው የእጅ መንሻ መጨመር ሊያሳስበን ይገባል። ምን ነካህ? ዋናውን?” ሲሉኝ አንገቴን ደፋሁ። በድርጊቴ ተፀፅቼ ቀና ብዬ ዓይናቸውን ማየት አፈርኩ። እሳቸውም ገብቷቸው፣ “ተወው ልጄ፣ ተወው! ብቻህን ተናደህ አትችለውም ልጄ፤ ብቻህን ጮኸህ አትዘልቀውም . . .” ሲሉኝ ተናደድኩ። ‘ዱብ ዱብ ባይ እንደ በረዶ’ የሚለው ፉከራችን ለምን ይሆን የጦር ሜዳ ብቻ ወኔ የሚሆነን? ‹‹ሌብነትን ከመዋጋት ከአንድ ብርጌድ ጋር መዋጋት ይቀላል፤›› ያሉት የአራዳ ልጆች ናቸው፡፡

ከባሻዬ ጋር እንዲህ ስል እቆይና እግሬ ወዳቀናው ስበር ልጃቸውን ያገኘሁት እንደሆነ ደግሞ ከእሱም ጋር ቆም ብዬ አንድ ሁለት እባባላለሁ። አንድ ሁለት ስል እጫወታለሁ ማለቴ ነው። በጠራራ ፀሐይ ያላበው ቢራ የሚያንቆረቁር ስታዩ እኔ ትዝ እንዳልላችሁ አደራ! ግን እንዲህ ያሉት ሰዎች እንዴት ቢደላቸው ይሆን ሕዝበ አዳም ሲራወጥ እነሱ ተረጋግተው የሚጋቱት? ለነገሩ አትፍረድ ነው! ምን ይታወቃል የዘንድሮ ሐኪም የማያዘው ነገር አለ ብላችሁ ነው? “ምነው በቀኑ?” ብትሉት “ሐኪም አዞልኝ ነው፤” ሊላችሁ ይችላል። ታዲያ መቀበል ግድ ነው። ዘንድሮ ካመኑበት መድኃኒት የማይሆን ምን አለ ብላችሁ ነው? ጉድ ነው እኮ! ባለፈው ሰሞን ከእዚህ ጋር በተያያዘ የሰማሁትን የሱስ ቀልድ ላጫውታችሁ። አባት ‘ቼን ስሞከር’ (‘ሰንሰለት አጫሽ’ ብዬ ብተረጉመው አይክፋችሁ። ሕልምና እንግሊዝኛ እንደፈቺው ነዋ! ስንቱ አሜሪካ የገባው በምን መሰላችሁ?) የሚባል ነው። ኋላ ሳንባውን ይታመምና ለጥቂት ጊዜ ማጨስ እንዲያቆም ይነገረዋል። እንዳልኳችሁ ‘ቼን’ አጫሽ ስለሆነ ግን በአንዴ መተው አይችልምና በይዘቱ ቀላል የሚባል ሲጋራ እንዲያጨስ ታዘዘ። ለአባትዬው ሁሌም ሱቅ እየተመላለሰ ትምባሆ የሚሸምተው ልጁ ቀላል ተብዬውን አንድ ቀን ሲሞክር አባት ደረሰበት። ወዲያው በመምከርና በመገሰጽ ፋንታ “እውነትህን ነው፣ ያ ዶክተር እየተጫወተብኝ ነው። እሱ ለእናንተ ነው ለእኔ ያንን የለመድኩት ገዝተህልኝ ና!” አለና መልሶ ልኮት አረፈው። ከቀልድነቱ አልፎ እውነት ቢሆንስ የሚለው ሐሳብ ሲጫነኝ፣ የዘንድሮ ወላጅና አስተዳደጉ ጉዳይ ሕመሜ ነውና ይነሳብኝ ጀመር። በስንቱ ታምሜ ልችለው ይሆን ግን? በዚህ ማኅበራዊ ጉዳያችን፣ በዚያ ፖለቲካችን!

የእኔ ነገር የባሻዬን ልጅ ሳገኘው ብዬ ጀምሬ አልጨረስኩላችሁም። አዎ! የባሻዬን ልጅ አባቱን አግኝቼ በተለየሁበት ስሜት ሆኜ ሳገኘው የማወራው አይቶና ሳያዩ ስለማደግ ነው። “አይተን ስለማናድግ እኮ ነው ብር ብርቃችን ሆኖ አገር በሌብነት የታመሰችው፤” ስለው ስለአስተዳደግ ያብራራልኛል። “ብለህ ነው አንበርብር? ምነው እንደሱ ከሆነ በሀብታም አገሮችስ ይኼው ችግር አልተገታ?” ይለኝና እንዲያው ነው መጨነቃችን በሚል ስሜት ሰማይ ሰማዩን ማየት ይጀምራል። “ከእሱ ይልቅ የዘመኑ ልጆች አስተዳደግ ያስፈራኛል። የእኛ ወላጆች እያላቸው ደብቀው፣ ማድረግ እየቻሉ ሸሽገው ያሳድጉን ነበር። ለምን? ስትላቸው ልጅ ከመጠን በላይ ከበላ፣ ከጠጣና ገንዘብ ከቆጠረ ዓላማና ጉዞ አይኖረውም በሚል ነበር። የአሁኑን ጊዜ ስታይ ግን ሕፃናት በአምስት ዓመታቸው ሁሉንም አውቀው ሁሉም ተሟልቶላቸው የሕይወት ትርጉም እየተዛባባቸው ነው የሚያድጉት። ሳያይ ያደገው አሁን በሌብነት አስቸገረን ካልን፣ አይቶ ያደገው ምን ሊያመጣብን ነው? የሱስ ቁራኛ ሲሆን ምን እንይዝ ምን እንጨብጥ ይሆን?” አለኝ ክፉኛ ተብሰልስሎ። አንዱ ሲናገር ሌላው ማድመጥ ትቶ እንጂ የሁሉም ነገር መፍትሔ ሚዛናዊ ይሆን ነበር። የሚቃወመውም የሚደግፈውም፣ ገዢውም፣ ተገዢውም አገርን ማዕከል ቢያደርጉ ምንኛ በታደልን ነበር። ያውም ዕድሜ ለፌስቡክ በቃርሚያ ወሬ ስንቱ የሚያዝገን አገርና የግል ጉዳዩ እየተምታቱበት እኮ ነው!

እስኪ በሉ እንሰነባበት። ከባሻዬ ልጅ ጋር ጊዜና ሁኔታ አመቻችተን በወጉ ግሮሰሪያችን ተገኝተናል። “አየህ እንዴት የባጥ የቆጡን ስናወራ ሳምንቱ ያለ ሥራ እንደሚከንፍ?” አልኩት የጊዜው ሩጫ ገርሞኝ። “ምን ታደርገዋለህ? ቫት ያልተጀመረው ወሬ ላይ ብቻ ሆኖ እኮ ነው?” ሲለኝ የሳምንቱን ምርጥ ሳቅ ከልቤ ሳቅኩኝ። “እውነቴን እኮ ነው አንበርብር! ልማትን እኮ ሁሌ በመዋጮና በብድር ብቻ ማከናወን አይቻልም። ቆራጥ አስተሳሰብና ድፍረት እኮ ይቀረናል። ሁሌም የሚገመገም የሕዝብ ወኔ፣ የሥራ ተነሳሽነትና ወሬን የማያበረታታ አፈጻጸም ጭምር ያስፈልጋል፤” ካለኝ በኋላ፣ “ሳይሠሩ መብላትና ሳይሠሩ ማውራት በሚበረታታበት ሁኔታ ውስጥ ልማት ለእኔ ህልም ነው፤” ሲለኝ ቺርስ ልለው ብርጭቆዬን አነሳሁ። “በወሬ ላይም ቫት እንዲጀመር!” ሲለኝ ደግሞ ብርጭቆዬን ሞቅ አድርጌ አጋጨሁ። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ እንደሚለው እዚህ አገር ወሬ በጣም በዝቷል፡፡ ፖሊሲው ሳይሳካ ሲቀር የአፈጻጸም ችግር ነበር ተብሎ ይወራል፡፡ ለምን አልተሳካም በማለት ከመገምገምና ዕርምጃ ከመውሰድ ይልቅ አፈጻጸም አጀንዳ ሆኖ በወሬ ይቀራል፡፡ “አንበርብር በየደረስንበት ለሻይ፣ ለማኪያቶ፣ ለሳንቡሳና ለመሳሰሉት ሳይቀር ቫት የሚጣልብን ከሆነ በስፋት ያለ ገደብ በሚሠራጨው ወሬ ላይ ቫት ቢጣል ውጤቱን ታየው ነበር፤” አለኝ፡፡ “ግን ገደብ አልባ ወሬ ቫት ተጣለበት ቢባል ምን ይፈጠር ይሆን?” ስለው፣ “ወሬኛውም ወሬ ተቀባዩም ሰላማዊ ሠልፍ ይወጡ ነበር . . .” እያለኝ ሲስቅ እኔን ደግሞ ፉከራ አማረኝ፡፡ ፍሬን የሌለው አንደበት በዛ እኮ! መልካም ሰንበት!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት