Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በፀጥታ መደፍረስ ምክንያት የግብርና ምርቶችን የሚሰበስብ የሰው ኃይል እጥረት ተከሰተ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰፋፊ እርሻዎች ባሉባቸው አካባቢዎች በየጊዜው እያጋጠመ ያለው የፀጥታ መደፍረስ በፈጠረው ሥጋት፣ ባለሀብቶች የግብርና ምርቶችን የሚሰበስብ የሰው ኃይል ማግኘት እንዳይችሉ እንዳደረገ ገለጹ፡፡

በተለይ በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በጋምቤላና በአፋር ክልሎች ምርት መሰብሰብ በነበረበት ጊዜ እያጋጠመ ያለው ደም አፋሳሽ ግጭት፣ የሰው ኃይል ወደ ሥፍራው እንዳይንቀሳቀስ አድርጓል ተብሏል፡፡  

በተለይ በዚህ ወቅት በእነዚህ አካባቢዎች የተመረቱትን ጥጥና ሰሊጥ የሚሰበስብ የሰው ኃይል በመጥፋቱ፣ ሊከሰት የሚችለው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ከወዲሁ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የጥጥ ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር አቶ መሰለ መኩሪያ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በተለይ በአማራ ክልል መተማ አካባቢ መንገድ በመዘጋቱ ጥጥና ሰሊጥ የሚሰበስቡ ሠራተኞችን ማግኘት አልተቻለም፡፡

አቶ መሰለ ጨምረው እንደገለጹት፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በተከሰተው ግጭት ጥጥና ሰሊጥ የሚሰበስቡ ሠራተኞችን ማግኘት አልተቻለም፡፡

‹‹ብዙም ባይሆን የተከሰተው ችግር በአገር ደረጃ ችግር የሚፈጥር እንደመሆኑ መጠን በጋምቤላና በአፋርም የሠራተኞች እጥረት ተከስቷል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልልና በአፋር ክልል የቀን ሥራ ያልተለመደ በመሆኑ ነዋሪዎች ተሳታፊ አለመሆናቸውን፣ አሁን ግን ነዋሪዎቹን አሠልጥኖ ለማሰማራት እየተሞከረ መሆኑን አቶ መሰለ ጠቁመዋል፡፡  

ምርት በሚሰበሰብበት በዚህ ጊዜ አንድ እርሻ ብቻ ከ2,000 እስከ  3,000 ሺሕ ሠራተኞች እንደሚፈለግ፣ አብዛኛውን ጊዜ ሠራተኛ የሚገኘው ከአማራ ክልል ከጎጃም አካባቢና ከደቡብ ክልል ከወላይታ አካባቢ እንደሆነ ይነገራል፡፡

ከአማራ ክልል የሚገኙት ሠራተኞች ብዙ ጊዜ ምርት የሚሰበስቡት መተማ፣ ቋራና ቤንሻንጉል ጉምዝ አካባቢ ተጉዘው ሲሆን፣ ከወላይታ የሚነሱት ሠራተኞች ደግሞ ጋምቤላና አፋር ክልሎች በመጓዝ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ያስረዳሉ፡፡

በጋምቤላ ክልል የተሰማራው የእርሻ ልማት ድርጅት ባለቤት አቶ አብርሃሌ ይደግ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዚህ ዓመት በ1,215 ሔክታር መሬት ላይ ጥጥ አልምተዋል፡፡ ነገር ግን ዘንድሮ የተሻለ ምርት እንደሚያገኙ ቢያስቡም፣ ከሌላው ጊዜ በተለየ የሰው ኃይል እጥረት ገጥሟቸዋል፡፡

‹‹ሦስት ካምፖች አሉን፡፡ በአንደኛው ካምፕ 530 ሔክታር መሬት ላይ ጥጥ አልምተናል፡፡ ከዚህ እርሻ ብቻ እስከ 20 ሺሕ ኩንታል ጥጥ ይገኛል፡፡ ነገር ግን እስካሁን የተሰበሰበው 700 ኩንታል ብቻ ነው፤›› በማለት የሚናገሩት አቶ አብርሃሌ፣ በአጠቃላይ ካለሙት 1,215 ሔክታር መሬት እስካሁን ድረስ 50 በመቶ መሰብሰብ የነበረበት ቢሆንም፣ መሰብሰብ የተቻለው ግን አሥር በመቶ ብቻ ነው ሲሉ፣ የችግሩን ስፋትና እያንዣበበ ያለውን ውድመት ያስረዳሉ፡፡

‹‹አብርሃሌ ይደግ እርሻ ልማት ድርጅት በአሁኑ ወቅት 2,000 ሠራተኛ ይፈልግ ነበር፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ሠራተኛ ባለማግኘቱ ድርጅቱ ከፍተኛ ሥጋት ተጋርጦበታል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ መንግሥት ባስቀመጠው ዕቅድ፣ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በመመደብ ልማቱን አካሂደን ነበር፡፡ ነገር ግን ምርት የሚሰበስብ ሠራተኛ በመጥፋቱ ከፍተኛ የአገር ሀብት ለውድመት ተዘጋጅቷል፤›› ሲሉ አቶ አብርሃሌ መንግሥት በፍጥነት ለዘርፉ እንዲደርስ ጠይቀዋል፡፡

በዚህ ዓመት ለኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ 58 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የተዳመጠ ጥጥ ይገኛል ተብሎ ታቅዶ ነበር፡፡ ጥጥ ከእርሻ ላይ በወቅቱ የሚነሳበት ዕድል በመጥበቡና ከሚቀጥለው ወር በኋላ ዝናብ ይጥላል ተብሎ ስለሚገመት፣ የምርት ውድመት ያጋጥማል ተብሎ ተሠግቷል፡፡

አቶ መሰለ እንደሚሉት፣ ይህንን አሳሳቢ ችግር ለመፍታት ኢንስቲትዩቱ ከክልል መንግሥታትና ከፀጥታ መዋቅሮች ጋር እየተነጋገረና መፍትሔ ለማበጀት ጥረት እያደረገ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች